- በቋንቋው ጠንቅቆ የሚያስተምር መምህር ባጣው በአዲሱ የቄለም ወለጋ ሀ/ስብከት በተሐድሶ መናፍቃን ከተወረሩት ሰባት ወረዳዎች በአንዱ ወረዳ በሚገኙ ሰባት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሴቶች ካህናቱን አንበርክከው ይጸልዩላቸዋል፤ ‹ቅዳሴ አያስፈልግም፤ ቅዱሳን አያማልዱም› የሚል ክሕደት በግልጽ እየተነገረ ነው”/የሀገረ ስብከቱ ሪፖርት/፤
- የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመንበረ ፓትርያርኩን 35% ድርሻ ብር 24 ሚልዮን ገቢ አደረገ፤ “ኑሯችን ለምንሰብከው ምእመን ምሳሌ የሚሆን ነው ወይ?” ሲሉ የጠየቁት የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ “እጃችን መሰብሰብ አለበት” ሲሉም መክረዋል፤ ጉባኤው ለሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ ከመቀመጫው ተነሥቶ ከፍ ያለ ጭብጨባ/standing ovation/ ችሯቸዋል
- በከምባታ አላባ እና ጠንባሮ ሀ/ስብከት በአንድ ቀን እስከ 2228 ሰዎች ተጠምቀዋል፤ በዕለቱ የሀገር ሽማግሌዎች የሀ/ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን ዝናም እንዲያዘንሙላቸው ጠይቀዋል፤ በተደረገውም እግዚኦታ ለ40 ደቂቃ ያህል ዝናም ዘንሟል፤
- በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ከ70 በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን 52ቱ ደቡብ አፍሪካውያን ካህናት የሚያስተዳድሯቸው ናቸው፤
- ከሰሜን አሜሪካ ሦስት አህጉረ ስብከት የሁለቱ (የዋሽንግተን ዲሲ እና የካሊፎርኒያ) ሊቃነ ጳጳሳት በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ “በዋሽንግተን ዲሲ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት” በሚል ከሊቃነ ጳጳሳቱ የበላይ የሆነ አካል መቋቋሙን በመቃወም እና በፓትርያርኩ ደርሶብናል በሚሉት በደል ዙሪያ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለፓትርያርኩ የጻፏቸው ደብዳቤዎች በጉባኤተኛውና በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆነዋል /መረጃዎቹ ደርሰውናል፣ ዝርዝሩን ወደፊት እናቀርባለን/፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 20/2011)፦ ሐሙስ፣ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2004 ዓ.ም፤ ከተጀመረ ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው 30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በ1991 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ለ13 ዓመታት ያህል በሥራ ላይ የቆየው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ እንዲሻሻል በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው የጀመረውን ውይይት ትናንት ሐሙስም በመቀጠል በቃለ ዐዋዲው መሻሻል ላይ ሐሳብ በተለዋወጠበት ወቅት እንደተመለከተው፣ በሥራ ላይ በሚገኘው ቃለ ዐዋዲ ውስጥ የማይሠራባቸው ድንጋጌዎች በርካታ መሆናቸውን አስታውሶ ለአብነትም ያህል፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ በየደረጃው እንዲቋቋም የታዘዘው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ (ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ/) ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በቀር በወረዳ እና በመንበረ ፓትርያርኩ ደረጃ አለመቋቋሙን ጠቅሷል፡፡
በማሻሻሉ ሂደት እንደ አርመን እና ሩስያ ያሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ልምድ /ምርጥ ተሞክሮ/ መዳሰስ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ በውጭ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በየሀገሩ መንግሥት “ደንባችሁን አምጡ” እየተባሉ ሲጠየቁ ቃለ ዐዋዲው ከየሀገሩ ሕግ ጋራ በተገናዘበ መልኩ በዓለም አቀፍ ቋንቋ ባለመተርጎሙ ሲቸገሩበት ቆይተዋል፤ በመሆኑም የሚሻሻለው ደንብ ቢያንስ በእንግሊዝኛ ቋንቋም እንዲተረጎም ተጠይቋል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቤቱ ለቃለ ዐዋዲው መሻሻል ያለውን ድጋፍ እጅ በማውጣት እንዲያሳይ በጠየቁት መሠረት ቤቱ በሙሉ ድምፅ ድጋፉን በመግለጡ የማሻሻሉ ሥራ በመጪው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳነት የመያዙ ጉዳይ ርግጥ ሆኗል፡፡
በውይይቱ ላይ ከተነሡት ሌሎች ጥያቄዎች ውስጥ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ በ120፣ በሀገረ ስብከት ደረጃ በ72፣ በወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ በ36 እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ በ24 አባላት/ቤተሰብ በሚቋቋመው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ኮሚቴ በየመዋቅሩ አንድ ከመቶ እንዲሰበሰብ ተላልፎ ስለነበረው ውሳኔ የሚመለከተው ይገኝበታል።
ቀሲስ ዘሩባቤል ገብረ መድኅን ይህን አስመልክተው ባቀረቡት ጥያቄ፣ ከ48 አህጉረ ስብከት ይህ ውሳኔ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ብቻ ነው፤ በሌሎቹስ ስላልተቻለ ወይስ ስላልተፈለገ ነው በማለት ስለ አፈጻጸሙ እና ስለ ቀጣይነቱ ማብራሪያ ይሰጠኝ ብለዋል፡፡
ለጉባኤው በተዘጋጀው ቃለ ዐዋዲ መጽሔት ላይ በሰፈረው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት፣ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው እና ማጠናከሪያው የአንድ ከመቶ ሒሳብ ወደ ማዕከል የላኩት ሁለት አህጉረ ስብከት ብቻ ሲሆኑ መጠኑም ብር 9,837.27 ነው፡፡
ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተቋቋመው ሀገር አቀፍ ም/ቤት ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ የተለያዩ አካላት ሽልማት መሰጠቱን ያስታወሱት ቀሲስ ዘሩባቤል በግንቦት ወር አጋማሽ ከብር 21 ሚሊዮን በላይ ያበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንስ ለምን አልተሸለመችም? የሰጠችው ገንዘብ አያሸልማትም ወይስ ገንዘቡ ከሚፈለገው ቦታ አልደረሰም? ውስጥ ውስጡን ከምንተማማ በግልጽ እንነጋገርበት ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ “ምኞቴን ለመናገር አልከለከልም” በሚል መቅድም “ቤተ ክርስቲያናችን የራሷ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያ ስለምን በኬንያ እና በጅቡቲ አታቋቁምም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “ወደ አዲስ አበባ ለየስብሰባው ስንመጣ ቆባችንን ቀሚሳችንን እንደለበስን ማደሪያ ፍለጋ በየቦታው እንከራተታለን፤ እኔ በበኩሌ አንድ መነኩሴ ከምሸት 12 ሰዓት በኋላ መንገድ ላይ ሲዞር ባይታይ ደስ ይለኛል፤ እንዲያው በማርያም ለምን በአንድ ማደሪያ የሚሰበስበን ማረፊያ አይዘጋጅልንም?” በማለትም አክለዋል፡፡
የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሓላፊ የሆኑት አቶ ይሥሐቅ ተስፋዬ ባቀረቡት የአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት ውስጥ መልካም አስተዳደር የፍጽምና ደረጃ ላይ የደረሰና ምንም ችግር የሌለ አስመስሎ የሚያሳየውን አቀራረብ ተችተዋል፤ “የአሠሪ እና ሠራተኛ ሕጉ እየተጣሰ እስከ ዕምባ ጠባቂ፣ ሰብአዊ መብት ኮምሽንና እስከ ቅዱስነታቸው ጽ/ቤት የደረሰ ጉዳይስ የለምን?” ሲሉ በአንድ ጊዜ ፍጹምና የተሟላ የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ላይ መድረሳቸውን የተናገሩትን አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሪፖርት አጠራጣሪነት ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚገኙ 48 አህጉረ ስብከት (ከጉጂ ቦረና ሊበን በቀር) ሪፖርት መስማት ትናንት ተጠናቋል፡፡ ሪፖርታቸውን ትናንት ካቀረቡት 11 አህጉረ ስብከት ውስጥ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን - ሰቲት ሁመራ ሀ/ስብከት ለአብነት መምህራን ከሀ/ስብከቱ የአምስት ከመቶ ድጎማ መመደቡ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የሀ/ስብከቱ ማዕከል ለአብነት መምህራን በየዓመቱ ብር 15,000 ማበርከቱ፣ ለካህናት ሥልጠና ብር 50,000 መስጠቱን ጉባኤው በጭብጨባ አመስግኗል፡፡ በወላይታ በሕገ ወጥ ሰባክያንና ማኅበራት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መካሄዱ፣ በከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀ/ስብከት ከ1030፤ በከንባታ አላባ እና ጠንባሮ ሀ/ስብከት በአንድ ቀን 2228 በላይ በሌላ እምነት የነበሩ መጠመቃቸው ተገልጧል፡፡
በከንባታ አላባ እና ጠንባሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በተገኙበት በአንድ ቀን በተደረገው 2228 ምእመናንን የማጥማቅ እና ማቁረብ ሥርዓት ወቅት የሀገሩ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ብፁዕነታቸውን በመምጣት አንድ ጥያቄ ይጠይቋቸዋል - “ለብዙ ጊዜ ዝናም ሳይዘንም በመቆየቱ በድርቅ ተቸግረናል፤ ስለዚህ አባታችን ሆይ፣ ዝናም አዝንምልን?” ይሏቸዋል፡፡
የሥራ አስኪያጁ ሪፖርት እንደሚገልጸው የሀገር ሽማግሌዎቹ ጥያቄ እጅግ አስጨናቂ ቢሆንም ብፁዕነታቸው “ኑ፣ እግዚኦታ እናድርስ”ብለው እግዚኦታው ተደርጎ ትምህርትና ምክር ተሰጥቶ እንዳበቃ ለ40 ደቂቃ ያህል ዝናም ዘንሟል፡፡ በዚህም ተዓምር የተደነቁ 50 የሀገሩ ሰዎች ወዲያው መጥተው “እኛንም አጥምቁን” ብለው መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡ “አሁን እየሠራን ያለነው ሰው ላይ እንጂ ገንዘብ ላይ አይደለም” ያሉት ሥራ አስኪያጁ ለመንበረ ፓትርያርኩ ገቢ ያደረጉት የ35% ገቢ ብር 26,000 ነው - ‹ቢያንስም እንዳትቀየሙ› ማለታቸው ይሆን?
በሪፖርቱ አፈጻጸም የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት ያመሰገኑት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ቀድሞ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የነበሩትና በሞተ ዕረፍት የተለዩንን ብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅን በማስታወስ የሚከተለውን ቃል ተናግረዋል፡- “ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የማይሰለቹ የወንጌል ገበሬ ነበሩ፡፡ በእርሳቸው ቦታ የተተኩት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሰምተነው የማናውቀው፣ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚያኮራ ሥራ ሠርተዋል፡፡ በቁመተ ሥጋ ስናያቸው አጭር ደቃቃ ናቸው፤ ግን ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋራ ይስጥልን፡፡”
የሆሮ ጉድሩ ሀ/ስብከት ‹አንዳንድ› ያላቸውን የማኅበረ ቅዱሳን አባላት አድማ በመቀስቀስ እና በጣልቃ ገብነት ችግር እየፈጠሩ መሆኑን በመጥቀስ ከሷል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ለምን በሪፖርታቸው ይህን እንዳሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከሆኑ የማኅበሩ ተሳታፊዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፡- “አንድ የእናንተ አባል ተሐድሶ ስላለኝ ተናድጄ ነው፤” ማለታቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል፡፡ ሀ/ስብከቱ ሕገ ወጥ ዘማርያንና ሰባክያንን በመቆጣጠር ረገድ ሥራዎችን መሥራቱ የተገለጸ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንም የሀ/ስብከቱን እንቅስቃሴዎች በመደገፍ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቄለም ወለጋ ሀ/ስብከት ቀደም ሲል ከነበሩት 11 ወረዳዎች ሰባቱ በመናፍቃን የተወረሩ እንደነበር፣ በ1991 ዓ.ም መኪና አደጋ በሞተ ዕረፍት የተለዩንን እንደ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በነበሩት አባቶች እና በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ላይ ድንጋይ ይወረወርበት እንደነበር በሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊነት የተሻለ ሁኔታ ያለ ቢሆንም የአካባቢውን ቋንቋ ዐውቆ ጠንቅቆ ትምህርተ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተምር መምህር በመታጣቱ በመናፍቃን ከተወረሩት ሰባት ወረዳዎች አንዱ ሙሉ በሙሉ በተሐድሶ መናፍቃን ተውጧል፤ በዚህ ወረዳ በሚገኙና በተሐድሶ መናፍቃኑ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ሰባት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ “ቅዳሴ አያስፈልግም፤ ቅዱሳን አያማልዱም፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ ጫማ ማውለቅ አያስፈልግም” የሚሉ ክሕደቶች በግልጽ እየተሰበከ ነው፤ ሰበካ ጉባኤያቱም በቃለ ዐዋዲው መሠረት የተቋቋሙ አይደሉም፡፡ ከዚህም የባሰው ደግሞ ሴቶች ‹ካህናቱ›ን አንበርክከው፣ እጃቸውን ጭነው ይጸልዩላቸው መባሉ ነው፡፡
በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ላይ በመመሥረት ከቤቱ በተሰጠ አስተያየት፣ “ሁኔታው ወንድ አጣ ነው የሚያሰኘው፤ ቢያንስ ጉዳዩን በማስረጃነት ይዞ ወደ ፍትሕ አካል ማቅረብ አይገባም ነበር ወይ?” የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የጥያቄውን ምላሽ በዛሬው ውይይት እንሰማው ይሆናል፡፡ በቃለ ዐዋዲ መጽሔት ላይ በቀረበው ሪፖርት ግን ሀ/ስብከቱ በቀጣይ፡- በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ለሠራተኞች፣ ካህናት እና የሰበካ ጉባኤ አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት፣ በየወረዳው ሰበካ ጉባኤትን ለማጠናከር፣ አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ካርታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ አብነት መምህራንን በመቅጠር ት/ቤቶችን ለማጠናከር፣ የሀ/ስብከቱን ጽ/ቤት ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተመልክቷል፡፡
ውዳሴ ከንቱ ሳያበዙና ወባ እንደያዘው ሰው ሳይንቀጠቀጡ ሥራቸውንና ስኬታቸውን ማዕከል ባደረገ መልኩ እጥር ምጥን ያለ ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገ/ሥላሴ፣ ሪፖርቱን እስከሚያቀርቡበት ዋዜማ ምሽት ድረስ ምክንያቱን በውል የማይረዱት አድማ እና ስም ማጥፋት በአንዳንድ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እየተካሄደባቸው መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በሙስና እና አድልዎ ላይ ባላቸው የማይናወጥ አቋም በአዲስ አበባ ካህናት ዘንድ እንደ ልዩ ጸጋ የሚታዩት ሥራ አስኪያጁ፣ “የእኔና የብፁዕ አባታችን ዓላማ አንድና አንድ ነው - ሥራን በቅንነትና በንጽሕና መሥራት የሚቻልበትን መንገድ አሳይቶ መሄድ” በማለት በጀመሩት የአስተዳደር ዘይቤ እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል፡፡ “እኛ መምህራን፣ ሰባኪዎች ነን፤ ለምእመኑ የምንሰብከውን በመኖር ምሳሌ ልንሆነው ይገባል፤ አለባበሳችን፣ አነጋገራችን ምሳሌ የሚሆን ነው ወይ?” በማለት ከጠየቁ በኋላ “ይቅርታ አድርጉልኝና እጃችንን መሰብሰብ አለብን” ሲሉ ግልጽ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ንቡረ ዕዱ መተጋገዙ ካለ የበለጠ ሊሠራ እንደሚችል ገልጸው “ከቆመ ሙዳዬ ምጽዋት ብቻ የተገኘ ነው” ያሉትንና ከፍተኛውን የ35% የመንበረ ፓትርያርክ ድርሻ የሆነውን የብር 24 ሚሊዮን ቼክ በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አማካይነት ለፓትርያርኩ አስረክበዋል፡፡ ሪፖርታቸውን ሲጨርሱና ወደ ቦታቸው ሲመለሱም ሙሉ ጉባኤተኛው ከመቀመጫው ተነሥቶ በጋለ ጭብጨባ አድናቆቱን ገልፆላቸዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ሪፖርት ከተጠናቀቀ በኋላ ከሀገር ውጭ የሱዳን፣ የኬንያ፣ የጅቡቲ እና የደቡብ አፍሪካ አህጉረ ስብከቶች ሪፖርት ቀርቦ ተሰምቷል፡፡ ፓትርያርኩ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በዘጋቢ ፊልም መልክ ለጉባኤው ቀርቧል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ካሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን 52ቱ በደቡብ አፍሪካውያን፣ 22ቱ በኢትዮጵያውያን ካህናት እንደሚመሩ በፊልሙ ላይ ተዘግቧል፡፡ በቅዱስ ያሬድ ስም የካህናት ማሠልጠኛ ተገንብቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ካህናት እና እናቶች መዝሙር ሲያቀርቡም ታይተዋል፡፡ ከኢየሩሳሌም ገዳም ሊቀ ጳጳሱም ተወካዩም ባለመገኘታቸው የቀረበ ሪፖርት የለም፡፡ በኬንያ ማኅበረ ቅዱሳን ለመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ገቢ ማስገኛ የገበያ ማዕከል ዲዛየን መሥራቱን፣ ከፀረ-ሰላም እና ሕገ ወጥ ሰባክያንና ካህናት ለመጠበቅ የሚያስችል ሥልጠና መሰጠቱ ተጠቅሷል፡፡ በሱዳን አንድ ካህን ቤተ ክርስቲያኑን ለመከፋፈል ያደረጉት ጥረት በምእመኑና በአስተዳደሩ ጥረት መገታቱ መገለጡ ተዘግቧል፡፡
ጉባኤው ዛሬም በመቀጠል የውጭ አህጉረ ስብከት ሪፖርቶችን ያዳምጣል፤ ውይይትም ያደርጋል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 9/2004 ዓ.ም)
No comments:
Post a Comment