ሞአ አንበሳ የዘውድ ምክር ቤት በላሊበላና አካባቢዋ ለሚገኙት ወደ ሦስት ሺሕ ለሚጠጉ የአብነት (ቆሎ) ተማሪዎች አገልግሎት የሚውል አዳሪ ትምህርት ቤት በአምስት ሚሊዮን ብር ለማሠራት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፆ ለተግባራዊነት አስፈላጊውን እንቀስቃሴ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ባካሔደው እንቅስቃሴ ሥራውን የሚከታተልና የሚያስተባብር ኮሚቴ ያዋቀረና ለሕንጻው ግንባታ የሚውል ቦታ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ጄኔራል ዓባይ አማኑ የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የምክር ቤቱ ደጋፊ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚሰበሰበው ገንዘብ የሚሠራው ይኸው ትምህርት ቤት ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍሎ የወጣውን የቅዱስ ላሊበላን ቤተ ክርስቲያን ቅርጽ የያዘ ነው፡፡
በመከናወን ላይ ያለው የሕንጻው ዲዛይን ሥራ እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ ተጠናቅቆ ወደ ግንባታው ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ የግንባታው ሥራ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የተማሪዎችን የመጠለያ ችግር በማቃለል ለመማር ማስተማሩ ሥራ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንሚያደረግ ተናግረዋል፡፡
አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ እንደገለጹት ከሆነ፣ ትምህርት ቤቱን ለማሠራት የላሊበላ ነዋሪዎች ስብሰባ አድርገው ተወያይተዋል፡፡ የተጀመረውንም ጥረት ከዳር ለማድረስ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅና ለዚህም እውን መሆን የጠራ ፕሮጀክት ትልመ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ማቅረቡ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያሉት የአብነት ተማሪዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም ከሁለት ሺሕ በላይ ይሆናሉ የሚል ግምት አለ፡፡ እነዚህንንም ተማሪዎች ቅኔ፣ ዝማሬ፣ ቅዳሴ፣ አቋቋም ወዘተ. የሚያስተምሩ 61 መምህራን እንዳሉና ዝርዝራቸውም ለጠቅላይ ቤተክህነት መተላለፉን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ዓባይ ሀብቴ የላሊበላ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ስለዚሁ ጉዳይ በስልክ ተጠይቀው፣ “በደብሩ አካባቢ ለአብነት ትምህርት ቤት ማሠርያ የተያዘ ቦታ መኖሩን በማስተር ፕላኑ ላይ ተቀምጦአል፡፡ ከዚህ ውጭ ክልሉን የሰጠነው ወይም ያስረከብነው ቦታ የለም፤” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ደብሩ ቅዱስ ላሊበላ ከልደት እስከ ዕረፍታቸው ድረስ ያከናወኑትን መንፈሳዊ ተግባራት የሚያመለክት ሙዚየም ለማሠራት ማቀዱን አባ ገብረ ኢየሱስ ጠቅሰው ደረጃውን የጠበቀ ይኸው ሙዚየም ለቱሪስት መስህብ በእጅጉ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሙዚየሙም የሚሠራው ልዩ ስሙ መካነ ልዕልት ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ መሆኑን አባ ገብረ ኢየሱስ ገልጸው፣ የቦታውንም ጥያቄ በቅርቡ ለላሊበላ ማዘጋጃ ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለሕንጻው ግንባታ በሚውለው በዚሁ ቦታ ላይ በሚገኙ አምስት አባወራ አርሶ አደሮች የመሬት ካሣ 3 ሚሊዮን ብር ማስፈለጉንም ከአባ ገብረ ኢየሱስ ማብራርያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በታደሰ ገብረማርያም
No comments:
Post a Comment