Thursday, August 11, 2011

ትንቢቱ ሲፈጸም

ትንቢቱ ሲፈጸም በመጽሐፍ ያለው፣
ወገኔ አትደንግጡ ይህ ሊሆን ግድ ነው።
ቅዱሳን ሳይቀሩ የተመረጡቱ፣
በመጨረሻው ቀን በዓለም እንዲስቱ፣
ቀድሞ በመጽሐፍ ተነግሯል ትንቢቱ።


የእውነት ደብዛ ጠፍቶ ሐሰት መሰልጠኑ፣
ሥርዓት ተጥሶ ነውሩ ጌጥ መሆኑ፣
አይቀሬ ነውና ወገን አትደንግጡ፣
ከመጣብን ቁጣ በጸሎት አምልጡ።

የእግዚአብሔር ሰገነት ሲቀየር በጣዖት፣
በቅዱሱ ሥፍራ ሲፈጸም እርኩሰት፣
በአደባባይ ሲታይ ሰይጣን አካል ነሥቶ፣
ከዚህ የበለጠ ምን ይመጣል ከቶ?

ቅዱሳን ተናቁ አፈኞች ተሾሙ፣
ንጹሐን ተዋርደው ሌቦች ተሸለሙ።

በቅዱስ መስቀሉ በድኅነት ምልክት፣
የእብነ በረድ ሐውልት ጣዖት ባረኩበት፣
ጸጋ ቢሰጣቸው መንጋ እንዲጠብቁ፣
በውዳሴ ከንቱ በገንዘብ ወደቁ።

ብዙ ፈርኦኖች በኢትዮጵያ ነገሱ፣
የአባቶችን ድንበር ሥርዓት አፈረሱ፣
በውል ሳይታወቅ ማን እንደሾማቸው፣
በቤቱ ቀለዱ እነርሱ እንዳሻቸው፣
አየ የጥፋት ቀን የዓለም መጨረሻ፣
የሐሳዊ መሲህ የአውሬው መንገሻ፣

እጅግ ያሳዝናል ኢትዮጵያ መሆኗ፣
ትንሽ ሳታገግም ከትናንት ሀዘኗ።
በገንዘብ ተገዝተው ሀሰት ቢናገሩ፣
በውዳሴ ከንቱ በዓለም ቢኖሩ፣
ሁዋላ አይጠቅምም ከቶ በሞት ስንጠራ፣
እግዚአብሔር ፊት ሲቀርብ የሠራነው ሥራ፣

መሳሳት ያለ ነው መውደቅ መነሳቱ፣
ፍጹም ስላልሆነ ሰው በሰውነቱ፣
ነገር ግን ትልቁ ሊያድን የሚችለው፣
ሰው ስህተቱን አውቆ ሲመለስ ብቻ ነው፣
ስለዚህ ኤልዛቤል አክዓቦችም ሁሉ፣
የናቡቴን ርስት እንቀማ ስትሉ፣
አምላክ ተቆጥቶ እንዳያጠፋችሁ፣
መመለስ ይሻላል ከክፉ ሥራችሁ።

እናንተም አባቶች አበው ቅዱሳኑ
መከራን ሳትፈሩ በእምነታችሁ ኑሩ
(አግናጢዎስ ዘጋስጫ)

4 comments:

  1. kale hiywot yasemalin!!!

    ReplyDelete
  2. ewnet new gizewun yeweje sina gitim new kale hiwot yasemalin!!!!

    ReplyDelete
  3. ewnet new betselotmekelakelu teru new

    ReplyDelete
  4. ewnet new betselotmekelakelu teru new

    ReplyDelete