Sunday, November 6, 2011

አባ ሰረቀ ከሹመት ታግደው ይቆያሉ፤ ንቡረ እድ አባ ገ/ማርያም የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ሆነው እንደተሾሙ እየተነገረ ነው


 አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ከተጠረጠሩበት የሃይማኖት ሕጸጽ ነጻ መሆናቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በማንኛውም ቦታ በሓላፊነት እንዳይመደቡ ዛሬ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንደወሰነ ዘግይተው የደረሱን የመረጃ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ ደብዳቤ ደርሷቸው የነበሩት ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ እንዲሆኑ መወሰኑን እነዚሁ ምንጮች ጨምረው አመልክተዋል፡፡ ርግጡን ቆይተን እናየዋለን፡፡


ትናንት የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ እንዲሆኑ ‹በፓትርያሪኩ እና በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ስምምነት ተመርጠዋል› የተባሉት አባ ኅሩይ መሸሻ መምሪያውን በሲኖዶሱ ከተላለፉት ውሳኔዎች አኳያ አስተባብሮ የመምራት ጉዳይ ጥያቄ ቢነሣባቸውም ለጊዜው የተሰማባቸው ለውጥ እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡

ዛሬ ከቀትር በፊት በነበረው የስብሰባው ማጠናቀቂያ ላይ በተላለፈው በዚሁ ውሳኔ የፓትርያርኩ የምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት ሹመት ሐሳብ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በቋሚ ሲኖዶስ ተመርጦ እስኪቀርብ ድረስ እንዲቆይ፣ የቀድሞው ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ግን ቀደም ሲል እንደተገለጸው ወደ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሥራ አስኪያጅነት የመዘዋወራቸው ጉዳይ አይቀሬ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 25/2004 ዓ.ም)
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

No comments:

Post a Comment