Sunday, October 9, 2011

“የቤተክርስቲያኒቱ ፈተናዎች” ጸሐፊ በወንጀል ተጠየቁ


  • “በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ተንሰራፍቶ ይገኛል”
  • “እየተፈፀመ ላለው አስተዳደራዊ ብልሽት ሁሉ ቅዱስ ፓትሪያሪክ ተጠያቂ ናቸው”
  • ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ “መጽሐፍ በመጻፍ ከባድ ወንጀል” ተጠይቀዋል
  • አንዳንድ የደብር አለቆች በማደሪያ ቤታቸው ሙዳየ ምጽዋቶችን እንደሚቆጥሩ አረጋግጠዋል
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ “የሌቦች መደበቂያ በመሆን ባያገለግሉ መልካም ነው” ሲሉ ተችተዋል
- ከመጽሐፉ የተወሰደ
(አዲስ አድማስ  መስከረም 28/2004) “የቤተክርስቲያን ፈተናዎች” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፋይናንስ እና የሰው ኃይል አስተዳደር ችግሮች እና የገንዘብ ምዝበራ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ የጻፉት አቶ ምሐባው ዓለሙ፤ “ሕዝብን በማነሳሳት ከባድ ወንጀል” በሚል በፖሊስ ተይዘው ለአራት ቀናት ከታሰሩ በኋላ መስከረም 16 ቀን 2004 ዓ.ም በመስቀል በአል ዋዜማ መጽሐፉን ከሚያስተዋውቁበት እና ከሚያሰራጩበት መስቀል አደባባይ በድጋሚ በፖሊስ ተይዘው ካዛንቺስ ወደሚገኘው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ጸሐፊው፣ መጽሐፉን ለምን እንደጻፉና ማን መረጃ እንደሰጣቸው መጠየቃቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

አቶ ምሐባው መስከረም 18 ቀን 2004 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ደረጃ ከተማ ነክ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ “መጽሐፍ በመጻፍ ከባድ ወንጀል” በመፈፀማቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለፀው ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር፡፡
የተጠርጣሪው ጠበቃም ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀበትን ምክንያት እንዲያስረዳ የጠየቁ ቢሆንም ፖሊስ “የማጣራው ነገር ስላለኝ” በማለቱ ፍ/ቤቱ ለሰኞ፣ መስከረም 22 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና ጸሐፊው በቀጠሮው ቀን ፍ/ቤት ሳይቀርቡ መስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት ተጠርተው በዋስ ከእስር መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ “ስንፈልግህ እንጠራሃለን” በመባላቸው በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አስተዳደራዊ ችግሮችን በዝምታ ማለፋችን በቤተክርስቲያን የአስተዳደር ሰዎች ዘንድ ብልሹ አመራር እንደ ትውፊት እንዲቆጠር መደረጉን በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ያሰፈሩት ጸሐፊው፣ የመጽሐፋቸው ዓላማ አስተዳደራዊ ችግሮችን በግልጽ ማሳየትና ለመፍትሔው ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ ከእያንዳንዱ ባለ ድርሻ አካል የሚጠበቀውን የመፍትሔ ሥራ ማሳየት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ ከፍተኛ ብክነት መኖሩን በማስረጃ ያሳዩት ፀሐፊው፤ በተለይም በአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት ብክነቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝ “በዳሰሳ ጥናት ለማረጋገጥ ተሞክሯል” ብለዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የደብር አለቆች በማደሪያ ቤታቸው ሙዳየ ምጽዋቶችን እንደሚቆጥሩ መረጋገጡን ለማጋለጥ ይሞክራሉ፡፡ “በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ያህል ችግር ያለበት ሌላ ምንም ተቋም ሊኖር አይችልም” በሚል በእርግጠኛነት የጻፉት አቶ ምሐባው፤ እርሳቸው በሰበካ ጉባኤ አባልነት ባገለገሉበት ማኅደር ስብሐት ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን የሁሉም የገቢ መሥመሮች ትክክለኛ የገቢ መጠኑ እንደማይታወቅ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከወጪ ገቢ በልዩነት እስከ 3,168,227 ድረስ የት እንደገባ እንደማይታወቅ፤ ከሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2003 ዓ.ም የቀረበውን የሒሳብ ሪፖርት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡በቤተክርስቲያን ታሪክ የቤተክርስቲያን አስተዳደር እንዳሁኑ ዘመን ተበላሽቶ አያውቅም የሚሉት አቶ ምሐባው፤ “በማንኛውም መንገድ እየሆነ ላለው አስተዳደራዊ ብልሽት ሁሉ ቀዳሚ ተጠያቂ የሚሆኑት ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ናቸው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያብራሩ፤ ከእያንዳንዱ ብልሹ ሥራ ጀርባ ፓትሪያሪኩ እንዳሉበት፤ የእርሳቸው እጅ ሳይኖርበት የተፈጠረ ብልሽት ካለም ወቅቱን በጠበቀና ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ የመፍታትና የማረም ሐላፊነትና ግዴታ ስላለባቸው ከተጠያቂነት ነጻ እንማይሆኑ አስረድተዋል፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከተከበቡበት የሥጋ ዝምድና ወጥተው በመንፈሳዊ ዝምድና የሁሉም አባት መሆናቸውን ተገንዝበው፣ በየዘርፉ የሚያማክሩ ባለሞያ ሰዎችን የቅርብ ረዳቶች እንዲያደርጉ የመከሩት ፀሃፊው፤ “የሌቦች መደበቂያ በመሆን ባያገለግሉ መልካም ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ የመጨረሻው የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚጠበቅበት መጠን እየመራ ባለመሆኑ የወቀሱት አቶ ምሐባው፤ ሲኖዶሱ ውሳኔዎቹን ማስፈፀም አለመቻሉን ይጠቁማሉ፡፡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ዕድገት እና ውድቀት በመወሰን ረገድ ወሳኝ የሆኑት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ፍርሃትንና ጥቅመኝነትን አስወግደው፤ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ተቋቁመው ዐቅዶ መሥራትና በዕቅዱ መመራት ዝርዝር ሪፖርት ለመረጣቸው አካል በማቅረብ ቤተክርስቲያን በልማት ጐዳና እንድትገሰግስ፣ አገልጋዮቿም የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው መጣር እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ምእምናንም በብልሹ አመራር የተጠመዱ አገልጋዮችን በማጋለጥ ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት በሦስት ዙሩ ሪፖርት እንዲያቀርቡላቸው በመጠየቅ የቤተክርስቲያኒቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

2 comments:

  1. አቶ ምሐባው፤ የማኅደር ስብሐት ቅድስት ልደታ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ሊቀመንበር መሆናቸውን ማውሳት አያስፈልግ ይሆን ???

    ReplyDelete
  2. gov't should stop its support for aba paulos.now a time when people start to write the truth of our church -OTWeahido,why the gov't intervene????please keep out of religion-the gov't!!!

    ReplyDelete