Sunday, November 13, 2011

“የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አከብራለሁ፣ የተመደብኩበት ቦታ እሄዳለሁ” ብፁዕ አቡነ አብረሃም


  • ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ልካኝ አሜሪካን መጥቼ ነበረ፤ አሁንም ቤተ ክርስቲያን ወደ ላከችኝ ቦታ እሄዳለሁ” በማለት ሲናገሩ በበዓሉ የተገኙት ምእመናን እና ካህናት በእንባ እንደተራጩ በቦታው የተገኙ የአይን ምስክሮች ገልጸውልናል::

በሲልቨር እስፕሪንግ ሜሪላድ ኆኅተ ምሥራቅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ቤት ለማክበር የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብረሃም ወደ ኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ መደባቸው ሀገረ ስብከት እንደሚሄዱ ገለጹ:: ብፁዕነታቸው የተመደቡበት ቦታ የሚገልጽ ደብዳቤ ህዳር 1፣ 2004 ዓ/ም እንደደረሳቸው ገልጸው፤ ነገር ግን ለዚህ ሀገረ ስብከት ስለተመደበ አባት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል:: ብፁዕነታቸው አንዳንድ ጅምር ሥራዎች ሥላሉዋቸው እስከ ታህሣሥ ወር አጋማሽ ድረስ ለመቆየት ለቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ መጻፋቸውም ጭምር ገልጸዋል:: በዕለቱም ትምህርታቸው “እኔ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እና ቀኖና ይከበር ብዬ እያስተማርኩ፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የምጥስበት ምክንያንት ምንም የለኝም” በማለተ ተናግረዋል:: አንዳንድ ሰዎች “ዛሬ ለምን የቅዳሴ ቤቱን አከበርክ”? ብለው ይጠይቁ ይሆናል፤ ነገር ግን ዛሬ የተገኘሁበት ምክንያት አስቀድሞ የተያዘ መርሀ ግብር በመሆኑ እንዲሁም ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ መነሳቴ እንደ እናተው ዜና ከማንበብ ውጪ ሌላ ምንም የደረሰኝ መልዕክት ስላልነበረ ነው:: ሥለዚህ በዛሬው እለት የቅዳሴ ቤት ማክበሬ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን የወጣ አይደለም ብለዋል::

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ልካኝ አሜሪካን መጥቼ ነበረ፤ አሁንም ቤተ ክርስቲያን ወደ ላከችኝ ቦታ እሄዳለሁ” በማለት ሲናገሩ በበዓሉ የተገኙት ምእመናን እና ካህናት በእንባ እንደተራጩ በቦታው የተገኙ የአይን ምስክሮች ገልጸውልናል::

በሰሜን አሜሪካን የኢ/ኦ/ተ/ቤ ታሪክ ሀገረ ስብከት የሚለውን ስም እንኳ በምእመናን ዘንድ አይታወቅም ነበረ:: ብፁዕ አቡነ አብረሃም እዚህ አካባቢ ተመድበው ከመጡ በኋላ ግን ሀገረ ስብከት በስም ከመታወቁም በላይ፤ ለሀገረ ስብከቱ ጽፈት ቤት የአካባቢው ምእመናን አሰባስበው አስተምረው እንዲገዛ አድርገዋል:: ብፁዕነታችው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤ መግዛት ብቻ ሳይሆን፤ መንበረ ጵጵስና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲመሰረት አድርገዋል:: እንዲሁም ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና እንዲከበረ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ እስቴቶች በመዘዋወዛር ምእመናንን እያስተማሩ በርካታ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ እንዲመሰረቱ አድርገዋል:: ለቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ሥርዓት መከበር የማይበገረው ብርቱ አቋማቸው በተለይም በወጣቶች ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅ አባት ናቸው::

“የእኔ እና የእናንተ አባቶች ንጽሕት ሃይማኖት ከሙሉ ሥርዓቱ ጋር፤ እንዲሁም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሳያፋልሱ ከቀደሙት አባቶቻቸው የተረከቡትን ለእኛ አስረክበውናል። ለእኔ እና ለመሰሎቼ በመንፈስ ቅዱስ ለምንወልዳቸው ልጆቻችን፣ ለእናተ ደግሞ በሥጋ ለምትወልዱዋቸው ልጆቻችሁ በዚህ በዲያስጶራው ዓለም ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አስረክበናቸው ልናልፍ ይሆን?” በማለት በተገኙበት ቦታ ሁሉ የቤተ ክርሲያናችን ቀኖና እንዲጠበቅ የሚያስተምሩት ብፁዕነታቸው በዛሬው እለትም ይህን ትምህርታቸው እንደደገሙት ተገልጾልናል::

በተለያየ መልኩ በዘር፣ በፖለቲካ፣ በገንዘብ እንዲሁም ደግሞ በሃይማኖት የተከፋፈለችው የሰሜን አሜሪካን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለማስታረቅ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል:: ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጪ ያሉት ገለልተኛ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር እንዲገቡ ጥረት ያደርጉ እንደነበረም ይታወቃል:: ብፁዕነታቸው አሳምነኝ እና እኔም ላሳምንህ የሚለው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መከበረ በየዙት አቋማቸው ምክንያት በተለያየ ነገር የተያዙት አጥቢያዎች ወደ ቤተ ክርስቲቷ መዋቅር ስር ሊገቡ አልቻሉም::

ብፁዕነታቸው በሰሜን አሜሪካን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ሕግ መሰረት የአሜሪካን መንግስት እንዲያውቃት እና መብቷም እንዲከበረ (patent right) እንዲኖራት ብዙ ጥረዋል::

በዛሬ ዕለት በቤተ ክርስቲያናችን ሕግ እና ሥርዓት መሰረት በሲልቨር እስፕሪንግ ሜሪላንድ የተቋቋመው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜያዊ ኮሚቴው ስለ ቤተ ክርስቲያኑ መመስረት አስመልክቶ መልዕክት ተላልፎ ነበረ:: መሉ መልዕክቱም ደርሶናል እንደሚከተለው ቀርቧል::

+++

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ሐዋርያዊት እና ሲኖዶሳዊት ናት። ይህች ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እኛ በምንኖርበት አካባቢ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ቀኖናዋ ተጥሶ በተለያየ መልኩ ውጥን ቅጡ በማይታወቅ ሁኔታ አንድነቷ ተንዶ ፈተና ላይ ትገኛለች:: ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ ችግር አይቶ ለዘለቄታው መፍትሔ እንዲገኝለት ሊቀ ጳጳስ በመመደብ ሀገረ ስብከት ተመስርቷል። ሀገር ስብከቱም ከተመሰረተ ወዲህ በዓይን የሚታዩ ለውጦች አሉ፤ ለምሳሌ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መመስረት፣የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መኖሪያ እና ጽ/ቤት ግዢ መፈጸም የሚጠቀሱ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናችን ከገጠማት ፈተና መፍትሔ ከሚሆኑ ሥራዎች መካከል አንዱ ከእናት ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ሰንሰለት ያላተቋረጠ እንዲሁም ደግሞ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያላፋለሰ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናትን መመስረት ነው። ከግንዱ ያልተለዩና ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መዋቅር የጠበቁ አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት በየቦታው ከተመሰረቱ፤ የሚቀጥለው ትውልድም ግራ ሳይጋባ እና ከማንም ጋር ሳይካሰስ ቤተ ክርስቲያኒቷን ይረከባል። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ የበለጠ ሥር ሰዶ ትውልዱም እያወቀ ሲመጣ ግራ በመጋባት ከቤተ ክርስቲያን ይሸሻል። ስለዚህ ሐዋሪያዊት ለሆነችህው የኢ/ኦ/ተ/ቤ እውነተኛ ድምፃን የሚሰማባቸው፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያላፋለሱ፣ ሐዋሪያዊ ትውፊቷ የጠበቁ አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት እንደሚያስፈልግ በማመን ይህን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመመስረት ተገደናል::

የዚህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመመስረት ውይይት የተጀመረው የካቲት 12፣ 2002 ዓ/ም አንዲት እህታችን ወልዳ አራስ ለመጠየቅ የተሰባሰቡ ወንድሞች አማካኝነት ነው:: ውይይቱም እየሰፋ መጥቶ ጉዳዩን ወደ ብፁዕ አባታችን አቡነ አብረሃም ዘንድ በግንቦት ወር 2002 ዓ/ም መነሻ ሀሳቦቻችን ይዘን ሄድን:: ብፁዕነታቸውም በደስታ ሀሳቡን ተቀብለው፤ በሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ለመርዳት ከጎናችን እንደሆኑ ቃል ገብተውልን ተለያየን::

የብፁዕ አባታችን ቡራኬ እና መመርያ ከተቀበልን በኋላ ሀሳቡን ለአካባቢው ምእመናን የሚዳረስበት ሁኔታ እያጠናን ቆየን:: በተለያዩም ወቅታዊ በሚያጋጥሙን የቤተ ክርስቲናችን ፈተናዎች ምክንያትም የጀመርነው ሥራችን በጣም ወደ ኋላ አዘገየን:: ምንም እንኳ ቢዘገይም የእግዚያብሔር ፈቃድ እስካለበት ድረስ አጥቢያው መመስረቱ እንደማይቀር እናምን ነበረ::
የዚህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መመስረት ምክንያት የሆኑን ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:-

1. በሲልቨር እስፕሪንግ እና አካባቢው ለምንኖር የቤተ ክርስቲያኒቷ ልጆች ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የምንሰማበት ምቹ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሰረት የተመሰረተ አማራጭ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አለመኖር።
በዚሁ አካባቢ ከላይ እንደተጠቀሰው በተለያዪ ግለሰቦች እና ቡድኖች ስም አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ቢኖሩም፤ ነገር ግን በኢ/ኦ/ተ/ቤ ቀኖና እና ሥርዓት መሰረት የተቋቋመ ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያኒቱ ድምጽ የሚሰማበት ምንም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ በአካባቢው የምንኖር ምዕመናን ያለፍላጎታችን ወደ ተጠቀሱት አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት እንድንሄድ ተገደን ነበረ። ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ በዚህ አካባቢ ለምንኖር የቤተክርሥቲያኒቷ ልጆች የምንገለገልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያሥፈልገናል ብለን ወሰንን::

2. በኢ/ኦ/ተ/ቤ ሥርዓት እና ቀኖና መሰረት በሀገር ስብከቱ ውስጥ የተቋቋመው መንበረ ጵጵስና ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ሩቅ በመሆኑ ተገልጋዮች ለእንግልት ተዳርገን ነበረ::
ወደ መንበረ ጵጵስና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ግዴታ ከአንድ ሰዓት ያላነሰ መንዳት ይጠበቅብናል፡ መኪና መንዳት ለማይችሉ ምእመናን ደግሞ ምንም አይነት የትራንስፖርት አማራጭ አለመኖሩ ሰንበትን በቤታችን እንድናሳልፍ እንገደዳለን። ታዲያ ይህን ችግር ለመፍታት የአካባቢውን ሁኔታ ተጠንቶ ለህዝብ ትራንስፖርት አመቺ በሆነ ቦታ እዚሁ አካባቢ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ቀኖና መሰረት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መመስረት የግድ መሆኑን በሙሉ ድምጽ ተስማማን።

3. አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ከተቋቋመ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን፣ ቀኖናዋን፣እውነተኛ ድምፃን ለአካባቢው ነዋሪዎች የምታስተምርበት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል የሚል አቋም አለን።

የኢ/ኦ/ተ/ቤ ሐዋሪያዊ ተልኮዋን የምትፈጽምበት በዚህ በሲልቨር እስፕሪንግ እና አካባቢው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የላትም። ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ትክክለኛውን መንገድ የማስተማር ግዲታ አለባት። ሥለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍና ቤተ ክርስቲያን እውነተኛውን ሐውሪያዊት እና ሲኖዶሳዊት ተልኮዋን በትትክክል ለልጆቿ የምታስተላልፍበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መቋቋም ግድ እንደሆነ አምነን ጀመርነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

ከአሐቲ ተዋሕዶ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment