(by Birhanu Admass Anleye )እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ በመጥፋቴ ይቅርታ እየጠየቅሁ ለጊዜዉ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የሃይማኖት ዐምድ ‹‹ሃይማኖት እና ሴቶች›› በሚለዉ የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ላይ ከእኛ እምነት አንጻር ያቀረብኳትን ትንሽ መጣጥፍ እነሆ ብያለሁ፡፡
ቤልጄየም ዉስጥ በምትገኘዉ የአንትወርፕ ከተማ አይሁድ ይበዙባታል፡፡ በዚሁ ምክንያት በዚያ ሀገር ሱቆች እንኳ ሳይቀር በብዛት የሚይዙት ለአይሁድ የሚሆኑትን ልብሶችና ሌሎች የእነርሱን ፍላጎት የሚያሟሉ ነገሮች ነዉ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ለሁለት ሺሕ ዐመታት በተሰደዱባቸዉ ቦታዎችም ባሕላቸዉንንና ዕሴቶቻቸዉን ጠብቀዉ የሚኖሩ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ የተማሩት ትምህርትና የደረሱበት ሥልጣኔና ዘመናዊነት ምንም ያህል ተጽእኖ እንዳያመጣ አድርገዉ መቛቛማቸዉም ሥልጣኔና ዕሴትን አንዴት አስታርቆ መሔድ እንደሚቻልም ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡
ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ በሚኖሩበት ሀገር ባህልና ፖለቲካዊ ርእዮት የተማረኩ ትንሽም ቢሆኑ ስለሚኖሩ በሁለቱ መካከል የሚፈጠሩ ክርክሮች አይጠፉም፡፡ ከማልረሳቸዉ ነገሮች አንዱ የሚመለከተዉ ነበር፡፡ በቅርቡ ለቤልጄየም ፓርላማ የሚወዳደር አንድ አይሁዳዊ ወንድ ሚስቱ ወጥታ ድምጽ እንድትሰጠዉ ይጠይቃታል፤ ይህንኑ እንድታደርግም አጥብቆ ይከራከራታል፡፡ በዚህ ጊዜ ሴቲቱ ወደ ሕግ በማምራት ባለቤቷ እምነቷና ባህሏ የማይፈቅደዉን እንድታደርግ እየወተወታት መሆኑን በመግለጽ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ካለበለዚያም በሕግ እንዲፈታት በመጠየቅ የሴትነት መብቷን አስከብራለች፡፡ ለአንዲት አይሁዳዊት ሴት ይህም ሴትነትን አለማክበር ነዉና፤ ለዚያዉም በአዉሮፓ ዉስጥ ከሁለት ሺሕ ዐመታት ኑሮ በኋላ፡፡ ይህም ማለት ለምርጫ መዉጣትና ድምጽ መስጠት ለአንዳንዶቹ መብትን በማስከበር የተገኘ ክብር ተደርጎ ሲቆጠር ከላይ እንደጠቀስናቸዉ ላሉት ሴቶች ደግሞ ክብራቸዉ ለምርጫ አለመሰለፍ ነዉ ማለት ነዉ፡፡በሌላ ቛንቛ ክብሩ የሚመነጨዉ ከድርጊቱ ሳይሆን ከእምነቱና ከፍልስፍናዉ ነዉ ማለት ነዉ፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸዉን ሁለቱን ዐይነት ሴቶች ብቻ እንኳ ብንወስድ በሴትነታቸዉ አንድ ሆነዉ ሳለ ነጻነታችን መብታችን ክብራችን ለሚሉት ነገር የተለያዩት ለምንድን ነዉ ስንል ልዩነቱን የዕሴቶቻችን መለኪያ (value parameter) ልዩነት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ይህን በአንድ ሌላ ምሳሌ አስረድቼ ልለፍ፡፡ ከጥቂት ዐመታት በፊት ኢትዮጵያን መጥቶ ከጎበኘ በኋላ ስለኢትዮጵያ የጻፈ አንድ ፈረንጅ ትዝብቱን ሲጽፍ‹‹ኢትዮጵያዉያን ለልጆቻቸዉ ፍቅር የላቸዉም፤ ምክንያቱም ከወላጆች አንዳቸዉም ከቤት ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ልጆቻቸዉን አይስሟቸዉም(የዛሬን አያድርገዉና እዉነቱን ነዉ እንደሁኑ ከተሜ ልጅ መሳም አልነበረም፤ አሁንም በገጠሩ ኢትዮጵያ የለም)›› ብሎ ነበር፡፡ በመጽሐፍ ላሳተመዉ ለዚህ ሀሳቡ በመጽሐፍ መልስ የሰጡት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ስሕተቱን የገለጹለት ለአስተሳሰቡ መሠረት ከሆነዉ ግንዛቤ በመነሳት ነበር፡፡ እርሱ የሚያዉቀዉ የፍቅር መግለጫ መሳም ስለነበር የኢትዮጵያዉያኑን የፍቅር መገለጫ ሳይጠይቅ በድፍረት ‹ፍቅር የላቸዉም› ለማለት የበቃዉ የራሳችን ዕሴት በመዘንጋቱ ነበር፡፡በእኛ የጥንቱ ባህል ልጅን መደበቅ፣ እንግዳም ሲመጣም ወደ ጓዳ ማስገባት፣ ድንገት እንግዳ ሲመጣባቸዉም በቀሚሳቸዉ ደበቅ ማድረግና የመሳሰሉት ሁሉ የስስትና የፍቅር መግለጫዎች ነበሩ፡፡ምክንያቱም ሰዉ ሲያይባቸዉ በዐይን ራሱ የሚጎዳባቸዉ ስለሚመስላቸዉ (ይህ ሁሉ ገና ያልተጠና ስለሆነ ሊነቀፍ የሚችል አይመስለኝም) እጅግ አድርገዉ ለልጃቸዉ ይሳሳሉ፤ ይንሰፈሰፋሉም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዉያን ለልጆቻቸዉ በነበራቸዉ ፍቅር ከምዕራቡ ሰዉ ቢበልጡ እንጂ የሚያንሱ አልነበረም፡፡ ሆኖም ፈረንጁ የእኛን ማኅበረሰብ ዕሴት ሳይጠይቅ በመጻፉ ትልቅ ስሕተት ለመፈጸም ደፍሯል፡፡
አሁንም ደግሞ የበለጡ ስሕተቶች ሲፈጸሙ የምናየዉ በተመሳሳይ መንገድ ነዉ፡፡ ከጥቂት ዐሥርት ዐመታት ጀምሮ ያሉ አንዳንድ የኮሚኒስት አስተሳሰብ ግራ ያጋባቸዉ ሰዎች መለኪያቸዉ በሙሉ ያዉ ርእዮተ ዓለም ስለሆነ ብዙ ነገሮቻችን ያጣጥሏቸዋል፡፡ የእኛ ዘመን ትዉልድ ደግሞ መለኪያዉ ሁሉ ምዕራባዊ ብቻ ይሁን የተባለ ይመስል የብዙ ነገራችንን ሚዛን አዛብቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ምሁራኑም በእዉነተኛ ጥናት ላይ ተመሥርተዉ ለመንግሥት ፖሊሲ ቀረጻ ለማኅበረሰቡም አስተሳሰብ አቅጣጫ መጠቆም የቻሉ አይመስልም፡፡ ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል አንዳንድ ሰዎች ሁሉንም ነገር በሌሎች መነጽር እያዩ የማኅበረሰብ ብዥታን (confusion) በመፍጠር ላይ የሚገኙት፡፡
ከብዥታዎቹ አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ የሴቶችን እኩልነት አያሳይም፤ ስለዚህ ክርስትናም ለወንዶች ያደላ ነዉ የሚለዉ ተጠቃሽ ነዉ፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቀሰዉ ደግሞ ‹‹ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ … ባል የሚስት ራስ ነዉና›› /ኤፌ 5 ፥21/ የሚለዉ ዋናዉ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ይጠቀሳሉ፡፡
በርግጥ በብሉይ ኪዳን ጊዜ የወንዶች ትምክህት ከፍተኛ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ወንዶች በቀዳሚነት ሔዋን የስሕተት ምክንያት ነች በማለት ዳግመኛም የቀደመዉ አዳም ሴቲቱን ሔዋንን ያለ ሴት አስገኝቷል ፤ እናንተ ሴቶች ግን ወንድ ብትወልዱም ያለ ወንድ አትችሉም እያሉ ይመኩ እንደነበር ትዉፊቱን የመዘገቡ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህና መሰል ትምክህቶች ሁሉ ግን የወንዶቹ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ አልነበሩም ፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ክርስቶስም ሰዉ ሆኖ በመገለጥ የማዳን ሥራዉን ሲሠራ የጀመረዉ ይህን የወንዶችን ትምክህት ከመናድ ነዉ፡፡ ስለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመምረጥ ከእርሷ ተወለደ፡፡ በዚህም ሔዋን(ሴት) የስሕተት ምክንያት እንደሆነች ሁሉ እመቤታችንም (ሴት) የድኅነት ምክንያት ሆነች፡፡ አዳም ሔዋንን ያለ ሴት እንዳስገኘ ሁሉ እመቤታችንም ጌታን በድንግልና በመዉለድ ወንዱን ያለወንድ በማስገኘት የወንዶችን ትምክህት አፈረሰችዉ፡፡ እመቤታችንም ጌታን በመዉለድ የከበረች ስለሆነ ከፍጥረት ሁሉ (ከመላእክትም ጭምር) ትበልጣለችና መልዕልተ ፍጡራን ትባላለች፡፡ እመቤታችን የሴቶች መመኪያ የምትባለዉም ለዚህ ነዉ፡፡ ስለዚህ ክርስትና የተጀመረዉ የትዕቢትና የመናናቅ ምክንያት የሆኑትን አስተሳሰቦች ከማጥፋት ነዉና ተወቃሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ የተረፈ ካለም የሰዎች እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ወይም የቤተ ክርስቲያን አይደለም፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስም ዐላማ ሰዉን ማጽደቅ ስለሆነ በጸጋ፣ በእምነት፣ በሥራ በሚገኝ ዋጋ፣ … በመሳሰሉት ነገሮች የልዩነት መነሻዉ የራስ እምነት እንጂ ጾታ አይደለም፡፡ የወንዶችም የሴቶችም ቅዱሳን በብዛት አሉንና፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ብለን ያነሳናቸዉን ጥቅሶች መሠረት በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠያቂ ለማድረግ የሚጣጣሩ አሉ፡፡ በመሠረቱ አንድ የተማረ ሰዉ እንደሚያደርገዉ የቅዱስ ጳዉሎስን ሌሎች መልእክቶች በማንበብ ብቻ እንኳ ትርጉሙን ወይም መልእክቱን ለመረዳት ብንጥር በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታዉቁ እወዳለሁ›› /1ኛ ቆሮ 11፥3/ የሚለዉን ሌላዉን ጥቅሱን ብንመለከተዉ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ከዚህ ጥቅስ ‹‹ የክርሰቶስም ራስ እግዚአብሔር›› የምትልዋን ስንመለከት የራስ ትርጉም መበላለጥ፣ የበላይነትና የበታችነት ጉዳይ እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ምክንያቱም ጌታ ራሱ ‹‹ እኔና አብ አንድ ነን›› // እንዳለ በጌትነት፣ በሥልጣን፣ በመለኮት አንድ ናቸዉና፡፡ ስለዚህ ራስ የሚለዉ ቃል ትርጉም ከዚህ የራቀ እንደሆነ ይገባናል፡፡ ራስ ማለት መገኛ ማለት ነዉ፡፡ ስለዚህ ‹‹የክርሰቶስ ራስ እግዚአብሔር ነዉ›› ሲል እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ በዘመን ሳይቀዳደም በመለኮት ሳይተናነስ ከአብ የተገኘ ነዉ ማለት እንደሆነዉ ሁሉ ‹‹ የሴት ራስ ወንድ ነዉ›› ሲልም ሔዋን በባሕርይ ሳትተናነስ የተገኘችዉ ከኣዳም ነዉ ለማለት ነዉ፡፡ ስለዚህ የጥቅሱ ትርጉም መገኛነትን የሚያመለክት እንጂ የተለየ የጨቛኝነት መልእክት የለዉም፡፡
በሌላ መንገድ ስናየዉ ደግሞ (በተለይ ጥቅሱ የተጠቀሰዉ ለባለትዳሮች ነዉና) መልእክቱ እጂግ ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፡፡ ራስ ያለዉ ጭንቅላትን ስለሆነ ለወንዶች የተሰጠዉን ኃላፊነት የሚያመለክት ነዉ፡፡ ምክንያቱም በአንድ አካል ዉስጥ አንድ ራስ እንዳለ ሁሉ በአንድ ቤተሰብም ዉስጥ አንድ ራስ አለ፤ እርሱም ባል ነዉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሁለት ነዉ፡፡ አንደኛ አካል ከህልዉና ተባብሮለት በመገኘት አዳም ይቀድማል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሃይማኖታዊ በሆነዉ ጋብቻ ዉስጥ የወንዱ ዕድሜ መብለጥ ይገባዋል፡፡ይህም የሚሆነዉ በተፈጥሮኣቸዉ ዉስጥ ያለዉን ልዩነት አጣጥሞ ትዳሩን ዘላቂ ለማድረግ ጭምር ነዉ፡፡ ስለዚህ ወንዱ ከሴቲቱ በዕድሜና በተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ይበልጣልና የራስን ሓላፊነት አሸከመዉ፡፡ በአንድ አካል ዉስጥ ያለ ራስ የትኛዉንም የሰዉነት ክፍል አይጨቁንም፤ ይልቁንም ብልቶችን ሁሉ ይቆጣጠራል፣ ይመግባል፣ ይንከባከባል እንጂ፡፡ ከሰዉነት ክፍሎች አንዱ ቢታመምም ያንን የታመመ ብልት የበለጠ ይጠነቀቅለታል፣ ተንከባክቦም ወደ ጤንነት ይመልሰዋል፡፡ ስለዚህ ወንድ ራስ ነዉ ሲባልም ሓላፊነቱ ልክ እንዲሁ ቤተሰቡን መንከባከብ፣ መመገብ፣ ጤንነቱን መመለስ ነዉ፡፡ አንድ የሰዉነታችን ክፍል ሲታመም ራሳችን እንደሚያመን ሁሉ ባልም የቤተሰቡን ሁሉ ሕማምና ችግር የሚካፈል የሚፈታም ማለት እንጂ ራስ በመባሉ የበላይ ገዥ ነዉ ማለት አይደለም፡፡ ከሰዉነት ብልቶች ራስ የሚረግጠዉ ብልት የለም፡፡ ይረግጣል የምንለዉ እግር እንኳ መሬትን እንጂ አካልን አይረግጥም፡፡ ምናልባት ሚስቱን ወይም ሴቶችን የሚበድል ወንድ እንኳን ራስ ሊሆን እግርም ለመሆንም አቅቶታል ማለት ነዉ፡፡የሰዉነት ብልቶች ሁሉ ለራስ (ጭንቅላት) ያለማመንታት እንደሚታዘዙ እንዲሁ የቤተሰብ አባላትም በዚሁ መንገድ ለቤተሰቡ ራስ ለባል መታዘዝ ይኖርባቸዋል ማለት ነዉ፡፡ በሰዉነት ዉስጥ ይህ መስተጋብር ቢጠፋ ሰዉየዉ ለሞት እንደሚሰጠዉና አካልም እንደሚፈርሰዉ ልክ እንደዚሁ ሁሉ በቤተሰብም ዉስጥ በሰዉነት ዉስጥ ያለዉን ፍጹም አንድነትና መስተጋብር ከሌለ ትዳርም ማኅበረሰብም ሕይዎት አይኖራቸዉም፡፡ ስለዚህ ወንድ የሴት ራስ የሚለዉ በአንድ አካል ዉስጥ ያለ ሓላፊነትንና ዉሕደትን እንጂ የልዩነትና የመበላለጥ ዋቢ አይደለም፡፡ የሰዉነት ክፍሎች ሁሉም ራስ ሊሆኑ አይችሉም፤ ቢሆኑም አይጠቅሙም፡፡የአንድ ሀገር ዜጎች ሁሉም መሪ እንደማይሆኑ ቤተሰብም ሁሉ መሪ ቢሆን ጉዳት እንጂ ጥቅም የለዉም፡፡ ስለዚህ ራስነት ለአንዱ ብቻ ነዉና በሥነ ተፈጥሮ ሕግ ወንዱ ራስ እንደሆነ ይኖራል፡፡
ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ትርጉማቸዉ በዚሁ መንገድ የሚፈታ ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ትልቁ ችግር የተፈጠረዉ በመጽሐፉ ወይም በእምነቶቹ ሳይሆን ከላይ እንደጠቆምኩት እምነታዊ ቃላቱን ዳርዊናዊ መሠረት ባለዉ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ወይም ደግሞ ፍጹም ሊበራል በሆነ ምዕራባዊ መስፈሪያ ከመለካት ሙከራ የሚመጣ ስሕተት ነዉ፡፡ እያልኩት ያለሁት የሴቶች መብት አይከበር አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት የትኛዉ ነዉ ክብራቸዉ፣ መብታቸዉ፣ ጥቅማቸዉ (በዘመኑ ቛንቛ ለመናገር እንጂ ክብራቸዉ ክብራችን፣ ጥቅማቸዉም ጥቅማችን፣ …ነዉ) የሚለዉን ጠይቀን በእኛዉ እሴቶች መዝነን፣ አጥንተን መጠቀም ሲገባ ሌሎቹ ጠጥተዉ ባሸተቱን ቁጥር ቀድመን ማግሳቱን እናቁምና ለእኛዉ በሚጠቅመን መንገድ እናድርገዉ ነዉ፡፡ ለእሥራኤላዊቷ ሴት ክብሯና መብቷ የሆነዉ ነገር በምዕራባዊ እሴት ለምትኖር አንዲት ሴት ሊሆናት አይችልም፡፡ ስለዚህ ልዩነቱ የፍልስፍና የእምነት የባህልና የዕሴት ሆኖ ሳለ በዚያዉም ላይ የትኛዉ የተሻለ ጠቃሚ እንደሆነ ሳናጠና ሁሉንም በሰዉ መነጽር እያየን መልኩን ባናክፋፋዉ ይሻለናል፡፡ ስለዚህ ‹‹ወንድ-የሴት ራስ›› የጥቅም እንጂ የጉዳት፣ የክብር እንጂ የዉርደት ፣ የመከባበርና የመዋሐድ ትእዛዝ እንጂ የመበላለጥና የመለያየት ትእዛዝ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ባልገባን ነገር ገብተን አካልን አንገነጣጥል፣ ቤተሰብንም አንፈትን፡፡
Selam andadirgen endat keremachehu beterefe gen anderson lengerachehu never minor kechalachehu post yemetadreguten never lebezu anbabi endiwel pdf betadergut bryan Teri new egezabehar yemesgen Selam keremylgn
ReplyDeleteThis is a good lesson for the activist of women right.Extremism in women right does not helping here in western world except disructing family life and shortening the length of marriage to a few years.
ReplyDeleteDear birhanu i am really glad with what u dig about the concept where every body is running blindly. i wish if every body can give awhile to understand from deep root.
ReplyDeleteYAKOyYILIN
Dear Andadirgen, please write your source well, when you take article of others. because in this it means that dn. birhanu wrote for this blog. but i don't think so because i read this article on his facebook page. it is a good habit to credit and ask the writers before you take their work.
ReplyDeleteseems a small comment
Hi,
ReplyDeletePls post the pdf formate of your writings so that we could access it from any computer.
Thank you