Wednesday, March 7, 2012

የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አንድነትና እርቅ ጉባዔ በሐምሌ ይቀጥላል

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተወሰደ
  • በአሜሪካ በተካሄደው ጉባኤ የተሻለ መግባባት ላይ ተደርሷል ተባለ
በኢትዮጵያና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶችን ለማስማማት ከየካቲት 4-9 2004 ዓ.ም አሜሪካ በሚገኘው በፊኒክስ አሪዞና 2310 ኢስት ኃይላንድ ሆቴል ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን ካሁን ቀደም ሲል ከተደረገው ጉባኤ የተሻለ መግባባት እንደታየበት ተገልጿል፡፡ ጉባኤው በሐምሌ ወር የሚቀጥል ሲሆን የመጨረሻ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደጠቆሙት በሐምሌ የታሰበው ስምምነት ከተደረሰ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተለምዶ “ተቃዋሚ ሲኖዶስ” ይባል የነበረው በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት መሪዎች በየሃገረ ስብከቱ እንደየፍላጎታቸውና ባለው ክፍት ቦታ ይመደባሉ ተብሏል፡፡ የጉባኤው ምንጮች እንዳሉት አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ሃገር ቤት የመመለስ ፍላጎት ካላቸው በመረጡት ስፍራ ክብራቸዉ የሚመጥን መኖሪያ ቤትና ደመወዝ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

ጳጳሳቱና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ከፊኒክስ ጉባዔ በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ የጉባኤው መነጋገርያዎች ስለ ቀኖና ቤተክርስትያን እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የሚመለከቱ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ “ቀደም ሲል የሰላምና አንድነት ጉባኤ ባወጣውና ልዑካኑ በተስማማንበት ባለ አምስት ነጥቦች የመወያያ መመርያ መሠረት የመፍትሄ ሃሳብ አቅርበናል፡፡

ሁለቱም ልዑካን ባቀረብናቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ልዩነት በመታየቱ የሰላምና አንድነት ጉባዔው ሁለቱን ያስማማል ያለውን የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ከዚያም የሰላምና አንድነት ጉባዔው ባቀረባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ከተነጋገርንበት በኋላ ጉዳዩን ጊዜ ወስዶ በጥልቀት ማጥናት እንደሚያስፈልግ በመግለጥ ለሚቀጥለው ጉባዔ የደረስንበትን ውጤት ለማቅረብ ተስማምተናል፡፡” የሚለው መግለጫው “የሃይማኖቱ አባቶች ለሰላም እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከማድረግ፣ ከመፃፍና ከመናገር እንዲቆጠቡ እና ለኢትዮጵያ ሰላም ሁሉም ተግቶ እንዲፀልይ እንዲሁም ሁሉም ወገን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሰላምና አንድነት ጉባዔን እንዲተባበር ተማፅነዋል፡፡” ይላል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የፊኒክስ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ፡- ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ኦትናቴዎስ እና ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ፤ ከውጭ ሀገር፡- ብፁዕ አቡነ መልከ ፄዲቅ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ መልአከ ገነት ገዛኸኝ ገብረክርስቶስ እና ሊቀካህናት ምሣሌ እንግዳ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

1 comment:

  1. Egziabher le Abatochachin Tesmamtew 1 yemihonubeten leb endisetachew emegnalehu

    ReplyDelete