Monday, September 19, 2011

“አቡነ ጳውሎስን እና አቡነ መርቆሬዎስን የማስታረቁ ጥረት ቀጥሏል”



(ነጋድራስ፤ ቅጽ 08 ቁጥር 296፤ ዓርብ፣መስከረም 05፤ 2004 ዓ.ም)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሥርዐተ ጵጵስና በምትመራበት ፍትሐ ነገሥት፣ በአንድ መንበርና ዘመን ሁለት ፓትርያሪክ መሾም እንደማይቻል መደንገጉን የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ይህ ድንጋጌ በ1984 ዓ.ም ላይ አክባሪም አስከባሪም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኗ አራተኛ ፓትርያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት እያሉ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተመርጠው መንበረ ፓትርያሪኩን እንደተረከቡ ይታወሳል፡፡





“በጤና ምክንያት ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀዋል” የጠባሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አሜሪካ ከገቡ በኋላ፣ ‹ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያሪክ ነኝ› የሚል አቋም በመያዝ የራሳቸውን ሲኖዶስ አቋቁመዋል፡፡ ለበርካታ አባቶችም የጵጵስና ማዕርግ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

ሁለቱን አባቶች ለማቀራረብና ለማስማማት ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆንም ጎላ ብሎ የሚጠቀሰው ባለፈው ዓመት በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሐቅ የተጀመረው ድርድር እንደሆነ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ አትናቴዎስ፣ አቡነ ቀውስጦስ በአባልነት፣ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በጸሐፊነት የሚገኙበት የመንበረ ፓትርያሪክ ተወካዮች ሆነው እንዲደራደሩ ሲደረግ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በዋና አስታራቂነት ከተመረጡት ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡


በአሜሪካ ከሚገኙት የሃይማኖት አባቶች በኩል በሽማግሌነት የተመረጡት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሥሐቅ ድርድሩ እንደቀጠለ መሆኑንና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አለመኖሩን ለነጋድራስ ገልጸዋል፡፡. . . “በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ብሔረሰቦች ዘንድ ሰው የገደለ ሳይቀር በሽማግሌ ታርቆ ሰላማዊ ኑሮ ይኖራል፡፡ ነገሥታት ተዋግተው በሽምግልና ተቀምጠው ይቅር ለእግዜር ተባብለው በሰላም መኖራቸው ታሪክ ይገልጣል፡፡ የዚህ ዘመን የፖሊቲካ መሪዎች በባህላዊው መንገድ ችግራቸውን ለምን መፍታት አልቻሉም? የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ምን ድረስ የተሳካ ሥራ እየሠራ ነው?” በማለት ነጋድራስ ጠይቋል፡፡ “ይህ ባህል አልተለወጠም ብዬ አምናለሁ፤ የተለመደው ባህላችን እንዲቀጥል በሁሉም በኩል እየሞከርን ነው፤” በማለት መልስ የሰጡት ፕ/ር ኤፍሬም ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ለመግባት ዝግጁ አለመሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡

from Dejeselam

2 comments: