Wednesday, August 31, 2011

የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው!


By Elizabth Teklehana 

የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት አባት ቅዱስ ፀጋዘአብ በሸዋ ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህን ነበሩ፡፡ መጋቢት 24 ቀን አባታችን ተክለሃይማኖት ተፀነሱ በታህሣስ 24 ቀን በ1190 ዓ.ም አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከእናታቸው ከቅድስት እግዚሐሪያ እና ከአባታቸው ከቅዱስ ፀጋዘአብ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በ3ኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመሠገኑ፡፡


 በተወለዱ በ40ኛው ቀን ክርስትናን በመነሳት ፍስሐ ጽዮን “የጽዮን ደስታ” ተበለው ተጠሩ፡፡ አባታችን 7 ዓመት እስከሞላቸው ድረስ ከአባታቸው ከፀጋዘአብ ዘንድ እየተማሩ አደጉ፡፡ አባታችን በ15 ዓመታቸው ዲቁናን ከጌርሎስ ዘንድ ተቀበሉ፡፡ አባታችን በ22 ዓመታቸው ከአቡነ ጌርሎስ ዘንድ ቅስናን ተቀበሉ፡፡ በከተታ አውራጃ 3 ዓመት ወንጌልን እያስተማሩ ብዙ ድንቅ ነገርን አደረጉ፡፡ 

አባታችን በዳዊት ፀሎት ከነቢያት ምስጋና ሌሊቱን ሙሉ ይተጉ ነበር በያንዳንዱ መዝሙርም 10፣ 10 ስግደትን ይሰግዱ ነበር፡፡ በሕዳር 24 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደ ላይ ነጠቃቸው (አወጣቸው) ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ካህን ሆነው የሥላሴን መንበረን “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አጥነዋል፡፡ በሐይቅ 10 ዓመት በደብረዳሞ 12 ዓመት ኖረዋል፡፡ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በ1267 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስን በአት አድርገው ኖሩ፡፡ ለ22 ዓመት ቆመው በመፀለይ የአንድ እግራቸው አገዳ ተሠበረ ደቀ መዝሙሮቻቸው በጨርቅ ጠቅልለው ቀበሩት፡፡ በአንድ እግራቸው ለ7 ዓመት በፀሎት ቆሙ በጠቅላላው ለ29 ዓመት በፀሎት ከቆሙ በኋላ በ99 ዓመት ከ10 ወር ከ10 ቀን ነሐሴ 24 ቀን 1290 ዓ.ም አረፉ አባታችን ባረፉ 54 ዓመታቸው በ1354 ዓ.ም ለአባታችን ለአቡነ እዝቅያስ ተገልጸው አጽማቸው ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ ግንቦት 12 ቀን እንዲፈልስ አድርገዋል፡፡ 

  • ህዳር 24 ቀን 25ተኛ ካህናተ ሰማይ ሆነው በሠማይ የሥላሴን መንበር ያጠኑበት
  • ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን ልደት 
  • ጥር 24 ቀን የአባታችን ስባረ አጽም 
  • መጋቢት 24 ቀን የአባታችን ጽንሠት 
  • ግንቦት 12 ቀን የአባታችን ፍልሰተ አጽም 
  • ነሐሴ 24 ቀን የአባታችን እረፍት

የአባታችን ቡራኬ ይድረሰን አሜን!

“ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኩሴ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ እርስ በእርሳችሁም ተዋደዱ ትዕዛዛቱንም ጠብቁ” የሐዲስ ኪዳኑ ሙሴ የአባታችን የተክለሃይማኖት ምክር!!!



ስለ አቡነ ተክለ ሐይማኖት ከተዘመሩ ጣዕመ ዜማዎች አንዱን በድምፅ እና በግጥም እንደሚቀጥለው አቅርበንላችኋል




አባ አቡነ አባ መምህርነ
መምህርነ አባ ተክለሃይማኖት /2/
አባ አቡነ አባ መምህርነ
መምህርነ አባ ተክለሃይማኖት/2/

እምአእላፍ እምአእላፍ ኅሩይ
እምአእላፍ ኅሩይ
እምአእላፍ  እምአእላፍ  ኅሩይ
እምአእላፍ ኅሩይ………………………….   አዝማች

አምላክ የጠራህ ለታላቅ ክብር
ተክለሃይማኖት ብጹእ መምህር
ሐዋሪያ ነህ በዚች በምድር
በዚች በምድር/2/

ጸሎት ምህላህ በእውነት ተሰማ
ክብርህ ታወቀ በላይ በራማ
.........................................አዝማች

ደብረ ሊባኖስ ተቀደሰች
በእጅህ መስቀል ተባረከች
ተባረከች
ኤልሳእ ልበልህ ቅዱስ ዮሐንስ
ተክለሃይማኖት ጻድቅ ነህ ቅዱስ
ጻድቅ ነህ ቅዱስ

.........................................አዝማች

ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ
ፀሎትህ ሆኖናል መድኃኒት እና ፈውስ
መድኃኒት እና ፈውስ
ዛሬም ስንጠራህ ቃልኪዳንህን አምነን
በረክትህ ለሁላችን  ይሁን/2/

.........................................አዝማች

1 comment: