Tuesday, November 1, 2011

ቅ/ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በምልአተ ጉባኤው የተገሠጹትን አቡነ ፋኑኤልን ለአሜሪካ ሾመቅዱስ ሲኖዶስ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች ተመርምረው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲጠራ ወሰነ
 • ፈቃድ የሌላቸው ሕገ ወጥ ሰባክያን በማንኛውም መድረክ ማገልገል አይችሉም፤ እነርሱን በሚጋብዙ አለቆች እና የስብከተ ወንጌል ክፍሎች ላይ ጥብቅ ርምጃ ይወሰዳል፤ ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሰላም በመንሳት ካለው ባሕርይ ውጤት አኳያ ከግብረ ሽበራ ጋርም በተያያዘ ሊያስጠይቅ ይችላ ብሏ
 • የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራትበቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ አስጠነቀቀ
 • በምልአተ ጉባኤው ያልተሳተፉትና በሌሉበት ጉዳያቸው የታየው ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተነሥተው በምትካቸው አወዛጋቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል እንዲተኩ ተወስኗል፤
 •  ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በምልአተ ጉባኤው የተገሠጹት አቡነ ፋኑኤል ከአህጉረ ስብከቱ አስተዳደር እና ምእመናን ጠንካራ ተቃውሞ እንዳይገጥማቸው ተፈርቷል
 • በነገው ዕለት እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ‹‹የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች እና ጠቋሚ የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርእስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት ላይ ማምሻውን መወያየት ጀምሯል፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድርጅታዊ መዋቅር ሊፈተሽ እና ዲዛየኑም ሊሻሻል እንደሚገባውየመከሩት ም/ዋ/ሥራ አስኪያጁ ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም ሚና ያላቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቤተ ክርስቲያንን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል ርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል(ዳሰሳዊ ጥናቱ ደርሶናል፤ ወደፊት እናቀርበዋለን)

(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 21/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 1/2011)፦ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአጀንዳ ተራ ቁጥር ዐሥር ላይ በተመለከተው ‹‹በቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ እምነት ላይ ያለውን ችግር በቀረበው የጽሑፍ ማስረጃ (ላይ) ተወያይቶ መወሰን››በሚለው ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ በመወያየት ዐብይ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከቀትር በፊት በነበረው ውሎ የአባ ሰረቀን ሕጸጸ ሃይማኖት የሚመረምረው ኮሚቴ በሰው ኀይል ተጠናክሮ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች እንዲመረምርና በአስቸኳይ ለሚጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሪፖርት እና የውሳኔ እንዲያቀርብ ወስኗል፡፡ የኮሚቴው አባል በመሆን ማስረጃዎቹን መርምረው ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ቀደም ሲል ከተመደቡት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ እና ብፁዕ አቡነ ያሬድ ጋር ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ከሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ እና ሊቀ ሥዩማን አስራደ አስረስ መጨመራቸው ታውቋል፡፡
 • በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት 131 ሰንበት ት/ቤቶች፣ የፀረ ተሐድሶ ሰባክያን ፅምረት እና ቀናዒ ምእመናን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን አስመልክቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባቀረቧቸው ሰነዶች ውስጥ ስማቸው የተዘረዘሩት
 • ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራት ማንነታቸው እና ሥራዎቻቸው (ኅትመቶቻቸው) በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ፤
 • በሰነዶቹ የተዘረዘሩትና ፈቃድ ሳይኖራቸው ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያካሂዱፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጅ ግለሰቦችም በማናቸውም መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ በመሆኑ በሁሉም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን አድባራት እና ገዳማት እንዳያገልግሉ፤ ይህንንም በሁሉም አህጉረ ስብከት የሚገኙ የገዳማት እና አድባራት አለቆች እንዲቆጣጠሩ፤ ለእኒህ ሕገ ወጥ ግለሰቦች/ቡድኖች ጥሪ በማድረግ መድረክ የሚሰጡ አስተዳደሮች ርምጃ እንዲወሰድ፤ ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት እና ሰላም በመንሳት ካለው ባሕርይና ውጤት አኳያ ከግብረ ሽበራ ጋርም በተያያዘ ሊያስጠይቅ እንደሚችል፤
 • በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት(መድረኮች) ላይ ማስተማር የሚችሉት በአጥቢያው(በክፍሉ) የተመደቡ ሰባክያነ ወንጌል ብቻ እንደሆኑ ታውቆ ለአፈጻጸሙ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲካሄድበት፤
 • በአዲስ አበባ እና በተለያዩ አህጉረ ስብከት ከተሞች በበዓላት ቀናት እና በዐውደ ምሕረት በሊቃውንት ጉባኤ ያልተመረመሩ ኅትመቶችን (የኤሌክትሮኒክስ ይሁን የኅትመት) የሚሸጡ አካላት እንዲታገዱ፤ ከአቅም በላይ ከሆኑ ለመንግሥት አካላት በማሳወቅ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ያዘዘው ምልአተ ጉባኤው ለሚመለከተው አስፈጻሚ አካል መመሪያ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ምልአተ ጉባኤው በትንት ዕለት ከቃለ ዐዋዲው እና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን በተራሪ ቅዱስ ሲኖዶስ ሳይመክርበት መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ በማድረግ እንዲቋቋም በፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ የታዘዘውን ‹‹የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት›› እንዲዘጋ መወሰኑን ተከትሎ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እናየካሊፎርኒ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እንዲመጡ በመጥራት /እንዲነሡ?/ በምትካቸው አወዛጋቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል ሁለቱንም ደርበው እንዲይዙ ወስኗል፡፡

ሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ አብርሃም እና አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ለመኖሪያ ፈቃድ እና ለዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እድሳት የድጋፍ ደብዳቤ ከመጻፍ ጋር በተያያዘ በፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ እና በሀ/ስብከታቸው (ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ) የደረሰባቸውን እንግልት በመዘርዘር በቅርቡ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ደብዳቤ ጽፈዋል፤ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም ጉዳዩን ተመልክቶ ውሳኔ እንዲሰጣቸው በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡

በተለይም ብፁዕ አቡነ አብርሃም በፓትርያኩ ‹‹የበቀል ጥመኛነት›› የተነሣ በግል ከደረሰባቸው እንግልት በተጨማሪ ‹‹በፓትርያኩ ያለደብዳቤ ተልከዋል›› ያሏቸው አቡነ ፋኑኤል በእርሳቸው አህጉረ ስብከት አራት አጥቢያዎች ሥልጣነ ክህነት በመስጠት እና አዲስ ቤተ ክርስቲያንን በመባረክ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከመጣሳቸውም በላይ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ መዋቅር እና አሠራር ባፈነገጠ መልኩ በሰሜን አሜሪካ እየተስፋፋ ለመጣው የ‹‹ገለልተኝነት›› አካሄድ ሽፋን መስጠታቸውን በመጥቀስ ድርጊታቸውን ኮንነዋል፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ ተወያይቶ የማያዳግም እርምት እንዲሰጥበትና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑበት የሚገኘውን አህጉረ ስብከታቸውን እንዲያስከብርላቸው ተማፅነው ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም በደብዳቤያቸው እንዳመለከቱት ምልአተ ጉባኤው ዛሬ ባካሄደው ዐሥረኛ ቀን ስብሰባው አቡነ ፋኑኤል በሌላው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገብተው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በፈጸሙት ተግባር በግልጽ ገሥጧቸዋል፡፡ በተለይም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣‹‹ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን በሚባሉት ተገኝተው የሚባርኩት፣ ሥልጣነ ክህነት የሚሰጡት ማን ፈቅዶሎት ነው? በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የሾሟቸው ‹ካህናት› ክህነት ወድቅ እንደሚደረግ አያውቁም? እርስዎ ባቋቋሙት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስነታቸው ስም ይጠራበታል? የሚጠራበት የእርስዎ ስም ነው፤ ይህ ሕገ ወጥነት ነው፤ ተገቢም አይደለም!!›› በማለት በከፍተኛ ኀይለ ቃል ገሥጸዋቸዋል፡፡ አቡነ ፋኑኤልም ‹‹እኔን ለምን ትወቅሱኛላችሁ፤ አቡነ አብርሃም ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን ሄደው አይባርኩም፤ ሄደህ አገልግል ብለው ፓትርያኩ ስላዘዙኝ ነው፤›› በማለት ችግሩ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እንዳሉት ከወደላይ መሆኑን አጋልጠዋል፡፡ አቡነ ፋኑኤል ይህን ጉድ ሲገልጡት ርእሰ መንበር ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ አንገታቸው ዘልሰው አንዳችም ቃል አለመናገራቸው ምልአተ ጉባኤውን ማስገረሙን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

የጉባኤው ምንጮች ጨምረው እንደሚያስረዱት አቡነ ፋኑኤል በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከፈጸሙት ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት በተቃራኒ እዚያው እንዲሾሙና ምፀታዊ በሆነ መልኩ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲነሡ መወሰኑ ሁለት መንሥኤዎች ይኖሩታል - አንድም ሁለቱም በደላቸውን በአካል ተገኝተው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ወሳኝ አካል ለማስረዳትና ጉዳያቸውን ለመከላከል ባለመፍቀዳቸው፤ በሌላ መልኩና በዋናነት የእነርሱን ቦታዎች የሚሹ አባቶች በመኖራቸው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ሁኔታም ለምን እንደማይታይ (እስከ መቼ እዚያ እንደሚቆዩ) እንደ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ባሉት አባቶች ጥያቄ የቀረበበት ቢሆንም የተሰጠ ግልጽ ምላሽ የለም፡፡

አወዛጋቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፋኑኤል በፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ በመፈጸሙት ኢ-ቀኖናዊ ተግባር የሹመት ሽልማቱን በዚህ መልክ ያግኙ እንጂ በአህጉረ ስብከቱ ግን ጠንካራ ተቃውሞ /የተቀባይነት ማጣት እንደሚጠብቃቸው የምልአተ ጉባኤውን ውሳኔ ተከትለው የወጡ የታዛቢዎች አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡
ቀጣይ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከባሌ ጋራ ደርበው ወደያዙት ጉጂ ቦረና/ሊበን/ ሀ/ስበከት እንደሚዛወሩ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀ/ስብከትን እንደሚይዙ፤ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ደግሞ ሥራቅ ሐረርጌ እና ጅጅጋ አህጉረ ስብከት እንደሚሾሙ ተነግሯል፤ ምሥራቅ ሐረርጌ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያሬድም ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅሊቀ ጳጳስ ሆነው ይዛወራሉ፤ በ2003 ዓ.ም ከግንቦቱ ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኋላ ያረፉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ በነበሩበት ምዕራብ ጎጃም ሀ/ስብከት የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ተመድበዋል፤ በእርሳቸው ምትክ የአዊ እና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ምሥራቅ ጎጃምን ደርበው ይመራሉ፡፡
የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የመላው አፍሪካ፣ የመላው አፍሪካ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምዕራብ ሐረርጌ፣ የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን - ዓዲ ግራት ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዕርግና ምክንያት የመቐለ ሀ/ስብከትን ደርበው ይመራሉ ተብሏል፡፡ ያም ሆነ ይህ ይኸው በአጀንዳ ተራ ቁጥር ስምንት ‹‹ዝውውርን በጽሑፍ በጠየቁ ሊቃነ ጳጳሳት›› የተመለከተው ጉዳይ የጳጳሳትን ምደባ እንዲያጠና ምልአተ ጉባኤው የሠየመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ በነገው ዕለት በሚያቀርበው ሐሳብ ፍፃሜ እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል ምልአተ ጉባኤው በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋር የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር የሚነጋገሩት አካላት በተስማሙበት መንገድ ከየካቲት 2 - 9 ቀን 2004 ዓ.ም በአሜሪካ አሪዞና ግዛት እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፤ ለዚሁ ጉዳይ በመዲናዋ አዲስ አበባ የሚገኙት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ አለማየሁ እና ሊቀ ማእምራን ዶ/ር አማረ ካሳዬ ይህንኑ ውሳኔ የሚገልጽ ደብዳቤ መቀበላቸውም ተዘግቧል፡፡ ሁለቱንም አካላት በመወከል በዕርቀ ሰላም ንግግሩ የሚሳተፉት አባቶችም/ሽማግሌዎችም ከቀድሞው ልዩነት የሌለው መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

3 comments:

 1. Who assigned Aba Fanueal as a bishop of America?If this is so,I think EOTC goes from the frying pan to the fire!Every thing becomes a fertile ground for tehadiso,if Aba(?)Fanueal has got that place.Now thinking to me,every thing becomes bitter when we think about religion.
  WUBSHET

  ReplyDelete
 2. I know I agree with you WUBSHET,

  ReplyDelete
 3. betam yasazinal ay sinodos be'and bekul sikib beand bekul yaferisewal min waga alew
  Egiziabiher betekirisitiyanin yitebikilin enji.

  ReplyDelete