BY HENOCK YARED
‹‹ዳሞ ደስ ይበልኪ
ተሠርገወ ደብርኪ››
ትግርኛን ከግእዝ ጋር አስተባብሮ ‹‹ደስ ይበልሽ ደብረዳሞ፤ ተራራሽ አምባሽ አሸበረቀ፤ ተዋበ፤›› እያለ ግጥሙን ያቀረበው አንድ የአካባቢ ነዋሪ ነው፡፡
ጭራ ዋጣውም (ባለማሲንቆው አዝማሪ) በበኩሉ
‹‹አረጋዊ ፀሓዬ
መፅኤአለኹ ናብ መፅብዓዬ››
(አረጋዊ ፀሐዬ ወደ ስለቴ መጥቻለሁ)
ጭራ (ማሲንቆ) እና ድምፁን ሲያስማማ በዙርያው ያሉት ምዕመናንም እየተቀባበሉ መዘመራቸውን አልተውም፡፡ ይህም የተሰማው፣ የተስተጋባው ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ዓመታዊው የአቡነ አረጋዊ በዓል በተከበረበት ዕለት በጥንታዊውና ታሪካዊው ደብረ ዳሞ ገዳም በተገኘበት ጊዜ ነው፡፡
‹‹ዳሞ ደስ ይበልኪ
ተሠርገወ ደብርኪ››
ትግርኛን ከግእዝ ጋር አስተባብሮ ‹‹ደስ ይበልሽ ደብረዳሞ፤ ተራራሽ አምባሽ አሸበረቀ፤ ተዋበ፤›› እያለ ግጥሙን ያቀረበው አንድ የአካባቢ ነዋሪ ነው፡፡
ጭራ ዋጣውም (ባለማሲንቆው አዝማሪ) በበኩሉ
‹‹አረጋዊ ፀሓዬ
መፅኤአለኹ ናብ መፅብዓዬ››
(አረጋዊ ፀሐዬ ወደ ስለቴ መጥቻለሁ)
ጭራ (ማሲንቆ) እና ድምፁን ሲያስማማ በዙርያው ያሉት ምዕመናንም እየተቀባበሉ መዘመራቸውን አልተውም፡፡ ይህም የተሰማው፣ የተስተጋባው ጥቅምት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ዓመታዊው የአቡነ አረጋዊ በዓል በተከበረበት ዕለት በጥንታዊውና ታሪካዊው ደብረ ዳሞ ገዳም በተገኘበት ጊዜ ነው፡፡
በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተቆረቆረው ገዳም በከፍታማ ተራራ ላይ የሚገኝና ዙርያው ገደል በመሆኑ መወጣጫው ከቆዳ በተሠራ ሐብል (ገመድ) በመጠቀም ነው፡፡ ለ14 ክፍለ ዘመን ያህል ወደ መወጣጫው ሀብል (አምባው ስር) ለመድረስ ለምእመናን (ነጋድያን /Pilgrimage)፣ ለጎብኚዎች እጅግ ፈታኝ የነበረውን ወጣ ገባና ተረተር የለወጠ 1.2 ኪሎ ሜትር የሚደርስ በሦስት አቅጣጫ መረማመጃ ደረጃዎች መሠራቱ ነው፡፡ ‹‹መንገዱ እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ስለነበረ ከርቀት ከመስኩ ላይ ሆነን ነበር ጸሎታችንን ስናደርስ የኖርነው፡፡ አሁን ግን መወጣጫው መሠራቱ ሳንቸገር መድረስ ችለናል›› ያሉን አረጋዊው አቶ ተስፋሚካኤል ተክለሃይማኖት ናቸው፡፡ የእናቶችም አስተያየት ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡
‹‹ሕዳሴ አቡነ አረጋዊ ዘ ደብረ ዳሞ›› በሚል መሪ ቃል እየተንቀሳቀሰ ያለው የአቡነ አረጋዊ ደብረ ዳሞ ገዳም ልማት ኮሚቴ፣ 1.5 ሚሊዮን ብር አካባቢ በሚደርስ ወጪ ካስገነባው የደረጃ መንገድ ሌላ ከአምባው ላይ ያለው ገዳሙ የወንዶች ብቻ በመሆኑ ወደ ላይ መውጣት ለማይፈቀድላቸው ሴቶችና በመወጣጫ ሐብል ወደ ገዳሙ የመውጣት ጉልበት ለሌላቸው ወንዶች ገዳሙ ከሚገኝበት አምባው ስር ፀበል እንዲያገኙ ከገዳሙ የሚወርድ ፀበል የሚጠራቀምበት ታንከር ተሠርቷል፡፡
ምእመናን ከታች ኾነው የገዳሙን ቅዳሴና መንፈሳዊ ትምህርት በሚገባ እንዲከታተሉ የሚያስችልም የድምፅ ማስተላለፊያ (ሳውንድ ሲስተም) ከማስገባቱም ሌላ አምባው ሥር ምዕመናንን ሊያስተናግድ የሚችል ማረፊያ ቦታ ሠርቷል፡፡
ደብረ ዳሞ ገዳም መንፈሳዊ እሴቶቹና ታሪካዊ ቅርሶቹ ተጠብቀው ምእመናን፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎች የሚጎርፉበት ኢትዮጵያዊ መስህብ ማድረግ አንደኛው የኮሚቴው ራዕይ መሆኑን የጠቆሙልን አቶ ተወልደ ብርሃን ታደሰ የአቡነ አረጋዊ ደብረ ዳሞ ገዳም ልማት ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡
የጥንታዊውና ታሪካዊው ደብረ ዳሞ ገዳም ለኢትዮጵያም ሆነ ለአኅጉሪቱ ያለውን ፋይዳ የሚያንፀባርቅ ምእመናንና ጎብኚዎች የሚማሩበትና የሚያውቁበት ሙዚየም በአምባው ሥር የመሥራት እቅዱን እውን ለማድረግም ኮሚቴው ጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኑሯል፡፡
ሙዚየሙን ስዊዘርላንዳዊው ሚስተር ኩርት ፕፍስተርና ቤተሰባቸው እስከ 1.2 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለማሠራት ቃል የገቡ ሲሆን፣ ሥራውን ለማስጀመር 30,000 የአሜሪካ ዶላር መስጠታቸውን ኮሚቴው ይፋ አድርጓል፡፡
በምረቃውና የመሠረት ድንጋይ በተጣለበት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት በትግራይ ክልል የምሥራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ ባደረጉት ንግግር፤ ‹‹አቡነ አረጋዊ ደብረ ዳሞ ገዳም ማንነታችን፣ ታሪካችንና የጥንት አባቶቻችን ጥበብ የሚገልጽ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ቋሚ መለያ ቅርሳችን ነውና የተሟላ መሠረተ ልማት እንዲያገኝ ማድረግም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
የገዳሙ ልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በተወካያቸው በአቶ ገብረ እግዚብሔር ናይዝጊ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ኃላፊ በኩል ባስተላለፉት መልእክት፣ ‹‹ገዳሙ በሥነ ሕንፃ ጥበብ ጥንታዊም እንደመሆኑ መጠን ለአገራችን ቱሪዝም አንዱ ትልቅ መስህብ ስለሆነ አገሩንና ታሪኩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ታሪካዊውን ገዳም በመጎብኘት እንዲማርና እንዲያጠና እንዲሁም ገዳሙ ጥንታዊ ታሪካችንንና ሥልጣኔያችን እየጠበቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያሸጋገር የበኩሉን ሚና ይጫወት፤›› ብለዋል፡፡
ደብረ ዳሞ ማነው?
ደብረ ዳሞ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ትግራይ በ535 ዓ.ም. የታነፀ ገዳም ነው፡፡ መጠርያ ስሙንም ያገኘው ከአምባው ሲሆን፣ ከባሕር ወለል 2216 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ ደብረ ዳሞ ገዳም እስካሁን ህልውናው የተጠበቀ ከ1400 ዓመት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡
ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የአክሱምን ሥነ ሕንፃ ጥበብ ተከትሎ የተሠራና የዚያን ዘመን አሻራ የያዘ ነው፡፡ ከአዲግራትና እንትጮ ከተሞች መካከል በጉሎ መከዳ ወረዳ የሚገኘው ገዳሙ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ገዳምና የምንኩስና ሥርዓት የተጀመረበት ነው፡፡ ዙርያው ገደል የሆነ የጠረጴዛ ቅርጽ ወዳለው አምባ የሚወጣውና የሚወረደው በጠፍር ገመድ እየተንጠለጠሉ ነው፡፡
በአባ ገብረኢየሱስ ኃይሉ ድርሳን እንደተጻፈው፣ ደብረ ዳሞ አንድ ለተራራው መውጫ አንድ ለሰው እግር መርገጫ የሚሆነው ቦታ አይገኝበትም ነበር፡፡ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑ አቡነ አረጋዊ (አቡነ ዘሚካኤል አረጋዊ) በ6ኛው ምእት ዓመት መጀመርያ የተከሉት ነው፡፡
እሳቸው ከምድራዊ ዓለም ርቀው ከሰው ማኅበር ተለይተው፣ በሕሊናቸው ወደ እግዚአብሔር እንደቀረቡት መጠን፣ እንዲሁም በቦታ ወደ ሰማይ የሚያቀርባቸው መካንን ፈለጉ፡፡ የደብረ ዳሞ ተራራንም አገኙ፡፡ በተራራው እግርጌ አንድ በዓት (ቦታ) አለ፤ እሱም በዓተ ኤሌም ይባላል፡፡ እዚያው ለመጀመርያ ጊዜ መጠጊያን አገኙ፡፡ ነገር ግን እርሳቸው የተመኙት ተራራው ጫፍ ላይ መውጣት ነበር፡፡ ከናታቸው ከእማሆይ አድናግ በጸሎትና በመንፈስ ንቃት የላይ ላዩን ሲያስቡ፣ አቡነ አረጋዊ ምኞታቸው እየጋለ በመሔዱ ወደ ላይ ለመውጣት በሞከሩ ጊዜ አንድ ትልቅ ዘንዶ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ የሆነው ጭራቸውን ወደ ታች አወረደላቸው፡፡ እሳቸውም ይህ ነገር በእግዚአብሔር የታዘዘላቸውን መውጫ መሆኑን አመኑና በጽኑ ሃይማኖት አላንድ ስጋት የተዘረጋላቸውን ገመድ መሳይ ይዘው እስከ ደብሩ ጫፍ ወጡ፡፡ እዚያው ከደረሱም በመጀመርያ ከልባቸው የፈለቀ እግዚአብሔርን ማመስገን ሆነና ‹‹ሃሌ ሉያ›› በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋናን አቀረቡ፡፡ ደብሩም በሌላ መጥርያው ደብረ ሃሌ ሉያ ተባለ፡፡
የአፄ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል የደብሩን ቤተ ክርስቲያን አሠሩ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃም ከአክሱም የመነጨ የሥነ ጥበብ ፍሬ ነውና በቅርጹም ባተናነፁም ያክሱም ትምህርት መሆኑ ጐልቶ ይታያል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን በማሠራት ዕቃዎች ወደ ላይ ለማስወጣት አስፈላጊ ስለሆነ፣ ዓለቱ ላይ በውቅር የመሰላል ደረጃዎች ተጠርቦበት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከተፈጸመ ወዲያ ግን መሰላሉን በአቡነ አረጋዊ ትእዛዝ አፈረሱት፡፡ ቦታውም ወደ ዱሮው ሁናቴው ተመለሰ ይባላል፡፡
ዳሞ የሚለው ስያሜ አቡኑ ‹‹ዳህምሞ›› (አፍርሰው) ካሉት ተነሥቶ የተሰጠ ስያሜ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በሌላ መልኩም ይህ ‹‹ደመመ›› ከሚለው አንቀጽ የዕፁብ የመንክር ነገር መግለጫ ከሆነው ግስ የመጣ ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ፡፡
ደብሩን ለማየት ማናቸውም ሰው ወደ ደብሩ ሲወጣ ርዝመቱ 16 ሜትር ከሆነው ገመድ ተንጠልጥሎ ከላይ ተስቦ ይወጣዋል፡፡ ‹‹የሊፍት›› ፍልስፍና በደብሩ መነኮሳት የታቀደ ይመስላል፡፡ ደብሩ በለማበት ጊዜ ጫፍ ላይ እስከ ስድስት ሺሕ መነኮሳት፣ በግርጌውም እስከ ሁለት ሺሕ መነኮሳይያት የነበሩበት ነው፡፡ እዚያው ጫፍ ወጥቶ ዙርያው ያለውን አገር ለማየት የቻለ ሰው ዕድለኛ ያሰኘዋል፡፡
ደብረ ዳሞ የሥነ ጽሑፍና ሥነ ጥበብ ማዕከል
የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ ወደ ብራና ጽሑፍ ሽግግር ባደረገበት ዘመነ አክሱም የመጀመርያዎቹ ጽሑፎች ከተጻፉባቸው ቦታዎች አንዱ ደብረ ዳሞ ነው፡፡
በ4ኛው ምእት ዓመት በፍሬምናጦስ ጊዜ የተጀመረው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከግሪክና እብራይስጥ ወደ ግእዝ መተርጐሙ የቀጠለውና የተስፋፋው በ5ኛውና በ6ኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያኑ ሊቃውንት ከዘጠኙ ቅዱሳን ጋር በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ ክፍሎችንና የነገረ መለኮት (ቴኦሎጂ)፣ የሥርዓት መጻሕፍትን ከግሪክና ከሶርያ ቋንቋዎች መልሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገዳማት የሚተዳደሩበትን ስለሥርዓተ ምንኩስና የሚያወሳው ‹‹ሥርዓት ወትእዛዝ ዘ ጳኩሚስ›› የተተረጐመው በደብረ ዳሞ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በደብረ ዳሞ ከሥነ ጽሑፍ ሌላ የቁም ጽሕፈትና የሥዕል ትምህርት የሚሰጥበት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ መነኮሳት ትምህርትና ሥርዓቱን ቀስመው በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በመዘዋወር አምሳያ ማዕከላትን ለመመሥረት ያስቻላቸው ነው፡፡
በአክሱም አካባቢ ተወስኖ የኖረውን ገዳማዊነት በብዙ የኢትዮጵያ ክፍላተ አገር እንዲስፋፋ መሠረቱን የጣሉት አባ ኢየሱስ ሞዐ (1211-1292) የተማሩት በደብረ ዳሞ ነው፡፡
የተማሩትን መንፈሳዊ ትምህርትና ሥርዓተ ገዳማት ደሴ አካባቢ በሚገኘው ሐይቅ ደሴት ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ባቋቋሙት የአንድነት ገዳም በማስፋፋት ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል፡፡
በ13ኛው ምእት ለተቋቋሙት ታላላቅ ገዳማት ምሥረታም መነሻ ሆኗል፡፡ ደብረ ሊባኖስ (ዜጋ መልን) የመሠረቱት አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ በጣና ሐይቅ የሚገኘው ዳጋ እስጢፋኖስን ያቋቋሙት አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጋስጫ ገዳምን የወጠኑት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና ሌሎችም የተገኙት ደብረ ዳሞ ከወለደው የሐይቅ እስጢፋኖስ የአንድነት ገዳም ነው፡፡
ደብረ ዳሞ በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እንደተጻፈው የደብረ ዳሞ መነኮሳት በ13ኛው ምእት ላይ ለጽሕፈት ሥራ ትኩረት ሰጥተው ነበር፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ቁም ጽሕፈት በሚገባ ተምረው አራቱን ወንጌል (ማቴዎስና ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ) ጽፈው ለገዳሙ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ወንጌል በውስጡ ሥዕል ስለነበረው ለዘመኑ ኪነ ጥበብ አንድ መለኪያ ነው፡፡
አናባቢ የሌለው በጥንታዊ ግእዝ የተጻፈ የድንጋይ ላይ ጽሑፍም የተገኘበት ነው፡፡ ‹‹አነ ጸለየከ›› [እኔ ጸለይኩ] የሚለው ጽሑፍም ኢትዮጵያውያን ክርስትናን በተቀበሉበት ጊዜ በቦታው እንደነበሩ አመልካች መሆኑ የታሪክ ምሁራን ጠቁመዋል፡፡
አፄ ገብረ መስቀል፣ ‹‹አክሱምሂ ቤተ መንግሥትነ
ዳሞሂ ቤተ ጸሎትነ›› (አክሱም ቤተ መንግሥታችን ዳሞ የጸሎት ቤታችን) በማለት የተናገሩትም ቤተ ክርስቲያኑ በቅዱስ ያሬድ ማህሌታይ ጥዑመ ዜማ በተመረቀበት ጊዜ ነው፡፡
አቡነ አረጋዊ ከአፄ ገብረ መስቀል ጋር በመኾን በመጀመርያ በጎንደር ዙር አባ (ዙራምባ) ከዚያም በደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ብርብር ማርያም ድረስ ማስተማራቸው ይተረካል፡፡
ሴቶች መውጣት የተከለከሉት ለምንድነው? «እስከ ርእየ ሕማማ ለዓመቱ» የባሪያይቱን(የሔዋንን) ውርደት ተመልክቶ በሔዋን ልጅ በማርያም ክብርና ጸጋ ተመልሶላቸው የለም እንዴ? የሔዋን ዘር እርግማን በቅድስት፤ ንጽህትና ብጽዕት ማርያም ወርዶ የለም እንዴ? እግዚአብሔር ቃልን ለመሸከም ከሴት ዘር የተገኘው መመረጥ ተረስቶ እንዴት ሴቶችን እናሳንሳለን? ዛሬም በኦሪቱ እርግማን ሴቶችን ማሰብ ክርስትና አይደለም።የአዲስ አበባው ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና የደብረ ዳሞው ቤተክርስቲያን የተለያየ ክብር ይኖራቸው ይሆን ወይስ ሴት የኃጢአት ምንጭ ናት የሚል ምንኩስናዊ ደንብ ስላለ ይሆን? አድራጎታችሁ ባህል እንጂ ሃይማኖት ስላልሆነ ብዙም አይደንቅም።
ReplyDeleteYewendochna Yesetgoch Gedam Yemil Sirat Silalen Newu.
ReplyDelete‹‹ ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› አሉ አበው! በዕርግጥም ልክ ናቸው፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ከአስተያየትህ/ሽ አለማወቅንና አለማስተዋልን እረዳለሁ፡፡ እንዳልከው/ሽው በህግ ሽረት የመጣው እርግማን በሰማያዊው ንጉስ በአምላካችን በጌታችንና በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም የተዋህዶ ሚስጢር ከእናታችን ከቅድስተ-ቅዱሳን ከድንግል ማርያም በነሳው አዳማዊ ስጋ የማያዳግም መስዋዕት በቀራኒዮ ተራራ ላይ አቅርቦ፤ እራሱም መስዋዕት አቅራቢ፤ እራሱም መስዋእት ተቀባይ፤ እርሱ እራሱ መስዋዕት ሆኖ የእዳ ደብዳቤያችንን ፍቆታል፡፡ በዘመነ-ብሉይ እንኳን የነበሩ ቅዱሳን ፅድቃቸው እንደመርገም ጨርቅ ሆኖ ስለነበረ ገነትን ሊያገኟት አልቻሉም፡፡ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚወለድ ድረስ!!!!! የብዙሃን እናት የሆነችው ሄዋን የበለሱን ፍሬ ቀጥፋ በመብላቷና ባሏንም በማስበላቷ ምክንያት በጊዜ ወሊድ የሚፈጠረው ጭንቀት(ምጥ) እንደቅጣት ተበይኖባታል፡፡ አዳምም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ጥሮ ግሮ እንዲበላ ተወስኖበታል፡፡ ይህ የአዳምና ሄዋን ቅጣት ለዘር ተላልፎ እስካሁን ድረስ የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ ይበላል፤ ሴትም በምትወልድበት ሰአት በምጥ ትጨነቃለች፡፡ ይሄ ማለት ግን የአምላካችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን ስራ አለመጠናቀቁን አያሳይም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የዘመነ-ብሉይ ቅዱሳንና ቅዱሳት ፅድቃቸው በአዳም አባታችን በሄዋን እናታችን ሀጥያት ታንቆ ተይዞ ስለነበረ ቢፀድቁም እንኳን ገነት አይገቡም ነበረ፤ ሲኦልን እያዩ ይኖሩ ነበረ፡፡ በዚህም ያለቅሱ፤ ያዝኑ፤ ወደ አምላካቸው ይጮሁ ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም ለአዳም የገባውን ቃልኪዳን ሚፈፅምምበት ጊዜ ሲደርስ የድንግል ማርያምን ስጋ ተዋሃደና ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ሆኖ የአዳምና ሄዋን ሀጥያት ፅድቃችንን አንቆ እንዳይዝ የእዳ ደብዳቤያችንን ፋቀ፤ ደመሰሰ፡፡ የሰው ልጅ ገነትን እንዳይወርስ ገድቦ የያዘውን የጥል ግድግዳ በመስቀሉ አፈረሰው፡፡ መላእክትና የሰውልጆች በአንድ ማዕድ ሰማያዊ ህብስት የሆነውን የእግዚአብሄርን ምስጋና ተቋደሱ፡፡
ReplyDeleteሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለተለያዩ ሀገራት መልዕክታትን ሲፅፍ ስለ ሴት ልጅ እና ስለ ወንድ ልጅ ደረጃ በግልፅ ፅፎ ነበረ፡፡ ‹‹ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ … ባል የሚስት ራስ ነዉና›› /ኤፌ 5 ፥21/ ፣ ይህ ጥቅስ ስንመለከት ካላስተዋልን በስጋ አይናችን ለመመርመር ስንሞክር ቃሉ እራሱ መጥፊያችን ይሆናል፡፡ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያንን በደሙ የዋጃት ራሷ/ገዢዋ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሄዋንን ሲፈርድባት ‹‹ ባልሽ ገዢሽ ይሁን›› ባሏታል፡፡ ነገር ግን አምላካችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳኑን ስራ ከፈፀመም በኋላ ይህ ህግ በቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት ተገልጿል፤ ይህ ማለት ግን የብሉይ ዘመን እርግማን አሁንም ድረስ አለ ማለት ነው? ( በአንተ/ቺ አባባል ከሄድን)፤ መልሱ አይደለም ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ የተሳሳተ ትርጓሜ ከሄድን የመጽሀፍ ቅዱሱ ቃል እንዳለ በዜሮ መባዛት አለበት ማለት ነው፡፡ ግን ክብር ይግባውና ለመንፈስ ቅዱስ! ቃሉ ፍፁም ትክክል ነው፡፡ ገላ 3፡28 ‹‹ በአይሁድና በግሪክ፣ በባርያና በነፃ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፡፡ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ፡፡›› ይህን ቃል ስንመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ ሁለት ተፃፃራሪ ነገሮችን ሚሰብክ ሊመስለን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተመራው ሀዋርያ አንድ ቃል ነው የተናገረው፡፡ ባል ሚስቱን እንደሚጠብቅ ክርሰቶስ ቤተ-ክርስቲያንን ይጠብቃል፡፡ የብሉይ ዘመን እርግማን እንደተሻረ ሀዋርያው በግልፅ ሲናገር ገላ 3፡13 ‹‹ በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ እርጉም ነው፤ ተብሎ እንደተፃፈ ክርስቶስ ስለእኛ ርግማን ሆኖ ከህግ ርግማን ዋጅቶናል፡፡ ›› ቃሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ከእርግማን እንዳወጣ ያትታል፡፡ ስለዚህ በብሉይ ዘመን የነበረ ስርዐትና አባባል በሀዲሱም ቢደገም የክርስቶስን ማዳን ጥያቄ ውስጥ ሊከት አይገባም፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ቃሉን መርምር/ሪ፡፡
ሌላው እና ዋናው ነጥብ ወደ ደብረ-ዳሞ ገዳም ሴቶች እንዲገቡ አለመፈቀዱ ሴቶችን ማሳነስ ነው ብለህ /ሽ ምታስባ/ቢ ከሆነ እንደተሳሳትክ/ሽ ቅዱስ ቃሉን ተንተርሼ ለመናገር እወዳለሁ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ጢሞቲዎስ በላከው መልዕክት 2፡11 ላይ እንዲህ ብሎ ስርአት መስርቶ ነበረ፤ ጢሞ 2፤11 ‹‹ ሴት በፀጥታና በሙሉ መገዛት ትማር፡፡ ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ስልጣን ይኖራት ዘንድ አልፈቅድም፡፡...........ደግሞም የተታለለው አዳም አይደለም፤ የተታለለችውና ሃጢያተኛ የሆነችው ሴቷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ሴት በእምነትና በፍቅር በቅድስናውም ራሷን እየገዛች ብትፀና ልጅ በመውለድ ትድናለች፡፡›› ታዲያ ስለእርግማን መሻርና ስለወንድና ሴት እኩልነት ሲያወራ የነበረው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለምን እንዲህ አለ??? ህግና ስርአትን ያወጡ ዘንድ ለአባቶች ስልጣን እንደተሰጣቸው መፅሀፍ ይናገራል፤ ህጉን መጠበቅ ገድሞ የእኛ ግዴታ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሴት ልጅ በአውደ-ምህረት ቆማ እንዳታስተምር ያዘዘበት ምክንያት ወንዶች በእርሷ እንዳይስቱ በማሰብ ነው፡፡ ሄዋን አዳምን አሳስታዋለችና!!! ስለዚህ የገዳማችን ስርዐት በቅዱሳን አባቶቻችን ተደንግጎ የፀደቀ ንፁህ ስርአት ነው፡፡ በገዳሙ የሚኖሩ አባቶች ፍትወተ-ስጋ ስንዳያታልላቸው ሴት እነርሱ ወዳሉበት አትገባም፡፡ እነርሱም ሴቶች በሚኖሩበት ገዳም አይገቡም፡፡ ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል!!! በመጨረሻም አድራጎታችን የቅዱሳን ሀዋርያትን ፈለግ የተከተለ እንጂ ባህልን የተከተለ አይደለም፡፡ ጠይቅ/ቂ፤ ተረዳ/ጂ፤ እወቅ/ቂ ከዚያም ተናገር/ሪ!!!!!! ስብሃት ለአብ ስብሃት ለወልድ ስብሃት ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሄር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር