Friday, October 14, 2011

‹‹ይህ ድንቅ ነገር ነው ›› የዮሐንስ ወንጌል 9፤30



  • ‹‹የቤተክርስትያን ፍቅር ለካስ እንዲህ ያስለቅስ ኖሯል ? ፍቅሯ ለካ አጥንት አልፎ ይሰማል››
  • ‹‹ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ›› ትንቢተ ዳንኤል 9፤21 
(አንድ አድርገን ፤ ጥቅምት 2 2004 ዓ.ም) ጊዜው ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን የአሰቦት ገዳም ጉዞ ከሚሄዱ ምዕመና አንዱ ነበርኩኝ የጉዞ ፕሮግራሙ ቀጥታ ከአዲስ አበባ አሰቦት ገዳም ገብቶ ማደርና  ጠዋት ኪዳን ካደረስን ፤ ቅዳሴ ካስቀደስን በኋላ ቀጥታ በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኙት ኮራ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሚካኤል እና የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ተሳልሞ ቦታውን ተመልክተን ፤ በቦታ ላይ የተደረገውን ገቢረ ተዓምራት ሰምተንና አይተን  በቀጣዩ ቀን ወደ አዲስ አበባ መመለስ ነበር::


አሰቦት ገዳምን ሐረር-ድሬደዋ ስመላለስ መግቢያ መንገዱንና ጠቋሚ ታፔላውን እንጂ ቦታው ላይ ቀደም ሲል ስላልሄድኩ ቦታውን ለመርገጥ በጣም ጓጉቼ ነበር፡፡ ‹‹ሰው ያስባል እግዚአብሄር ይፈፅማል›› ነውና እንደ እግዚአብሔር መልካም ፍቃድ በሰላም ተነስተን በሰላም አሰቦት ገዳም ደርሰናል ፡፡መኪናው የሚያደርሰን ቦታ ካደረሰን በኋላ የአንድ ሰዓቷን ዳገት ግን እኛ ደክመን በረከት እንድንቀበልበት የዳገቱን መንገድ ጀምረን በመሐል የሚገኝውን የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግን ቤተክርስትያን ተሳልመን ያሰብንበት ቦታ ስንደርስ ፀሐይ ለመግባት አጋድላ ነበር፡፡

ቦታው ላይ እንደደረስን የገዳሙ መነኮሳት ጌታችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሐሙስ የሐዋርያትን እግር አጥቦ ትህትናን እንዳስተማራቸው የእኛንም እግራችንን አጥበው ፤ መኝታ አዘጋጅተው ፤ አብልተውና አጠጥተው ገዳም ማለት የአብርሐም ቤት መሆኑን አስተምረው ምንም ሳይጎድልብን አስተናገዱን :: የገዳሙን ታሪክ አንዳች ሳያስቀሩ ነገሩን ፡፡ በሚቀጥለው ቀን በ11 ሰዓት ኪዳን አድርሰን ፤ ቅዳሴ አስቀድሰን ስናበቃ  መነኮሳቱ ፀሀይ ሳትበረታባችሁ መንገድ ጀምሩ ‹‹እግዚአብሔር ይከተላችሁ›› ብለው ሸኙን ፡፡ እኛም ‹‹መጥተን አንጣችሁ እግዚአብሔር ይስጥልን›› ብለን አመስግነን ማታ የወጣነውን ዳገት በጠዋት መውረድ ተያያዝነው፡፡


ኮራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን የሚገኝው አሰቦት መገንጠያ ሳይደረስ ትንሽ ሲቀረው ሲሆን ከዋናው የሐረር መንገድ 7 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ቀኝ ፒስታ መንገድ ገባ ይላል፡፡ ቤተክርስትኑ በዘመነ ደርግ ቢጀመርም ለብዙ ዓመታት ያህል በአካባቢው ላይ ሰላማዊ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት  በሰማንያዎቹ መጨረሻ ነበር ተጠናቅቆ ቅዳሴ ቤቱ ሊከብር የቻለው፡፡ ፡፡ በአካባቢው ላይ የሚገኙት 98 በመቶ ያህል ነዋሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው ቦታው ከፈተና እፎይ ያለበት ጊዜ የለም፡፡ በአካባቢው ላይ የሚገኙ የክርስትያኖች ብዛት ከ28 የማይዘሉ ሲሆን በየጊዜው የዲያቆናት የቀሳውስት የቤተክርስትያን አስተዳዳሪ እጦት እንደሚያጋጥማቸው እና ካህን ካለ አገልግሎት እንደሚኖር ካህን ከሌለ ግን አገልግሎቱ እንደሚስተጓጎል እና ለብዙ ጊዜያት ይህ ቋሚ ችግራቸው መሆኑን ተረድቻለሁ ይህ ማለት ከጧፍ ፤ ከእጣን እና ቤተክርስትያኗ ከሚያስፈልጓት ነገሮች ችግር እንዳለ ሆኖ ነው::

ቀድመው ይህን ፕሮግራም ያዘጋጁልን አባት እንደምንመጣ ቀድመው ነግረዋቸው ኖሯል ሁሉም ከሌላቸው ላይ ለእንግዳ መቀበያ አዋጥተው እኛን ለመቀበል ያደረጉትን ነገር ሳስብ ይገርመኛል፡፡ መኪናችን ወደቤተክርስትያኑ በር ሲቀርብ 25 የማያህሉ ክርስትያኖች ግማሹ ደስ ብሎት እልል ሲል ግማሹ ደግሞ ሲያለቅስ በመመልከቴ ውስጤን አንዳች ነገር አራደኝ፡፡ ከመኪናው ወርደን ለምን እንደሚያለቅሱ ስንጠይቃቸው ‹‹እንዲህ እንደ እናንተ ብዙ ሰው እዚህ ቤተክርስትያን  ሲመጡ አይተን አናውቅም እኛም ለካስ  ወገን አለን፤ እኛንና ቤተክርስትያኑንም ለመመልከት ስለመጣችሁ ደስታው ፈንቅሎን ነው ያለቀስነው ›› ሲሉን ለደቂቃዎች ዝምታ ሰፍኖ ሁሉም ሰው ራቅ ራቅ ብሎ  ሲያለቅስ ተመለከትኩኝ፡፡ እኛ ቁጥራችን 30 ነው ለካስ 30 ሰውም ብዙ ነው?

ቤተክርስትያኑ ተከፈተልን ውስጥ ገብተን ተሳልመን ጸሎት አድርሰን ደስ አለን፡፡ ውስጡ የገጠር ቤተክርስትያን ይዞታ አለው የጣራ ክዳኑ ረዘም ያለ ጊዜ በመቆየቱ የተነሳ አልፎ አልፎ ተሸንቁሮ ፀሀይቱ  በሽንቁሩ በኩል ያመላክታል፡፡ ከበሮ ወጥቶልን እኛ 30 እነሱ 25 በጠቅላላው 60 የማንዘል ምዕመናን ከላይ እንደ እሳት የሚያቃጥለው ፀሀይ ከታች የአካባቢው ወበቅ ምንም ሳይመስለን  መዝሙረኛው ዳዊት 

እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት።
በችሎቱ አመስግኑት በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት።
በመለከት ድምፅ አመስግኑት በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት።
በከበሮና በዘፈን አመስግኑት በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።
ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት።
እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን


                                  መዝሙረ ዳዊት 150፤1-6 
እንዳለው በመዝሙር እግዚአብሔርን ስናመሰግን ለ30 ደቂቃዎች ዘለቅን፡፡  እውነቱን ለመናገር ዘምረን ፤ እልል ብለን ፤ አመስግነን ልንጠግብ አለመቻላችንን ብቻ ነው ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቤተክርስትያኑ ጥግ ላይ 70 ዓመት የዘለላቸው ኑሮ  ያጎሳቆላቸው አንዲት እናት ለደቂቃ እንኳን እንደ ማየ የክረምት ዥረት የሚወርደው እንባቸውን ማቆም አልቻሉም ነበር፡፡ የቤተክርስትያን ፍቅር ለካስ እንዲህ ያስለቅስ ኖሯል ? ፍቅሯ ለካ አጥንት አልፎ ይሰማል ፡፡ ፍቅሯ ገብቷቸው በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነወ  ከላይ ንዳዱን ከታች ወበቁን ፤ ቀን ከሌት የአህዛብን ፈተና ችለው ተቋቁመው ቤተክርስትያኒቷን ኖሯቸው እና ተርፏቸው ሳይሆን ካላቸው ላይ ሰጥተው እንዴት እንደሚጠብቋ ስመለከት ውስጤን መንፈሳዊ ቅናት አነደደኝ ::ብዙ ቦታ እግሬ ተንቀሳቅሶ ሄጃለሁ ነፍሴን ሐሴት የሞላት ግን ይህ ቦታ ነው፡፡

የቤተክርስትያኗ አስተዳዳሪ ሃያዎቹ መጨረሻ ያሉ አባት ናቸው፡፡ እሳቸው ከነገሩን  ቦታው ላይ ከተደረጉት ገቢረ ተዓምራ ውስጥ አንዱን ዛሬ ልነግራችሁ ወደድሁ፡፡ ‹‹ተዓምር ያላመነውን እንዲያምን በር የሚከፍት ያመነን ደግሞ በእምነቱ እንዲፀና የሚያበረታታ ጉልበት የሚሆን የእግዚሐብሔር ድንቅ ስራ ነው፡፡››

ቤተክርስትያኗ የምትተዳደረው በእነዚህ ጥቂት ክርስትያኖች መዋጮ እና በአንዳንድ ክርስትያኖች ድጎማ ሲሆን ለብዙ ዓመታት ቤተክርስትያኒቱን የሚጠብቅ ጠባቂ ዘበኛ በወር 80 ብር ይጠብቅ እንደነበር እና ከጊዜ ወዲህ ግን የአካባቢው ምዕመን በኑሮ ውድነት እና ከኑሮ ተርፎ ለቤተክርስትያን የሚሰጥ ገንዘብ በማጣት 80 ብር በወር በቋሚነት መክፈል ያቃታቸው ጊዜ ላይ በመድረሳቸው  በነገሩ ላይ ብዙ ተወያይተው ፤ ብዙ ተነጋግረው ብሩን በቋሚነት ለማግኘት ግን ሳይቻል ቀረ :: ስለዚህ ያለው መፍትሄ ‹መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቤቱን ራሱ ይጠብቅ› ብለው በፊት ሲያገለግል የነበረውን ጠባቂ ማሰናበት ብቻ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ይህን ውሳኔ ሲወሰኑ ግን እያዘኑ እና ውስጣቸው ስለቤተክርስያን ሐዘን እየተሰማቸውና አንዳቸው ላንዳቸው ሳይናገሩ እያለቅሱ ነበር፡፡ በዚያን ቀን ማታ የሰርክ ፀሎት አድሰው ቤተክርስትያኑን ዘግተው ‹‹ቅዱስ ገብርኤል ሆይ ቤትህን ጠብቅ›› ብለው አስረክበውት ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ‹‹ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ›› ትንቢተ ዳንኤል 9፤21 እንዲል መፅሀፉ  በዚያን ሰዓት የሆነው ነገር የአካባቢው ማህበረሰብ ሆነ እነርሱ አይተውት ሆነ ሰምተውት የማያውቁት ነገር ነበር፡፡ 

አንድ ትልቅ የሚባል ዘንዶ ከቤተልሔሙ ጀርባ ካሉት መቃብር ስፍራዎች ሲመጣ አዩ ቤተልሔም በሩ ላይ ሲደርስ ተጠቅልሎ ሲያርፍ ሲመለከቱ በአይናቸው ያዩትን ነገር ማመን አቅቷቸው ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ዘንዶ በህይወታቸው ከዚያን ቀን በፊት አካባቢው በረሐ ስለሆነ በዓይናቸው አይተውም ይሁን አለ ሲባል ሰምተው  አያውቁም ፡፡ እነሱ ስለ ቤተክርስትያን ጠባቂ ሲጨነቁ ሀሳባቸውን የሚያውቅ እግዚአብሔር በጊዜው ሳያረፍድ ጠባቂ  ሊልክላቸው ችሏል፡፡ ይህ ዘንዶ ለብዙ ጊዜያት ማታ እየመጣ ቤተልሔም በር ላይ ተጠቅልሎ እንደሚተኛና ቤተክርስትያኑን እንደሚጠብቅ ጠዋት ካህናት ቅዳሴ ከመግባታቸው በፊት ደግሞ ተመልሶ እንደሚሄድ ሲነግሩን  ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤››የዮሐንስ ራእይ 15፤3-4   ‹‹ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።›› መዝሙረ ዳዊት 139፤14 ብሎ የእግዚአብሔርን ስራ ከማድነቅ ፤ እሱን ከማመስገንና ፤ ውስጥን በሐሴት ከመሙላት ውጪ ‹‹አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ከእኛ ጋር ይሁን አይተወንም፥ አይጥለንም›› መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 8፤57 የሚያስብል ነበር፡፡ ‹‹ለካስ እግዚአብሔር አይተወንም››  እኛ ነን እንጂ ሰውኛ ምክንያት እየደረደርን እሱን እንተዋለን ፤ ከቤቱ በሆነው ባልሆነው ምክንያት እንቀራለን፤ ከሰርክ ጉባዬ ይልቅ የካፍቴሪያዎችን ጫጫታ መርጠን እንዲህ አይነት ቦታ ጊዜያችንን በማሳለፍ ቀን በቀን እንርቃለን እንጂ እግዚአብሔር ግን ለደቂቃም ቢሆን አይተወንም፡፡

‹በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም›› ማቴ 16፤18 የተባለላትን አንዲት ቅድስት ቤተክርስትያናችንን እኛ በዘመናችን ሐላፊነታችንን ሳንወጣ ስርዓቷን ከአባቶቻችን ተቀበልነውን ትውፊቷን፤ ያሬዳዊ ዜማዋን ፤ ቅዳሴዋን ፤ ሰዓታቷን ፤ በየገጠሩ የሚገኙ አጥቢያ አብያተክርትያናትን እና ገዳማትን ከጠላት ሴራ ከመናፍቃን እና እናድሳት ከሚሉት ተሀድሶያውያን ነቅተን በመጠበቅ የተቀበልነውን ለልጆቻችን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ቢያቅተን ‹‹ይብላኝልኝ ለእኛ መክሊታችንን ለቀበርን›› እንጂ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በእለተ አርብ በቀራንዮ በመስቀል ላይ ሆኖ በደሙ የዋጃትን ቤተክርስትያን ለሰከንዶች እንኳን እንደማይተዋት ማወቅ አለብን፡፡  

ይህን የመሰለውን ቦታው ላይ የተደረገውን ተዓምር ሲነግሩን ውስጤ እኔስ ያየሁትን ለሌሎች መቼ ነው የምፅፈው ፤ ያላዩትን ጓደኞቼን መቼ ይሆን ቦታውን ይዜ ሄጄ የማሳያቸው እያልኩ አስብ ነበር፡፡መልአኩ በቤቱ በደንብ አድርጎ ስለያዘን ከዚያ ከ10 - 12 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝውን ብዙ ተዓምራት የተደረገበትን ከዚህ በባሰ በአህዛብ የተከበበውን  የቅዱስ ሚካኤልን ቤተክርስትያን ማየት አልቻልንም፡፡

ሌሎች የሚገርሙ ከዚህ በፊት  ያልተሰሙ ተዓምራትን እኛም በጆሯችን ሰምተን ፤ በአይናችን ያየናቸው ገቢረ ተዓምራትን ተመልክተን እግዚአብሔርን እያመሰገንን መሄጃ ሰዓታችን ስለደረሰ ስለ አቀባበላቸው አመስግነን ያየነውንና ፤ የሰማነውን ተዓምራት በአይኔ ላይ እየተመላለሱብኝ ወደ ቦርደዴ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ጉዙ ጀመርን፡፡

መርዳት ለምትፈልጉ ሰዎች

ቦታውን ሄደን ማየት እንፈልጋለን ቤተክርስትያኖቹንም መርዳት እንፈልጋለን  ለምትሉ ሰዎች 0913-833532 (የቦርደዴ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስቤተክርስትያ አስተዳዳሪ ስልክ ነው )፡፡  ይህን ስልክ በመጠቀም በእሳቸው አማካኝነት በበረሀ አካባቢው የሚገኙትን የኮራ ገብርኤል፤ የሚካኤልን ፤የቦርደዴየአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስን  የኪዳነ ምህረትን አብያተክርስትያናትን በጧፍበእጣን በቤተክርስትያ መገልገያዎች መርዳት ይችላሉ ፡፡
ለዛሬ ባልፅፈውም ቀጣዩን በሌላ ቀን  ለአንባቢያን ለማድረስ አስቤአለሁ ፡፡ ስራውን ለመመስከር የእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ይሁንልኝ፡፡ አሜን

19 comments:

  1. KALE HIWOT YASEMALN

    ReplyDelete
  2. ‹‹ለካስ እግዚአብሔር አይተወንም›› እኛ ነን እንጂ ሰውኛ ምክንያት እየደረደርን እሱን እንተዋለን ፤ ከቤቱ በሆነው ባልሆነው ምክንያት እንቀራለን፤ ከሰርክ ጉባዬ ይልቅ የካፍቴሪያዎችን ጫጫታ መርጠን እንዲህ አይነት ቦታ ጊዜያችንን በማሳለፍ ቀን በቀን እንርቃለን እንጂ እግዚአብሔር ግን ለደቂቃም ቢሆን አይተወንም፡፡

    ReplyDelete
  3. Amen - - - Kale Hiwote Yasemalin - - - Berta

    ReplyDelete
  4. kalehiwot yasemalin. berta .e/r keante ga yihun egnam bizu neger eyastemarken new betam enameseginalen ...

    ReplyDelete
  5. So nice to here this .What i learned is trust in God if we believe him ,there is nothing he can not do for us.So Let us support on him and reach for the far end churches.May God give us strength on this to do some thing helpful.Kale Hiwot ya semalen.

    ReplyDelete
  6. Kalehiwot yasemalen, please tell us more about this special stories of our betekerestian.

    ReplyDelete
  7. kalehiwot yasemalen.Awon Egziabher betun aytewem.Nolawi tiguh newna.

    ReplyDelete
  8. Betam des yemil teamir new melaku eganm yitebiken kale hiwoten yasemalin Amen.

    ReplyDelete
  9. kale hiywet yasemaln EGZIABHER HULGIZE KEGNA GAR NEW AMEN.

    ReplyDelete
  10. egezere yehen bota lemayet yabekage yehon.tehufun sanebew salawek alekeshalehu .geduse gebereil ebakehe asebege. tigist from canada

    ReplyDelete
  11. በእግዚአብሔር ስም መጀመሪያ እንደምን ዋላችሁ እንደምን ከረማች ክብሩ የተመሰገነ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን
    ከዚህ በመቀጠል የምጠይቃችሁ አሰቦት ገዳም ለመሄድ ሴቶች ይችላሉ ወይ ስለአሰቦት ገዳም አካባቢ እና እንዴት መሔድ እንደምችል በህብረትም ከሆነ እንዲሁም በአካባቢው ስላሉ ቤተክርስቲያናት ችግር ተካፋይ እንድንሆን በደንብ ተንትናችሁ አስረዱን

    ReplyDelete
  12. egziabher yerdahi berta wendemacen egziabher
    ysitlne

    ReplyDelete
  13. kale hiwoten yasemlen!

    ReplyDelete
  14. egzihabehere yimesegen.

    ReplyDelete
  15. God bless you.You have told us a miracle done by All mighty God.My brother,
    please keep on writing so that we can learn a lot.

    ReplyDelete
  16. yehenen yanbebhut eyileksehu new E/ZHAR yestlegnter

    ReplyDelete
  17. amesgnalehu 100000000 gezi

    ReplyDelete
  18. ‹‹አሕዛብ ሸሆች ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለጠላት አሳልፈው አይሰጡም የኦርቶዶክስ እምነት አባት የሆኑት ፓትርያርክ ግን ልጆቻቸውን ‹አሸባሪ› እያሉ ለጠላት አሳልፈው እየሰጡ ነው›› እያልን አንማዎት! የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና በመጻረርና ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ የሚጎዳ ሥውር ሥራ በመሥራት የክርስቶስን አካል አያድሙ!

    ReplyDelete