Friday, November 4, 2011

ፓትርያርኩ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የሚጻረሩ ዝውውሮች እና ሹመቶች እያካሄዱ ነው


  • ከሓላፊነታቸው በተነሡት በአባ ሰቀረ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ምትክ በቅርቡ ከአሜሪካ ተመልሰው የአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አባ ኅሩይ መሸሻ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሓላፊ ሆነው እንደተሾሙ ተመልክቷል፤ አባ ኅሩይ በፓትርያርኩ ከቀረቡት የጵጵስና ሹመት ተስፈኞች ዝርዝር ውስጥ እንደነበሩበት ምንጮች እየገለጹ ነው።
  • ውጤታማው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ያለሲኖዶሱ ዕውቅና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው ተገልጧል፤
  • የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ያለሲኖዶሱ ውሳኔ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 24/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 4/2011, READ IN PDF)፦ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ እየመረጠ የመሾም ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፤ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ክፍል (አንቀጽ 30 ንኡስ አንቀጽ 9) ደግሞ የምክትል ሥራ አስኪያጁን አቀራረብ ሲያስረዳ “ሥልጣነ ክህነት፣ በቂ የትምህርት ደረጃና ችሎታ ያላቸውን ሦስት ሰዎች ለም/ሥራ አስኪያጅነት በእጩነት ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቦ ያስመርጣል፤ በምርጫውም ቅዱስ ሲኖዶስ ሲስማማበት የተመረጠው ሰው በፓትርያርኩ ይሾማል፤ የሚጻፍለት ደብዳቤም በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የሚፈረም ሆኖ በፓትርያርኩ ፈቃድ እንደተሾመ ይገለጻል” ይላል፡፡


ዛሬ የተገለጸው የጠ/ቤ/ክ የመንፈሳውያን ጉዳዮች ዘርፍ ም/ዋ/ሥራ አስኪያጅ ከሓላፊነታቸው የተነሡበት ይሁን የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመ/ፓ/ም/ዋ/ሥራ አስኪያጅነት መሾም በቋሚ ሲኖዶስ ቀርበው ስለ መመረጣቸው አልተረጋገጠም፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አባላት ስምምነትም አልተገለጸበትም፤ በተቃራኒው ብዙዎቹ የምልአተ ጉባኤው አባላት ለዚህ መረጃ እንግዳ እንደሆኑ የጉባኤው ምንጮች አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም በሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያን የሚደረገውን ስምሪት በመግታት፣ በጉቦ እና በዝምድና የሚደረገውን ቅጥር፣ ዝውውር እና ምደባ በማስቀረት፤ አጥቢያዎች በገንዘብ እና ንብረት ቁጥጥር ረገድ ከሙስና እና ከዘረፋ የጸዳ አካሄድ የሚከተሉበትን አሠራር በመዘርጋት የአጥቢያዎቹ ይሁን የሀገረ ስብከቱ ገቢ እንዲሻሻል ብሎም በ2003 የበጀት ዓመት በእርሳቸው አገላለጽ “ከሌሎች ምንጮች የተገኘው ገቢ ሳይቆጠር ከቆመ ሙዳዬ ምጽዋት ብቻ” ለመንበረ ፓትርያርኩ 35/65 በመቶ ብር 24 ሚሊዮን ፈሰስ ያስገቡ ውጤታማ ሥራ አስኪያጅ እንደሆኑ የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ ንቡረ እዱን በግትርነት የሚከሱ ወገኖች በመርሕ የተገደበው አካሄዳቸው ለዓመታት በሀ/ስብከቱ ውስጥ ከተዘረጋው የጥቅመኞች ኔትወርክ እና አልፎም ከሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር እንዳላስማማቸው ነው የሚናገሩት፡፡

ይህም በቀደመው የዋና ዋና ዜና ጥቆማችን ላይ እንዳመለከትነው በአንዳንድ ሁኔታዎች የአቋም መለሳለስ አሳይተዋል የተባሉት እና ከሁሉም መግባባት የሚሹት ሊቀ ጳጳስ መልቀቂያ እንዲያቀርቡ ሳይገፋፋቸው እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ የምልአተ ጉባኤው ምንጮች እንደሚያስረዱት በሥራ አስኪያጁ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዘዋወር ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ በሚገምቱት ምክንያት አዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ደርበው የያዙት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ያቀርቡታል የተባለው መልቀቂያ መታለፉን አስረድተዋል፡፡

በ30ው የመ/ፓ/አጠ/ሰ/መ/ጉ ስብሰባ ላይ ሥራ አስኪያጁ የሀ/ስብከቱን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ሊረዱት በማይችሉት ሁኔታ ሪፖርቱን እስከሚያቀርቡበት ዋዜማ ምሽት ድረስ በአንዳንድ አድባራት እና ገዳማት አለቆች አድማ እየተጎነጎነባቸው እንደሆነ በማስታወቅ ካህናት እና መምህራን “እጃችንን በመሰብሰብ” (ከሙስናው ለማለት ይመስላል) ለሚያስተምሯቸው ምእመናን ምሳሌያዊ መሪ መሆን እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህን በሐዘን የተሞላ ንግግራቸውን የሚያስታውሱ ሌሎች ታዛቢዎች፣ ለውጤታማው ሥራ አስኪያጅ መነሣት ከሙዳዬ ምጽዋት ቆጠራ ርቀው ታዛቢ እንዲሆኑ የተደረጉት የአንዳንድ አድባራት አለቆች፣ ፀሐፊዎችና ቁጥጥሮች ከእነ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋር የሸረቡት ሤራ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 35 መሠረት ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የሁሉም አህጉረ ስብከት ማዕከል የሆነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው ልዩ ደንብ እና መመሪያ እንደሚተዳደር፣ በቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ እንደሚመራ የተገለጸ ቢሆንም “የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት” በሚል የሚሾሙትም ሊቃነ ጳጳሳት “የፓትርያርኩ ረዳት /ሊቀ/ጳጳስ” እንደሚባሉ ይታወቃል፡፡  

በሌላ በኩል በሃይማኖት ሕጸጽ የተጠረጠሩት አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልየትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሆነው መሾማቸው እየተነገረ ነው፤ አሁን የመምሪያው ዋና ሓላፊ ሆነው የሚሠሩት መጋቤ ሥርዓት ዳንኤል ወልደ ገሪማ ወዴት እንደተዘዋወሩ አልተገለጸም፤ ቀደም ሲል አባ ሰረቀ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ የተጻፈላቸው ደብዳቤ በገጠመው ተቃውሞ ውድቅ ተደርጓል ተብሏል።

ዛሬ በተሰማው ሹመት አባ ሰረቀ በአቅማቸው ይሁን በመሠረታዊ ዓላማቸው ይቅርና ለዚህ ግዙፍና ውስብስብ ግብ ፍጻሜ ሊበቁ ራሳቸውን አደራጅተው በየአህጉረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሚገኙትን ሰንበት ት/ቤቶች እንኳን አስተባብሮ ለመምራት እንደማይመጥኑ ስድስት ዓመት በተግባር ተፈትነው የወደቁበት ተመክሯቸው ምስክር ነው።

የቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ኮሌጆች) እና የአብነት ትምህርት ቤቶች በበላይነት የማስተባበር ሥልጣን የተሰጠው ይህ መምሪያ በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ከነበረበት በባሰ ሁኔታ እንዲዳከም ህልውናውም እንዲዘነጋ ከተፈረደባቸው መዋቅሮች አንዱ ስለመሆኑ የመምሪያው የቀድሞ ሓላፊዎች በምሬት እንደሚናገሩ ተዘግቧል፡፡

በ30ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው በተያዘው የበጀት ዓመት መምሪያው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚያበቃ የዕውቀት ምንጭ የሆኑት የአብነት ት/ቤቶች ትምህርት ከዘመናዊው ጋር ተቀናጅቶ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሥርዐተ ትምህርት እንዲያዘጋጅ፤ ለአብነት ት/ቤቶች መምህራንና ደቀ መዛሙርት የሚደረገው ድጋፍና ክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ሦስቱ ኮሌጆች በበጀት ራሳቸውን ለማጠናከር በሚያደርጉት አበረታች ጥረት እንዲተጉና በሥነ ምግባር የታነጹ ደቀ መዛሙርትን ኮትኩተው እንዲያስመርቁ ብርቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ”አሳስቦ ነበር፡፡ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤም የመምሪያው በጀት ተሻሽሎ እንዲሠራለት ትእዛዝ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አባ ኅሩይ መሸሻ
በተያያዘ ዜና ከሓላፊነታቸው በተነሡት በአባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ምትክ በቅርቡ ከአሜሪካ ተመልሰው በመምጣት የአየር ጤና ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አባ ኅሩይ መሸሻ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሆነው እንደተሾሙ ተመልክቷል፤ አባ ኅሩይ በፓትርያርኩ ከቀረቡት የጵጵስና ሹመት ተስፈኞች ዝርዝር ውስጥ እንደነበሩበት ምንጮች እየገለጹ ነው። (ይህንን ጉዳይ ወደፊት በጥልቀት እንመለስበታለን)::

ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም 13 ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቃለ ጉባኤዎቹን እየተናበበ በአንዳንድ አጀንዳዎች ላይ የተወሰነውና በጽሑፍ የሰፈረው ሲያወዛግብ በዋለበት ሁኔታ፣ ፓትርያርኩ ሰሞኑን ውድቅ የተደረጉባቸውን አጀንዳዎቻቸውን እና ሐሳቦቻቸውን በዐይነት ለመመለስ በሚያስመስል አኳኋን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚፃረሩትን እኒህን ዝውውሮች እና ሹመቶች እንዲከናወኑ ማድረጋቸው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ እና ጉዳዩን ሲከታተሉ በሰነበቱት አካላት ዘንድ አነጋጋሪና ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን

No comments:

Post a Comment