Sunday, August 14, 2011

ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላል?


ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት ማወቅ ይቻላል?» የሚለው የሰው ሁሉ ጥያቄ ነው። ብዙዎቻችን መመዘኛችን ሥጋ ዊ በመሆኑ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ፥ ለመቀበልም እንቸገራለን። የሚነገረው ሁሉ ለኅሊናችን መልስ ስለማይሆን አጥ ጋቢ መልስ አላገኘሁም እንላለን። ለምሳሌ፦ ከአይሁድ የተላኩ ካህናትና ሌዋውያን፦ መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስን፦ «እንኪያስ አንተ ማነህ? አንተ ኤልያስ ነህን?» ባሉት ጊዜ፦ «አይደለሁም ፤» ብሏቸዋል። ዮሐ ፩፥፳፩። ነቢዩ ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ቢያርግም በስሙ የተነገረ « እነሆ፥ ታላቋና የምታስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ቴስብያዊው ኤል ያስን እልክላችኋለሁ።» የሚል ትንቢት አለ። ሚል ፬፥፭። ይኽንን ይዘው ነው፥ «ኤልያስ ነህን ?» ያሉት። ዮሐንስ «አዎን ነኝ፤» ማለት ይችል ነበር። ምክንያቱም ጌታችን ፦ «ልትቀበሉትስ ብትወዱ ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።» በማ ለት እንደመሰከረለት በሁሉ ኤልያስን ይመስለዋልና። ማቴ ፲፩፥፲፬። ነቢዩ ኤልያስ፦ ፀጉራም ፥ጸዋሚ ፥ተሐራሚ፥ ዝጉሐዊ፥ ባሕታዊ ፥ ድንግላዊ ነው። ቅዱስ ዮሐንስም ልብሱ የግመል ፀጉር ሆኖ፦ ጸዋሚ ፥ ተሐራሚ ፥ ዝጉሐዊ ፥ባሕታዊ ፥ ድንግ ላዊ ነው። ይሁን እንጂ «አይደለሁም፤» ያለው፦ «ነኝ፤» የሚለው እውነት ለአይሁድ ለኅሊናቸው መልስ ስለማይሆን ነው። ለእኛም ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር የሚነገረው እውነት ሁሉ ለኅሊናችን መልስ አይደለም። 
ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ በሕግ በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልጋል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ወደ እር ሱ ቅረቡ ፥ ያበራላችሁማል ፥ፊታችሁም አያፍርም፤» ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፴፫ ፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም፦ « እግ ዚአብሔርን ቅረቡት ፥ ይቀርባችሁማል፤» ብሏል። ያዕ ፬፣፰። ከዚህም ሌላ፦ የእኛ ሥጋዊ ፈቃድ ከእግዚአብሔር መንፈሳዊ ፈቃድ ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይኽንን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ ፥ መን ገዴ እንደመንገዳችሁ ፥ አይደለምና ፥ ይላል እግዚአብሔር። ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ ፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ የራቀ ነው።» በማለት ከእግዚአብሔር የሰማውን ተናግሯል። ኢሳ ፶፭ ፥ ፰። በመሆኑም ለራሳችን ስንል፦ ፈቃደ ሥጋችንን እና የዓይን አምሮታችንን ትተን ለፈቃደ እግዚአብሔር መገዛት አለብን። ምክንያቱም ሁልጊዜ ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዳናውቅ የሚጋርደን ፈቃደ ሥጋችን ነውና። ለበጎ ነገር ሁሉ አብነት የሆነን አምላክ ኢየሱስ ክርስ ቶስ ፦ «አባቴ ሆይ፥ የሚቻልስ ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይደለም።» ብሏ ል። ማቴ ፳፮፥፴፱። ይህም ለእኛ አብነት ፥ ለእኛ አርአያና ምሳሌ ሲሆን ነው። እንግዲህ ጌታ እንዳስተማረን የራሳችንን ፈቃ ድ ስንተው ያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምናውቅበት ልቡና ፥ የምናይበት ዓይን ፥ የምንዳስስበት እጅ ይኖረናል። የእግ ዚአብሔር ፈቃድ ሁልጊዜ ለእኛ መልካም ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ፦« እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና ፥ የሚያ ሰጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ።» ያለው በጎ ፈቃዱን ነው። ፩ኛ ጴጥ ፭፥፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ « እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግ ዚአብሔር ግለጡ።» ብሏል። ፊል ፬፥፭። 

ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ የምንጓዝበት መንገድ መንፈሳዊ መሆን አለበት። ኢያቡር የተባለ የአብርሃም ሎሌ ለይስሐቅ ሚስት አጭቶ እንዲያመጣ በተላከ ጊዜ፦ « የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ ፥ ለጌታዬ ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ ፥በዚህ የውሃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ ፥ የዚችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት፤ እርስዋም አንተ ጠጣ ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።» ሲለ ተንበርክኮ ጸለየ። ወዲያው ርብቃ መጣችና የተባለችውን ሁሉ በበጎ ኅሊና ፈጸመች። እርሱም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር። ማንነቷን እና በአባቷ ቤት ማደሪያ እንዳለ በጠየቃት ጊዜም፦ «እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግም ሥፍራ አለን፤ » አለችው። ይህን ሁሉ ያደረገችው በበጎ ኅሊና በጎ መሥራት እንደሚገባ አምና እንጂ ለትዳር እመረጣለሁ ብላ አይደለም። እርሱም፦ «ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች መራኝ፤» ብሎ አመሰገነ። ዘፍ ፳፬፥፩-፳፯።

‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ››

2 comments:

  1. kale hewot yasemaline ....agelgelotachune amelke yebarke ...yegetaye enat azagetua tirdachue

    ReplyDelete