Sunday, August 21, 2011

እመቤታችን ከማረፏ ከሰዓታት በፊትና በኋላ ምን ሆነ?

ማርያም ስጋኪ ዘተመሰለ ባሕርየ
ተሓፍረ ሞት አኮኑ ሶበ ነጸረ ወርእየ
እንዘ በደመና ብሩህ የዐርግ ሰማየ
እንኳን አደረሰን

እመቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት ዓመትአሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ /ዘጠኝ ወር በቤተ ዮሴፍ/፣ ከመድኃኒታችን ጋር ሰላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ፣ በቤተ ዮሐንስ አሥራ አምስት ዓመት፤ ጠቅላላ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ኑራለች::

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለአገልግሎት ወደ ኤፌሶን በሄደበት ወቅት የቤተ መቅደስ አለቆች ልጆች የነበሩ ደናግል እግሯን እያጠቡ እየተላላኩ ያገለግሏት ነበር:: እመቤታችን ጐልጐታ በሚገኝው የመቃብር ቦታ እየሄደችም አዘውትራ ትጸልይ ነበር:: መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በመቃብሩ በምትጸልይበት ጊዜ ከዚህ ዓለም በሥጋ ስለምታርፍበት ሁኔታ ከነገራት በኋላ ታመመች:: ያን ጊዜ አገልጋዮቿና ጎረቤቶቿ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ ብዙ ድውያንም ወደእርስዋ እየመጡ ያመሰግኗትና ይፈወሱም ነበር:: እመቤታችንም ደስ ብሏት ትባርካቸዋለች::


የዓለምን አልጫነት በወንጌል ጨውነት ያጣፍጡ ዘንድ ለአገልግሎት የወጡ ክቡራን ደቀ መዛሙርትም እመቤታችን ከማረፏ በፊት በረከትን ሊቀበሉና በክብር ሊያሳርፏት ተሰበሰቡ :: ከመላእክትም ጋር በአንድነት ቅድስት ቡርክት ወደሆነች እመቤታችን ቤት ገቡ:: ከእግሯ በታችም ሰገዱ “ጸጋን ፍጹም ደስታን የተመላሽ ሆይ ሰላምታ ለአንቺ ይገባሻል ፣ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ አትደንግጪ :: ከአንቺ የተወለደው ክርስቶስ በታላቅ ምስጋና ከዚህ ዓለም ሊለይሽ ፣ ወደብርሃን ቤቶችም ሊወስድሽ ነውና ” እያሉ ያረጋጓጓት ነበር::

እመቤታችን ማርያምም ተነሥታ “እኔ እንደታመምሁ የነገራችሁ ማን ነው? ከየትስ አገር ወደ እኔ መጣችሁ? በምን ተጭናችሁስ ፈጥናችሁ ደረሳችሁ? ስለ እኔ የነገራችሁን እግዚአብሔርን ላመሰግን እወዳለሁ ” አለቻቸው:: ቅዱስ ጴጥሮስም “እያንዳንዳችሁ ወደዚህ እንዴት እንደመጣችሁ ንገሯት” አላቸው::

አስቀድሞ የመጣ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ:: “በኤፌሶን ሳለሁ መንፈስ ቅዱስ ወደ እኔ መጣ:: ዮሐንስ ሆይ የጌታህ እናት ከዚህ ዓለም የምትለይበት የዕረፍቷ ዕለት ደርሷልና ሒድ ፤ ልታይህም ትሻለች አለኝ:: ዳግመኛም መንፈስ ቅዱስም በሀገሮች ሁሉ እሔዳለሁ ፤ ለሐዋርያትም ለሕያዋኑም፣ ለሙታኑም እነግራቸዋለሁ ፤ ወደ ቤተልሔም ወደርሷ ይሔዱ ዘንድ ይሳለሟትም ዘንድ ስለ ማርያም እነግራቸዋለሁ አለኝ:: እነሆም መንፈስ ቅዱስ በደመና በድንገት ነጠቀኝ :: በዚህች ሰዓትም ከማርያም ዘንድ አደረሰኝ::” በማለት መሰከረ:: የቀሩትም ሁሉ በድንቅ አጠራሩ ስቦ ያቀረባቸው መሆኑን መሰከሩ:: ሉቃስ ወንጌላዊ ፣ ስምዖን ቀነናዊና እንድርያስ የተጠሩበት አጠራርም እጅግ ያስደንቅ ነበር :: ከመቃብር ተጠርተው ነበርና:: መላእክትም ከእነርሱ ጋር ነበሩ::

ቅዱሳን ሐዋርያት ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ከእለታት ሁሉ በምትከብር በእለተ ሰንበት “ከዚህ ዓለም እናቱን ይወስዳት ዘንድ በእርሷ ላይ ክብሩን ይገልጣል” እንዳላቸው ሆነ:: የሰው ልጆች ሁሉ እናታቸው ሔዋን፣ የእመቤታችን እናት ሐና ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ “የክብሩ ማደርያ ትሆኝ ዘንድ የመረጠሽ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አሏት::” ፤አባታችን አዳም ፣ ልጁ ሴት ፣ ኖኅ ፣ ሴም ፣ አብርሃም ፣ ይስሐቅ ፣ ያዕቆብ ፣ ዳዊት ፣ የእሳት ማእጠንት የያዙ ሌሎችም ነቢያት ከእመቤታችን ፊት ሰገዱ ፤ ሄኖክና ሙሴም በእሣት ሰረገላ ተጭነው መጡ ፤ቁጥራቸው የብዙ ብዙ የሚሆን የከበሩ መላእክት ከዚህ ዓለም የማርያምን መለየት ያዩ ዘንድ መጡ :: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤልና በሱራፌል ሰረገላ ተቀምጦ ተገለጠ:: እናቱንም ጠርቶ የሰማያትን ምስጢር ሁሉ አሳያት :: የሲዖልና የገነት ነፍሳትን ሁሉ ጎበኘች:: መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ ፣ በስሟ መሥዋዕት ለሚያሳርጉ ሁሉ ቃል ኪዳን ከተቀበለች በኋላ በጥር ሃያ አንድ ቀንም ዐረፈች::

የከበረ ወንጌላዊ ዮሐንስ እጆቿን አነሣ አቃናት፤ ዓይኖቿንም ከደነላት ፤ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም እጆቿንና እግሮቿን አስተካከሉ:: በእርሷ ላይ ያለውን ልብሷን ግን አላወጡትም፤ መንፈስ ቅዱስ የማይመረመር ታላቅ ብርሃናዊ ልብስን አልብሷታልና:: የከበረ ሥጋዋን በጌቴሴማኒ ሊያሳርፉ ቅዱሳን ሐዋርያትና የተወደዱ የክርስትያን ወገኖች ተሰብስበው ሳለ፤ ለክፋት የማያርፉ አይሁድ ተነሱባቸው:: “በድነ ሥጋዋን እንወስዳለን እናቃጥላለንም ” አሉ::

ታውፋንያ የተባለ ጭፍራም ልከው የእመቤታችንን ሥጋ የያዘውን አልጋ እንዲጥል እጁን በዘረጋ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ መታው፤ ሁለት እጆቹንም ከትከሻው ቆረጣቸው አልጋውም ላይ ተንጠለጠሉ:: ታውፋንያም አለቀሰ ፤ ወደ ሐዋርያትም ጮኽ፤ ሐዋርያትም አልጋዋን ትስብባት ዘንድ የወደድህ ማርያምን ለምናት አሉት:: “ እናቴ ማርያም ሆይ ይቅር በይኝ ” አለ:: እመቤታችንም እጆቹ ይመለሱለት አለች:: በቅዱስ ጴጥሮስም “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፤ ቅድስት በሆነች በማርያምም ስም እንደነበራችሁ ሁኑ ” ሁኑ አላቸው:: በዳነ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ አለው “ እመቤታችን ማርያም በአንተ ላይ ያደረገችውን ለአይሁድ ንገራቸው፤ እነርሱ እመቤታችንን ይሰድቧታልና ፤ በሕይወቷ አሸንፋናለች ፤ ዛሬ ግን እኛ ሥጋዋን እናቃጥላለን ብለዋልና ” አለው::

ከዚህ በኋላ ልአከ እግዚአብሔር የከበረ ሥጋዋን ሰውሮ በአጸደ ገነት አኖረው:: ይህ ምስጢር የተገለጠለት ጌታውን ይወድ የነበረ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የነገራቸውን ለማየትና ሥርዓተ ቀብሯን በሚገባ ባለማድረጋቸው ሲያዝኑ ኖረዋልና ምስጢር ተከፍሎባቸው እንዳይቀር ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው በያዙት ሱባዔ “ ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር ” እንዲሉ በነሐሴ አሥራ አራት ቀን የከበረ ሥጋዋ ተሰጥቷቸው በታላቅ ጸሎትና ዝማሬ ቀብረዋታል::

ለአገልግሎት ሩቅ አገር ሂዶ የቆየው ሐዋርያው ቶማስ ከዚህ ታላቅ ምስጢር ተለይቼ እያለ ደመና ጠቅሶ በታላቅ ሐዘን ወደ ሐዋርያት ሲመጣ እመቤታችን እንደልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ተመለከተ:: ምስጢር ተከፍሎበት የመሰለው ቶማስ ሲያዝን ፤ የመጀመሪያው የወላዲተ አምላክ ትንሣኤ ምስክር መሆኑን ተረዳ:: የትንሣኤዋን ዜና ያበስር ዘንድም የመግነዟን ጨርቅ ምልክት እንዲሆነው ሰጠችው::

ከሐዋርያት ሲደርስም የሆነውን አጫወቱት :: ይህ እንዴት ይሆናል? አላቸው:: ቀድሞ የጌታህን ትንሣኤ ተጠራጥረህ ተገስጸህ ነበር:: አሁን የእናቱን እረፍት እየነገርንህ ትጠረጥራለህን? አሉት:: መቃብሯን አሳዩኝ ብሏቸው ሊያሳዩት ወደጌቴሴማኒ በሄዱ ጊዜ መቃብሩ ባዶ ሆኖ አገኙት:: ቶማስም የሆነውን እንድታምኑ እንጅ እኔስ ጠራጥሬ አይደለም :: በማለት የምሥራች አላቸው:: በዚህም ታላቅ ደስታን አደረጉ:: ከዚያን ጊዜ ወዲህም በኦርቶዶክስ አቢያተ ክርስትያናት ሁሉ ዘንድ ከሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ከትውፊት እንዳገኝነው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰቷ፣የትንሣኤዋና የዕርገቷ በኣል መጽሐፋዊ ፣ትውፊታዊና ማኅሌታዊ በሆነ ሥርዓት፤ በጾምና በጸሎት በሱባዔም የሚከበር ታላቅ በኣል ነው::

የወላዲተ አምላክ ረድኤትና በረከት አይለየን:: አሜን!

by Mengisteab Aranshi on Saturday, August 20, 2011

10 comments:

  1. kalehiwot yasemalin!!

    ye dingil bereket ayileyegn!! amen!!

    ReplyDelete
  2. emebetie tesetelign selenatachen erieftei manbebe ye enba sika berebesheignme yetensayewa neger lebein molaw abatochie behsan aymeroyei negerawegne yenebere behonem bezemenie hulu yerswa neger addis tafache newena hiweto bebereketwa yetemola yehunlo Egziabher yestelegne

    ReplyDelete
  3. enta hoy men yahel endemewdesh tawkalesh aydel anchen tesfa seladerku new yan holw hatyat yersahet.engi enma???

    ReplyDelete
  4. kale hiwot yasemaln yeagelgilot zemenachun yabizalachu ye enatachin miljana bereket ayleyen amen!!!

    ReplyDelete
  5. Tiru chewata endaymesel lemen yete endetesafe atnegrunem! Ende ewnetu kehone, Colonelen Colonel,Wotaderen Wotader malet meche newe yemetejemerut............Ke Geta Eyesus...Ke lejua gare lemamaesasel memokerachehu tegebi aydelem........Ebakachehu..wode kalu enemeles? Ke mot hiwot yeshala ena!!!

    ReplyDelete
  6. ቃለ ህይወት ያሰማልን:: የእመቤታችን ፍቅር የበዛለት ሰው ምንኛ መታደል ነው::

    ReplyDelete
  7. amen wo amen leyikun leyiun

    ReplyDelete
  8. በእውነቱ እጅግ አስደማሚ ጽሁፍ ነው ቃለ ሕይወት ያሰመማልን መጽሐፋዊ ነው ወይስ ትውፊት አልተገለጸም ቢጠቀስ

    ReplyDelete
  9. የእመቤታችን በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን እሜቤቴ ቅድስት ድንግል ማረያም እባክቨን የአስራት ልጆችሸን ከመከራ እሳት ጠቢቂን ጠላቶቻችን በዝተዋል እጃቸውን ተዋህዶ ላይ አንስተዋል ሰላምን አውርጅልን ፡፡

    ReplyDelete
  10. የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማረያም በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!!!!

    ReplyDelete