Tuesday, November 15, 2011

ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት

  • አሰግድ ሣህሉ በድብደባ ወንጀል ክስ መጥሪያ ወጥቶበት እየተፈለገ ነው
  • መ/ር ዘመድኩን በቀለ ለሰዓታት በእስር ቆይቶ ተለቀቀ
  • አሰግድ ሣህሉ ቅዱስ ሲኖዶስ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ አጣጣለው
  • የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በአሰግድ ሣህሉ እና ትዝታው ሳሙኤል ላይ ክስ ሊመሠርት ነው
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 5/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 15/2011)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ባለችበት አዳክሞ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ አልያም ከውስጥ በማተራመስ ለመከፋፈል የሚካሄደውን ሤራ በድልድይነት በማስተሳሰር(ኔትወርኪንግ) እና ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የሚጎርፈውን ከፍተኛ ፈንድ በማሠራጨት እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት አሰግድ ሣህሉ
በድብደባ ሙከራ ወንጀል ክስ ተመሥርቶበት፣ መጥሪያ ወጥቶበት እየተፈለገ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡ ምንጮቹ እንደገለጹት የመናፍቁ አሰግድ ሣህሉ የድብደባ ሙከራ ወንጀል የተፈጸመው ዛሬ፣ ኅዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡30 ላይ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቅጽር ውስጥ ነው፡፡

ሰዓቱ መ/ር ዘመድኩን በቀለ "ማራኪ" ለተሰኘ መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ እና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን"የሰባኪው ሕጸጽ" በተሰኘ መጽሐፋቸው "በሃይማኖት ጉዳይ ያልተማረ፣ ማይም እና ተሐድሶ ነው በሚል ሞራሌን ነክተዋል፤ ከሕዝብ ልብ እንድወጣ አድርገውኛል" በሚል በበጋሻው ደሳለኝ የተመሠረተባቸው ክስ ተቋርጦ መዝገቡ ለፍትሕ ሚ/ር እንዲመለስ ትንት ሚ/ር ዴኤታው ብርሃኑ ጸጋዬ ለቦሌ ፍትሕ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ መሠረት የወትሮውን ዐቃቤ ሕግ ሙሉ ግደይን ተክተው በተገኙት ሌላ ዐቃቤ ሕግ ፊት ይኸው ትእዛዝ በዳኛው ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡ ክሱ ተቋርጦ፣ መዝገቡ ተዘግቶ እንዲመለስ ምክንያት የሆነው መ/ር ዘመድኩንና ዲያቆን ደስታ ጌታሁን የተከሰሱበት ጉዳይ የሃይማኖት በመሆኑ እና ቅዱስ ሲኖዶስምግል ተበዳዩንና መሰሎቹን ሃይማኖት በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት በጥናት ላይ በመሆኑሃይማኖታዊ በሆነ መልኩ በቤተ ክህነቱ በኩል እንዲታይ በማለት እንደሆነ ተገልጧል፡፡
መ/ር ዘመድኩን
በፍትሕ ሚ/ሩ ማሳሰቢያ መሠረት ክሱ መቋረጡ እና መዝገቡ መዘጋቱ በዳኛው ተገልጾ ችሎት መልስ ከሆነ በኋላ ባለጉዳዮችና የችሎቱ ተከታታዮች በመውጣት ላይ ነበሩ፤ በዚህ መሀል ከችሎቱ በራፍ ውጭ በዳኞች ቢሮ ደጃፍ ከመ/ር ዘመድኩን ጋ ወደፊት ቀድመው በማለፍ ላይ የነበሩትን ዲያቆን ደስታ ጌታሁንን አንድ እጅ ከኋላ ማጅራታቸውን ጨምድዶ በመያዝ፣ "በዚህ ብታመልጠን በሌላ እናገሃለን፤ አታመልጠንም!!" እያለ አንገታቸውን ይወዘውዛቸዋል - አሰግድ ሣህሉ ነበር፡፡

እርሳቸውም በሕግ አምላክ በሚል ግለሰቡን ሥርዐት እንዲያደርግ በማስጠንቀቅና ጉዳዩን ለዳኛው በማስረዳት ዳግመኛ በችሎቱ እንዲሠየሙ ሆኗል፤ ዲ.ን ደስታና አሰግድ ወደ ችሎቱ ተያይዘው ገብተው በዳኛው ፊት ከቆሙ በኋላ ዲ.ን ደስታ የተፈጠረውን ነገር ለዳኛው አስረድተዋል፡፡ በሁኔታው ከፍተኛ ብስጭት የገባቸው ዳኛው ተደናግጦ ወደቆመው አሰግድ ፊታቸውን አቅንተው፣ የድብደባ ሙከራው የተፈጸመው በችሎቱ አዳራሽ ውስጥ ቢሆን ኖሮ እዚያው ውሳኔ ይሰጡ እንደነበር በመግለጽ ድርጊቱ ከችሎቱ ውጭ የተፈጸመ በመሆኑ ዲያቆን ደስታ ምስክሮቻቸውን አሰምተው ክስ መመሥረት እንደሚችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት በግብረ ገብ የለሹ አሰግድ ሣህሉ ላይ ክስ ተመሥርቶ፣ ምስክር ተሰምቶ የክስ መጥሪያ ወጥቶበት እየተፈለገ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ መጥሪያው አሰግድ ሣህሉ ለኅዳር ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት እንዲቀርብ የሚያዝዝ ነው ተብሏል፡፡

ከአሰግድ ጋ አብረው በችሎቱ የነበሩት ታሪኩ አበራ፣ ሀብታሙ ሽብሩ እና ናትናኤል የተባሉት ሲሆኑ የአሰግድ አነጋገር ሕገ ወጡ ቡድን እነ መ/ር ዘመድኩንን በተጨማሪ ክሶች በማሸማቀቅ ከፀረ ፕሮቴንታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴያቸው ለመግታት እንደ አንዳንዶቹም ምኞት ከሀገር ወጥቶ እንዲሰደድ ለማስገደድ ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም መዝሙር ቤቱ እና መኖሪያ ቤቱ በፖሊስ የተበረበረውና ንብረቶቹ የተወሰዱበት መ/ር ዘመድኩን በቀለ ከዛሬው ችሎት መጠናቀቅ በኋላ ከ4፡30 - 6፡40 ድረስ በፖሊስ ተይዞ በቅጽሩ ውስጥ ከእስረኞች ጋር ከቆየ በኋላ ችሎቱን ለመከታተል ተገኝተው ከነበሩት የፀረ-ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት አባላት መካከል በዘማሪ ልዑል ሰገድ ጌታቸው(ቋንቋዬ ነሽ) የመኪና ሊቢሬ በቂ ዋስትና በማቅረቡ የዋስ መብቱ ተጠብቆ ሊፈታ ችሏል፡፡

የሕገ ወጦቹ በተከታታይ ክሶች የማስጨነቅ ስልት - ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘና በፀረ - ተሐድሶ አጀንዳ ዙሪያ መሠረተ ሰፊ የምእመኑን ንቅናቄ እየፈጠሩ ከሚገኙት ሥራዎች ግንባር ቀደም ሆነው በ"አርማጌዶን ቪሲዲ"ምክንያት ጨርሶ በመጠላታቸውና ከቤተ ክርስቲያን መድረኮች ላይ ምእመኑ እያነቀ በማውረድ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የመተግበር ርምጃ መውሰድ በመጀመሩ ሳቢያ የተፈጠረ ቀቢጸ ተስፋ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ይህንኑ ቀቢጸ ተስፋ የሚያመለክት ንግግር ባለፈው ሳምንት ታትመው ከወጡት መጽሔቶች በአንዱ ላይ በተስተናገደው ቃለ ምልልስ ላይ በከፋ መልኩ ተስተውሏል፡፡ ቃለ ምልልሱን የሰጠው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግልጽ ተመጻዳቂነቱን በተለያዩ መጽሔቶች ላይ በሚሰጣቸው ቃለ ምልልሶች እያሳየ የሚገኘው ተሐድሶውአሰግድ ሣህሉ ነው፡፡

ተሐድሶው (በአንዳንዶች ዘንድ አቶ ፓስተር ይባላል) አሰግድ ሣህሉ በዚህ ቃለ ምልልሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሐምሌ 2 ቀን 1990 ዓ.ም በአምስት የተሐድሶ ኑፋቁ አራማጆች ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ"ሕጋዊ ያልሆነ ፍትሕ" በማለት አጣጥሎታል - ሕግን በሚያገለግለው የፍትሕ አካል ፊት ለድብድብ የሚጋበዘው አሰግድ ያለ አቅሙና ያለ ብቃቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ለመተቸት መሞከሩ የተለየለት ተመጻዳቂ እና በወቅቱ በሲኖዶሱ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ግለሰቦች (እነ ‹አባ› ዮናስ ጋር) ያለውን የጠበቀ የዓላማ አንድነት ፍንተው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

የአሰግድ ተመጻዳቂነት በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ዋዜማ ላይ በመንበረ ፓትርያክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም የፀረ ፕሮቴስታንታዊ - ተሐድሶ ትዕይንት በማሳየት ሲኖዶስ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በሙሉ ድም ያለ ልዩነት ያስተላለፈውን ውሳኔ ለመጠየቅ የተሰበሰቡትን ሰላማዊ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ "የሰንበት ተማሪ ያልሆኑ፣ ስለሃይማኖታቸው በቂ ዕውቀት የሌላቸው፣ ምንም ዐይነት የሃይማኖት ዝንባሌ የሌላቸው፤ ኦ አባ እያሉ የዘመሩት መዝሙር ዐመፅ እና ድራማ እንጂ መዝሙር አይደለም" በማለት ነቅፏል፡፡

በወቅቱ በሕገ ወጦቹ በኩል የእንቀስቃሴው አስተባባሪ እንደነበር በቃለ ምልልሱ የተናገረው ግብዙ አሰግድ እርሱ ግን፣ "ማንም የነሱን (የተቃዋሚዎቹን) መንገድ እንዳይከተል ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲናገር እንደነበር" በመወሽከት ዋሽቷል፡፡ ለደጀ ሰላም የደረሰው ፊልም ግን አሰግድ ሣህሉ አንዱን የሰንበት ተማሪ በቃሪያ ጥፊ ካልመታሁ እያለ ሲገለገል የሚያሳይ ነው፡፡

ማርሻል አርትስ ሥልጠና (ባለ ጥቁር ቀበቶ) እንደ ሆነ የሚነገርለት አሰግድ በቃለ ምልልሱ ላይ "እንደእነርሱ መደባደብም ይቻላል" ባለው መሠረት ዛሬ ነገሮች በሕግ እና በሕግ ብቻ በሚዳኙበት ችሎት ለጠብ ሲጋበዝ፣ ዛቻውን ማስፈራሪያውን ሲያንጎደጉደው አገኘነው፤ በዚህ ድርጊቱም ለእነ መ/ር ዘመድኩንና ዲያቆን ደስታ ያሰበው ክስ ወደራሱ ተገለበጠበት/ ዞረበት፤ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነትም በዚሁ የአሰግድ ቃለ ምልልስ እና ትዝታው ሳሙኤል በተመሳሳይ መልኩ ለማራኪ መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ ክስ ለመመሥረት እያሰቡበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የአሰግድን ቃለ ምልልስ፣ የሚኒስትር ዴኤታውን ደብዳቤ እና የ1990 ዓ.ም የቅ/ሲኖዶስን ምልዓተ ጉባኤን ቃ መመልከት (HERE) ይችላሉ።

1 comment:

  1. minew mezigebu kendegena endinkesakes mebalun lemin atitsifum

    ReplyDelete