Tuesday, August 7, 2012

በባቦጋያ መድኃኒዓለም የመሬት ጉዳይ የታሰሩት ክርስትያኖች ከእስር ተፈቱ


  • አዲሱ አስተዳዳሪ ሰበካ ወንጌሉንና ሰንበት ትምህርት ቤቱን ሰብስበው የማህበረ ቅዱሳን አባል የሆነ ሰው እዚህ ቤተክርስትያን መጥቶ እንዳያገለግል የሚል መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

(አንድ አድርገን ነሐሴ 2 2004 ዓ.ም)፡- ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው በባቦጋያ መድኃኒዓለም የጥምቀት ታቦት ማሳደሪያ ቦታ ላይ ከባቦጋያ ሪዞርት ባለቤት ከአቶ ታዲዎስ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ገልጸን በየጊዜው መረጃ በብሎጋችን ላይ ማውጣታችን ይታወቃል ፤ በአዲሱ የባቦጋያ መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ ቀሲስ መስፍን  ፤ በአቶ ጌታቸው ዶኒ እና በሪዞርቱ ባለቤት ጠበቃ አማካኝነት በተሸረበ ክስ ከ13 በላይ ስለ መድኃኒዓለም ቦታ ዘብ የቆሙ ክርስትያኖች  ሰኔ 19 2004 ዓ.ም መታሰራቸው ይታወቃል ፤ እነዚህ ሰዎች ላይ ያለአግባብ በሪዞርቱ ባለቤት እና በጌታቸው ዶኒ የሀሰት ክስና የሀሰት ምስክርነት መሰረት 7 ወር ተፈርዶባቸው መታሰራቸውን  በጊዜው ገልጸን መጻፋችን ይታወቃል ፤ በጊዜውም የተፈረደውን ፍርድ በርካቶች የተቃወሙት ሲሆን ፖሊስ ከፍርድ ቤት የማሰሪያ ትእዛዝ አውጥቶ ሰዎቹን ይዙ በሚሄድበት ጊዜ ከ400 የማያንስ ምእመናን ወደ እስር ቤት በእንባ ሸኝቷቸዋል ፤
እነዚህ ሰዎች ከታሰሩ በኋላ ከደብረዘይት አዳማ ከተማ ድረስ ያለመሰልቸት ለተከታታይ ሳምንታት  በአንድነት በመሆን በርካታ ምዕመናን ጠይቀዋቸዋል ፤ ይህ እንዲህ እያለ በጊዜው ያለአግባብ የተፈረደባቸው እስረኞች ለምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ይግባኛቸውን በአግባቡ መመልከት አልቻለም ነበር፤ ከበታች ፍርድ ቤት ፍትህን ያጡ እነዚህ ወገኖች የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ችሎት ይግባኛቸውን ያቀረቡ ሲሆን ይግባኙ ከቀረበበት በሶስት ቀጠሮ ሰዎቹ ላይ የተፈረደው ፍርድ ህግን ያልተከተለ እና ግልጽነት የጎደለው ፤ የግለሰቦች ሃሳብ መሰረት ያደረገ መሆኑን ካስረዳ በኋላ የአደአ ፍርድ ቤት ሰኔ 19/2004 ዓ.ም ለ7 ወር የፈረደባቸውን ሰዎች በድፍን አንድ ወሩ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በመከበር ላይ ሳለ ሐምሌ 19 /2004 ዓ.ም በነጻ ከእስር ተለቀዋል፡፡


በወቅቱ ያለአግባብ ለባለሀብቱ የተሰጠው ከ10ሺህ ካሬ በላይ የጥምቀትና ደመራ በዓል ማክበሪያ ቦታ ላይ የነበረውን መስቀል እንደ ተራ ነገር ያስቆረጡት ቀስሲ መስፍንና ለዚህ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ይሆነው ዘንድ በአስር ሺዎች ብር ከሪዞርቱ ባለቤት የተመደበለት የነበረው አቶ ጌታቸው ዶኒ ከባለሃብቱ ጋር በመመሳጠር  አስተዳዳሪውን በመያዝ እንዳስቆረጡት ይታወቃል፡፡  ህዝቡም ይህ መስቀል ያለአግባብ ከተቆረጠ በኋላ ለምን? ብሎ ሲጠይቅ በአስተዳዳሪው የተሰጠው መልስ ቢኖር “መስቀል ምን ያደርጋል እንጨት ነው ዝም ብላችሁ አትጩሁ” የሚል ሲሆን ይህ መልስ ህዝቡን በማስቆጣቱ የቀድሞ የባቦጋያ መድኃኒዓለም አስተዳዳሪ ቀስሲ መስፍንን አቡነ ጎርጎርዮስ ከደብሩ በማንሳት ወደ ደብረ ዘይት ቃጅማ ደብረ ገነት በአስተዳዳሪነት ቦታ ቀይረዋቸዋል፡፡

እኝው የአቶ ጌታቸው ዶኒ ባለውለታ ወደ ደብረ ገነት ተቀይረው ወር ሳይሞላቸው ሐምሌ 24/2004 ዓ.ም ቃጅማ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ስብከተ ወንጌል ባዘጋጀው የህዝብ ጉባኤ ላይ የተጋበዙትን መዘምራንና እንዳያገለግሉ አግደዋችዋል፡፡ በወቅቱ ስብከተ ወንጌሉ እና ሰ/ት/ቤቱ አብረው በዚህ ሁኔታ ወደፊት  መቀጠል እንደማይችሉ በግልጽ ነግረዋቸዋል፡፡ በጊዜው ህዝቡም ተቃውሞውን ሲገልጽና መዘምራኖቹ ለምን እንደታገዱ ሲጠይቅ እንደነበር ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘማሪዎቹ ከአዲስ አበባ የመጡ ሲሆኑ እነሱን በመሳሪያ የሚያጅበው ወንድም ደግሞ የባቦጋያ መድኃኒዓለም የመሬት ጉዳይ የህግ ጠበቃ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ፤ በተጨማሪም አዲሱ አስተዳዳሪ ሰበካ ወንጌሉንና ሰንበት ትምህርት ቤቱን ሰብስበው የማህበረ ቅዱሳን አባል የሆነ ሰው እዚህ ቤተክርስትያን  መጥቶ እንዳያገለግል የሚል መመሪያ እንዳስተላለፉላቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጊዜው የእግዚአብሔርን ቃል ለምዕመና ያስተላለፈው ዲ/ን ተስፋዬ ሞሲሳ የተሀድሶ ክንፍን በመቃወም የሚታወቅ ሰባኪ ወንጌል ሲሆን ይህን አቋሙን የሚያውቀው ከተሀድሶያውያን ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራውበጠቅላይ ቤተክህነት የሚገኝው የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ መምህር አመረ አሸብር አማካኝነት የማገልገል ፍቃድ ስለተከለከለ ማገልገል በፈለገበት ቦታ ከደብር አስተዳዳሪዎች ጋር በመመሳጠር እንዳያገለግል እንቅፋት እየሆነው ይገኛል ፤ በየቦታው እኒህን የመሰሉ ወንድሞች ላይ ቀድሞ አገልግሎታቸውን በማደናቀፍ መምህር አመረ አሸብር የውስጥ እሾህ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡

አሁንም በቦታው የሚገኝው ምዕመናን ጥያቄ አንድና አንድ ነው “ያለ አግባብ የተሸጠው ቦታ ይመለስ” የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የቦታዉ ጉዳይ ዳግም በሕግ እየታየ ይገኛል ፤ አቡነ ጎርጎርዮስም ከሕዝቡ ጋር መታረቅና መነጋገር እንደሚፈልጉም  የገለጹ ሲሆን ከእስር በተለቀቁት ክርስቲያኖች መታሰር ዙሪያ  ግን ፍጹም እጃቸዉ እንዳሌለበትና ጉዳዩንም እንደማያዉቁት ለምዕመኑ ተናግረዋል፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን

2 comments:

  1. beyedebiru eytesema yalew asazagn dirgit nw .yehaymanot abtoch silehayimanotachew kalitekorekoruna yibism "meskel enchet nw"bemalet diyabilos enkuan yeminketeketibetin legil tikim sibal yihen mefetem tegebi aydelem.yihe endale hono ..and astedadary chigir endalebet eyetaweke lemin wede lela debir yizewaweral ??? ezam bihed ketenikolu eskalitareme dires gudat masiketelu gilit nw .gn ahun ahun eyasasebegn yemetaw betechirstiyanachinin yemiyastedadiruat tekulawoch kehonu mimenun lemimenu man lihon nw eregn .egizihabiher hayimanotachinin yitebik AMEN!!

    ReplyDelete
  2. I'm really afraid of our fathers who teach laying instead of preaching the truth, look this word "አቡነ ጎርጎርዮስም .... ከእስር በተለቀቁት ክርስቲያኖች መታሰር ዙሪያ ፍጹም እጃቸዉ እንዳሌለበትና ጉዳዩንም እንደማያዉቁት ለምዕመኑ ተናግረዋል፡፡". The Bishop know everything from day to day information, why he need to lay? There pack of evidence he has direct link with the bishoftu resort owner Tadiyose. I wish God give the mercy to our fathers who forget their objectives and the sheep who lost the truth way. I was very kid when Abune sold this place two-times. Time flaying instead of confessing still our Abune laying....laying, so how could these people believe the holy words from ur mouth. You will get all of ur wadge from up!

    Let use this holy time our father God bless our church.
    Thank you Andadirgen for your committed work to reveal the truth! Don't give up!

    ReplyDelete