Wednesday, August 8, 2012

እግዚአብሔር የዋልድባ ገዳም አባቶቻችንን እንዲህ ይሰማቸዋል



(አንድ አድርገን ሐምሌ 3 ፤ 2004 ዓ.ም)፡, በዋልድባ ገዳም በዘመናት በርካታ ተዓምራት ተፈጽመዋል ፤ በጽሁፍ ሰፍረው ለትውልድ የተላለፉ እንዳሉ ሆነው ያልተጻፉ ተዓምራ በርካታ ናቸው ፤ የዋልድባ ገዳምን ታሪክን መሰረት አድርጎ ከተጻፈ  አንድ መጽሃፍ ላይ ያገኝነውን ተዓምር በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ላይ እጃቸውን ላነሱ ሰዎችና ተባባሪዎቻቸው መማሪያ ይሆን ዘንድ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ከዓመታ በፊት በዚህ ቦታ የተፈጸመ  አንድ ተዓምር አለ ፤ ይህ ገዳም በተመሰረተበት ጊዜ ጌታ እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ ይሁንላችሁ ብሎ ባርኮ የሰጣቸው ውሃ አለ ፤ ይህ የዮርዳኖስ ውሃ ተባርኮ እንደ ዮርዳኖስ ወንዝ ይሁንላችሁ ተብሎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ አንድም ቀን ደርቆ አያውቅም ፤ በገዳሙ አካባቢ የሚገኝ ህዝብና እንዲሁም ራቅ ካለው አገር የሚኖረው ምዕመናን በየዓመቱ በዓለ መስቀልን ለማክበር በመጋቢት 27 ቀን ከገዳሙ እየተገኝ በዓሉን ማክበር ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ወደዚሁ በዓል በየዓመቱ  የሚመጡት ምዕመናን በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው ፤ በዓሉን ለማክበር የመጣው ህዝብ ከዚሁ ከዮርዳኖስ ውሃ ስምረትን በተቀበሉ መነኮሳት እየተቀዳ ይታጠባል ፤ ይጠጣል ወደ ቤቱ ይዞ ይሄዳል ፤ ውሃው የፈለቀው አለት ከሆነ ቦታ ላይ ሆኖ ከአንድ ከተደላደለ ቦታ ላይ ነው ፤ አለቱን እንደ እህል  አውድማ ክብ አድርጎ በመሃንዲስ እንደተሰራ ጉድጓድ አድርጎ ነው ያፈለቀው ፤ ታዲያ በበዓሉ ቀን ይህን ሁሉ ህዝብ ሲቀዳው አይጎልም ፤ በአዘቦት ቀንም ተርፎ አይፈስም ፤ ሁል ጊዜ ከከንፈሩ እንደሞላ ይታያል ፡፡


በመጋቢት 27 ቀን በዓለ መስቀል የሚከበርበት ቀን ከአምስት በላይ ስምረት የተነሱ መነኮሳት ተሰልፈው እየቀዱ ለምዕመኑ ይሰጣሉ እንጂ  ምዕመኑ እንዲቀዳ አልተፈቀደለትም ፤ በአል ባልሆነበት ጊዜም ወደ ገዳሙ ያመራ ሰው ስምረትን በተቀበሉ መነኮሳት ነው ከማዬ ዮርዳኖስ ተቀድቶ የሚሰጠው ፤ ይህን በተመለከተ ከአስርት ዓመታ በፊት ይህ ሆኗል ፤ ጊዜው 1959 ዓ.ም በጥር ወር ነበር ፤ ከገጠር የመጡ ስምረት ያልተነሱ ሰው ማዬ ዮርዳኖስ ለመቅዳት ይቀርባሉ ፤ በዚህ ጊዜ ዮርዳኖስ ውሃ ባለበት ቦታ ላይ ሁነው ጸሎት ሲያደርሱ የነበሩት የማህሩ አባል የሆኑት የገዳሙ መነኩሴ አባ ወልደ ተንሳኤ የተባሉ ጸበሉን ለመቅዳት ለቀረቡት ሰው “እርስዎ እንዳይቀዱ ክልክል ነው ትንሽ ይቆዩና ጸሎቴን ስጨርስ እኔው ቀድቼ እሰጥዎታለሁ” ቢሏቸው እንቢኝ ብለው በስልጣናቸው ተጋፍተው ገብተው ቀድተው ይወስዳሉ ፤ በበነጋታው ጠዋት ጸበሉ ቢታይ ፈጽሞ ውሃ የነበረበት ሳይመስል ብዙ ዘመን ጸሃይ ሲመታው የቆየ አለት መስሎ ደርቆ ተገኝ ፤ ከጥር ወር 1959 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 27 1959ዓ.ም ድረስ 3 ወር ሙሉ ደርቆ ከቆየ በኋላ በመጋቢት 27 ቀን በዓሉን ለማክበር የመጣው ምዕመን ይህ ነገር ተመለከተ ፤ የደረቀበትንም ምክንያት ከማህሩ ጠይቆ ተረዳ ፤ ከዚህ በኋላ ህዝቡ በሙሉ ተሰብስቦ ከማህበሩ ጋር በአንድነት ሁኖ  ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ሳያቋርጥ ሳይቀመጥና ሳይተኛ ለሊቱን በሙሉ  ምህላ ሲያደርግ አደረ  ፤ በበነጋታው  ጠዋት ማዬ ዮርዳኖስ እንደ ጥንቱ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ተገኝ ፤ ምህላ የተጀመረው ዓርብ መጋቢት 26 ቀን  ከምሽቱ 1 ሰዓት ሲሆን ማዬ ዮርዳኖስ ሞልቶ የተገኝው ቅዳሜ ጠዋት በ12 ሰዓት መጋቢት 27 ቀን 1959 ዓ.ም ነበር ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ተዓምር ተፈጸመው በመቶ ሳይሆን በሺህ ሚቆጠር ምስክር ባለበት መሃከል ነው ፤ በዚህ ጊዜ  እልልታ ቀለጠ በቦታው ላይ ታላቅ ደስታ ሆነ ፤ መዝሙረኛው ዳዊት 66፤20 ላይ “ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን።” እንዳለ ፤ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ስለሰማ እጅጉን አመሰገኑ፡፡  

አሁንም ለመቶኛ ጊዜ እንናገራለን ዋልድባ ገዳም ላይ የሚሰራ የስኳር ልማት ለማንም አይጠቅምም ፤  ብዙ ብር ወጥቶበት የሚገነባ የውሃ ግድብ በአንድ ቀን ደርቆ እንደማያድር እርግጠኞች ሆነን መናገር አንችልም ፤ የአባቶቻችን አምላክ አሁንም ከእኛ ጋር እንደሆነ እናምናለን ፤ ዋልድን ነክቶ ሰላም ማደር እንደሌለ የተመለከታችሁ ይመስለናል ፤ ይህ የተቀመጠው ተዓምር ከመቶ ዘመናት በፊት የተደረገ አይደለም ፤ ከዛሬ ሰላሳ እና አርባ አመታት በፊት የሆነ ሺዎች በጊዜው የነበሩ ምዕመናን በአሁኑ ሰዓት የሚመሰክሩለት ተዓምር ነው ፤ የዮርዳኖስን ጸበል በአንድ ቀን ለሊት ጸሎታቸውን ሰምቶ እንባቸውን አይቶ መተላለፋቸውን ሳይመለከት እንደ ቀድሞ የመለሰ አምላክ ለመሰራት የታሰበውን ግድብ በአንዲት ጀምበር ጸሎት ሊያደርቅ ይችላል ፤ እባካችሁ ቆም ብላችሁ አስቡ ፤ ሰው ጭንቅላት የተሰጠው እንዲያስብበት እንጂ ተሸክሞት እንዲዞር አይደለም ፡፡

ከዚህ ታሪክ በተጨማሪ በ1974 ዓ.ም አንድ ከደብረ ዳሞ የመጡ መነኩሴ እንደዚሁ በገዳሙ ስርዓት መሰረት ማህበሩን ሳያስፈቅዱ በስልጣናቸው  ስለቀዱ  ዮርዳኖስ ጨርሶም ሳይደርቅ በቀን አንድ ፍንጃል የሚሆን ውሃ እየተቀዳ ባጅቶ ክረምቱንም በዚሁ ዓይነት ከርሞ እስከ መጋቢት 27 ቀን 1975 ዓ.ም ድረስ ቆየ ፤ በዚሁ ቀን በዓሉን ለማክበር የመጣው ህዝብ ነገሩን ሰማ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ ህዝቡ በአንድ ላይ ሆኖ ማህበሩን ይዞ ምህላ ሲያደርግ አደረ ፤ በበነጋታው ጠዋት ዮርዳኖስ በእግዚአብሔር ቸርነት ሞልቶ ተገኝ ፤ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለ24 ሰዓት የማይለዩ  ሁለት መነኮሳት እየተመደቡ በየተራ እንዲጠብቁት ማህበረ መነኮሳቱ ወሰነ ፤ እኛ ደግመን ደጋግመን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስርዓትን እንተላለፋለን ፤ ይቅር ባይና ታጋሽ አምላካችን ሁል ጊዜ መተላለፋችን ሳይመለከት በምህረቱ ይጎበኝናል ፤ ይህ ተዓምር የተፈጸመው የመጀመሪያው ተዓምር ከተፈጸመ ከ16 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው ፤ አሁን ደግሞ ሁለተኛው ተዓምር ከተፈጸመ ከ30 ዓመት በኋላ በገዳሙ ቦታ ላይ መንግስት ግድብ እገድባለሁ በማለት ተነስቷል ፤ የዚያን ጊዜ በጸሎታቸው ዮርዳኖስን የሞላላቸው አምላክ አሁንም ለጸሎትና በምህላቸው  አምላክ መልስ እንደሚሰጣቸው አንጠራጠርም ፤ ዝናብ የሚሰጥ እግዚአብሔር ፤ የሚከለክልም እርሱ ሆኖ ሳለ የሚዘንበውን ዝናብ የሚወርደውን ውሃ ተማምኖ  ዋልድባ ላይ ግድብ ለመገደብ መሞከር ሞኝነት ይመስለናል ፡፡

“ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች።” የያእቆብ መልዕክት 5፤17 ይህን ቃል መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ሰፍሮ እናገኝዋለን ፤ አባቶቻችን በእምነት ይጸልያሉ ፤ የጠየቁትን የማይረሳ ፤ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እንዲህ ይሰማቸዋል ፤ አሁንም በአባቶቻችን ጸሎት እኛ ልጆቻቸው እንታመናለን ፤ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውን እንደሚሰማቸው እናምናለን ፤ የኤልያስ አምላክ ከእኛ ጋራ ነው፡፡”የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።” መዝሙረ ዳዊት 46፤10

ከዚህ ሌላ ደግሞ በማህበሩ ፈቃድ ከማህበሩ ተለይተው በግርማ ለሊት በድምጸ አራዊት ተከበው ለየብቻቸው በየአንዳንዱ ዋሻ ወድቀው ፍርጣጣ ሚባለውን ትልቅ ዛፍ ፈልፍለው ከውስጡ ገብተው የተቀመጡ ለሊትና ቀን ለኢትዮጵያ ከዚያም አልፈው ለዓለም ሕዝብ ደህንነት ጸሎት የሚያደርጉ ከ7 ቀን አንድ ቀን ብቻ በዕለተ እሁድ ቋርፍ የሚቀምሱ አባቶች አሉ ፤ በዚህ ዓይነት በሳምት አንድ ቀን ብቻ አንድ ጭልፋ ቋርፍ እየቀመሱ ሌትና ቀን ጸሎት እያደረሱ ከዘንዶውና ከአንበሳው ከነብሩ ጋር እየተጋፉ ከ15 እስከ 40 ዓመት ያደረጉም አሉ፡፡ ለአሁኑ ትውልድ ይህን  አይነት ነገር ሲገለጽ ለማመን  ይከብድ ይሆናል ፤ እማሆይ ወለተ እየሱስ የተባሉ ሴት ከቄሱ ባለቤታቸውና ለልጆቻቸው ተለይተው ከሃማሴን በምናኔ ወደዚሁ ገዳም መጥተው ገቡ ፤ በመጀመሪያው ጊዜ  ዋልድባ ሰቋር በተለይ ማርፋዴ ከተባለው ቦታ 20ዓመት ያህል፤ ቀጥለውም ከዚሁ ቦታ ወጥተው ወደ ዋልድባ አብረንታንት ገብተው 37 ዓመት ያህል በድምሩ 57 ዓመት በሁለት ዋሻ ብቻቸውን ተቀምጠዋል ፤ 37 ዓመት በቆዩበት ዋሻ በነበሩ ጊዜ ማህበሩ የመደበላቸውን እረድ የሚመገቡትን ቋርፍ በሳምንት አንድ ጊዜ እየመጣ ይሰጣቸዋል ፤ ከተመገቡ በኋላ ካሉበት ዋሻ በአጠገብ በግምት 40 ሜትር በሚሆን እርቀት በጋ ከክረምት ሳያቋርጥ የሚፈስ ውሃ ስላለ እማሆይ አዝግመው እየሄዱ ከዚሁ ውሃ ይጠጡ ነበር ፤ በዚህ ሁኔታ ብዙ ዘመን እንደቆዩ 1943 ዓ.ም በጸና ታመው ተኙ ከወንዙ ሂዶ ውሃ ቀድቶ የሚያቀርብላቸው ሰው ታጣ ፤ በዚህ ጊዜ ከተኙበት ዋሻ  ከራስጌያቸው ውሃ ፈለቀ ፤  ታመው ከመተኛታቸው በፊት ፍጹም የሆነ ደረቅ አለት እንደነበረና ታመው በተኙ ጊዜ እንደፈለቀላቸው ማህበረ መነኮሳቱ በጊዜው መስክረዋል ፤ ይህ ውሃ አማሆይ ከደዌያቸው እስኪድኑ ድረስ አልደረቀም ነበር፤ ይህ ድንቅ ተአምር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እኒህ እናት በምናኔ ወደ ዋልድባ ገዳም ሲገቡ ቄስ ባለቤታቸው ደብረ ቢዘን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀብለው ይኖሩ ነበር ፤ እኒሁ በደብረ ቢዘን ይቀመጡ የነበሩት ባለቤታቸው በሞቱበት ቀን “ዛሬ ባለቤቴ በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተዋል” ብለው ተናግረዋል ፤ ይህንን ቃል ረዳታቸው ሰምቶ ለማህበሩ በፍጥነት በመሄድ ነገረ ፤ ማህበሩም የተናገሩበትን ቀንና ሰዓት ወሩንና ዘመኑን መዝግበው አስቀመጡ ባለቤታቸው በአረፉ በ2ተኛው ዓመት ልጃቸው እናቱን ለመጠየቅ ከሃማሴን ወደ ዋልድባ አብረንታንት በመምጣቱ  ማህበሩ አባቱ መቼ እንደሞተ ቢጠይቀው አባቱ ያረፉበት ቀንና ሰዓት እማሆይ ወለተ እየሱስ በተናገሩበት ጊዜና ሰዓት ሆኖ አገኙት ፤ እኒህ ቅድስት እናት በዋልድባ ሰቋርና አብረንታንት  57 ዓመት በጾም በጸሎት በስጊድ በዋሻው ብቻቸውን ቆይተዋል ፤ ለ67 ዓመት የተቀመጡበትን ዋሻ በራሳቸው ፍቃድ ወደ ሌላ ዋሻ  መነኮሳት እንዲወስዷቸው ካደረጉ በኋላ ጥቂት እንደቆዩ  በ1969 ዓ.ም አረፈዋል፡፡

እስኪ በዚህ የሱባኤ ወቅት ዋልድናን እናስብ ፤ እግዚአብሔር ዋልድባ ገዳምን ይጠብቅልን
ቸር ያሰማን 

ግብዓት ፡ “የዋልድባ ገዳም ታሪክ” ከበሪሁን ከበደ  መጽሀፍ የተወሰደ 

2 comments:

  1. ክርስቲያኖች ይኸን ይሏል ፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ ፤ ልቦና ያለውም ልብ ይበል ፡፡ ይኸ ታሪክ ቢመስለንም ቀላል ምክርና ማስጠንቀቂያ አይደለም ፡፡ መንፈሳዊ ሥፍራዎችን የሚያስከብራቸው የሚመሰገንባቸውና የሚወደስባቸው ፈጣሪ ነው ፡፡ በውስጡ ተጠልለው የሚኖሩ አገልጋዮች መልእክታቸውንና ጸሎታቸውን ደጋግመው ማሰማትና መወትወት ብቻ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ሌላውን ሥራ ራሱ ስለሚከውነው ተስፋ አንቆርጥም ፡፡ ለዚሁ ጉዳይ ሲሉ ለሚደክሙ ሁሉ እግዚአብሔር ይርዳቸው ፡፡

    ReplyDelete
  2. የእግዚአብሄር ስራ ድንቅ ነው የአባቶቻችን አምላክ እርሱ አያሳፍረንም ስለኛ ይዋጋል በዚህ በሱባዔ ጊዜ ገዳሞቻችንን በጸሎት እናስብ እናንተም ትጉ እ/ር ይባርካችሁ

    ReplyDelete