Friday, August 12, 2011

'' ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ” ሉቃስ 18:14


 ዲያቆን ሳሙኤል ብርሃኑ

ከላይ ያለውን ቃል የተናገራው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ቃሉንም የተናገረው እራሳቸውን ስለሚያመጻድቁና ሌላውንም ስለሚንቁ ሰዎች በምሳሌ ሲያስተምር ነው። ሁለት የተለያየ ህብረተሰብን የሚወክሉ ሰዎች ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ እንደሔዱ እና ሁለቱም ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ጸሎት ቢያቀርቡም አንደኛው ብቻ ጸድቆ ወደቤቱ እንደ ተመለሰ ይናገራል።ለጸሎት እንደ ሄዱ ከተነገረላቸው መካከል አንዱ ፈሪሳዊ ነው።

ፈሪሳዊ
ፈሪሳውያን የነቢያትን መጽሐፍ የሚቀበሉ፡ የሙሴን ህግ የሚጠብቁ፡ በትንሳኤ ሙታን የሚያምኑ የሮምን ቅኝ ገዥነት የሚቃወሙ ስለ ሀገራቸው ነጻነት ግድ የሚላቸው ከምግባር ይልቅ፡ ትኩረታቸው ወግና ስርአት ላይ ብቻ የሆነ ሰው የሚድነው ሕግንና ስርዓትን በመጠበቅ ብቻ ይመስላቸው የነበረ በዚህም ባሕርያቸው ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮች ስለምትመስሉ ወዩውላችሁ ያላቸው ውጪያቸው ብቻ የጠራ ውስጣቸው ግን በክፋት የተሞላ በመሆኑ አስቀድማችሁ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥሩ በማለት የገስጻቸው ሲሆኑ ይህ ሰው ከእነርሱ ወገን የነበረ ነው። ማቴ. 23፡1፡27 ማቴ. 15፡2 ማር. 7፡13 መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስና የሕግ መምህሩ ኒቆዲሞስ የዚህ ማሕበረሰብ ክፍል አባል ነበሩ።

ቀራጭ/ግብር/ታክስ ስብሳቢ
ሮም እስራኤልን በገዛችበት ወቅት ከሕዝበ እስራኤል ትጠብቀው የነበረው ግብር መክፈልን ነበር፡ ለዚህም አገልግሎት እንዲመቻት፡ ከዛው ከእስራል ህዝብ ዜግነታቸው አይሁድ የሆኑትን ሰው በመጠቀም ቀረጥ ትሰበስብ ነበር። በዚህም ሙያ የተሰማሩት ግብር ሰብሳቢዎች ቀረጥ ሰብሳቢ ወይም ቀራጭ ተብለው ይጠሩ ነበር። ለሮማ ስለሚሰሩና አብዝተውም ከተተመነላቸው በላይ ስለሚመዘብሩ በህዝቡ ዘንድ የተጠሉና እንደ ከሃዲ እና ሃጢያተኛ ይቆጠሩ ነበር። ለዚህም ነው መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ባጠመቀ ጊዜ፡ እነዚህን ሰዎች “ከታዘዘላችሁ በላይ አብልጣችሁ አትሰብስቡ” ብሎአቸውል።ሉቃ፦.3፡13። በሐጢአተኛም ይመሰሉ ስለነበር ጌታም ሓጢአተኞችን ለማዳን እንደመጣ ለማስተማር በቀራጩ በማቴዎስ ቤት በማዕድ ተቀምጧል። ብዙ ቀራጮችም እየተጠራሩ በመምጣት ለማዕድ አብረውት ተቀምጠዋል።ማቴ. 9፡9-11።

ቤተ መቅደስ/ቤተ ክርስቲያን/
ከላይ የጠቀስናችው ፈሪሳዊ እና ቀራጩ ለጸሎት በቤተ መቅደስ ተገናኙ፡ ለመሆኑ ይህች ቤተ መቅደስ ምን አይነት ነች::የቅዱስ ዳዊት ልጅ ሰሎሞን አባቱ የጀመረውን የቤተ መቅደስ ግንባታ በፈጸመ ጊዜ ታላቅ ጸሎት አቅርቦ ነው። ከዚህም ጸሎት መካካል የተናገረው ነገር ቢኖር በዚህ ቦታ (በቤተ መቅደሱ) ለሚጸለዩ ጸሎቶች እግዚአብሔር ጆሮዎቹን እነዲያዘነብል አይኖቹንም ከፍቶ እንዲመለክት፡ ተመልክቶ እና አይቶም ለጸሎት ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር::
እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው፡-
"ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥  በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ ጆሮቼም ያደምጣሉ"።2ዜና፦7፡12

ስለዚህ ቤቱ የጸሎት ቤት የእግዚአብሔር ጆሮዎች የሰዎችን ልምና ለመስማት፡ እነርሱንም ለማየት በረድኤት የሚገለጥበት ቤት ነው። ጌታም በወንጌሉ ቤቴ የጸሎት ቤት ነው ብሎ አውጇል። አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ታላቅ ራዕይ ያየበትን ቦታ የድንጋይም ምልክት አስቅምጧል። ይህች ቤት የሰማይ ደጅ ናት ብሏል። አዎን ሰማያዊው አምላክ በረድኤት የሚገለጥባት መላእክት የሚወጡባት የሚወርዱባት ቤት ነች። እነዴት ያማረች ቤት ነች ? እኛስ ቤተክርስቲያንን በዚህ መልኩ እናያት ይሆን? እንግዲህ በዚህች የሰማይ ደጅ በምትባል እግዚአብሔር ዘወተር ወደ ሚመለክባት ቦታ ለጸሎት ፈሪሳዊው እና ቀራጩ መጡ።
  • የፈሪሳዊው ጸሎት፡

ፈሪሳዊው ህግ አክባሪ ወግ ጠባቂ በመሆኑ በቤተ መቅደስ የተገኘው እንደ አንድ ፈሪሳዊ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ነው። በመሆኑም የእግዚአብሔርን ስም ከጠራ በሗላ፡ ቀማኛ አመንዝራ ስላላደረገው አመሰገነ፡ በመቀጠልም ፡ በአጠገቡ የቆመውን ቀራጭ በመመልከት እንደዚህ ቀራጭ ስላላደረከኝ አመሰግንሃለሁ ሲል ተናገረ። ሌላውን መናቅ አልበቃ ያለው ፈሪሳዊ አሁንም በመቀጠል ስለ ሚሰራው የጽድቅ ስራ ዝናውን ማውራት ጀመረ።በሳምንት ሁለቴ እንደ ሚጾምና አስራት እንደሚያወጣ አስረዳ። ፡

ኢዮብ በመጸሐፍ፦“ በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን? ። ኢዮብ 4፡17 ብሎ የተናገረውን ሳያስተውል እኔ ጻድቅ ነኝ ብሎ በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት ተናገረ። በእውነት በማን ፊት እንደ ቆመ የት እንዳለ አላስተዋለም። ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን ደሙን ያፈሰሰላት ጌታ ፊት ቀርበን ስንቶቻችን ስለ ሰበክነው ስብከት ስለ ዘመርነው ዝማሬ ስለሰራናቸው ቤተ ክርስቲያናት፡ ስለ ተካፈልናቸው ጉባኤያት ስለ ተጎዝነው መንፈሳዊ ጉዞ ስለ ያዝነው ሱባኤ በአጠቃላይ ስለምናደርጋቸው መንፈሳዊ ስራዎች የምንመጻደቅ የሌሎችን ህይወት እያነጻጸርን እነርሱን እየናቅን እራሳችንን ከፍ ያደረግን እንኖራለን። ይህ የፈሪሳዊ ጠባይ ነው።

ሕግን መፈጸሙን እንጂ ፈሪሳዊው የት ቦታ እነደቆመ አላስተዋለም እንደ አቤል ተጠቦና ተጨንቆ በእግዚአብሔር ቤት አልተገኘም፡ ዛሬም ምን አልባት፡ በልማድ ብቻ በዘወትርና በበዓል ቤተ ክርስቲያን የምንገኝ ስለምናደረገው ጸሎትና ስለምናቀርበው አገልግሎት የማንጨነቅ የግብዝነት ጸባይ ያለን እንኖራልን። ሕግ መፈጸም በራሱ የትም አያደርሰንም። ይልቅስ እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ምግባርን ከሃይማኖት ጋር በመያዝ በተሰበረ ልብ በቤተክርስቲያን መገኘት ይጠበቅብናል።
  • የቀራጩ ጸሎት
ቅዱስ መጸሀፍ ቀራጩ ቤተ መቅደስ ከገባ ጀምሮ መጨነቁንና መጠበቡን ያሳያል። ቤተ መቅደስ ገብቶ እራቅ ብሎ ቆመ። ጴጥሮስ እኔ ሐጢያተኛ ነኝና ከእኔ እራቅ እንዳለው የትሕትና መግለጫ ነበር። ሉቃስ፦5፡8። ወደ ሰማይ እንካን ፊቱን አላነሳም። በአምላኩ ፊት ምን ያህል የቆሸሸ መሆኑ ስለገባው፡ ወደታች አቀርቅሮ ደረቱን እየመታ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ማረኝ በማለት የትሕትና የንስሐ ጸሎት አቀረበ። ይህ አይነት የትሕትና ጸሎት ፍጹም የንስሐ ልመና የሚመነጨው በማን ፊት እንደቆመ ለተገነዘበ ብቻ ነው። ቤተ ጸሎት /ቤተክርስቲያን/ የሰማይ ደጅ የእግዚአብሔር ዙፋን የሚዘራጋባት አይኖቹ ዘወትር የሚያርፉባት መሆኑን በመገነዝብ ይህንን ልመና በትሕትና አቀረበ። ነቢዩነቢዩ ኢሳይያስ ጌታን በትልቅ ዙፋን ላይ ተቀምጦ መላእክቱ በዙሪያው ቆመው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ሲያመሰግኑት ቢሰማና ቢመለከት በጻድቁና በንጽሑ እግዚአብሔር ፊት መቆሙን በማስተዋል እኔ ሐጢአተኛ ነኝ በሠራዊት ጌታ ፊት ቆምኩ ወዮልኝ ብሎአል። ኢሳ፦6፡1-5 “--እኔም ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ”

ይህም ቀራጭ ከዚህ ባልተለየ መልኩ በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ በደለኛ መሆኑን በማመን በራሱ ፈረደ። በራሱ የፈረደ ደግም ከሳሽና ምስክር አያስፈልገውም ወደ እውነተኛ ንስሐም በፍጥነት ይደርሳል። ቅዱስ ጳውሎስ በተደጋጋሚ ኃጢያተኛ ነኝ። ከሁሉ የማንስ ነኝ በማለት ይናገር ነበር። እነደውም ጌታ ወደ እስጢፋኖስ ቤተሰብ ሊልከው በወደደ ጊዜ፡ በእስጢፋኖስ ሞት መተባበሩን ተናግሮዋል በደሉን አልሸሸገም። ሐዋ.ሥራ፦22፡20 “የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ።”


የሰው ልጅ ደግሞ ኃጢአት የሚስማማውን ሥጋ ስለ ለበሰ ኃጢአት የለብኝም ቢል እራሱን እያሳተ ከእግዚአብሔር ሊያገኝ የሚገባውን ይቅርታን ያጣል እኔ ንጹሕ ነኝ የሚል ካለ እሱ ዋሽቷል።1.ዮሐ፦1፡8 “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም”ይልቅስ እራስን ከማመጻደቅና ከመኩራራት በራስ ከመመካት ሐጢአታችንን ሳንሰውር ንስሐ በመግባት የእግዚአብሔርን ምሕረት ማግኘት ጠቃሚ ነው።ሐጢአታችንን ብንሰውር እንጎዳለን እንጂ አንጠቀምም።ምሳ፦28፡13 “ ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል”። ከፈሪሳዊው በተለየ መልኩ ኃጢአቱን ሳይደብቅ በትህትና ሆኖ ምሕረትን በመጠየቁ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዶ ጻድቆ ሆኖ ይህ ቀራጭ ተመለሰ።ፈሪሳዊው ግን እራሱን ስላጸደቀ በከንቱ በመመጻደቁ በጽድቁ ጠፋ። “ራሱን ጻድቅ የሚያደረግ በጽድቁ ይጠፋል” መክ.7፡15-18

በዚህ በአሁኑ ዘመን አንዳንዶቻችን የቤተ መቅዱስን ባለቤት ሳይሆን በወስጡ የተመረጡትን አገልጋዮች የምግባር ጉድለት በመመለከት ቤተ ክርስቲያን ይህን ሁሉ ጉድ እየሰራች እንዴት ጸድቄ ልመጣ እችላለሁ ልንል እንችላለን። አንዳንዶቻችንም ቤተክርስቲያን መሔድ አቁመን ይሆናል። መሔድ የቻልነውም በተረጋጋ መንፈስ አንድ አባታችን ሆይ ማለት አቅቶን ተመለስን ይሆናል።ነገር ግን ይህ መዳናችንን የማይወድ የጠላት ዲያብሎስ መሰናክል መሆኑን እንገንዘብ፡፡ልጅ ሳይኖራት ለብዙ አመት ታዝን የነበረቸውና ባልዋ እነኳን ከሌላኛው ሚስቱ በማስበለጥ እጥፍ እድል ፈንታ ቢሰጣትም አብልጦ ቢንከባከባትም መጽናናትን ያለገኘችው ሐና በጊዜው ወደ ነበረው ወደ እግዚአብሔር ቤት ለጸሎት ትሔድ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል።

በጊዜው የነበሩት አገልጋዮች ደግሞ የዔሊ ልጆች በቤተ መቅደስ የማይገባ ስራ ይሰሩ ነበር።አባታቸውም ዔሊ ሊመክራቸውና ሊመልሳቸው አልቻለም። ነገር ግን ሐና እነሱን አልተመለከተችም እራሷን በሐያሉ በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰች።እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ ምኞቷን ልመናዋን ፈጸመላት።ሳሙኤልን የሚያክል ልጅ አገኘች።ሐና ግን ጸሎቷን ካቀረበች በሗላ ደስ ብሎዋታ ወደ ቤትዋ ሔደች።1ሳሙ፦1-18። በዔሊና በልጆቹ በሚደረግ የሐጢአት ብዛት እግዚአብሔር በተቀደሰው አደባባይ የሚቀርብለትን ልመና ከመስማትና መልስ ከመስጠት አልተቆጠበም። ብዙውን ጊዜ እራሳችንን ተመልክተን ስለ ሐጢአታችን እራሳችንን በመውቀስ ፈንታ የሰውን ድካም እየተመለከትን እግዚአብሔር እኛን የመታገሱ እና ለንስሐ እድሜ የመስጠቱ ምስጢር እኛ ከክፋታችን ከመጥፎና አጸያፊ እርሱ ከማይደሰትበት የሐጢአት ግብር እነድንለይ መሆኑ ያልገባን ብዙ ሰዎች አለን። ሰለዚህ በተሰጠን የንስሐ ዘመን ልንጠቀምበት የገባል።ከፈሪሳዊው ተምረን የራሳችንን ህየወት ልንመረምር ይገባል።በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያንም እግዚአብሔር ከልብ ሆነን የምንጸልየውን ጸሎት በተሰበረ ልብ ሆነን የምንገባውን ንስሐ ይቀበላልና። እንግዲህ ወገኖቼ ፡ ሁላችንም ለመዳን ለጽድቅ መሽቀዳዳም አለብን። ቤተ መቅዱስም የምንገኝበት ዋና አላማ ለእውነትና ለጽድቅ ሊሆን ይገባል። ለዚህም የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን የእመቤታችን የቅድሰተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለይን አሜን።አሜን።


‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ››

No comments:

Post a Comment