Monday, November 21, 2011

ሙታን እፎይ ማለት አልቻሉም


አሁን ባለንበት ሰዓት ብዙ ለጆሮ የሚከብዱ ፤ ለማመን የሚያስቸግሩ ፤ ሰዎች ያደርጓችዋል ብለን የማንገምተው ነገር ሁሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ማህበረሰባችን ምን አይነት ዝቅጠት ውስጥ እንደገባና ፈሪሀ እግዚአብሔር የሚባልመም ነገር የሌለበት ሆኗል፡፡ ሰው በምድር ላይ እግዚአብሔር ፈቀደለትን ዘመን ይኖራል፡፡ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር›› ስለተባለ ከባለቤቱ ጥሪ ሲደርሰው ፤ መልአከ ሞት ከተፍ ሲል ፤ ይችን ምድር ተሰናብቶ ስጋው ከነፍሱ ተለይታ ይህችን ዓለም ይሰናበታል፡፡ ወዳጅ ዘመድ ይሰበሰባል ይለቅሳል ፤ ይታዘናል ግብአተ መሬት ይፈጸማል ፤ 


አሁን ላወራችሁ የፈለኩት ነገር ሙታን ‹‹ማረፍ አልቻልንም› ለማለት ምንም የቀራቸው አይመስልም፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ አንዳንድ ደብሮች ላይ ከሚደረጉ ህገ ወጥ ምግባሮች አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን መኖርም መሞትም የሚከብድ የሚመስልበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ሰው ይወለዳል ፤ ይኖራል ፤ ይሞታል ፤ ሞቶም ግን በአግባቡ ማረፍ አልቻለም፡፡ በፊት በፊት ሰው ከሞተ በኋላ ግብዐተ መሬት ተፈፅሞለት ጅብ ሬሳውን እንዳይጎትት ይፈራ ነበር ፡፡ አሁን ግን የጅቡን ቦታ የያዙት ሰዎች ሆነዋል፡፡ አስከሬን መገልበጥ እና ሳጥኑን ለአስከሬን ሳጥን ቤቶች መልሶ መሸጥ ፤ ለሟች የመጣውን አበባዎች መውሰድ  ፤ የመተዳደሪያ ስራ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የአንድ ሰው ሬሳ ውድ የሚባል ሳጥን ውስጥ ካረፈ የዛ ሰው መቃብር ሳጥን በሚቀጥለው ቀን ለማግኝት አዳጋች ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለሊት የዚህ ስራ ተዳዳሪዎች ዶማ እና አካፋ ይዘው ይመጣሉ የተቀበተበት ቦታ ቆፍረው ሬሳውን ገልብጠው ሳጥኑን ይወስዳሉ ፤ ለሚመለከተው ክፍል ረከስ ባለ ዋጋ ያስረክባሉ፡፡ እነዚህ ተግባሮች በአዲስ አበባ ዳር ዳር ባሉ አብያተክርስትያናት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡


በቅዱስ ዮሴፍ ቤ/ን ውስጥ የሚገኙትን መቃብሮች በየጊዜ የተሰሩባቸውን እምነበረዶች ፍለጋ ፤ በዙሪያቸውን ያለውን ብረት ለቀማ ፤ ከፀሀይ የሚከላከላቸውን ላሜራዎች ፍለጋ ሌቦች ተሰማርተው ለፖሊስ ፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ፤ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ዜና አሳዛኝም አሳፋሪም ጭምር ነው፡፡ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስትያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆነም ፤ ያልሆነም ሰው የሚቀበርበት የመቃብር ስፍራ አለ ፡፡ ለሀገራችን ትልቅ አስተወፅዎ ያደረጉ አሻራቸውን በትውልድ ላይ ማስቀመጥ የቻሉ ብዙ ሰዎችም ይገኙበታል፡፡ አትሌት አበበበ ቢቂላ ፤ ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ ፤ ድምጻዊት ብዙነሽ… ሌሎችም ያረፉት ግብዓተ መሬት የተፈጸመላቸው በዚህ ቦታ ላይ ነው ፡፡

በአሁኑ ሰዓት 75 በመቶ የሚሆኑ መቃብሮች ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ሀውልቶቹ የተሰሩበት እምነበረድ ፤ የከበባቸው ብረት ነቅለው ተወስደዋል፤ መቃብሮች ተበርብረዋል ፤ አንድ ሰው መጥቶ የወዳጁን ፤ የእናትና አባቱን ፤ የእህት የወንድሙን ቦታ ለማግኝት አስቸጋሪ ሆኗል ፤ ለምን ቢባል ያን ሰው የሚወክል መቃብር የተሰራበት እምነበረድ ተሰርቋል ፤ የታጠረበት አጥር ተወስዷል ፤ ስሙ የተፃፈበትም ሳይቀር በቦታው የለም ፤  ስለዚህ ማግኝት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

የአባቷን እርም ለማውጣት የመጣች ወጣት
የአንድ የቤተሰብ አባወራ  የዛሬ 2 ዓመት ግድም ያርፋሉ በጊዜ ስርዓተ ቀብራቸው የተከናወነው በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስትያ ነበር:: በሀዘኑ ጊዜ አሜሪካ ሀገር የነበረችው እህት ከ2ዓመት በኋላ መጥታ የአባቴን እርም አወጣለሁ መቃብሩን አሳዩኝ ብላ ወንድ እህቶቿን ትጠይቃችዋለች ፡፡ እነርሱም እሺ ብለው አባትየው የተቀበሩበት ቦታ ሲሄዱ ያዩትን ሁሉም ለማመን አቅቷቸው ነበር፡፡ መቃብሩ ብረቱ የለም ፤ እምነበረዱም የለም ፤ ስማቸው የተፃፈበትም ፅሁፍ የለም ፤ መቃብሩ በጎን በኩል ተከፍቶ ሬሳ ሳጥኑ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ይህን አይቶ ማመን ያቃታት አንዲት እህታቸው እዛው ራሷን ልትስት ችላለች፡፡ ወንድማቸውም ‹‹ኣባቴ ከሞተበት ቀን ይልቅ ዛሬ ነው በጣም ያዘንኩት›› እያለ ነበር ምሬቱን ሲገልፅ የነበረው፡፡ ከውጭ የመጣችው እህታቸውም ሀዘኗ በሆነው ነገር አጥንት አልፎ የሚገባ ነበር፡፡ ‹‹ሞት ሁሉም ይሞታል ግን እንዴት ሰው ሞቶ እንኳን ማረፊያ ያጣል ፡፡›› ብላ ነበር፡፡

የኪሮስ አለማየው ባለቤት
ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ ለሀገራችን በትግረኛ ዘፈኖቹ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው የጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ በህይወት በነበረበት ጊዜም ብዙ ካሴቶችን በመስራት ለጥበብ ሰዎች እንካቹ ብሏል፡፡ በሰሜኑ ክፍል በተወለደበት አካባቢ በሰራው ስራ ፤ለጥበቡ ባደረገው አስተዋፅኦ መንግስት ትልቅ ቤተ መፅሀፍት ተገንብቶለታል ፤ አንቱታንም ያገኝ  ሰው ነበር፡፡ እሱም አስከሬኑ ቅዱስ ዮሴፍ ቤ/ን ነበር ያረፈው፡፡ የእሱ ከሌሎቹ የሚለየው ቢያንስ ስሙ በእምነበረድ የተፃፈው በመገኝቱ እንጂ የሁሉም እጣ ፈንታ ነበር ደረሰው ፤ ባለቤቱ ሁኔታውን ስታስረዳ በጣም ሀዘን ውስጧን እያነደት ነበር፡፡ እንዴት ለአይከኖቻችን  ዋጋ  አንጣ ?   ይገርማል ፤ ሰዎች በየዓመቱ የሞቱትን ዘመድ አዝማዳቸውን ስም በቅዳሴ ላይ ለማስጠራት ወደ ቤ/ን ሲመጡ ሀውልቱን ማግኝት ተቸግረው ተመልክተናል፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ብሎ የሰው ሀውልት ላይ ሄዶ ማልቀስም የተለመደ ይመስላል፡፡ መንግስት ግን ይህን ሁሉ ነገር እያየ እየሰማ እንዴት ዝም ይላል?

 የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ
እንዲህ አሉን ‹‹ይህው ሁሉን ነገር እንደምታዩት ነው እኛ ዘበኛ በ800 ብር ቀጠርን አንዱኝ ዘበኛ ደበደቡት አንዱት አይኑን አጠፉት ፤ ሁለቱም በዚህ ምክንያት ስራቸውን ለቀቁ ፤ እንደገና የጥበቃ ማስታወቂያ አወጣን ሁሉም ሰው ለነፍሳችን እንፈራለን በማለት ሰው አግኝተን ልንቀጥር አልቻልንም ፤ ዝርፊያው በለሊት ብቻ የሚከናወን አይደለም ፤ በጠራራ ፀሀይ መንግስት ባለበት ሀገር ፤ ህግ ባለበት ሀገር ነው የሚዘርፉት ፤ እኛ ከአቅማችን በላይ ነው ብዙ ጊዜ ለመንግስት አቤት ብለናል ተገቢ መልስ ግን ልናገኝ አልቻልንም ፡፡ ስለዚህ ምንም ማድረግ አልቻልንም›› ነበር ያሉት:: ጨምረውም ‹‹ ብረቶቹን ለመንቀል ፤ እምነበረዱን ለማፍረስ በግሩፕ 6-8 ሆነው ነው የሚመጡት ፤ እኛን ምን አድርጉ ትሉናላችሁ ፤ አንድ ጊዜ አንድ ዲያቆን ሰርቀው ሲወጡ አይቶ ማስጣል ሲሞክር ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰበት ፤ ስለዚህ ከአቅማችን በላይ ነው::

ፖሊስ
ፖሊስ ከተሰረቁት ከ100 አስር በመቶ የማይሞላ ቁርጥራጭ ብረታ ብረት በጣቢያ ከማከማቸት ውጪ የረባ ስራ የሰራው የለም፡፡ ሬሳ አውጥተው ጥለው ሬሳ ሳጥኑን በኢግዚቢትነት ቢይዝ ምንድነው ጥቅሙ? እምነበረዱ ተገሽልጦ ፤ ብረቱ ተነቅሎ ፤ ሰዎች ላይ ማህበራዊና አእምሯዊ ቀውስ መጥቶ ደፍቷቸው ሳለ የእነሱ መዝገብ መመርመር ፤ የሌባውን የኋላ ታሪክ ማጥናት ምን ሊረባቸው ፤ ምንስ ሊፈይድላቸው ፡፡

መልዕክት አለን
እናቶቻችሁን አባቶቻችሁን ፤ እህት ወንድሞቻችሁን በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስትያን ለቀበራችሁ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ትመለከቱ ዘንድ መልዕክታችን ነው፡፡
‹‹እግዚአብሔር ከእንደዚህ አይነት ነገር ይሰውረን››

3 comments:

 1. ያሳዝናል፤ መፍትሔው ግን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሐውልት እንደማይፈቅድማስተማር ነው፡፡

  ReplyDelete
 2. ያሳዝናል፤ መፍትሔው ግን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሐውልት እንደማይፈቅድማስተማር ነው፡፡

  ReplyDelete
 3. ያሳዝናል፤ መፍትሔው ግን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሐውልት እንደማይፈቅድማስተማር ነው፡፡
  The theft is not good But i wish totally any type of Hawult will be eradicated from our church. It is not spiritual

  ReplyDelete