- ትእዛዙን የጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ አልተቀበሉትም፤
- “ጠቃሚ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ቀንድ ቀንዳቸውን እየተባሉ ይወጣሉ፤ ሰዎቹ ከጠ/ቤተ ክህነት ፈሰስ ተደርጎም ቢሆን ሥራቸውን ይቀጥላሉ›› (ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ)፤
- “ቤተ ክርስቲያንንና መንግሥትን በግልጽ እንዲለያዩ ያደረገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት 16 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ሲታይ 50 ሚልዮን የሚሆነውን የምእመን ብዛትና ከፍተኛ የሚባል የገንዘብና ካፒታል መጠን ይዘን ብዙም አልተራመድንም፡፡. . .ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በስትራቴጂክ ፕላን እንዲመራ በማድረግ የዕቅዱን አፈጻጸም በየጊዜው መገምገም ሲገባው ወይም እየገመገመ የሚያቀርብለት የባለሞያዎች ቡድን መሠየም ሲገባው እስከ ዛሬም ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን የልማት አቅጣጫ፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የበጀት አያያዝና አፈጻጸም የማያመረቃ ሆኖ ቆይቷል፡፡” /አቶ ልዑል ሰገድ የቤተ ክህነቱን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች ከዳሰሱበት የዳሰሳ ምልከታ ጽሑፍ የተወሰደ
- ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ 40ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ላይ ለመገኘት ግብጽ - ካይሮ ገብተዋል፡፡ የመንበረ ማርቆስ ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 40 ዓመታት እና የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 20 ዓመታት ምንና ምን ናቸው? እንገምግመው፤ እንወያይበት፡፡
ከደጀ ሰላም፤ ኅዳር 4/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 14/2011
የሦስቱም ከፍተኛ ሓላፊዎች ደመወዝ የሚሸፈነው ለጋሽ አካላት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በኩል በሚሰጡት ርዳታ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ ይኸው ከለጋሾች የሚሰጠው የበጀት ርዳታ ገቢ እንዳልተደረገ በመግለጽ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጻፉትን ደብዳቤ ሰበብ በማድረግ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ካለፈው ወር መጨረሻ ጀምሮ የሦስቱም የሥራ ውል መቋረጡ ተገልጾ እንዲሰናበቱ እንዲደረግ ለኮሚሽነሩ የቃል ትእዛዝ እንደሰጡ ተነግሯል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አማራጭ የበጀት ምንጮችን በመጥቀስ የትእዛዙን ተፈጻሚነት ተቃውመዋል፡፡ “ቤተ ክህነቱ ደኅና ሰው አይበረክትለትም፤ ጠቃሚ ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ቀንድ ቀንዳቸውን እየተባሉ ይወጣሉ፤” በማለት ፓትርያርኩ ሰጥተውታል በተባለው ትእዛዝ ማዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በበኩላቸው፣ “ከፍተኛ ሓላፊዎቹ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ካዝና ፈሰስ ተደርጎ ደመወዛቸውን ቀንሰውም ቢሆን ይቀጥላሉ” በማለት የፓትርያርኩ ትእዛዝ ተቀባይነት እንደሌለው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ
የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ “የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች - የዳሰሳ ምልከታ” በሚል በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ያጠናከሩት ጥናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ቋሚ ሲኖዶሱ ከጽ/ቤታቸው ጋር በመሆን በሚያቋቁመው የአስተዳደር እና የሕግ ባለሞያዎች ኮሚቴ ተመርምሮ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ደንቦች እና መምሪያዎች ጋር ተገናዝቦ ቤተ ክህነቱን በሚያሠራበት መንገድ እንደሚዘጋጅ ብፁዕነታቸው መናገራቸው ተገልጧል፡፡
ይኸው የአቶ ልዑል ሰገድ የዳሰሳ ምልከታ ጥናት (Attached at the end of this news) ከጥቅምት 7 - 11 ለተካሄደው 30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ቀርቦ በውይይት ከዳበረ በኋላ ለጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የዳሰሳ ምልከታው አምስት አባላት ላሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማኔጅመንት ኮሚቴ አስቀድሞ ቀርቦ አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥቅምት 6 ቀን 2004 ዓ.ም ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ጥናቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣቸውን ደንቦችን እና መመሪያዎችን በማሻሻል ድርጅታዊ ዲዛይኑን ለመፈተሽ የሚያስችል በመሆኑ ቅዱስነታቸው አመራር እንዲሰጡበት ጠይቀው ነበር፡፡
ይሁንና አቡነ ጳውሎስ የዳሰሳ ምልከታው በጠቆማቸው ችግሮችና በተነጻጻሪ ባቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ደስ እንዳልሰተኙ የተመለከተ ሲሆን በዚሁ ቅያሜያቸው ሳይሆን እንዳልቀረ በተጠረጠረ ምክንያት ጥናቱ እንደታሰበው ለ30ኛው የመንበረ ፓትርያርኩ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ በሁኔታው ከፍተኛ ሐዘን የገባቸው አቶ ልዑል ሰገድም በአጠቃላይ ጉባኤው መክፈቻ ላይ ከተገኙ በኋላ ጉባኤው በተካሄደባቸው ተከታይ ቀናት በስብሰባው ላይ ሳይካፈሉ ቀርተዋል፡፡
በ14 ገጾች የተጠናቀረው የዳሰሳ ምልከታው በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጀንዳ ተራ ቁጥር 12 መርሐ ግብር ተይዞለት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለእያንዳንዳቸው ከታደለ በኋላ በንባብ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ጽሑፉ፣ “ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጎች፣ ደንቦችና መምሪያዎች፣ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግንኙነት በሰው ኃይል እና በፋይናንስ አስተዳደር ስላለው እንቅስቃሴ፣ ስለቁጥጥርና የሥራ ግምገማ ሊደረግ የሚገባውን ለመጠቆም” የተዘጋጀ “የአስተዳደር፣ ሥራና ሥራ አመራር ቅድመ ጥናት ንድፈ ሐሳብ /ፕሮፖዛል/” መሆኑንም ምልአተ ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡
ፓትርያርኩ የጥናቱን አንዳንድ ይዘቶች ከዐውዱ ውጭ በመውሰድ ለማጣጣል ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም ምልአተ ጉባኤው ጽሑፉ “በጥሩ ሁኔታ የተቀነባበረ፣ ሰሚ ጆሮ ያገኘ ተደማጭነት ያለው የቅድመ ጥናት ንድፈ ሐሳብ /ፕሮፖዛል/ ነው” ሲል ምስጋና ችሮታል፡፡ ጽሑፉን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋትና ደንቦች ጋር ለማገናዘብ እንዲቻልም በቋሚ ሲኖዶስ እና በአስተዳደር በሚሠየሙ የአስተዳደር ባለሞያዎች ተጠንቶ የቁጥጥር ተግባሩን ሁሉ በማካተት ለግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ስብሰባውን አጠናቆ ከተነሣ በኋላ ቀደም ሲል ከአሠራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ቁርቋሶ ያላጣው የምክትል ሥራ አስኪያጁ እና የፓትርያርኩ የሥራ ዝምድና የበለጠ እየሻከረ ሄዶ አባ ሰረቀ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከመሾማቸው ጋር በተያያዘ ወደ መካረር እንደ ደረሰ ተዘግቧል፡፡ ፓትርያርኩ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁን ወደ ቢሯቸው በመጥራት “በማኅበረ ቅዱሳን አባልነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት” ጭምር እንደወቀሷቸው በመግለጽ “የእኔ እንድትሆን ነው የምፈልገው” በሚል ግልጽ ማስጠንቀቂያ እንደሰጧቸው ተነግሯል፡፡
የማኔጅመንት፣ አካውንቲንግ እና ሕግ ባለሞያ የሆኑት የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ከባጀው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ‹ፖሊቲካ› ጋር እምብዛም የማይተዋወቁ ቀጥ ያሉ ቴክኖክራት እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ አቶ ልዑል ሰገድ ግርማ ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ ደመወዝ ሲሠሩባቸው ከቆዩባቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመልቀቅ ጥቅምት 16 ቀን 2003 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለሥራ አስኪያጅነት ቀርበው በመወዳደር ባሳዩት ብቃት ደመወዝ ቀንሰው መቀጠራቸው ተገልጾ ነበር፡፡ በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር ሌሎች ሁለት ባለሞያዎች የተቀጠሩ ሲሆን አንዱ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አሠራር በመመረር ፈጥነው መልቀቃቸው ታውቋል፡፡ ሌላዋ የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ ሓላፊዋ ወ/ሮ ጽጌሬዳም እንደ አቶ ልዑል ሰገድ ሁሉ የሥራ ኮንትራታቸው እንዲቋረጥ ትእዛዝ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የተቀላቀሉት የሕግ ባለሞያው መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ በአስተዳደር መምሪያ ሓላፊነት በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ መጋቤ ጥበብ በእምነት ከእርሳቸው ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ የተቋቋመውንና ዐሥር አባላት ያሉትን በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት የሚመራ ኮሚቴ በማስተባበር የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የፌዴራል መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀት እና ለማጠናከር የወጣውን ዐዋጅ ረቂቅ ለውጤት ያበቁ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዐዋጁ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን በማከል የሕግ ዕውቅና ማግኘት ይችል ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲመራ ተወስኗል፡፡ የምልአተ ጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ በተከሠተው የሹም ሽር ውዝግብ ከአቶ ልዑል ሰገድ ጋር በመሆን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ሲረዱ የቆዩት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ ከልማት ኮሚሽን ጋር የገቡት የሥራ ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ በፓትርያርኩ ትእዛዝ ከተሰጠባቸው ሦስቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች አንዱ እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ እውነትም ከልባቸው የሚተጉ ደኅና ሰዎች ለቤተ ክህነቱ አይበረክቱለትም ያሰኛል!!
ይህን ዐይነቱን ትእዛዝ የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከሌሎች ስድስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት (ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ) ጋር በመሆን በተማረና በአግባቡ በተደራጀ የሰው ኀይል የምትመራው የኮፕት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት በሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 40ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ላይ ለመገኘት ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ወደ ግብጽ - ካይሮ አምርተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ጉዞውን እንዲቀላቀሉ በፓትርያርኩ ቢጋበዙም ግብዣውን እንዳልተቀበሉ ታውቋል፡፡ ለጉዞው ከብር 200,000 በላይ ወጪ መደረጉ የተዘገበ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በሚከበረው 20ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው ላይ እንዲገኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳን ይጋብዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመንበረ ማርቆስ ፖፕ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 40 ዓመታት እና የመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ጳውሎስ 20 ዓመታት ምንና ምን ናቸው? ደጀ ሰላማውያን ሆይ፣ እንገምግመው፤ እንወያይበት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤት አስተዳዳራዊ እና
መዋቅራዊ ችግሮች የዳሰሰ ምልከታ
አዘጋጅ፡- ልዑልሰገድ ግርማ
የጠ/ቤ/ክ/ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ
ጥቅምት 2ዐዐ4 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ማውጫ
1. ሕጎች ደንቦች እና መመሪያዎች 2
2. የቅዱስ ሲኖዶስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ግንኙነት 2
3. የፊስካል ኮሚቴ 3
4. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ 3
5. የሰው ኀይል አስተዳደር እና ልማት 4
6. የፋይናንስ አስተዳደር 5
7. የውጭ ግንኙነት እና የሕዝብ ግንኙነት 6
8. የቅርስ ጥበቃ እና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ 6
9. የስብከተ ወንጌል እና የሰንበት ት/ቤቶች መመሪያዎች 7
1ዐ. የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ 7
11. የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ 8
12. የልማት ድርጅቶች 8
13. የልማት ኮሚሽን 9
14. የዕቅድ እና ልማት መምሪያ 9
15. ኮሌጆች 1ዐ
16. የቤቶች እና ሕንጻዎች አስተዳደር ልማት ድርጅት 1ዐ
17. የግንባታ ፕሮጀክቶች 11
18. የውዝግብ አወጋገድ 11
19. ጠቋሚ የመፍትሔ ሐሳቦች 11
2ዐ. ማጠቃለያ 13
የመንበረ ፓትርያርክ ጠ/ጽ/ቤትን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግሮች የዳሰሰ ምልከታ
መግቢያ
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ታሪካዊነት እና ብሔራዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን ከማስፋፋት ዋነኛ ተልእኮዋ ባሻገር በሀገር አስተዳደር እና ልማት መጠነ ሰፊ አስተዋፅኦ ስታበረክት ቀይታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሀገራችንን ከወራሪ ጠላት ለመከላከል የተደረገውን ፍልሚያ ጭምር በድል እንዲደመደም ማድረጓም በታሪክ የተመሰከረ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በታሪክ የሚታወቁ እና ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ምሁራንን በማፍራት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት እና አንድነት መጠናከር አሻራዋን አሳርፋለች፡፡ አሁን ባለንበት ጊዜም በምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ ሰላምንና ዕርቅን ለማምጣት እያደረገች ያለችው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሥር ከመላቀቋ በፊትም ሆነ በኋላ የራሷ የሆኑ የመተዳደሪያ ሕጎች አላት፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እና መንግሥትን በግልጽ እንዲለያዩ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሕገ መንግሥት ዐሥራ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ሲታይ ኀምሳ ሚልዮን የሚሆነውን የምእመናን ብዛት እና ከፍተኛ የሚባል የገንዘብ እና ካፒታል መጠን ይዘን ብዙም አልተራመድንም፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቶቹ ደግሞ በስትራቴጂክ ዕቅድ አለመመራታችን፣ የሰው ኀይል እና የገንዘብ አስተዳደር ፖሊሲዎቻችንን እና አሠራሮቻችንን አለማሻሻላችን፣ በየትኛውም የመዋቅር ደረጃ ያለውን የሰው ኀይል ከዘመናዊ አስተሳሰብ እና ዕውቀት ጋር አለማስተዋወቃችን፣ ግሎባላይዜሽን የወለደውን በቴክኖሎጂ ዓለምን አንድ የማድረግ ስትራቴጂ ውስጥ አለመግባታችን፣ እጅግ ድንቅ፣ ብርቅ፣ ውብ እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸውን ታሪካዊ ቦታዎቻችንን እና አብያተ ክርስቲያናትን ዘመኑ በሚጠይቀው ቱሪዝምን የማጐልበት አስተሳሰብ እና አሠራር አለመዘርጋታችን፣ በየጊዜው በተለያዩ ቦታዎች የሚነሡትን ሃይማኖታዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችንና ውዘግቦችን የመከላከል እና የመፍታት ስትራቴጂዎች አለመንደፋችን. . .ወዘተ ናቸው፡፡
ከላይ በተጠቀሱት እና በሌሎችም ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ማሻሻል እና በጥልቀት ማየት የሚጠበቅባት ሲሆን የበላይና ወሳኝ አካል ለሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ቢቀርቡለት ሐሳቦቹን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ ሊያሳልፍ የሚችል መሆኑን በማመን የተወሰኑ ጠቋሚ የሆኑ ችግሮች ከነመፍትሔ ሐሳቦቻቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ጠቃሚ ችግሮች
1. ሕግች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች
ቤተ ክርስቲያናችን ግንቦት 9 ቀን 1991 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሥራ ላይ እንዲውል ባጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እየተመራች ትገኛለች፡፡ ከ1991 ዓ.ም በፊት በነበረው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተመሥርተው የወጡ ሁለት ደንቦች ማለትም የሥራ መመሪያ ደንብ/1984/ እና የሠራተኛ አስተዳደር ደንብ/1988/ 1991 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋር መጣጣም አለመጣጣማቸው ሳይፈተሽ እስከ ዛሬ ድረስ ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን እና ደንቦቹ ምን ያህሉ ሥራ ላይ እንደዋሉና ምን ያህሉ እንደተሸራረፉ የተጠና ጥናት ባይኖርም ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከሚመጡ ጉዳዮች አብዛኞቹ የሚያመለክቱት የሕጉ እና የደንቦቹ ግንዛቤ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩን ነው፡፡ በተለይም የሠራተኛ ምደባን፣ ዝውውርን እና ቅጥርን በተመለከተ እጅግ የተምታቱ አሠራሮች ከመኖራቸውም በላይ አባቶችን አማላጅ በመላክ እና እግር ላይ ወድቆ እና አልቅሶ ለማስፈጸም የሚጣጣረው ሠራተኛ ብዛት ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ደንቦች አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣሙና መንግሥት ሥራ ላይ ካዋለው የአሠሪ እና ሠራተኛ ሕግ ጋር አብረው የማይጓዙ ናቸው፡፡
ሕገ ቤተ ክርስቲያናችን እና በሥራ ላይ ያሉ ደንቦች የሥራ መዋቅርንና ተዋረድን በግልጽ ያስቀመጡ ቢሆንም አሁን በሚፈለገው ሁኔታ የተቃኙ ባለመሆኑ ችግር ማስከተላቸው አልቀረም፡፡ የአስተዳደር ማንዋሉ ዝርዝር መመሪያዎች ቢኖሩትም ከጊዜው ጋር እንዲሄድ ያልተደረገ በመሆኑ ከአሠሪ እና ሠራተኛ ሕጉ ጋር የሚቃረኑ አሠራሮች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡
2. የቅዱስ ሲኖዶስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ግንኙነት
ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻው ሕግ አውጭ እና ወሳኝ አካል እንደመሆኑ በራሱ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የተፈጻሚነት ደረጃ ለመገምገም እና የቤተ ክህነት ባለሥልጣናትንና የመምሪያ ሓላፊዎችን የሚጠይቅበት ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና አሠራር የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ሥርዐት በግልጽ እንደምንመለከተው ሕግ አውጭው አካል ሁሉንም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ ኮሚሽኖችንና ሌሎችንም አስፈጻሚ አካላት በየጊዜው እየጠራ ያዳምጣቸዋል፡፡ የተሳሳቱ አካሄዶችም ካሉ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ዐይነት አሠራር ባለመከተሉ የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሠራር ሊዳብር አልቻለም፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የበታች አካላት ያልተመለከቷቸውን ጉዳዮች በቀጥታ ሲመለከትም ይታያል፡፡ ይኸው አሠራር በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ደረጃ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማትም የሚጠየቁበት የአሠራር ሥርዐት አልተዘረጋም፡፡ በአህጉረ ስብከት ያልታዩ ጉዳዮች በቀጥታ የሚታዩበት ሁኔታም እጅግ የበረከተ ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በስትራቴጂክ ፕላን እንዲመራ በማድረግ የዕቅዱን አፈጻጸም በየጊዜው መገምገም ሲገባው ወይም እየገመገመ የሚያቀርብለት የባለሞያዎች ቡድን መሠየም ሲገባው እስከዛሬ ይኸው ባለመፈጸሙ የቤተ ክርስቲያናችን የልማት አቅጣጫ፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የበጀት አያያዝ እና አፈጻጸም የማያመረቃ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ የጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአህጉረ ስብከት ግንኙነት ልል እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የረጅም ዓመታት ስትራቴጂክ ፕላን የሚያስፈልጋት የነበረ ሲሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተዘርግቶ ከላይ እስከ ታች አንድ ቋንቋ መናገር የሚቻልበት ደረጃ አልተደረሰም፡፡ አንድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚገኝ ዲፓርትመንት ስትራቴጂክ ፕላን ቢኖር ራሱን የትልቁ ዕቅድ አካል አድርጎ የት መድረስ እንዳለበት ያስቀምጥ ነበር፡፡
አንዲት መርከብ በኮምፓስ እየተመራች በባሕር ላይ የምትንቀሳቀሰው የት እንደምትደርስ አስቀድማ ስላቀደች ነው፤ በመንገዷም ላይ የሚያጋጥሟትን ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች በተለያዩ ዘዴዎች አልፋ የምትጓዘውም ወደዚያው ወዳለመችበት የመድረሻ ቦታ ብቻ ነው፡፡ ሳያቅዱና ኮምፓስ ሳይዙ በባሕር ላይ መጓዝ መጨረሻው የአውሬዎች እና የውኃ ሰለባ ሆኖ መቅረት ብቻ ነው፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ የአህጉረ ስብከት አቅም እየተገነባ የሚሄደው ደርዝ ያለው ስትራቴጂክ ፕላን ሲኖር ብቻ ነው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊ ገዳማት እና ቅዱሳት መካናት እንዳንጸባረቁ መኖር የሚችሉት ዕቅድ ባለው ሁኔታ ሲጠበቁ እና ሲታደሱ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ የዚህ ዕቅድ እንዲኖር ማድረግ የሚችል ዋናውና ብቸኛው አካል መሆኑ ይታመናል፡፡ በርግጥ ቤተ ክርስቲናያናችን የስትራቴጂክ ፕላን ዋነኛ አካላት የሚባሉትን ርእይ እና ተልእኮ ይዛ ተፈጥራለች፡፡ ስትራቴጂክ ፕላን ይኑራት ሲባል ኮምፓሱን በደንብ የሚያንቀሳቅሰውን ስትራቴጂክ አካሄድ ይነደፍ ማለት ነው፡፡
3. የፊስካል ኮሚቴ
ቅዱስ ሲኖዶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በሥሩ የሚገኙትን አህጉረ ስብከቶች እና ድርጅቶች የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዐት፣ በጀት እና የፋይናንስ ሪፖርቶች የሚተነትንና አስተያየት የሚሰጥ አካል የለውም፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን ግልጽነት የሌለውና ኋላ ቀር የሆነ የሒሳብ አሠራር ሥርዐት ለመከተል ዳርጓታል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር አገልግሎት መመሪያም ሥራውን በተጨባጭ ሁኔታና በውጤታማነት እንዳይሠራና በተመሰከረላቸው የሒሳብ ዐዋቂዎች እንዳይመረመር ሆኗል፡፡
4. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ
የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሥራዎቹን የሚያቀላጥፍበት የአሠራር መመሪያ /ማንዋል የለውም፡፡ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ቢሆንም የዘመናዊ አሠራር ፅንሰ ሐሳቦች እንዲሁም የትምህርት እና የሥራ ላይ ሥልጠና ስላልተመቻቸላቸውና ግልጽ የሆነ የጉባኤ አመራር መመሪያ ስለሌላቸው ጉባኤው ጊዜ የሚያባክን የሐሳብ መጓተት ይታይበታል፡፡ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጃችን ለአሠራር ያመች ዘንድ ያቋቋሙትን የማኔጅመንት ኮሚቴ እንኳን ጉባኤው በበጎ ጎኑ አይመለከተውም፡፡ ለዘመናት የቆየና ወደኋላ የቀረ አሠራር ጠቅላይ ቤተ ክህነትን ከሚያህልና “በመንግሥት ውስጥ ያለ መንግሥት” ከሚባል እንዲሁም ኀምሳ ሚልዮን የሚሆኑ ምእመናን የሚከተሏትን ቤተ ክርስቲያን ከሚመራ ተቋም ይህ ዐይነቱ የአስተዳደር ጉባኤ አሠራር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የጠቅላይ ጽ/ቤት እና የአስተደደር ጉባኤ የሥራ ግንኙነት ፣ የሚያያቸው ጉዳዮች ምንነት እና የአካሄድ ስልቱ በግልጽ መመሪያ ባለመቀመጡ ውሳኔዎቹም ተቀባይነት እያጡ በአህጉረ ስብከቶች እና በጠቅላይ ቤተ ክህነት መካከል አለመናበብ እየበረከተ መጥቷል፡፡
የጠቅላይ ጽ/ቤትም ቢሆን የአስተዳደር ጉባዔውንና በአጠቃላይም የቤተ ክርስቲያኒቷን አቅም የማጐልበት ሥራ እንዳይሠራ በርካታ ችግሮች ቀይደው የያዙት ሲሆን መቀራረብንና መነጋገርን የችግሩ ፈቺ ቁልፍ አድርጐ አልወሰደውም፡፡
5. የሰው ኀይል አስተዳደር እና ልማት
አንድ ሠራተኛ በሚቀጠርበት ወቅት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሊከተለው የሚገባ የአሠራር ሂደት በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም ተግባራዊ ሲሆን አይታይም፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ አንድ ቦታ ከተሰጠው በኋላ ሥራውን የሚሠራበት እና የሓላፊነቱን ወሰን የሚገልጽ የተጻፈ የሥራ ዝርዝር አይደርሰውም፡፡ የሥራ ዝውውር እና ዕድገት በሚሰጥበት ጊዜም በውትወታ፣ በምልጃ እና በልቅሶ ላይ ተመሥርቶ እንጂ የሠራተኛውን ብቃት፣ ክህሎት እና ልምድ ከሚሠራበት መምሪያ ጋር አቀናጅቶ በማየት አይደለም፡፡
በተለምዶ በሚዘጋጀው ዓመታዊ በጀት ውስጥ የሠራተኞችን አቅም ለማጐልበት የሚጠቅሙ ሥልጠናዎች ወጪዎች አይካተቱም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነታችን የሠራተኞቹን አቅም በመፈተሽ እና ክፍተቶችን በመለየት የአቅም ማጠናከርያ እና ማበልጸጊያ ሥራ ለመሥራት አስቦም አያውቅም፡፡ ለዚሀ ዓላማ የውጭ ርዳታን በማፈላለግ ሊያግዝ የሚችለውን የልማት ኮሚሽኑን እንከን አልተጠቀመበትም፡፡ በየጊዜው እየተገመገመ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሥራ ቸል ተብሏል፡፡ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኀይል ለድርጅት ዕድገት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አልተጤነም፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ መምሪያዎች እና ሠራተኞቻቸው የሚገናኙበት እና የሚወያዩበት መደበኛ ጊዜ የለም፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሠራተኞች በጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃም ሆነ በዲፓርትመንታቸው ውስጥ በየትኛውም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ተሳትፎ እንደሌላቸው ነው፤ የቡድን ሥራም አይስተዋልም፤ ሠራተኞች ለመምሪያቸው ወይም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በራሳቸው ተነሣሽነት እና ፈጠራ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የለም፡፡
ሠራተኛውን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ስለ ተጨባጭ ተመክሮዎችና ከተመክሮዎቹ ሊወሰድ ስለሚገባው ትምህርት መወያየት የማይታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሠራተኛን ከሥራው አንጻር የመመዘን ባህል አልተፈጠረም፡፡ ዕድገት እና የደመወዝ ጭማሪ በሥራ ምዘና ሳይሆን በእከከኝ ልከክልህና አንድን ሰው ከመጥቀም እና ከመጉዳት አንጻር ተግባራዊ ሲሆን ይታያል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነት በግልጽ የተቀመጠ የደመወዝ ስኬል ያለው ሲሆን አተገባበሩ ግን ብዙ የሚቀረው ሆኖ ይስተዋላል፡፡ በስኬል ከተቀመጠው የደመወዝ መጠን በተጨማሪ እንደ ጤና አገልግሎት፣ የአደጋ ጊዜ ኢንሹራንስ፣ የሥራ ላይ አጫጭር ሥልጠናዎች፣ የመደበኛ ትምህርት ክፍያ እና ሌሎች ጥቅሞች ፈጽሞ ታስበው አያውቁም፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በአህጉረ ስብከት የጡረታ አወጣጥ እና የጡረታ ይራዘምልኝ ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት መንገድ ግልጽነት የጐደለው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንቷን የጡረታ ጊዜያቸውን በማራዘም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቷን የምታሰፋበት መንገድ የሚበረታታ ቢሆንም ሁሉንም ጡረታ ሳይወጡ ማስቀረት ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በአህጉረ ስብከት የጡረታ ፎርም ያልሞሉ እምቢ ባዮች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡
6. የፋይናንስ አስተዳደር
ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር የሚጠይቀው ቻርት ኦፍ አካውንትስ በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በተዋረድ ባሉት መዋቅሮች አይታወቅም፡፡ በቻርት ኦፍ አካውንትስ ላይ የተመሠረተ እና ኮድ እየተደረገ የሚሠራና የሚያዝ ገቢ እና ወጪ የለም፡፡ ገቢዎቹም ሆኑ ወጪዎቹ በአግባቡ የተዘረዘሩ እና ደንብ ወጥቶላቸው የተቀመጡ አይደሉም፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዓመታዊ በጀቱን አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ያጸድቃል፤ ነገር ግን ወጪዎቹ ተግባራዊ የሚሆኑት ከበጀቱ ጋር እየተመሳከሩ አይደለም፡፡ የወጡት ወጪዎች እና በጀቱን የማመሳከር ሥራ አይሠራም፡፡ በበጀት ያልተያዙ በርካታ ጉዳዮች በወጪነት ይታዘዛሉ፡፡ ራሱን የቻለ የበጀት ክፍል ቢኖርም ሓላፊነቱን በሚገባ የሚያውቅ አይመስልም፡፡
ለጥቃቅን ወጪዎች የሚውለው የገንዘብ መጠን ጥናት ያልተደረገበት እና የአወጣጥ እና የአገባብ መርሕን የተከተለ አይደለም፡፡ አንድን ወጪ ለማውጣት የሚደረገው የመጻጻፍ ሂደት እጅግ የበዛ ነው፡፡ በቋሚነት የሚታወቁ ሀብቶች መለያ ኮድ አልተሰጣቸውም፡፡ ለቢሮ ጥቅም የሚውሉ አላቂ ዕቃዎች በሚፈለጉበት ጊዜ እንዲኖሩ የሚያስችል የክምችት ቁጥጥር ሥርዐት የለም፡፡ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ዐዋቂዎች ተመልክተውት አያውቁም፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየወሩም ሆነ በየዓመቱ የሚያቀርበው የወጪ ሪፖርት የለም፡፡ አሁን ያሉት የበጀት እና ሒሳብ ክፍል ሠራተኞች ይህን ለማድረግ የሚያስችላቸው የአሠራር ማዕቀፍም ሆነ ጠንከር ያለ የሒሳብ አሠራር ልምድ እንዲኖራቸው አልተደረገም፡፡ ሪፖርቶች በየወሩ ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ቀርበው አይጸድቁም፤ ሲኖዶስም በቋሚ ሲኖዶሱ አማካይነት ወይም በሚወክላቸው ባለሞያዎች አማካይነት በየሦስት ወሩ ቀርቦለት ቢመለከተው የተሻለ ነበር፡፡
የሀብት እና ዕዳ መግለጫ፣ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ማሳያ እና ማስታረቂያ፣ የባንክ እና የድርጅት ዶክመንቶችን ማስታረቂያ፣ የገቢ እና ወጪ መግለጫ፣ የበጀት እና የወጪ ማመሳከሪያና የመሳሰሉት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሒሳብ አሠራር ዕውቅና አልተሰጣቸውም፡፡ የቀጣይ በጀት ዓመት አቀራረጽ ባለፈው ዓመት የበጀት አፈጻጸም ላይ የተመሠረተ ሆኖ አያውቅም፡፡
አሠራሩ መሠረታዊ የሆኑና ሒሳብ ነክ ጉዳዮችን በብቃት እና በጥራት ማሳየት አለመቻሉ አንዳንድ ደመወዝ ተከፋዮች ከሁለት እና ሦስት ቦታዎች ጥቅም ሲያገኙ ይታያል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቁጥጥር መምሪያ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በስፋት ተገምግመው ርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ በመሆኑም የክፍተቱ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ አያጠየይቅም፡፡
7. የውጭ ግንኙነት እና የሕዝብ ግንኙነት
ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም አብያተ ክርስቲያናት መድረክ ያላት ግርማ ሞገስ እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ቁጥር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም መገኘት፣ እንደ ላሊበላ ያሉ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መኖር፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ጥልቅ የሆነ የሃይማኖት እና የዲፕሎማሲ ዕውቀት፣ በተወሰነ ጊዜ የሚከበሩ የአደባባይ በዓሎቻችንና የመሳሰሉት የውጭ ግንኙነታችን መሥመር ያለው እንዲሆን አድርገውታል፡፡
ከበርካታ ዓመታት በፊት በአገራችን ተከሥቶ የነበረውን የድርቅ አደጋም ጭምር በልማት ኮሚሽናችን በኩል በብቃት የተወጣችው ቤተ ክርስቲያናችን ድህነትንና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስንም የመዋጋቱን ሂደት የውጭ ግንኙነቷን እየተጠቀመችበት መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡
ሆኖም ለውጭ ግንኙነት እና ለሕዝብ ግንኙነት እየተጠቀመችበት ያለችው ክህሎት እና ልምድ የዘመኑን አካሄድ የተከተለ አለመሆኑ ግልጽ ነው ቋሚ የሆነ የመረጃ ስርጭት ፕሮግራም የላትም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ሲወያዩበት አይስተዋልም፡፡ አሁን በቤተ ክርስቲያናችን እየታተሙ ያሉት እንደ ጋዜጣ እና መጽሔት ያሉት በቂ አይደሉም፡፡ ይህን መሥመር ለማስያዝ የሚደረገው እንቅስቃሴም በድሮው እና በእኛው ብቻ ይቀጥል ባዮች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት መኖርና መጠናከር ግን ለገጽታ ግንባታ እጅግ የሚጠቅም መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
8. የቅርስ ጥበቃ እና የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ
ይህ መምሪያ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚገኘውን ሙዚየም ከመከባከብ ያለፈ ሥራ እየሠራ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገቡ አብዛኞቹ ቱሪስቶች ኦርቶዶክስ ነክ የሆኑትን ቦታዎች ይጎበኛሉ፡፡ ነገር ግን ይህ መምሪያ ለዚህ የሚያገለግል የቱሪስት ጋይድ መጽሐፍ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ብቃት ያላቸው አስጎብኚዎች፣ የጉብኝት ካርታ እና የመሳሰሉትን አላዘጋጀም፡፡ ይህ መምሪያ የኢትዮጵያ ባህል እና ቱሪዝም ኮሚሽን በተዋቀረበት ልክ መዋቀር የነበረበት ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በጊዜውና በቅርብ ሊከታተለው የሚገባ አካል ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም መምሪያ ተራ ሥራዎችን እየሠራ በመኖሩ ያስቆጫል፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የማበራከት ስትራቴጂ እንኳን የለውም፡፡
9. የስብከተ ወንጌል እና የሰንበት ት/ቤቶች መምሪያዎች
በዚሀ አጭር ምልከታ ላይ አስቀድሞ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ ርእይ እና ተልእኮ ቅዱስ ወንጌልን ማስፋፋት ሲሆን የስብከተ ወንጌል እና ሰንበት ት/ቤቶች መምሪያዎች ደግሞ ይህን ተልእኮ በማስፋፋት እና በማጠናከር ግንባር ቀደም ሓላፊነት አለባቸው፤ ነገር ግን ሁለቱ መምሪያዎች የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዐት የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰባክያን እና ዘማርያን እንዲሁም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ብዛት በግልጽ አይታወቅም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለቱንም መምሪያዎች ለማጠናከር አንዳንድ ተዛማጅ የሆኑ ትእዛዛትን ቢያስተላልፍም ሲተገበሩ አልታዩም፤ ለምን? ሁለቱ መምሪያዎች በቅንጅት መሥራት ሲገባቸው አንዳንድ ጊዜ በመካከላቸው ውዝግብ ሲነሣ ይታያል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰባክያን፣ ዘማርያን እና የሰንበት ተማሪዎችን ሊያደራጁ፣ ሊያስተባብሩ እና ሊያስተዳድሩ የሚችሉና ለሁሉም የሚሆኑ የሕግ ማዕቀፍ መመሪያዎች እና ደንቦች እንዲዘጋጁ አድርጐ ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
1ዐ. የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ
የሰበካ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛውን ሥፍራ ይዞ ይገኛል፡፡ ሆኖም ይህን የሚመለከተው መምሪያ ከየአህጉረ ስብከቱ የሚመጡትን የፐርሰንት ገቢዎች ሪፖርት ከማድረግ የዘለለ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ የኦርቶዶክስ ምእመናንን፣ የገዳማት፣ መነኮሳትን፣ የካህናት ቁጥርና ሌሎች ተዛማጅነት ያላቸው መረጃዎች አይገኙም፡፡ ይህ መምሪያ ራሱን ከፌዴራል ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በመለካት ማዋቀር የነበረበት ሲሆን የተለመደውን አካሄድ እየተከተለ ይገኛል፡፡ መምሪያው ከሌሎች መምሪያዎች ጋር በቅንጅት መሠራት ቢጠበቅበትም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ይህን ሲያቀናጅ እና ሲያግዘው አይስተዋልም፡፡
11. የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ
የቤተ ክርስቲናያችን የትምህርት ሥርዐት ባህላዊ ትምህርት እንዲቆይና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ ባህላዊ ትምህርቱን ጠንቅቀው የማያውቁት እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርጉት ካህናት እና የቤተ ክርስቲያን ምሁራን በዚሁ በቤተ ክርስቲናያናችን የትምህርት ሥርዐት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ይኸው የትምህርት ሥርዐታችን ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የትመህርት ሥርዐት መጣል ሁነኛ ሥፍራ እንዳለው የማይካድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዐት እየተጫወተች ያለችው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡
“ወርቃማው ዘመን” ተብሎ በሚጠራውና የቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት በ13ኛውና በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካከል የተስፋፉት ትምህርት ቤቶቻችን የጥንቱን በመጠኑ በጠበቀና በቅርስነት ሊመዘገቡ በሚችሉበት ደረጃ ዛሬም አሉ፡፡ የንባብ፣ የቅዳሴ፣ የአቋቋም፣ የዜማ፣ የቅኔ እና የመጽሐፍ ቤቶቻችን ዛሬም የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርት ሥርዐት ሆነው በአስደናቂ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡
በነዚህ ትምህርቶች ውስጥ ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያናችንን ባህሎች፣ መንፈሳዊ ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ሕግን ጠንቅቀው እንዲያውቁት ያስችላቸዋል፡፡ ከነዚህ ት/ቤቶች የወጡ ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ቁንጮ የሥልጣን ቦታዎችን በመያዝ አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ሊቃውንቱ የዕድሜያቸውን ግማሽ ያህሉን በነዚህ ትምህርቶች ተጠምደው ወደ ሊቅነት ደረጃ ቢሸጋገሩም ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ባለንበት ዘመን የሚያስፈልገውን የአቻ ግምት የትምህርት ደረጃ አላወጣችላቸውም፡፡ እነዚህ ከሥር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ ግምቶች ሠርተፊኬት፣ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ… ወዘተ በተሰጣቸው ነበር፡፡ ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ቤተ ክርስቲያናችን እንደገና ዲዛይን በሚደረገው ሂደት ከፍተኛ እገዛ ባደረገ ነበር፡፡ የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያችን ምን እየሠራ ይሆን?
12. የልማት ድርጅቶች
በጠቅላይ ቤተ ክህነት አደረጃጀት ሥር የሚገኙና የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረት ሳይለቁ ገቢ ማግኛ ተብለው የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ የቤቶች እና ሕንጻዎች ልማት ድርጅትን ጨምሮ የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ የአልባሳት እና የንዋየ ቅድሳት ማደራጃ እና የጎፋ ጥበበ እድ ማሠልጠኛ ከነዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
እነዚህ ገቢ ማስገኛ ተቋማት በኢንዱስትሪ መልክ ተቋቁመውና የቤተ ክርስቲያናችን ቦታ የሆኑትን ንዋየ ቅድሳት እና መጻሕፍት የአእምሮ ንብረት መብት በማስከበር ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር የነበረባቸው ሲሆን አሠራራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለና ወደ መዘጋቱ የደረሰቡት ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡
ከነዚህም ድርጅቶች መካከል በተለይም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤቱ በቂ ማሽኖች እና የሰው ኀይል እያለው የአመራር እና የአሠራር ችግር ተጋርጦበት ይገኛል፡፡ የድርጅቱ ሠራተኞች ምርታማ የሚሆኑበት የማትጊያ ስትራቴጂ ሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም ማተሚያ ቤቱን በሰው ኀይል እና በቁሳቁስ አደራጅቶ የኅትመት ሥራዎቹን በዚሁ ማተሚያ ቤት ማሠራት ሲገባው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በማውጣት በግል ማተሚያ ቤቶች እያሠራ ይገኛል፤ የማተሚያ ቤቱ ሠራተኞች በቂ የሆነ የደመወዝ ጭማሪም አላገኙም፤ የበጀት መጠኑም ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ መግለጫ የሆኑት ጃንጥላ፣ ዘቢብ፣ ጧፍ፣ ዕጣን፣ ሻማ፣ ምንጣፎች፣ የንዋየ ቅድሳት አልባሳት፣ አክሊል፣ ሞጣኅት. . .ወዘተ የመሳሰሉት በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁጥጥር ሥር በሙሉ አለማዋላቸውና የሌሎች እምነት ተከታዮች የንግድ መጠቀሚያ መሆናቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች በቤተ ክርስቲያናችን አንድ ወጥ በሆነ የኢንዱስትሪ ማዕቀፍ ቢታቀፉና ቢመረቱ የአእምሮ ንብረት መብትም ጭምር በተገኘባቸው ነበር፡፡
በአጠቃላይም የልማት ድርጅቶቹ ልማታዊነት ባልተረጋገጠበት የሠራተኞቹም ሞራል የሚጠበቅበት ሁኔታ እየተረጋገጠ አይደለም፡፡
13. የልማት ኮሚሽን
የልማት ኮሚሽናችን ቤተ ክርስቲያናችንን በመወከል ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴ በመጠቀም በርካታ የልማት ሥራዎች እየሠራ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ ኤች.አይ.ቪ./ኤድስን በመከላከል፣ ትምህርትን በማስፋፋት፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ በማገዝ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን በማሻሻል፣. . .ወዘተ ሥራዎች አመርቂ ሥራን የሠራ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው አስተዳደራዊ የሥራ ሂደት ግን ሊፈተሽ የሚገባው ሆኖ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ከገንዘብ ለጋሾች ጋር ያለው ትስስርም ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ የችግሩ ዐይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ከየአህጉረ ስብከቶች ጋር ያለው ግንኙነት እና ኮሚሽኑ የሚመድብላቸው/የሚልክላቸው በጀት አፈጻጸም በደንብ የተገመገመ አይደለም፡፡ የፕሮጀክቶችን ኦፕሬሽን ማኔጅመንት በተመለከተ የተሳካለት አካሄድን የተከተለ ሲሆን አስተዳደራዊ እና ፋይናንስ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን በሚፈለገው ደረጃ ባለመገኘታቸው ለጋሾች የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እየቀነሰ ፕሮጀክቶችም እየታጠፉ መጥተዋል፡፡ ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት ኮሚሽኑ ድርጅታዊ ዲዛይኑን በጊዜው ባለማስተካከሉ እንደ ሆነ ይገመታል፡፡
14. የዕቅድ እና ልማት መምሪያ
መምሪያው የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣትና የተለያዩ የሀብት ምንጮችን በማፈላለግ ዕቅዶቹ የሚፈጸሙበትን መንገድ በማፈላለግ አንድ የልማት ክንፍ ይሆናል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ መመሪያው ከሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ጋር በማቀናጀት ዓለም አቀፍ የልማት መርሖዎችንና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ቤተ ክርስቲያናችን የምእተ ዓመቱን የልማት ግቦች እንዲሁም የኢትዮጵያ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማዕቀፍ ውስጥ ተቀምጣ የራሷን ድርሻ የምትወጣበትን መሰላል አመቻች መሆን ነበረባት፡፡
መምሪያው አብያተ ክርስቲያናትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በደብዳቤ እንዲፈቀድ ከማድረግ የዘለለ ሥራ ያልሠራው ቤተ ክህነቱ በአጠቃላይ እየተከተለው ባለው ከዘመኑ ጋር የማይጓዝ የልማት ስትራቴጂ አካል በመሆኑ ነው፡፡ ከተልእኮው አንጻር መምሪያው መንፈሳዊ እና ዘመናዊ ዕውቀት ባላቸው ባለሞያዎች እየታገዘ የቤተ ክርስቲናያናችንን የልማት አቅጣጫ መምራት ሲገባው ከላይ የተጠቀሰውን ሥራ ብቻ እየሠራ መገኘቱ አሳባቢ ነው፡፡
15. ኮሌጆች
መንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ከምን ጊዜውም የተሻለ ሁኔታ ላይ ቢገኙም ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና ማኀበራዊ አገልግሎት ስኬታማነት የሚያግዙ መሪዎችን ግን እያፈሩ አይደለም፡፡ በኮሌጆቹ ውስጥ የመሪነት ካሪኩለም ተቀርጾ ከመንፈሳዊ እና ኮመን ኮርሶች በተጨማሪነት ለጊዜው ቢሰጥ ጠቃሚ የነበረ ሲሆን ኮሌጆቹ ወደፊት በሚኖራቸው ስትራቴጂክ ፕላን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንንና መሪነትን ማእከል ያደረገ ካሪኩለም እንደሚቀርጹ ይጠበቃል፡፡ ኮሌጆቻችን የቤተ ክርስቲያን ርእይ እና ተልእኮ የሚያስፈጽሙ እና የወደፊቱን መሪዎች ከመፍጠራቸው ባሻገር ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለኢትዮጵያ ሀገራችን የሚጠቅሙ ከፍተኛ ተመራማሪዎችን የማውጣት ተልእኮ ባነገቡ ነበር፡፡
16. የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት
ይህ ድርጅት የቤተ ክርስቲያናችንን ቤቶች ወርኀዊ ኪራይ በመሰብሰብ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ ከማድረግ የዘለለ ሥራ አልተሰጠውም፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራውን ሊገልጽለት የሚችል ስያሜ ማለትም “የቤት ኪራይ ሰብሳቢ ድርጅት” ተብሎ ቢባል ይመጥነው ነበር፡፡ በቅርብ ዓመታት የለማ ነገር አይታይም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ባዶ ቦታዎች እንዳሏት እየታወቀ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድርጅቱ ባዶ ቦታዎችን የማልማት አቅም እንዲኖረው አላስታጠቁትም፤ ያሉትን ቤቶች ለማስተዳደርም ቢሆን ሕግንና ደንብን ያልተከተሉ አሠራሮች የጐላ ሚና ነበራቸው፡፡ ድርጅቱ የሚሰበስበውን ገቢ ራሱ ባለማስተዳደሩ “ልማት” የሚባለው ቋንቋው ሕልም ሆኖ ቀርቶበታል፡፡ ገቢውን ራሱ አለማስተዳደሩ ያመጣበት ሌላው ጣጣ ደግሞ ከግብር ክፍያ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው፡፡ ገቢው ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደሚውል የታወቀ ቢሆንም ለታክስ አስተደደር ባለሥልጣናት ግን ይህን በዶክመንት አስደግፎ ማስረዳት አይቻልም፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በቤቶች ማስመለስ ሥራ እስከ አሁን አመርቂ ውጤትን ያስመዘገበች ሲሆን በድርጅቱ በኩል ቋሚ ሆኖ የመቀጠሉ ሂደት ግን ተዳክሟል፡፡ በቅዱስ አባታችን በይፋ የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራውን እየሠራ አይደለም፡፡ ቤቶቹ ኮምፒዩተራይዝድ በሆነ የመረጃ አያያዝ ሥርዐት ይካተቱ ቢባልም ዕንቅፋቱ ከቤቶቹ ቁጥር በልጧል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጠቃላይ የዚህን ኮሚቴ ሥራ በጥልቀት ባለመፈተሹ ምክንያት ጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ ድርጅቱ ሊቆጣጠሩት አልቻሉም፡፡ በግልጽ የተረከብናቸው እንደ ሰባት ወይራ ያሉት ቤቶቻችን ደግሞ ለንትርክ ዳርገውናል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቤቶችንና ቦታዎችን እስከ ዛሬ ድረስ ባለመረከባችን የአዲስ አበባ መስተዳድር በሚከተለው የመልሶ ግንባታ ፖሊሲ ምክንያት ተሸራርፈው እያለቁ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሳይቃጠል በቅጠል ሊሉት ይገባል፡፡
17. የግንባታ ፕሮጀክቶች
የግንባታ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት በርካታ ጥናቶችን የሚጠይቁ ሲሆን የቦታው ፈቃድ፣ አርክቴክቸራል ዲዛይንና የግንባታ ወጪ ግምት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ግንባታዎቹ ይህን በመሳሰለው ሂደት አልፈው ባለመጀመራቸው የፋይናንስ እጥረትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ሲደቀኑባቸው ይታያል፡፡
18. የውዝግብ አወጋገድ
ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየጊዜው ሊነሡ የሚችሉ ውዝግቦችን አስቀድመው የሚገምቱበትንና የሚከላከሉበትን መንገድ ያላበጁ ሲሆን ምሁራን የቤተ ክርስቲያኒቷን ልጆች በመጠቀም የቅድመ ውዝግብ ስልቶችንና ስትራቴጂን ማስነደፍ አለባቸው፡፡ አልፎ አልፎ የሚከሠቱ ውዝግቦችንም ከምንጫቸው ማድረቅ አለባቸው፡፡ ይህም ባለመሆኑ አንዳንድ ውዝግቦች መቋጠሪያ ውላቸው በፍጥነት ካለመገኘቱም ባሻገር እስከዚያው ድረስ አባቶችን የሚፈታተን ነገር ባልሰፋ ነበር፡፡ ወደፊት በሚከለሱ ደንቦች እና መመሪያዎች ውስጥ በስፋት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ጠቋሚ ምልክቶች ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ ይዳስሳሉ ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን አባይን በጭልፋ እንደ መጨለፍ ይቆጠራል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንመልከት፡፡
19. ጠቋሚ የመፍትሔ ሐሳቦች
- የጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ መመሪያ ደንብ እና የሠራተኛ አስተዳደር ደንብ ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ሕጎች እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንጻር በተቃኘ መልኩ እንደገና መቀረጽ አለባቸው፤ ልምድ እና ዕውቀቱ ባላቸው ባለሞያዎች መፈተሽ እና መዘጋጀት አለባቸው፡፡
- ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለው የመረጃ አያያዝ አሁን ባለበት ሁኔታ የማይጠቅም በመሆኑ አዲስ የመረጃ አያያዝ ሥርዐት ሊቀረጽ ይገባል፡፡
- አሁን ያለው የጠቅላይ ቤተ ክህነት መዋቅር ከሕገ ቤተ ክርስቲያን የመነጨ ቢሆንም በርካታ ችግሮች ያሉበት ሲሆን ዕውቀቱ እና ልምዱ ያላቸው ባለሞያዎች አዲስ የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት እንዲያደርጉ ቢታሰብበት ይሻላል፡፡
- ቅዱስ ሲኖዶስ በቋሚ ሲኖዶሱ በኩል ወይም ራሱ በሚያቋቁመው የባለሞያዎች ቡድን አማካይነት የግልጽነትንና የተጠያቂነትን መርሕ ለማዳበር እንዲረዳ የጠቅላይ ቤተ ክህነትንና የተለያዩ አካሎችን ሥራ በየጊዜው እንዲመረምር ማድረግ ይገባል፡፡
- ቅዱስ ሲኖዶስ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስትራቴጂክ ፕላን ዶክመንት የመኖሩን ሁለንተናዊ ጠቀሜታን ተወያይተውበት ከ5 - 1ዐ ዓመታት የሚደርስ መሪ ዕቅድ እንዲዘጋጅ በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን ለሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት አርኣያ እንድትሆን ማድረግ ይገባቸዋል፤
- የቤተ ክርስቲያናችንን የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽነት እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ አንድ የባለሞያዎች የፊሲካል ኮሚቴ ማቋቋም ይገባል፤
- የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ቋሚ ሲኖዶስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚመለከቷቸውን ጉዳዮች ደረጃ በግልጽ የሚያመለክት የአሠራር ማንዋል ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤
- የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዓመታዊ በጀት በሚዘጋጅበት ወቅት የሠራተኞችን አቅም ለማጐልበት የሚጠቅም ፈንድ ማዘጋጀት፣ ይህም እስከ አጥቢያ ድረስ እንዲወርድ ስልት እንዲነደፍ ማድረግ፤
- መደበኛ የሆነ የአሠሪ እና ሠራተኛ ምዘና ሥርዐት እንዲኖር ግልጽ የሆነ መመሪያ ማውጣትና ሠራተኛው በጤና እና የአደጋ ጊዜ ኢንሹራንሶች እንዲሸፈን ማድረግ ይገባል፤
- ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የሒሳብ አሠራር መርሖዎች መጠቀም እንዲቻል፡-
- ሀ. ዘመናዊ የሆነ የፋይናንስ ሥርዐት ልምድ እና ዕውቀቱ ባላቸው በውጭ ባለሞያዎች እንዲዘጋጅ ማድረግ፣
- ለ. ወጪዎች ከጸደቀ በጀት ጋር እንዲመሳከሩ ማድረግ፣
- ሐ. ሪፖርቶች ለጠቅላይ ጽ/ቤት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርቡ ማድረግ፣
- መ. የጠቅላይ ጽ/ቤት የቁጥጥር መምሪያ ተጠናክሮ የውስጥ ኦዲቲንግ ሥራውን እንዲያከናውን ማድረግ፣
- ሠ. ታማኝነትና ታዋቂነት ባላቸው የተመሰከረላቸው የሒሳብ ዐዋቂዎች ምርመራ እንደካሄድ ማድረግ ይገባል፡፡
11. የውጭ ግንኙነት እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው ዘመናዊ አሠራር እንዲተኩ ማድረግ፤
12. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚገኙ መምሪያዎች እና አህጉረ ስብከት እንዲሁም ድርጅቶች ከሚወክሉት የምእመናን ብዛት እና ከሚያስተዳድሩት ሀብት አንጻር ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዐት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ ዘመኑ እየተጠቀመበት ባለው የቴክኖሎጂ ምጥቀት አንጻርም በዚሁ ዘርፍ ቢታገዙ መልካም ይሆናል፡፡
13. የቤቶችና ሕንጻዎች ልማት ድርጅት የመረጃ አያያዝ ሥርዐቱ በኮምፒዩተር የታገዘና ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ከዓመታዊ የኪራይ ገቢ ላይ ቋሚ የልማት ፈንድ በመመደብ በርካታ ሕንጻዎች የሚሠሩበትን መንገድ በማመቻቸት የቤተ ክርስቲያን ገቢ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በመደገፍ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አስመላሽ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለድርጅቱ መሆን አለበት፡፡ ተቋማዊ ይዘት ከሌለው አካሄድ መውጣት ለተጠቀሰው ልማት መፋጠን አመቺ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያስብበት ይገባል፤
14. የግንባታ ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፍ አሠራር ስላላቸው ይህንኑ የሚከታተል አንድ የበጐ ፈቃደኞች የባለሞያ ቡድን ማቋቋም፡፡
2ዐ. ማጠቃለያ
ድርጅታዊ መዋቅርን መፈትሽ እና ዲዛይኑን ማሻሻል/መለወጥ ረጅም ጉዞን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ይህንንም እውንና ስኬታማ ለማድረግ የአመራሩን ጊዜ፣ ገንዘብ እና ባለሞያዎችን ይጠይቃል፡፡ የድርጅት ዲዛይን ማለት መዋቅሩን እና የሥራ ሂደቱን ማሻሻል ማለት ነው፡፡
ብቃት ያላቸውን ሰዎች መቅጠር ብቻ ድርጅታዊ ስኬትን አያረጋግጥልንም፡፡ እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሠራተኞች ድርጅታዊ ዲዛይኑ ደካማ በሆነበት የሥራ ቦታ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ደካማ እና ዝቅተኛ የድርጅት ዲዛይን ደካማ እና ዝቅተኛ ሞራል እና ምርታማነት ያላቸውን ሠራተኞች ይወልዳል፡፡
ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ባለሞያዎች እጥረት/አለመኖር፣ ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም ምርታማነት፣ የማያቋርጥ የአቤቱታ ብዛት፣. . .ወዘተ የመዋቅር እና የሥራ ሂደት መሻሻል እንዳለበት የሚያመለክቱ አመልካቾች ናቸው፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነታችን ውጤታማ የሆነ ድርጅታዊ ዲዛይን ባለመኖሩ ለሥራ የመትጋት ባህል ሊፈጠር አልቻልም፡፡ ይህም በመሆኑ ሠራተኞች የተጠያቂነታቸውን ደረጃ አያውቁትም፤ የድርጅታቸው ዓላማ እንዲሳካ ጥረት አያደርጉም፤ ለውጥ ማምጣት የሚችሉም አይመስላቸውም፡፡ ሠራተኞች ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ በመሆኑም ተገልጋዮች በጠቅላይ ቤተ ክህነትም ሆነ በአህጉረ ስብከት በሚያገኙት አገልግሎት ከፍተኛ ቅሬታ ያድርባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚባክነው ሀብት የትየለሌ ነው፡፡
ቀጣይነት ያለው ተቋዋሚ ውጤታማነትን ለመጐናጸፍ እና ለውስጥ እና ለውጭ ለውጦችና ፈተናዎች ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ስልቶችን መንደፍ፣ ብቃትን ማሳደግ እና መዋቅርን መፈተሽ፣ ሲስተሞችን ማሻሻልና ለመልካም ሥራዎች ማበረታቻ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የመልካም አመራር ዋነኛ መለያ ለውጦች የሕይወት አካል መሆናቸው ተገንዝቦ ለውጦቹ በሥርዐቱ እንዲጓዙ ማድረግ ነው፡፡ ዓለም በኀይለኛው ለውጥ እየተናጠች ባለችበት ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ የመረጋጊያ እና የመጠለያ ቦታ ለመሆን መዘጋጀት አለባት፤ ሃይማኖት እና ቤተ ክርስቲያን አትለወጥምና፡፡
የለውጥ ሂደት መኖር አለበት ተብሎ ሲታመን ከላይ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን ማኅበረ ካህናት እና ማኀበረ ምእመናን በስፋት ማሳተፍ አለባቸው ማለት ነው፡፡ የለውጡን የልብ ትርታ ማዳመጥ የሚቻለው በእያንዳንዱ ሰው የልብ ትርታ ውስጥ ነው፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና ሓላፊዎች የየአህጉረ ስብከት መሪዎች እና ተጠሪዎች በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያንን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም ሚና ስለሚኖራቸው ጥቅማቸው ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡ በመሆኑም ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩብን ትችቶች ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ሌሎችንም በርካታ ምክንያቶች ተንተርሰው ሲሆን በነዚህ በተወሰኑ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ርምጃ መውሰድ ጠቃሚነቱ የጐላ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የበላይ እና ጠቅላይ ቤተ ክህነትን የመቆጣጠር ሓላፊነትም ጭምር ስላለበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን እና ጨው መሆኗን በተጨባጭ ማስመስከር አለብን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
No comments:
Post a Comment