Monday, October 24, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተጀመረ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳ ረቂቅ ላይ ሲወያይ ዋለ 
  • በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እና በዕርቀ ሰላም ጉዳይ አጀንዳ ላይ ልዩነቶች አሉ፤ 
  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና ማኅበረ ቅዱሳን ከማ/መምሪያው ጋራ ስላለው ግንኙነት የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት በአጀንዳው ረቂቅ ውስጥ ተካተዋል፤ 
  • ያረፉ ብፁዓን አበው ሀብት እና ንብረት ወራሾች ነን” በሚሉ ሐሰተኞች ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየተቸገረ መሆኑ ተገለጸ፤
  • በኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ይጨመርበት፤ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ ጉዳይ የቀድሞው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይመለስ” (የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ)፤
  • ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትናንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም” (ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ)፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 11/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 22/2011)፦ ስምንት አባላት ያሉትን የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በመምረጥ ዛሬ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2004 ጠዋት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንዲያዙላቸው ካቀረቧቸው የአጀንዳ ረቂቆች መካከል በተጨማሪ ኤጶስ ቆጶሳት ሹመት እና የኮሚቴው አባላት ካቀረቧቸው አጀንዳዎች አንዱ በሆነው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዕርቀ ሰላም ጉዳይ ላይ ሲወያይ ውሏል፤ በፓትርያርኩ እና በተቀሩት የጉባኤው አባላት መካከል በታየው የአቋም ልዩነት ምክንያት ውሳኔ ሳይደረግበትም ለነገ አድሯል፡፡

የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ሆነው የተመረጡት ስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡- ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ናቸው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በ2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 30 ያህል ኤጲስ ቆጶሳትን መሾምን አስመልክቶ የነበራቸውን አቋም አጠናክረው ቀርበዋል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱም ከሹመቱ አስቀድሞ የኤጲስ ቆጶሳቱን አሿሿም በተመለከተ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የታዘዘውን ከማስጠበቅ እና በዚህም መንፈስ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ከማጠናከር እንዲሁም ከተሿሚ ዕጩዎቹ አኳያ የተገቢነት እና ወቅታዊነት ጥያቄ በማንሣት ከስምምነት ሊደረስ ባለመቻሉ አጀንዳው ለነገ አድሯል፡፡

ከትናንት በስቲያ ለኅትመት የዋለው የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ በበኩሉ፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በጳጳሳት ሀብት እና ንብረት ውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እና ዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ጋዜጣው በመስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም እትሙ ባሰፈረው ርእሰ አንቀጽ፣ ከቀድሞዎቹ አባቶቻችን ሲደረግ በቆየውና ዛሬም ድረስ በቀጠለው ጥረት “ቤተ ክርስቲያን ከድህነት መሥመር ወጥታ ካህናት አገልጋዮቿ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን” ያውጃል፡፡ በዚህም መሠረት አበው ጳጳሳት በወርሐዊ ደመወዝ፣ በትራንስፖርት፣ በሕክምና፣ በመኖሪያ (ማረፊያ) ቤት፣ በማዕድ አገልግሎት ሳይቀር የትናንቱ ሰቀቀን እንደቀረላቸው በመዘርዝር በሞተ ዕረፍት በሚለዩበት ወቅት ያስታመመቻቸው፣ የተንከባከበቻቸው ቤተ ክርስቲያን ሳለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡ ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ መሆናቸውን አትቷል፤ውርሱ ይገባናል ባዮቹ ይህን የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

ርእሰ አንቀጹ የችግሩ መንሥኤ በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ መሆኑን ገልጧል፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ጠይቋል፡፡

ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥ እና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም እንደሚገባቸው ያስታወሰው ርእሰ አንቀጹ፣ ይህን በማድረግ ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም እንደሚቻል አስገንዝቧል፡፡


/ሙሉውን የርእሰ አንቀጹን ይዘት ከዚህ በታች ይመልከቱ/

የዜና ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ
አስታማሚ ቤተ ክርስቲያን ወራሽ ቤተሰብ
/ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ 57ኛ ዓመት ቁጥር 122፤ መስከረም እና ጥቅምት 2004 ዓ.ም/


ከዛሬ ዐርባ ዓመት በፊት በነበረው የዘውድ መንግሥት ሥርዐት ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የጠበቀ ግንኙነትና ትስስር ነበራቸው፡፡በየዘመናቱ የሚነግሡትን ነገሥታት ሁሉ ቀብታ የምታነግሥ እሷ ነበረች፡፡ ከዚህም የተነሣ ነገሥታቱም ሆኑ መሳፍንቱ ለቤተ ክርስቲያናችን ይሰጡት የነበረው አክብሮት፣ ያደርጉት የነበረው ድጋፍ፣ ጥበቃና ክብካቤ እጅግ በጣም የተለየ ነበር፡፡ ከግብጻውያን የባርነት ቀንበር ተላቅቃ መንፈሳዊ ነጻነቷን ሙሉ በሙሉ እንድትጎናጸፍ የከፈሉትም መሥዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አልነበረም፡፡ የምትጠቀምበት ርስት ጉልት ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ በሕገ መንግሥታቸውም ከፍተኛ ሥፍራ ነበራት፡፡

ከዚህም ሌላ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በሞያቸው፣ በቅድስናቸው እና በአገልግሎታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን ከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበት ጊዜ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን የሚፈጽሙባቸው መኪናዎች፣ የእጅ መስቀሎችና አርዌ ብርቶች፣ ልብሰ ተክህኖም ጭምር ይሰጧቸው ነበር፤ ወርሐዊ ደመወዛቸውንም የሚያገኙት ከመንግሥት ነበር፤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትም መንግሥት መጠነኛ የገንዘብ ድጎማ ያደርግ ነበር፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲሦ መንግሥት አላት”እየተባለ ይነገር የነበረውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡

ይህም በመሆኑ ጳጳሳቱም ሆኑ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ካህናት በሙሉ በጸሎተ ቅዳሴያቸው ዘወትር ወደ ፈጣሪያቸው በሚያቀርቡት ጸሎት “ዕቀብ ንግሦ ወሠራዊቶ ለንጉሥነ እገሌ፤ አግርር ፀሮ ታህተ እገሪሁ” ማለት “ንጉሥን ከነሠራዊቱ ጠብቀው፤ ጠላቶቹንም ከእግሩ ሥር አስገዛለት” እያሉ በመጸለይ አያሌ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ ደብተሮቹ ወይም ያሬዳውያን መዘምራኑም በበኩላቸው በያሬዳዊ ዝማሬያቸውና በቅኔያቸው ጣልቃ እያስገቡ ነገሥታቱን ሲያወድሷቸው፣ ሲያሞግሷቸውና ንጉሣዊ ተግባራቸውን በማጋነን ሲገልጡላቸው ይስተዋሉ ነበር፡፡

ከዚህም በላይ እንደተገለጸው ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የመንግሥት ጥገኛ ሆና ራሷን ሳትችል መኖሯ በሁሉም ዘንድ የተሰወረ ምሥጢር አይደለም፤ በዘመነ ደርግ የደረሰባትን ከፍተኛ ተጽዕኖም ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ተረኛ ሆኖ አገሪቱን መምራትና ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ግን የተወረሱት ቦታዎች፣ ቤቶችና ንብረቶች ሁሉ ተመልሰውላት ራሷን በራሷ እንድትመራና እንድታስተዳድር መደረጉ ትጋትንና ጥንካሬን እንድታገኝ በእጅጉ ረድቷል፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጻ የወጣች እንጅ እንደ ትላንቱ ጥገኛ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ አሁን በሚመሯት ዓለም አቀፍ አባት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የበላይ መሪነት፣ በልጆቿ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስተዳዳሪነት የምትመራ ቤተ ክርስቲያን እንጅ እንደ ትላንቱ ቋንቋዋን የማያውቅ ምእመን ከቤተ መንግሥት ተልኮ የሚያስተዳድራት ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡

በኢኮኖሚውም አኳያ ያለፉት ብፁዓን አባቶቿና አገልጋዮቿ ካህናት ጦም ውለው ጦም አድረው ለዝንተ ዓለም በአክፍሎት እየኖሩ ያገለግሏት የነበረችው የትላንቷ ደሃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በድህነት መስመር አትገኝም፡፡ “አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው” እንዲሉ እነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን የመሳሰሉት አርቆ አስተዋዮች አባቶቿ በሰበካ ጉባኤ አደራጅተዋት ስለ አለፉ ዛሬ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ሆኑ አገልጋዮቿ ካህናት ሁሉ በሞያቸውና በአገልግሎታቸው መጠን ክፍያ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ዛሬ ገንዘብም ጭምር የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት እንጅ ቅኔ ብቻ የሚዘረፍባትና የሚነጠቅባት የትላንቷ ደሃ ቤተ ክርስቲያን የለችም፡፡ የትላንቱን አስተንትኖና ከፍተኛ ለውጡን በውል ተገንዝቦ ተመስገን ለማለት እንዲችል የዛሬው አገልጋይ እና ተጠቃሚ ሁሉ ትላንት ቢኖር ኖሮ ምንኛ መልካም ነበር፡፡

በቀድሞው ጊዜ የነበሩት የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ተጠርተው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉት ቤት ተከራይተው ነበር፤ ወይም እንደሀገራችን ባህልና ሥርዐት ለብፁዓን አበው በማይስማማና በማይገባ በሆቴል ቤት ነበር፤ ለቁመተ ሥጋ ያህል ወይም ጥቂት ጥቂት የሚመገቡትም ለብፁዓን አበው የማይስማማና የማይገባ የግዥ እንጀራ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ያለፉት ብፁዓን አበው እንደተመኙት በሞተ ሥጋ የተለዩት ዓለምአቀፍ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ አሁን ባሉት የቤተ ክርስቲያን ርእስ ከፍተኛ ጥረት በመላው አህጉረ ስብከት አስተዋፅኦ ተገንብቶ ዓለም አቀፍ እንግዶችን በማስተናገድ ቤተ ክርስቲያኒቱን እጅግ አኩርቷታል፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ መኖሪያና ቢሮ በመሆንም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ልዩ ገስት ሐውስም ተገንብቶ ቅዱስነታቸው አቻዎቻቸውን የውጭ ፓትርያርኮችን እያስተናግዱበት ነው፤ እንደ ትላንቱ ከፍተኛ ወጭ በሚጠይቁና ለአባቶች ክብር በማይስማሙ ታላላቅ ሆቴሎች ማስተናገዱ ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡


ከዚህም ጋራ ብፁዓን አበው ለስብሰባ ከየአህጉረ ስብከቱ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉበት ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት የሚበቃ ቤተ አበው በተሟላ ሁኔታ በዘመናዊ መልክ ተሠርቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ እንደ ትላንቱ ለአባቶች ክብር በማይመጥን መንደር ውስጥ ገብቶ ቤት መከራየትና ሆቴል ቤት ማደር የለም፤ እንደ ትላንቱ የግዥ እንጀራ ቢያምርም አይገኝም፤ አሁንም ዛሬ ባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ርእስ የተለየ ጥረትና ፍላጎት በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ለሚኖሩትም ሆነ ከየአህጉረ ስብከቱ ለሚመጡት ብፁዓን አበውና በግቢ ለሚኖሩት አገልጋዮች መነኮሳትም ጭምር በገዳም ሥርዐት የአንድነት ማዕድ ገበታ በነጻ ተዘርግቶላቸዋል፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የአባቶችን የአንድነት ገበታ በቅጡ ሲመለከቱት ሢመተ ጵጵስናው ብቻ ሳይሆን ሥርዐተ ማዕዱም ከግብጽ የመጣ ይመስላል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ተመርጠው ሢመተ ጵጵስና በሚቀበሉበትም ጊዜ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸው መኪናዎችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶችን ገዝታ የምትሸልማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ መኪናዎችን መግዛት ብቻም አይደለም፤ አደጋ ሲያጋጥማቸውና በአገልግሎት ብዛት ሲዳከሙም ጋራዥ በማስገባት አሳድሳ የምትሰጣቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ብፁዓን አበው ሲታመሙም እስከ ውጭ አገር ድረስ በመላክ የምታሳክማቸው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበትም ጊዜ የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ በክብር የምትሸኛቸውም ራሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለብፁዓን አባቶች የሚሰጠው ወርሐዊ ደመወዝ ከአባትነታቸው፣ ከአገልግሎታቸው ስፋትና ከኑሮው ወድነት ጋራ የማይመጣጠን ስለሆነ የተዘረዘረው በጎ አድራጎትና ክብካቤ ሁሉ ቢደረግላቸው የሚደሰት እንጂ የሚከፋው የለም፤ በረከትን እንጅ መርገምን ያመጣል ብሎ የሚያስብም ወገን አይገኝም፡፡

ይሁን እንጅ ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደርም ሆነ በምጣኔ ሀብት ራሷን ችላ ይህ ሁሉ እየተደረገ እያለ ብፁዓን አበው በዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በሚለዩበት ጊዜ ቀብታ የሾመቻቸውና ሲታመሙ ያስታመማቻቸው ቤተ ክርስቲያን እያለች “ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ወራሾች እኛ ነን” እያሉ የሐሰት የውርስ ሰነድ ይዘው የሚመጡት ቤተሰብ ተብዬዎች በሚያቀርቡት አቤቱታ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ሆኑ አስተዳደሩ ፍትሕ ለመስጠት እየተቸገሩ ናቸው፤ ውርሱ ይገባናል ባዮቹ አልፈው ተርፈውም ያንኑ የሐሰት ውርስ ሰነድ ይዘው ወደየፍርድ ቤቶች በመሄድ የብፁዓን አባቶቻችንንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በማጉደፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህን ሁሉ ችግር የፈጠረውና መልኩን ለውጦ የመጣው በቅርቡ በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን አበው በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ ገንዘባቸውንና ያፈሩትን ንብረት ሁሉ የሚያሳድጓቸው እጓለማውታዎችና የሚረዷቸው ችግረኞች ቤተሰቦች እንዲወርሱ በሥርዋጽ በገባው ቃል የተላለፈው ድንጋጌ ነው፡፡ ስለሆነም የብፁዓን አባቶችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ለመጠበቅ ሲባል የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ድንጋጌውን እንደገና እንዲፈትሸው ያስፈልጋል፡፡

ስለ ብፁዓን አበው ሀብትና ንብረት አወራረስ ጉዳይ የቀደሙት አበው የወሰኑት ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ሊሠራበት ይገባል፡፡ምናልባት በብፁዓን አባቶች ይረዱ የነበሩ እጓለማውታዎች ካሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በቤተሰብና በሕፃናት አስተዳደግ ድርጅት ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡ የእናትና የአባት ወይም የቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ግን “ዘኢኃደግ አባሁ ወእሞ፤ ወብእሲቶ ወውሉዶ፣ ኢይክል ይጸመደኒ” የሚለውን አምላካዊ ቃል መዘንጋት አያሻም፡፡

በጳጳሳት ምርጫ ጉዳይም እንደቀድሞው የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ ከተጨመረበት ከሞት በኋላ የሚመጣውን ጣጣ ለማስወገድ ያስችላል፡፡ ጵጵስና የሚሾመውን አባት መምረጥና መሾም የሚገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ምእመናንም “አክዮስ አክዮስ ማለት ይደልዎ ይደልዎ” ብለው መምረጥና መሾም ይገባቸዋል፡፡ ይህም ከሆነ ዘንድ ሁለንተናዊ ብቃት ያለው ወይም ነውርና ነቀፋ የሌለው አባት መምረጥና መሾም ይቻላል፡፡ ከሹመት በኋላ የሚመጣውን ወቀሳና ከሰሳ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሊሸከም አይችልም፡፡


የቀድሞዎቹ አባቶች በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በሚለዩበት ጊዜ አይኖራቸውም እንጅ ገንዘብና ሀብት ካላቸው የእግዚአብሔር ገንዘብ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መሰጠት ስለአለበት ገንዘባቸውንም ሆነ ሀብታቸውን ሁሉ የሚያወርሱት ለቤተ ክርስቲያን ነበር፤ ወይም በትውልድ መንደራቸውም ሆነ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን በማሠራት፣ ገዳም በማስገደም፣ ት/ቤት በመክፈትና የምግባረ ሠናይ ድርጅት በማቋቋም ከአባትነት የሚጠበቅ መልካም አርኣያነት ያለው ሥራ ሠርተውበትና ዝክረ ስማቸውን ተክለውበት ያልፉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ይህን ዓለም በመናቅ ሹመት በቃኝ ብለው በምናኔ ሕይወታቸውን በኢየሩሳሌም በርሓ የፈጸሙትን የቀድሞውን የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡

እኒያ እውነተኛ ብፁዕ አባት ቅድመ ሢመተ ጵጵስናም ሆነ ድኅረ ሢመተ ጵጵስና ከዕለት ምግባቸው እየቀነሱ ዕድሜ ልክ ባጠራቀሙት ገንዘብ በትውልድ ቀያቸው ዝክረ ስማቸው ለዘለዓለም ሲታወስ የሚኖርበት ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ በሚሞቱበትም ጊዜ በቁጠባ ገንዘብ ያሠሩት ቤተ ክርስቲያን እንዲገለገልበት በኑዛዜ አውርሰው በማለፋቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ “የታዴዎስን ነፍስ ይማር” እያለ በመገልገል ላይ የሚገኘው ብፁዕነታቸው በኑዛዜ ባወረሱት ገንዘብ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን የእኒህን ብፁዕ አባት አሠረ ጽድቅ ተከትለው የሚሠሩ አባቶች የሉም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ሆኖም ብፁዓን አበው እንደ ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ያሉ አባቶች በተጓዙበት መንገድ እየተጓዙ ቢያልፉ የራሳቸውንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናቸውን ክብር ሊያስጠብቁና ዝክረ ስማቸውን ተክለው ሊያልፉ ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ማለትም በውርስ እና በጳጳሳት ምርጫ ላይ ትኩረት በመስጠት መክሮ እናዘክሮ ከሞት በፊትም ሆነ ከሞት በኋላ በብፁዓን አባቶች ላይ የሚከሠቱ ችግሮች እንዳይኖሩ የቀድሞውን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባዋል፡፡



(መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ)

No comments:

Post a Comment