- “የቀረበብኝ ‘የሐሰት ውንጀላ’ ለመሥራት ስለማያስችለኝ የዕረፍት ጊዜ ይሰጠኝ” (አባ ሠርቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል)
- የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድርጅታዊ ዲዛየን እንዲፈተሽ የጠየቁት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የኮንትራት ውል እንዲቋረጥ ታዟል
- በድሬዳዋ ቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤተክርስቲያን ግንባታ ከ1.8 ሚልዮን ብር በላይ የደረሰበት አልታወቀም
- የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፓትርያርኩ በመሾማቸው ተቃውሞ ያቀረቡት አካላት፣ “እንከን የሌለበትን ንጹሕ እምነታቸውን ጥላሸት የቀቡ ከሳሾቻቸው” ማንነት እና የክሱ ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፤
- ‹ውንጀላው› እስከሚጣራ ድረስ “እጅግ መራራ ተጋድሎ በከፈሉበትና ውጤት ባሳዩበት” የቀድሞ ቦታቸው እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፤
- “እውነትንና ፍትሕን” ከቤተ ክርስቲያን እንደሚሹ “እውነትና ፍትሕ” ከቤተ ክርስቲያን ከጠፋ ግን ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመው መብታቸውን በማስከበር ከሳሾቻቸውን ለመበቀል ዝተዋል ::
- ከአዲሱ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሓላፊ ጋራ ርክክብ ያደርጋሉ፤
የተቃውሞው መንስኤ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም የቀድሞውን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ መምህር አባ ሠርቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልን በጠቅላይ ቤተክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አድርገው መሾማቸው ነው ተብሏል፡፡
የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ስለተፈጠረው የሥራ አለመግባባት ተጣርቶ በቀረበለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ መምህር አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ደመወዛቸውን እንደያዙ ወደ ሌላ መምሪያ እንዲዛወሩ፣ አለባቸው የተባለውን የእምነት ሕፀፅ በምልአተ ጉባኤው የተሰየሙት ሰባት ሊቃነጳጳሳት ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በመሆን ማስረጃዎችን አሰባስበው፣ መርምረውና አጣርተው ለምልአተ ጉባኤው እንዲያቀርቡ፣ የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ እና የማደራጃ መምሪያው ውስጠ ደንብ ከቤተክርስቲያኒቷ ሕግ እና ሥርዓት እንዲሁም ከጊዜው ሁኔታ ጋራ ተጣጥሞ እንዲሻሻል ነበር የወሰነው፡፡
ፓትርያሪኩ የመምህር አባ ሰረቀ ብርሃንን ሹመት በደብዳቤ ከማሳወቃቸው በፊት ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም ስለ ሹመቱ መረጃ የደረሳቸው የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ አባላት፣ መምህር አባ ሰረቀ ብርሃን ወደ ሌላ መምሪያ እንዲዛወሩ እንጂ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ አለመወሰናቸውን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተመርጦ ለቋሚ ሲኖዶስ ከቀረበ በኋላ ምልአተ ጉባኤው ሲስማማበት በፓትርያሪኩ የሚሾም መሆኑን በመጥቀስ ፓትርያሪኩን እንደተቃወሟቸው ተዘግቧል፡፡ ከምልአተ ጉባኤው አባላት ተቃውሞ ቀደም ሲል የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስም የመምህር አባ ሰረቀ ብርሃንን ሹመት በመቃወም ከሐላፊነታቸው እንደሚለቁ አስታውቀው ነበር ተብሏል፡፡ በእኒህ ጠንካራ ተቃውሞዎች ምክንያት ሕገወጥ ነው የተባለው ሹመት በቋሚ ሲኖዶስ ቀርቦ እስኪወሰንበት ድረስ በይደር እንዲቆይ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መካከል መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ተገልጧል፡፡
ሆኖም ፓትርያሪኩ ጥቅምት 27 ቀን በአድራሻ ለመምህር አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል በግልባጭ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለመንበረ ፓትርያሪኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ መ/ር አባ ሰረቀ ብርሃን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ ያስታውቃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ለፓትርያሪኩ እንዳቀረቡ መነገሩን ተከትሎ እየተካረረ በሄደው ውዝግብ አቡነ ጳውሎስ ለመ/ር አባ ሰረቀ ብርሃን የሰጧቸው ሹመት ስለመሻሩ እና በምትኩ አባ ሰረቀ ብርሃን ከዋና ሥራ አስኪያጁ በሚሰጣቸው የሥራ መደብ እየሠሩ እንዲቆዩ በአቡነ ጳውሎስ ስለመታዘዙ ጥቅምት 29 ቀን በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ በሆኑት አቡነ ገሪማ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡
በፓትርያሪኩ መልካም ፈቃድ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲያገለግሉ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የገለጹት መ/ር አባ ሰረቀ ብርሃን በበኩላቸው፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይቀርብባቸው ሕግን ብቻ መሠረት አድርጐ እንዲያገለግል አጥብቀው የተከታተሉት የማኅበረ ቅዱሳን አካላት የውንጀላ ሰነድ በማዘጋጀት በንጹሕ እምነታቸውና ማንነታቸው ላይ የሐሰት ስም ማጥፋት እንዳቀረቡባቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ መምህር አባ ሰረቀ ብርሃን ለፓትርያሪኩ በጻፉትና በንጹሕ እምነታቸው ላይ እየደረሰባቸው ላለው ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል አፋጣኝ መልስ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት በዚሁ ደብዳቤ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋራ በመሆን ለከፈሉት “እጅግ መራራ ተጋድሎ እና ላሳዩት ውጤት” መልካም መልስ ማግኘት ሲገባቸው የተፈፀመባቸው በደል ኢ-ሃይማኖታዊ እና ኢ-ሰብአዊ በመሆኑ ጉዳዩ እስከሚጣራ ድረስ የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹የእውነት እና የፍትሕ ምንጭ›› ከሆነችው ቤተክርስቲያን እውነትና ፍትሕ ከጠፋ ግን የሀገሪቱን ሕገ መንግስት በመጠቀም መብታቸውን እንደሚያስከብሩ አሳስበዋል፡፡
ከዚሁ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሹመት እና ዝውውር ጋራ በተያያዘ መ/ር አባ ሰረቀ ብርሃን በአቡነ ጳውሎስ ሊሾሙበት በነበረው የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቦታ እስከአሁን በመሥራት ላይ የሚገኙት ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ የአዲስ አበባ ሃ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነትንም ደርበው እንዲሠሩ፤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና በሀ/ስብከቱ ውስጥ ሰፍኗል የተባለውን በዝምድ እና በጉቦ ቅጥር፣ ዝውውር እና ሹመት የመፈፀም አሠራር በመቆጣጠር አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸው የሚነገርላቸው ንቡረ እድ አባ ገብረማርያም ገ/ሥላሴ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ ሆነው እንዲሠሩ መወሰኑን ጥቅምት 29 ቀን በአቡነ ገሪማ ፊርማ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተላከው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ በዚህም መሠረት ንቡረ እድ ኤልያስ የበፊቱ ሥራ አስኪያጅ ያስመዘገቡትን ውጤት ለማስጠበቅ የበለጠ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ተሰጥቷል፤ ለንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃም በትላንትናው ዕለት በሀ/ስብከቱ ሠራተኞች አቀባበል እንደተደረገላቸው ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የጠቅላይ ቤተክህነቱን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች የዳሰሰ ጥናታዊ ምልከታ በማቅረብ ድርጅታዊ ዲዛይኑ እንዲሻሻል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተክህነቱ በየጊዜው ያወጧቸው ደንቦች እና መመሪያዎች ተጣጥመው መዘጋጀት እንደሚገባቸው ጥናት ያቀረቡት የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ የሥራ ኮንትራት ውል ከትላንት ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እንዲቋረጥ ለልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ትእዛዝ መሰጠቱን የቤተክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡት ጥናት በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቀርቦ ከታየ በኋላ “በጥሩ ሁኔታ የተቀነባበረና ተደማጭነት ያለው የቅድመ ጥናት ንድፈ ሃሳብ (ፕሮፖዛል) ነው” በሚል ምስጋና እንደተቸረው ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም በቋሚ ሲኖዶስ እና በአስተዳደር በሚሰየሙ የሕግ እና የአስተዳደር ባለሞያዎች ተጠንቶ ለግንቦቱ የሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑ ተገልጧል፡፡
“በጠቅላይ ቤተክህነቱ ደንቦች እና መመሪያዎች ተጣጥመውና በአስፈጻሚዎች ዘንድ በየደረጃው በቂ ግንዛቤ አግኝተው የሠራተኞች አቅም የሚጐለብትበትና ውጤታማ የሚሆኑበት፣ ተዋረዱን የጠበቀ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚጠናከርበት አሠራር ለማስፈን ያስችላል የተባሉ የመፍትሔ ሀሳቦች ቀርበውበታል” የተባለው ይኸው ሒስ እና መፍትሔ አዘል ጥናት ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ የሥራ ኮንትራት ውል መቋረጥ መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮቹ ጨምረው ጠቁመዋል፡፡ ከእርሳቸውም ጋራ የአስተዳደር መምሪያው ሓላፊዋ መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ እና የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ ሓላፊ ወ/ሮ ጽጌረዳ ሥራ ኮንትራት ውል እንዲቋረጥ ለኮሚሽኑ ትእዛዝ መተላለፉም ተሰምቷል፡፡ የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ትእዛዙን መቃወማቸውን ምንጮቹ ጨምረው አመልክተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በድሬዳዋ ሀ/ስብከት በ1998 ዓ.ም ተጀምሮ በ2000 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የቅዱስ ገብርኤል ሕንፃ ቤተክርስቲያን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ላይ በተደረገ ኦዲት ከ1.8 ሚሊዮን ብር በላይ ጉድለት እንደተገኘ ተዘግቧል፡፡ እስከአሁን ለሕንፃው ሥራ 11 ሚሊዮን ያህል ብር ከምእመናን እና በጐ አድራጊዎች መሰብሰቡን የከተማው ምእመናን ለዝግጅት ክፍላችን የገለጹ ሲሆን ጉድለቱ በጠቅላይ ቤተክህነቱ ኦዲተሮች ከተረጋገጠውም በላይ ወደ ብር አምስት ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አብራርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግንባታው ከሚገባው በላይ እንደተጓተተ፣ በሕንፃው ጉልላት አካባቢም ከዲዛየኑ ውጭ መሠራቱን (መጣመሙን) ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በበጐ ልብ ተነሳስተው በተሻለ ወጪ በታቀደው ጊዜ ግንባታውን ለመጨረስ የሚችሉ፣ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ መልካም ስም ያላቸው ባለሞያዎች ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ተደርገው “የፓትሪያሪኩ ዘመድ” በሚል ተልከው የመጡ የግንባታ ሠራተኛ እና ሌሎች ሁለት ተባባሪዎቻቸው ከሀ/ስብከቱ አንዳንድ ሓላፊዎች ጋራ በመመሳጠር ምእመኑና አገልጋዩ በድሃ አቅሙ የሚያዋጣው ገንዘብ፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ እና ድንጋይ ለግል ጠቅማቸው በማዋል አላግባብ በመበልፀግ ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ምእመናኑ ምሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
(ከደጀ ሰላም፤ ኅዳር 2/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 12/2011)
- አባ ሰረቀ የተፈጸመባቸው “ከፍተኛ የስም ማጥፋት ውንጀላ” በሥራቸው ለመቀጠል እንደማያስችላቸው ገለጹ
- የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በፓትርያርኩ በመሾማቸው ተቃውሞ ያቀረቡት አካላት፣ “እንከን የሌለበትን ንጹሕ እምነታቸውን ጥላሸት የቀቡ ከሳሾቻቸው” ማንነት እና የክሱ ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፤
- ‹ውንጀላው› እስከሚጣራ ድረስ “እጅግ መራራ ተጋድሎ በከፈሉበትና ውጤት ባሳዩበት” የቀድሞ ቦታቸው እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፤
- “እውነትንና ፍትሕን” ከቤተ ክርስቲያን እንደሚሹ “እውነትና ፍትሕ” ከቤተ ክርስቲያን ከጠፋ ግን “ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመው” መብታቸውን በማስከበር ከሳሾቻቸውን ለመበቀል ዝተዋል
- ከአዲሱ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ሓላፊ ጋራ ዛሬ ርክክብ ያደርጋሉ፤
(ደጀ ሰላም፤ ኅዳር 2/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 12/2011)፦ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ዋና ሓላፊነታቸው ተነሥተው የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ የተደረጉት አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል የቀረበባቸው ከባድ “የስም ማጥፋት ወንጀል” ሳይጣራ በሥራቸው ለመቀጠል የማይቻላቸው በመሆኑ ከሥራ ጓደኞቻቸው ጋራ በመሆን “እጅግ መራራ ተጋድሎ ከፍዬበታለሁ፤ መልካም ውጤትም አሳይቼበታለሁ” በሚሉበት በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፤ ለአዲሱ የማደራጃ መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ኅሩይ መሸሻ የመምሪያው ሠራተኞች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በትናንትናው ዕለት ደግሞ ከቆሞስ አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ጋራ ርክክብ እንደሚካሄድ እየተጠበቀ ነበር፡፡
አባ ሰረቀ “በንጹሕ እምነቴ ላይ እየደረሰብኝ [ላ]ለው ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥልኝ ስለመጠየቅ” በሚል ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በጻፉት ሁለት ገጽ ደብዳቤ፣ “በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በመደበቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ፈጥሯል” ያሉት ማኅበረ ቅዱሳን እርሳቸውና “የሥራ ባልደረቦቻቸው” ባደረጉት መራራ ተጋድሎ “የተደበቀ ሥራው በሁሉም ወገን እየተገለጠ” በመምጣቱ ከዛቻና ማስፈራራት ባሻገር “በማንነታቸው እና በንጹሕ እምነታቸው” ላይ ጥላሸት እየቀባ ከፍተኛ ዘመቻ እንደከፈተባቸው አስታውቀዋል፡፡
ጥቅምት 25 ቀን 2004 ዓ.ም የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “የማ/መምሪያው እና የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አለመግባባት” በሚል በተመለከተው አጀንዳ ተራ ቁጥር 4፡- የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና ማኅበረ ቅዱሳንን ጭምር አስተባብሮ በመምራት ረገድ በከፍተኛ ድክመት የገመገማቸው እና አለባቸው የተባለውን የእምነት ሕጸጽ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በመሆን በማስረጃ መርምሮ የሚያቀርብ ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት ኮሚቴ ያቋቋመባቸው አባ ሰረቀ “የተፈጸመባቸው ከባድ የስም ማጥፋት ወንጀል” በማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከባድ ችግር የሚደቅንና “በማንነታቸው ላይ የተፈጸመ ግድያ(Character assassination)” አድርገው የሚቆጥሩት በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ ሳይሰጠው በአስቸኳይ እንዲጣራ ተማፅነዋል፡፡
ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም በራሳቸው ማኅተም በጻፉት ደብዳቤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አድርገው “በመልካም ፈቃዳቸው” በመደቧቸው ቦታ ላይ እንዳይሠሩ የተቃወሟቸው አካላት እና “ንጹሕ እምነታቸውን ጥላሸት የቀቡ” ከሳሾቻቸው ማንነት እንዲነገራቸው፣ ለክሳቸውም መልስ መስጠት ይቻላቸው ዘንድ የክሱ ጽሕፈት በዝርዝር እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡
ፓትርያርኩ ለአባ ሰረቀ የሰጧቸው ሕገ ወጥ ሹመት ደጀ ሰላምን ጨምሮ በየደረጃው በገጠመው ከባድ ተቃውሞ የተነሣ ጥቅምት 29 ቀን 2004 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ በተጻፈ ደብዳቤ የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው እንደተሻረና ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሚመድቧቸው ቦታ እንዲሠሩ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደታዘዘ የሚገልጽ ደብዳቤ ለአባ ሰረቀ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት አባ ሰረቀከሕፃናት፣ ወጣቶች እና ማኅበረ ቅዱሳን ንክኪ ርቀው “ወደሚሠሩበት” የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ መመደባቸው ተገልጧል፡፡
ይሁንና ማኅበረ ቅዱሳንን “ሰንሰለቱን ባልጠበቀ ማመልከቻ አቀራረብ” የሚከሱት ግብዙ አባ ሰረቀ የቅርብ አለቃቸው የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ተሻግረው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባቀረቡት አቤቱታ “የሐሰት ውንጀላ” ነው ያሉት ክስ በተሰጣቸው የሥራ መደብ ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የማያስችላቸው በመሆኑ እስኪጣራ ድረስ ቀድሞ በነበሩበት ቦታ እንዲቆዩ አልያም የዕረፍት ጊዜ እንዲሰጣቸውጠይቀዋል፡፡ የቀረበባቸው “ውንጀላ” ተጣርቶ እውነትንና ፍትሕን ከቤተ ክርስቲያን የማያገኙ ከሆነ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመው መብታቸውን በማስከበር ‹ከሳሾቻቸውን› እንደሚበቀሉ ዝተዋል፡፡
ይገርማል! አባ ሰረቀ “የእውነት እና ፍትሕ ምንጭ ናት” እንደሆነች በአቤቱታቸው ከጠቀሷት ቤተ ክርስቲያን በላይ እና በፊት ትምክህታቸው በሌላ ኖሯል! እንደ ምንኩስናቸው ቢሆን ኖሮ ይህ ዐይነቱ አቋም ከአባ ሰረቀ አይጠበቅም ነበር፡፡ ስለዚህም ይሆን ማኅበረ ቅዱሳን “ፖሊቲካ እና ሃይማኖትን እያጣቀሰ ስለ መሄዱ”የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙበትን የመስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም ስብሰባ አዘውትረው በጀብደኛነት የሚተርኩት? የአባ ሰረቀ ግብዝነት(hypocrisy) ማኅበረ ቅዱሳንን በሚከሱበት “ሰንሰለቱ ያልጠበቀ የደብዳቤ አቀራረብ” ብቻ ሳይሆን እርሳቸው ራሳቸው በአሜሪካ ሳሉ በራሳቸው አነጋገር “ማጣቀስ” ብቻ ሳይሆን ሲያደበላልቁት በቆዩትና መንግሥት በሚገባ በሚያውቀው ፖሊቲካዊ አሰላለፋቸውም ጭምር የሚገለጽ ነው/ዝርዝሩን በቆይታ እንመለስበታለን/፡፡
ከአባ ሰረቀ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው እንደሚነሡ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እየተስተዋሉ የሚገኙት ውሳኔውን ለማዳፈን የሚጥሩ ርብርቦች - አባ ሰረቀ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ፕሮጀክት ሕንብርት (መቋጠሪያ ነጥብ ወይም ውል)፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ደግሞ የፕሮጀክቱ ገዥ መሬት ለማድረግ የነበረውን የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ስትራቴጂእንደሚያመለክት እየተገለጸ ነው፡፡
ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም ምልአተ ጉባኤው አባ ሰረቀ ከማደራጃ መምሪያው ተነሥተው ደመወዛቸውን እንደያዙ ወደ ሌላ መምሪያ እንዲዛወሩ፣ ሃይማኖታዊ ሕጸጻቸውም እንዲመረመር በሙሉ ድምፅ ያለ ልዩነት የተላለፈው ውሳኔ በአማን ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ከውስጥ እና ከውጭ በማጠራቀቅ ለመከፋፈል አልያም ባለችበት አዳክሞ ማንነቷን ወደ ፕሮቴስታንታዊነት ለመለወጥ ለተሸረበው የኑፋቄ ፕሮጀክት ከባድ ምት ነው ለማለት እንደፍራለን!!
ደጀ ሰላማውያን፣ በቀጣይ ቅዱስ ሲኖዶሳችን በሙሉ ድምጽ ለወሰነው ውሳኔ ተፈጻሚነት በጽንዓት እንደምንሠራ እየገለጽን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን፣ ለታሪክም መዘክር ይሆን ዘንድ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም በአባ ሰረቀ ላይ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2004 ዓ.ም በስምንት የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቁ አራማጅ ማኅበራት እና በሕገ ወጥ ሰባክያን ላይ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ቃለ ጉባኤ እና ሌሎች ተከታይ ደብዳቤዎችን እንድትመለከቱ (ፒ.ዲ.ኤፉን ይክፈቱት)እንጋብዛለን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment