Tuesday, August 7, 2012

የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች የአስተዳደር በደል ደርሶብናል አሉ አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል


ኢትዮጵያ ውስጥ ብሎጋችንን ለማንበብ  www.andadirgen.com


በአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት አስተዳዳሪዎች፤ ሀገረስብከቱና መንበረ ፓትርያርክ የአስተዳደር በደል አድርሰውብናል በማለት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አመሩ፡፡ በሐገረ ስብከቱ በሚገኙ አብያተክርስትያናት እንድንሰራ በፓትርያርኩ ተመድበን ሥራችንን በአግባቡ ብናከናውንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቃለ አዋዲ በማይፈቅደው መልኩ ከሥራ ተባረን፣ ሰብዓዊና ሕጋዊ መብታችን ተጥሷል ያሉት አስተዳዳሪዎች፤ አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዳስገቡ ገለፁ፡፡ በተለያዩ ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች ክስ ብንመሠርትም፣ አንዳንድ የሥልጣን አካላት በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አንገባም በሚል የመዳኘት መብታችንን ስላላከበሩልን ሕግን ወደሚተረጉመው ከፍተኛ የሥልጣን አካል አምርተናል ብለዋል - ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት፡፡

ከአስተዳዳሪዎቹ አንዱ በደላቸውን ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ “በላዬ ላይ ሌላ አስተዳዳሪ ተሹሞብኛል፤ ንብረት እንዳስረክብ ደብዳቤ ስላልተፃፈልኝ ላለፉት ስድስት ወራት ቁልፍ በእጄ ይገኛል፣ የማስተዳድረው ቤተሰብም እየተራበ ነው” ብለዋል፡፡

ሌላው በደል ደርሶብኛል ያሉት አስተዳዳሪ በበኩላቸው፤ “ያለ ሀገረ ስብከቱ ፈቃድ መሬት አከራይተሃል ተብዬ ጉዳዩ ሳይጣራ ተባርሬአለሁ፤ የጣስኩት ሕግ የለም፤ ያከራየሁት በሕጉ አግባብ ነው” ብለዋል፡፡
ከመጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ መታገዳቸውን የገለፁ አስተዳዳሪ ደግሞ፤ ገቢ የተደረገ ገንዘብ በግለሰብ እጅ ከሚቀመጥ በሞዴል 64 ገቢ ይሁን በማለቴና የቀድሞውን የሐገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ፎቶግራፍ ቢሮዬ ውስጥ በመስቀሌ “ደጋፊ” በሚል ተከስሼ ተባርሬአለሁ ይላሉ፡፡
የታች ፍርድ ቤት የፈረደልን ይፅና፤ በትምህርት፣ በልምድና በብቃታችን እንሾም፣ በቃለ አዋዲ መሠረት ማስጠንቀቂያ አልተሰጠንም ያሉት አስተዳዳሪዎች፤ ማመልከቻቸውን ለአውሮፓ ሀገራት እና ለአሜሪካ ኤምባሲዎች፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ለሰብዓዊ መብት ጉባኤ እና ሌሎች አካላት እየላኩ መሆናቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ፤ የሥራ አስኪያጅነት ሥራ ከጀመሩ ወዲህ የሕግ መስመር የተከተለ አቤቱታ እንዳልቀረበና ሁለት ግለሰቦች በመንግስት መሥርያ ቤት ተቀጥረው ድርብ ሥራ ሲሰሩ በመገኘታቸው መባረራቸውን ገልፀዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ በተጨማሪም የሚቀርቡላቸው የአዲስ ቅጥር፣ የዝውውርና የእድገት ጥያቄዎች በቃለ አዋዲው መሠረት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተወሰደ

1 comment:

  1. pdfl binorachuh tir new manbeb alchalkum thanks

    ReplyDelete