Wednesday, November 2, 2011

የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት እና ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔውን እንዲያጤን ጠየቁ


(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 22/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 2/2011/ )፦ የቅዱስ ሲዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 21/2004 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ለዲሲ እና ለካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት የተመደቡትን የአቡነ ፋኑኤል ሹመት የቀሰቀሰውን የምዕመናንን ቁጣ ተከትሎ በሀ/ስብከቱ  ሥር የሚገኙ  11 አብያተ ክርስቲያናትም አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ ለቅዱስ ሲኖዶስም ባለ 5 ገጽ መልእክት አስተላልፈዋል። “በሰሜን አሜሪካ አሁን የሚታየው ችግር ተወሳስቦ ተወሳስቦ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው ከመጀመሪያው ጀምሮ  የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የማስጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ ባለመሰራቱና በወቅቱ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ  አስተዳደራዊ ችግሮች ሳይፈቱ በመቅረታቸው ነው” ያለው መግለጫው

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ  ግን የተሻለ  የአህጉረ ስብከት አደረጃጀት እየታየ በመምጣቱና የቤተክርስቲያን አንድነት እንደሚያስፈልግ በመረዳት  በሀገረ ስብከት ሥር የሚካተቱ አብያተ ክርስቲያናትም ቁጥር” እየጨመረ መምጣቱን አስታውሶ “በየትኛውም መልኩ ቢሆን  በአሜሪካ ደረጃ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ባልጠበቀ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያንን የመለያየት እና ለተለያዩ ከቤተክርስቲያን ውጭ ለሆኑ አመለካከቶችና አጀንዳዎች  ቤተክርስቲያንን አሳልፎ የሚሰጥና የቤተክርስቲያንን ክብር” የሚቀንስ መሆኑን አውስቷል። 

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት በብዕ አቡነ አብርሃም በርካታ ተግባራት እንዳከናወኑ፣ በዋሽንግተን ዲሲ መንበረ ጵጵስና ማቋቋማቸውን፤ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት መባረካቸውን፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ የምእመናን ቁጥር መጨመሩን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለው ግንዛቤ ማደጉን መግለጫው አውስቶ በብዕነታቸው የተጀመረውን መልካም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢደረግ ለቤተ ክርስቲያን ያለው ተጠሜታ ከፍተኛ መሆኑን የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት እና ካህናት አስምረውበታል

በተለይም አሁን በቅ/ሲኖዶስ ተሹመዋል የተባሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል ወደ አሜሪካ እንዲሔዱ መወሰኑ ሀ/ስብከቱ የጀመረውን አገልግሎት በብዙ ርምጃ ወደኋላ የሚጎትት መሆኑን አውስተው በሚከተሉት ምክንያቶች ማለትም፦
  • ከዚህ በፊት ያገለገሉበትና  አሁንም እየመጡ የሚያርፉበትን የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል በቤተክርስቲያን መዋቅር  ማስገባት ያልቻሉ ፤ቤተክርስቲያኑ በሀገረ ስብከት ስር ያልተካተተና ፓትርያርኩም ሆነ የብጹዓን አባቶች ስም የማይነሳ በመሆኑ
  • በሀገር ውስጥ በተለይም በሲዳሞ ሀገረ ስብከት የፈጸሙት አስተዳደራዊ ችግር በሰፊው እዚህ በሚኖሩ ምእመናን  የተሰማና ያሳዘነ ከመሆኑ በተጨማሪ እስካሁንም መፍትሔ ያላገኘ በመሆኑ
  • ከዚህ በፊት በአሜሪካን እንዲያገለግሉ ቢመደቡም  በነበራቸው  ችግር ምክንያት  ከካህናትና ከምእመናን  ባላቸው አለመግባባት የተነሳ በቅዱስ ውሳኔ መነሳታቸው  የሚታወስ በመሆኑ፦
  • በሀገረ ስብከቱ ሪፖርት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት  በመተላለፍ በአሜሪካ  የፈጸሙት ተግባር የታወቀና  በቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም  እስከመወቀስ የደረሱበት ጉዳይ በመሆኑ
የእርሳቸው አሜሪካን መቆጣጠር አደገኛ መሆኑን፣ “በአሜሪካ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር ሊኖራቸው የሚችለው ሚና በጣም አስቸጋሪ” እንደሚሆን አበክረው ገልጸዋል። ስለዚህም “ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ይደረግ ከተባለ ግን የቤተክርስቲያን አንድነት የበለጠ የሚናጋ፤ የቤተ ክርስቲያን እና አህጉረ ስብከት መዋቅር የሚዳከምና ሕዝበ ክርስቲያኑንም ለአባቶች ላይላቸውን ክብር የሚቀንስ እና ምእመናንንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ” እንደሚፈጠር መግለጫው አትቷል።
በመጨረሻም “የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሰላም ለመጠበቅ ሲባልና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአሜሪካ የሚገኙ ካህናትና ምእመናንን ድምጽ መስማት አባታዊ ኃላፊነት  እንዳለባችሁ በማመን  የሚከተሉት ሶስት አቤቱታ እናቀርባለን
1.      በቅድሚያ አሜሪካ ያለውን ችግር የሚያጠና  ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ  በመወከል  እንዲጠና እንዲደረግና ከሁሉም አቅጣጫ ያለሁን ሁኔታ እንዲመለከት እናተደረሰውን ጥናት መነሻ በማድረግ ያሉትን አህጉረ ስብከት ለማጠናከር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ቢደረግ
2.     ይህ ጥናት እስከሚደረግ ድረስ  አሁን የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምደባ በድጋሚ እንዲታይ እና ቢያንስ ለቀጣዩ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲዘገይ ቢደረግ
3.     የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በአካል ተገኝተው ዝርዝር ሁኔታውን እስኪያስረዱ ድረስ ጊዜ እንዲሰጣቸው፣” ሲል መግለጫው ይደመድማል።  

የመልእክቱ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ሠፍሯል።
ቸር ወሬ ያሰማን፤ አሜን።


++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።
ቀን --- ጥቅምት 21 2004 ዓ. ም

በአሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር  ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት
 ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ የቀረበ  አስቸኳይ አቤቱታ

በስብሰባው የተገኙ ሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ዝርዝር
  1. ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ባልቲሞር
  2.  ምሥራቀ ፀሐይ አቡነ ተክለ ይማኖት አሌክሳንደሪያ
  3.   መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
  4.   ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ሉዊቪል
  5.  አንቀጸ ምህረት በዓታ ለማርያም ሻርለት
  6.  መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አትላንታ
  7.  ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወአቡነ አረጋዊ
  8. ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ  ታምፓ
  9.  ደብረ ዕንቁ ቅድስት ማርያም ሜምፊስ
  10.  ደብረ ብርሃን ኪዳነ ምህረት ካንሳስ ሲቲ
  11.   ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ኦክላሆማ ሲቲ
  12.  የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን  ቨርጂኒያ
  13.  አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ቨርጂኒያ ቢች

አቤቱታ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ  አገልግሎት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ለቤተክርስቲያኒቱ እድገት መሰናክል የሆኑ በርካታ ፈተናዎች ያጋጠሙ ሲሆን አብዛኛዎች እነዚህ ፈተናዎች በእምነቱ ተከታይ በሆኑ  አንዳንድ ሰዎች መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል። በአሜሪካ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ፤ ካህናትና ምእመናን አንድነት ቢኖራቸው ኖሮ ዛሬ በኢትዮጵያ  ውስጥ ያሉ ገዳማትን አብነት ት/ቤቶችንና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በመርዳት ደረጃ  የሚኖራቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ይሆን ነበር ፤ ነገር ግን መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ የተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ሊሰጣቸው ስላልተቻለ አሁን ለምንገኝበት የተወሳሰበ ሁኔታ ላይ ተደርሷል። 
በሰሜን አሜሪካ አሁን የሚታየው ችግር ተወሳስቦ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰው ከመጀመሪያው ጀምሮ  የቤተክርስቲያን መዋቅር የማስጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ ባለመሰራቱና በወቅቱ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ  አስተዳደራዊ ችግሮች  ሳይፈቱ በመቅረታቸው ነው። ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ  ግን የተሻለ  የአህጉረ ስብከት አደረጃጀት እየታየ በመምጣቱና የቤተክርስቲያን አንድነት እንደሚያስፈልግ በመረዳት  በሀገረ ስብከት ሥር የሚካተቱ አብያተ ክርስቲያናትም ቁጥር እየጨመሩ መጥቷል።  ከዚህም በመነሳት በአሁኑ ጊዜ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት የተጠናከረ የአብያተ ክርስቲያናት  አንድነት እየታየ የመጣ ሲሆን ምእመናን ስለ ቤተክርስቲያን አንድነት ያላቸው ግንዛቤ አድጓል ።
አሁን በአሜሪካ  እየተደረገ ያለውን የቤተክርስቲያንን መዋቅር የማስጠበቅ ጉዳይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ ደጋፍ የሚያስፈልገው ሲሆን  በአሁኑ ወቅት በሰሜን አሜሪካ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ  የቤተክርስቲያንን መዋቅር የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑንም ማስገንዘብ እንወዳለን ።  በየትኛውም መልኩ ቢሆን  በአሜሪካ ደረጃ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ባልጠበቀ መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያንን የመለያየት እና ለተለያዩ ከቤተክርስቲያን ውጭ ለሆኑ አመለካከቶችና አጀንዳዎች  ቤተክርስቲያንን አሳልፎ የሚሰጥና የቤተክርስቲያንን ክብር የሚቀንስ መሆኑ የታወቀ ነው።
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በብጹዕ አቡነ አብርሃም በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን  በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሽንግተን ዲሲ መንበረ ጵጵስና ተቋቁሟል፤ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተዋል፤ ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡ የምእመናን ቁጥር ጨምሯል ፤ስለ ቤተክርስቲያን አንድነት ያለው ግንዛቤ አድጓል። ይህንን ስንመለከት በብጹዕነታቸው  የተጀመረውን መልካም ተግባር   ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቢደረግ  ለቤተክርስቲያን ያለው ተጠሜታ ከፍተኛ ነው ብለን እናምናለን ።
 ከዚህ በፊት ለቅዱስ ሲኖዶስ መስከረም 30 2004 ዓ.ም  ቀን በተጻፈ ደበዳቤ ላይ እንደተገለጸው  የሀገረ ስብከቱን እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ  የበለጠ ግንዛቤ እዳገኘ እናምናለን። ይሁን እንጂ በትላንት እለት ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም  ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈው  ውሳኔ በአሜሪካ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ብጹዓን አባቶች ተነስተው ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል መመደባቸውን ከተለያዩ ምንጮች ሰምተናል። ምንም እንኳን  ቅዱስ ሲኖዶስ ብጹዓን አባቶችን የማንሳትና የመመደብ ሙሉ ሥልጣን ቢኖረውም  እኛም እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነት  የተሰማንን ሐዘን ለቅዱስ ሲኖዶስ ስናቀርብ በቀና ልቦና ቅዱስ ሲኖዶስ ይመለከተዋል  ብለን በማመን ሲሆን  በተጨማሪም በዚሁ በአሜሪካ የምንኖር  እንደመሆናችን በሀገሩ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ፤ የአብያተ ክርስቲያናትን ችግርና የምእመናንን ስሜት በተመለከተ የተሻለ መረጃ ለቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት ማቅረብ እንችላለን ብለን በማመን ያለንን ሀሳብ ለመግለጽ ተገደናል።  
በእኛ አመለካከት ለቤተክርስቲያን አንድነት ለማጠናከር ጥሩ የሚሆነው በሰሜን አሜሪካ የሚመደቡ አባቶች ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ በተከሰቱ ችግሮች ያልተሳተፉ እና በበሰለ ሁኔታ ነገሮችን   ተመልክተው ውሳኔ የሚሰጡ፤ ካህናትና ምእመናንን የማግባባት መንፈስ ያላቸው ፤ በአባትነት ፍቅር ሰዎች መያዝ የሚችሉ ቢሆኑ መፍትሔ ለማምጣትና አንድነቱን ለማጠናከር አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለን እናምናለን።
የሰማነው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማለትም ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ ሁለት አህጉረ ስብከት  ተመድበው እንዲያገለግሉ  የተላለፈው  ውሳኔ በምን ሚዛን ታይቶ ውሳኔ ላይ እንደ ተደረሰ  ግራ ቢያጋባንም የተመደቡትን አባት (ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል)  በተመለከተ ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ማስታወስ እንወዳለን፦
·        ከዚህ በፊት ያገለገሉበትና  አሁንም እየመጡ የሚያርፉበትን የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል በቤተክርስቲያን መዋቅር  ማስገባት ያልቻሉ ፤ቤተክርስቲያኑ በሀገረ ስብከት ስር ያልተካተተና ፓትርያርኩም ሆነ የብጹዓን አባቶች ስም የማይነሳ በመሆኑ
·        በሀገር ውስጥ በተለይም በሲዳሞ ሀገረ ስብከት የፈጸሙት አስተዳደራዊ ችግር በሰፊው እዚህ በሚኖሩ ምእመናን  የተሰማና ያሳዘነ ከመሆኑ በተጨማሪ እስካሁንም መፍትሔ ያላገኘ በመሆኑ፡
·        ከዚህ በፊት በአሜሪካን እንዲያገለግሉ ቢመደቡም  በነበራቸው  ችግር ምክንያት  ከካህናትና ከምእመናን  ባላቸው አለመግባባት የተነሳ በቅዱስ ውሳኔ መነሳታቸው  የሚታወስ በመሆኑ፦
·        በሀገረ ስብከቱ ሪፖርት ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደተገለጸው የቤተክርስቲያንን ሥርዓት  በመተላለፍ በአሜሪካ  የፈጸሙትን ተግባር የታወቀና  በቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም  እስከመወቀስ የደረሱበት ጉዳይ በመሆኑ
በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱትና ከሌሎችም ጉዳዮች በመነሳት በእኛ ግንዛቤ በአሜሪካ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማጠናከር ሊኖራቸው የሚችለው ሚና በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለን እናምናለን። ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ይደረግ ከተባለ ግንየቤተክርስቲያን አንድነት የበለጠ የሚናጋ ፤ የቤተክርስቲያን እና አህጉረ ስብከት መዋቅር የሚዳከምና ሕዝበ ክርስቲያኑንም  ለአባቶች ላይ አላቸውን ክብር የሚቀንስና እና ምእመናንንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ይፈጠራል ብለን እንሰጋለን ።
ለቅዱስ ሲኖዶስ በሀገረ ስብከቱ ሥር የምንገኝ አብያተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ጉባኤ የደረስንበትን ውሳኔ በቃለ ጉባኤ በተደገፈ ሁኔታ ያቀረብነው ሪፖርት ሚዛን ሳይደፋ ከመዋቅር ውጭ የሆኑ አብያተክርስቲያናት ያቀረቡት ከሥርዓት የወጣ አቤቱታ ተደማጭነት አግኝቶ ይህ ውሳኔ  የሚያበቃ ውሳኔ መወሰኑ ከፍተኛ ሐዘን ፈጥሮብናል ።
የቤተክርስቲያንን  ውሳኔ ተግባራዊ  ለማደረግ  ሙሉ ኃላፊነት  ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ  የሚያስተላልፈው ውሳኔ  የምእመናንን ሐዘን የሚያስታግስ፤  አገልጋዮችን የሚያበታታ እና የቤተክርስቲያንን መዋቅር ለመስጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት ለከፈሉ ካህናትና ምእመናን መጽናኛ ይሆናል ብለን በማመን የሚከተለውን አቤቱታ በእግዚአብሐር ስም አቅርበናል ።
የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሰላም ለመጠበቅ ሲባልና  የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአሜሪካ የሚገኙ ካህናትና ምእመናንን ድምጽ መስማት አባታዊ ኃላፊነት  እንዳለባችሁ በማመን  የሚከተሉት ሶስት አቤቱታ እናቀርባለን
4.    በቅድሚያ አሜሪካ ያለውን ችግር የሚያጠና  ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ  በመወከል  እንዲጠና እንዲደረግና ከሁሉም አቅጣጫ ያለሁን ሁኔታ እንዲመለከት እና ተደረሰውን ጥናት መነሻ በማድረግ ያሉትን አህጉረ ስብከት ለማጠናከር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ቢደረግ
5.    ይህ ጥናት እስከሚደረግ ድረስ  አሁን የተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምደባ በድጋሚ እንዲታይ እና ቢያንስ ለቀጣዩ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲዘገይ ቢደረግ
6.    የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በአካል ተገኝተው ዝርዝር ሁኔታውን እስኪያስረዱ ድረስ ጊዜ እንዲሰጣቸው  

በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን ።

No comments:

Post a Comment