- “የቤተክርስቲያን መሪዎች መንግስት እንዳይነቀፍ ብለው ቤተክርስትያኒቱና ክርስትያኖች መብታቸው ሲነካ ዝም ብለው ካዩ የእግዚአብሔርን አደራ አልጠበቁም ፤ መንግስትንም ባለመምከራቸው ጎዱት እንጂ አልጠቀሙትም” አቡነ ጢሞቲዎስ
- “ከእግዚአብሔር የመጣው መዓት እግዚአብሔር መዓቱን እስኪመልሰው ድረስ ከመጸለይ በስተቀር ምንም ለማድረግ አይቻልም” አቡነ ጢሞቲዎስ
- “መንግስት ሃይማኖታችሁን ልንካ ካለ ግን ለሃይማኖታችሁ ፤ ለክብራችሁ ለመብታችሁ መሟገት እንዳለባችሁ እመክራችኋለሁ” አለቃ አያሌው ታምሩ
- “እውር ገደለ ታሰኝኛለህ እንጂ አንተን እዚህ እደፋ ነበር፡፡” ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ለአለቃ አያሌው ታምሩ የተናገረው
(አንድ አድርገን ነሐሴ 22 2004 ዓ.ም)፡-
ከዛሬ 12 ዓመት በፊት ህዳር 8 1992 ዓ.ም አቡነ ጢሞቲዎስ ከ”ምኒልክ መጽሄት” ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ
ዘወር ብለን ለናንተው ለማቅረብ ወደድን ፤ ይህ መጽሄት በጊዜው ለአቡነ ጢሞቲዎስ ያቀረበላቸው ጥያቄና እሳቸው
የሰጡት መልስ ጥቂቱን አሁን ካለንበት ሁኔታ ጋር ምን እንደሚመስል ለማየት እንሞክራለን ፤ በጊዜው አቡነ ጢሞቲዎስ የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሃላፊ ሆነው ያስተዳድሩ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመርቀው የሚወጡ አንዳንድ ወጣቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተክርስቲያንን በመክዳት ወደ ሌላ ኃይማኖቶች ሲለወጡ ይስተዋላል፡፡ ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ ኃይማኖታቸውን
ለመለወጥ የሚገደዱበት ምክንያት ምንድነው? በትምህርት አሰጣጡ ላይ እምነታቸውን የሚያስለውጡ ትምህርቶች ይሰጣሉ
ወይ?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡- አሉባልታ
ይመስለኛል አስተማሪዎቹ በጣም የታወቁ የኦርቶዶክስ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ትምህርቱም የተጣራ ነው፡፡ ነገሩ ያለው
ከስድስተኛው ጥያቄ ጋር ነው ፡፡ ይኽውም ተወራ እንጂ የካደ ልጅ ካለ ባውቀው ደስ ባለኝ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- በስልጣን
ላይ በተቀመጠ መንግስት በአደባባይ የሚሰራቸውን ስህተቶች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ከፓትርያርኳና
ከጳጳሶቿ የነቀፈችበትና የእርምት እርምጃ የወሰደችበት ጊዜ የለም ይባላል፡፡ በዚህ መሰረትነ በአሁኑ ወቅት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክነት የሚገኙት አቡነ ጳውሎስና ሌሎቻችሁም ጳጳሶች ቀደም ብለው ከነበሩት
ጳጳሶች የተለየ ነገር አልሰራችሁም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎን አስተያየት ቢያካፍሉን?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡ በስልጣን
ላይ ያለው መንግስት የሚሰራቸውን ስህተቶች ምን ዓይነት መሆናቸው ባይገለጹም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክና በጳጳሶቿ የነቀፈችበትና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቀችበት ጊዜ የለም የሚባለው
ትክክል ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በስተቀር ማንም ፓትርያርክና ጳጳስ መንግስትን አጥፍተሀል
ተመለስ ያለ አልነበረም፡፡ አሁንም የለም፡፡ ምክንያቱም የቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በሩ ሲታጠር ማንም የተነፈሰ
አልነበረም፡፡ አሁንም የቤተክርስቲያኒቱ መብት
በተለየ ቦታ ጊዜ ሲደፈር ማንም የቤተክርስቲያን መሪ የተነፈሰ የለም፡፡ ይልቁንም መንግስት ለራሱ ጸጥታ ሲል
በእያንዳንዱ ቦታ ጣልቃ ሲገባ ይታያል፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ ዝምታ ለመንግስት የሚመች አይመስልም፡፡ እንዲያውም
የቤተክርስቲያኒቱን መብት ከተጠበቀ ጸጥታ ይሰፍና መንግስትም በሰላም ይገዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን
መሪዎች መንግስት እዳይነቀፍ ብለው ቤተክርስትያኒቱና ክርስትያኖች መብታቸው ሲነካ ዝም ብለው ካዩ የእግዚአብሔርን
አደራ አልጠበቁም ፤ መንግስትንም ባለመምከራቸው ጎዱት እንጂ አልጠቀሙትም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከነበሩት ጳጳሳት
የባሰ እንጂ የተለየ ሥራ አልሰራንም፡፡ ሥራችን ይመሰክራል፡፡
ጥያቄ ፡- የቤተክህነት
ቀዳሚ ተግባር መንፈሳዊ ስራ እንዲጎለብት ማድረግ ነው፡፡ ይሁንና በውስጡ በከፋ ሽኩቻዎች እየታመሰች ትገኛለች ፤
እንዲህ አይነት ውጥረት ውስጥ ያለ መንፈሳዊ ድርጅት አንዴት አድርጎ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይችላል? በዚህ
ላይ አስተያየት ቢሰጡን?
አቡነ ጢሞቲዎስ፡- እርግጥ
የቤተክህነት ቀዳሚ ተግባር መንፈሳዊ ስራ እንዲጎለብት ከዚያም በላይ የበጎ ምግባር አብነት መሆን ነበር፡፡ ይሁን
እንጂ ከእግዚአብሔር የመጣው መዓት እግዚአብሔር መዓቱን እስኪመልሰው ድረስ ከመጸለይ በስተቀር ምንም ለማድረግ
አይቻልም፡፡
------------------------------
ይህ
ቃለ መጠይቅ የተካሄደው ከ12 ዓመት በፊት ነው ፤ ቤተክርስቲያኒቱ መብቷን የሚያስጠብቁላት መርጣ እና ከብዙዎች
ለይታ የሾመቻቸው ሊቃነ ጳጳሳት መጀመሪያ ካልተናገሩ ማን ቀድሞ ጉዳቷን መናገር ይችላል? ይህን ያልንበት ምክንያት
አለን ፤ በደርግ ጊዜ የነበሩን የቤተክህነት ኃላፊዎች ከዘመኑ ጋር አብረው ሲዘምኑ ነበር ፤ በጊዜው “እግዚአብሔር
የለም” የሚለው ትምህርት በኢትዮጵያ የተነገረበት የደርግ ዘመን ነው ፤ ይህ የክህደት ትምህርት የተነገረው
በቤተመንግስትና በሕዝባውያን ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በቤተክህነትም ነበር ፤ ይህ ዘመን በቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል
አዳራሽ ውስጥ “በስመ ማርክስ ኤንግልስ ወሌሊን ብንል ምናለበት?” ተብሎ እስከ መነገር የተደረሰበት ከፍተኛ ክህደት
የተፈጸመበት ጊዜ ነበር ፤ ሰዎች ወደ ቤተክርስትያን በይፋ ሄደው መሳለም የፈሩበት ፤ ልጆቻቸውን ክርስትና
ማስነሳት ያፈሩበት ወቅት ነበር ፤ ማርክሲዝም በቤተክርስትያን አውደ ምህረት ላይ ተሰብከዋል ፤ ግን በጊዜው ይህን
ሁሉ ነገር ሲፈጸም እያዩ እየሰሙ ተናጋሪ አባቶች አልነበሩም ፤ የመንግስትን ጡንቻ በመመልከት የእግዚአብሔርን
ኃያልነት የረሱ ብዙዎች ነበሩ
በኢቲቪ
ላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እንደ ሌሎች የእምነት ተቋማት መጤ ናት ተብሎ ፊልም ሲሰራ ተመልክቶ መጤ
አለመሆኗን ከመልከ ጼዲቅ ጀምሮ ያለውን የክርስትና አመጣጥ እና የቤተክርስትያኒቱን ታሪክ መሰረት በማድረግ
ማስተባበያ መስጠት የነበረበት አካል መልስ ሲሰጥ አልተመለከትንም ፤ የዋልድባ
መነኮሳትን ችግር ችግሩ አድርጎ ቤተክህነቱ አሁንም ድረስ ዝም ብሏል ፤ አሁንም ግርፋቱ እስራቱና ስደቱ ቀጥሏል ፤
ማን ያውቃል ከቤተመንግስቱ ሲጨርስ ወደ ቤተክህነቱ እንደማይዞር ? ስለ ቤተክርስቲያን ተከራክረው ኖረው ተከራክረው
የሞቱት ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ አሁን ላሉ አባቶቻችን ጥሩ አርዓያ ይሆናሉ ብለን እናስባለን ፤ አለቃ አያሌው
በወታደራዊው መንግስት ዘመን በሕዝብ ላይ የተፈጸሙትን ዘግናኝ ግፎችና በቤተክርስትያንና በአጠቃላይ በሃይማኖት ላይ
የተቃጣውን የክህደት ትምህርት በጥብቅ በመቃወማቸው በተደጋጋሚ ወደ ደህንነት ቢሮ ቀርበዋል ፤ በርካታ ጊዜ ከደርግ
ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር ፊትም ቀርበው በተግሳጽ እንደታለፉ የህይወት ታሪካቸው ይናገራል ፡፡ አሁን
ላለነው ምዕመናንና በአገልግሎት ለተቀመጡ አባቶች ትምህርት ይሆነን ዘንድ በጊዜው አለቃ አያሌው ታምሩ ከወታደራዊ
መንግስት ጋር ምን ያህል እንደተጋፈጡ ለማየት እንሞክር ፡ -
ደርግ
ስልጣን ከያዘ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ አንድና ሁለት ዓመታት የጎጃም ህዝብ የደርግን ስልጣን አልቀበልም ብሎ
ክፉኛ የተቃውሞ ድምጽ አሰምቷል ፤ የደርግ መንግስት በሃይማኖት ላይ የነበረው አመለካከት ይልቁንም “እግዚአብሔር
የለም” የሚለውን ኮሚኒስታዊ ዐዋጅ ስላልወደደው የጎጃም ህዝብ በከፍተኛ ደረጃና በግንባር ቀደምነት የደርግን
መንግስት በመቃወም በተለያዩ መልኮች ቅሬታውን በተደጋጋሚ ይገልጥ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር
ደርግ ከጎጃም ክፍለ ሀገር አውራጃዎችና ወረዳዎች ተወላጅ የሆኑ ፤ የህዝቡን ስነ ልቦና የሚያውቁ ፤ በህዝቡ ዘንድ
ተቀባይነት ያላቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሰዎችን አሰባስቦ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ከተጠሩት ሰዎች መካከል አለቃ
አያሌው ታምሩ አንዱ ነበሩ፡፡ ትዕዛዙን የሰጡት ኮለኔል አጥናፉ አባተ ሲሆኑ መልዕክቱም የሚከተለው ነበር፡፡
“ወደ
ትውልድ ቄያችሁ ሄዳችሁ ህዝቡ አላማችንን እንዲረዳና እንዲተባበረን አስረዱልን፡፡ የእኛ አላማ የሰፊው ህዝብ
መብትና ፍላጎት የሚከበርበትን ስራ መስራት ነውና በእኛ እና በህዝቡ መካከል የሽምግልና አገልግሎት እንድትሰጡ
መርጠናችኋል” አለቃ አያሌውም ይህን መልዕክት ተቀብለው ለመሄድ የማይችሉ መሆናቸውን ይናገራሉ ፤ በወቅቱ ሰሚ ግን
አላገኙም ፤ የሽምግልና አገልግሎት ስጡን የሚለው ጥያቄ መሸፋፈኛ ልብስ እንጂ መልዕክቱ ጫና የተቀላቀለበት ትዕዛዝ
እንደሆነ ግልጽ ሆኖ ገብቷቸው ነበር፡፡ የደርግን የትዕዛዝ ጫና በደንብ ሲያጠኑት ደግሞ የተመረጡት ሽማግሌዎች
በህዝባቸው ላይ ያንዣበበውን አደጋ የሚያሳያቸው ስለነበረ መሞከር የሚችሉትን ለመሞከር ተመካክረው ወደ ቦታው
አመሩ፡፡
አለቃ አያሌው ወደ ተላኩበት የትውልድ አካባቢያቸው ደርሰው ምክር እንዲለግሱ ከተሰበሰበው ሕዝብ ያደረጉት ንግግር ይህን ይመስል ነበር “ የተወደዳችሁ
ወገኖቼ ! አገራችሁ ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር እናንተም ህዝበ እግዚአብሔር ናችሁ ፤ የራሳችሁ ወግ ፤ ባህል ፤
ሃይማኖት ፤ ሰብአዊ ክብር ለይታችሁ እንደምታውቁ አምናለሁ፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሕዝቡን ወግ ፤
ባህል ፤ ሃይማኖት ፤ ሰብአዊ ክብር ጠብቄ አስተዳድራለሁ ባይ ነው፡፡ ይህ ቃሉን ከጠበቀ መልካም ነው፡፡ ከናንተ
የሚያጋጨው ነገር ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን ያለው መንግስት መብታችሁን ፤ ክብራችሁን ፤ ሃይማኖታችሁን
ልንካ ካለ ግን ለሃይማኖታችሁ ፤ ለክብራችሁ ለመብታችሁ መሟገት እንዳለባችሁ እመክራችኋለሁ” የሚል ነበር፡፡
አለቃ
አያሌው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ በደርግ ጽሕፈት ቤት እንደሚፈለጉ ይነገራቸዋል ፤ ከቤተመንግስት በተላከ
መኪና ወደዚያው ተወሰዱ ፤ የደርግ ሊቀ መንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም እና ምክትላቸው አጥናፉ አባተ ክፉኛ ተቆጥተው
በአንድ ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው ጠበቋቸው ፤ ኮሎኔል መንግስቱ በሽጉጣቸው ሰደፍ ጠረጴዛ ይደበድቡ ነበር ፤ በመጀመሪያ
ኮሎኔል አጥናፉ ጥያቄ አቀረቡ “አገር እንዲያረጋጉ ቢላኩ እንዴት ህዝቡን በእኛ ላይ እንዲነሳ ቀስቅሰው ይመጣሉ ?”
ብለው ለአለቃ በብስጭት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
አለቃም “ እኔ በመጀመሪያ ለእናንተ መልእክት አልመጥንም አትላኩኝ ብዬ ነበር ፤ አይሆንም ሄደህ ህዝቡን መብት
አክብረን እንደምናስተዳድረው አስተማምነህ ንገርልን ፤ ከእኛ ይልቅ አንተን ተወላጁን ያምናሉ አላችሁኝ ፤ ሄጄም
የላካችሁኝን ተናገርኩ ፤ ሌላ ምን አጠፋሁ?” ብለው መለሱ፡፡ ኮለኔል አጥናፉ ሌላ ጥያቄ አልጨመሩም ፤ መንግስቱ ኃ/ማሪያም በተራው “እውር ገደለ ታሰኝኛለህ እንጂ አንተን እዚህ እደፋ ነበር” በማለት ባበጠው ልባቸው ደነፉ፡፡ አለቃም ከነመሪያቸው እንዲወጡ ተነግሯቸው ከቤተመንግስት ወደ ቤታቸው አመሩ ፡፡
ወንጌሉ እንዲህ ይላል “ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።” የማቴዎስ ወንጌል 10፤18 ይላል ፤ አሁን
እኛ እየፈራን ያለነው ስለ እርሱ ብለን ቤተክርስቲያንና ምዕመኑ ላይ የሚደርሰውን በደልና የመብት ረገጣ ስንጠይቅ
ወደ ነገስታት መወሰድንና መታሰርና ነው፡፡ አሁንም የዋልድባ ጉዳይ ሰዎቹ የሚማሩ አይደሉም የፈርኦን ልብ በደነደነ
ቁጥር የእግዚአብሔር መቅሰፍት እንደሚበረታ አልተገነዘቡም ፤
አቡነ ጴጥሮስ ለምን በ8 ጥይት ጨው በረንዳ አካባቢ እንደተገደሉ የምናውቀው ታሪክ አለ ፤ ለፋሽስት ሀገሬ አትገዛም በማለታቸው በጊዜው የነበረውን አገዛዝ በግልጽ በመቃወማቸው ስለ አንዲት ኃይማኖታቸው እና ስለ ኢትዮጵያ ሐገራቸው ብለው ሰማዕትነትን
ተቀብለዋል ፤ አቡነ ቴዎፍሎስም በደርግ ዘመነ መንግስት ያደረሰባቸው ነገር ለኛ እንደ ክርስቲያን ስለ እምነታችንና
ስለ ቤተክርስትያናችን መከራን ባለመፍራት ሰማዕትነትን ባለመሰቀቅ ለመቀበል ብርታት ሊሆነን ይገባል እንጂ ታሪኩን
አንስተን ከንፈር የምንመጥበት መሆን መቻል የለበትም ፡፡
አሁን
ከፊታችን ያለው 6ተኛ የፓትርያርክ ምርጫ መንገዱ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን እሙን ነው ፤ በዚህ ጊዜ ከመንግስት
የሚመጣን ጥያቄ ስለ ህዝበ ክርስትያን እና ስለወደፊት ቤተክርስቲያን ብለው አባቶች በጽንአት መቆም ይገባቸዋል ፤
ባለፉት አምስት ያህል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የበላይ ጠባቂ የፓትርያርክ ምርጫ በጊዜው ከነበሩ
መንግስታት ነጻ የሆነበት ጊዜ አልተመለከትንም ፤ አሁን ግን አባቶች ይህ ነገር እንዲሆን ክፍተት መስጠት ያለባቸው
አይመስለንም ፤ የመንግስትን ትዕዛዝ በግድ ካላደረጋችሁ የሚባል ቀጭን ትዕዛዝ ቢመጣ እንኳን ተቃውመው ምዕመኑን
እንዲቃወም በር መክፈት መቻል አለባቸው ፤ ያለበለዚያ የታሰበውና የሚመረጠው የተገላቢጦሽ እንዳይሆን ስጋት አለ፤
ቋሚ
ሲኖዶስ በፊት ከነበረው ቁጥር ጥንካሬውን ለማጉላት ተጨማሪ ሰባት አባቶችን መምረጥ መቻሉ መልካም ነው ፤
የፓትርያርክ ምርጫው ላይ የተለያዩ አካላት የራሳቸው ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል ቀድሞ መታወቅ መቻል አለበት ፤
የበፊት አስተዳደር ሰዎች አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን ምርጫው
ላይ እንቅፋት መሆናቸው የማይቀር ነው ፤ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሰዎች የአባቶችንም ስም ለማጥፋ ሊነሱ ይችላሉ ፤
ስለዚህ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ችግሮች ቀድመው ቢታዩ እና አካሄድ ቢቀመጥላቸው ችግሮች ቢከሰቱ እንኳን
ለመፍታት የሚቀል ይመስለናል ፤ ዋናው ነገር የባለፉት ዓመታት ተሞክሮ በዚህ ምርጫ ላይ መንግስት እጁን ይሰበስባል
ማለት አይቻልም ፤ አይደለም የቤተክርስትያኒቱ የበላይ አካል ይቅርና የአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አብያተክርስትያናት
አስተዳዳሪ ለመሆን ሰዎች ምን አይነት መንገድ እንደሚሄዱ ተመልክተናል ፤ ነገር ግን አሁን ያሉት ጳጳሳት በህገ ቤተክርስትያን ብቻ ለመጓዝ አቋም ካላቸው የሚመጣውን ተጽህኖ ለመሸከም ራሳቸውን ካዘጋጁ ምርጫው ጥሩ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ ፤ ከሁሉ በፊት ግን ባሳለፍነው የፕትርክና ዘመን ስደተኛው እና ዋናው እየተባለ ለመጠራት የበቃ
ሲኖዶስ ለመመልከት ችለናል ፤ ትልቁ ነገር ከዓመታት በፊት የተጀመረውን እርቀ ሰላም ተጠናቅቆ ምርጫው ቢካሄድ ጥሩ
የሚል ሀሳብ አለ ፤ አሁን የሚመረጡት አባት የሁሉን ይሉኝታ ያገኙ ዘንድ ምርጫውም ያለ ምንም እንከን ያለምንም
ተቃውሞ ይከናወን ዘንድ እርቀ ሰላሙ መቅደሙ ግድ ይመስለናል ፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ፈተናዎች ከውስጥም ሆነ
ከውጭ ሲመለከቷቸው የሚያልፉ የማይመስሉ ፈተናዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ፤ ነገር ግን የሚመጡ ፈተናዎችን ለነገይቱ
ቤተክርስትያን በማሰብ በጽናት መቆም ያስፈልጋል ፤ የተከፈለችውንም ቤተክርስትያን በህይወተ ስጋ ሳላችሁ ወደ አንድ
በመመለስ የተበላሸውን የቤተክርስትያኒቱን ታሪክ ትመልሱ ዘንድ ተስፋችን በናንተ መሆኑን እወቁ፡፡
የመንግስትን ጡንቻ ብንፈራ እንኳን በእግዚአብሔር መታመን ይገባናል ፤ ስለቤተክርስትያን ያለውን ነገር በግልጽ መቃወም ካቃተን ነገ ለልጆቻችን የምናስተላልፋት ቤተክርስቲያን ምን አይነት እንደምትሆን መገመት አያዳግትም ፤ አሁን ይች ቤተክርስትያን የምትፈልገው ቆራጥ
አባት ነው ፤ ችግሯን የሚናገርላት እንዳልተመቻት የሚያስተጋባላት ፤ ከመንግስት እና የባለስልጣኖች ጥላ የሚያላቃት
፤ ነገ ህልውናዋ በዛሬዎቹ መሪዎች እንደሚናድባት የሚናገሩ ፤ ፍርሃት ካባቸው ያልሆኑ አባቶች ያስፈልጓታል ፤
አሁን ያለውን የዋልድባ ገዳም አባቶች ስደት የሚናገር አባት ያስፈልጋታል ፤ ለምን ? ብሎ የሚጠይቅ አባት
ያስፈልጋታል ፤ ከወራት በፊት ዋልድባ ላይ ከመንግስት ጋር መክረውው የሄዱት የቤተክህነት ሰዎች ምን አይነት ሪፖርት ይዘው እንደመጡ ተመልክተናል ፤ መንግስት ሲጀምር የላካቸው እንዲህ ብሎ ነበር “ በዋልድባ ገዳም ሄዳችሁ መነኮሳቱንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ከሰበሰባችሁ በኋላ የሚሰራው
ፕሮጀክት ገዳሙ ላይ ምንም ተጽህኖ እንደማያሳድር የማሳመን ስራ ስሩ ፤ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ 50
ሺህ ለሚጠጉ የአካባቢው ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር አስረዱ ፤ በተጨማሪም የገዳሙ መነኮሳት ግድቡ ተገድቦ
ሲጠናቀቅ ዓሳ በማጥመድ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚፈጠርላቸው ንገሯቸው” በማለት ነበር ፤ በጊዜው በተደረገ ስብሰባ ላይ የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቦታው በመገኝት በጸሎት ፕሮግራሙን ከመክፈት እና ከመዝጋት ውጪ አንድም ነገር አለመተንፈሳቸው ይታወቃል ፤ ከዚህ ስብሰባ በኋላ መነኮሳቱ ምንም
ጥያቄ እንደሌላቸውና ይህ የፖለቲከኞች ስውር አጀንዳ መሆኑን የመንግሰት ድምጽ ሆነው የቤተክህነት ሰዎች
ከባለስልጣኖች ጋር ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተው ካሜራ ፊት አጨብጭበው ተመልሰዋል ፤ መነኮሳቱ እለት
እለት መከራው እየባሰባቸው መገፋቱ እያየለባቸው መጥቷል ፤ በዋልድባ በአሁኑ ሰዓት የፖሊስ ዱላ እና መታሰር አዲስ
ነገር አይደለም ፤
በወረዳው የጸጥታ ኀይሎ ች “ገዳሙን ለቃችሁ ውጡ ፤ ታጋይ ገድላችሁ እናንተ በሰላም አትኖሩም፤” እየተባሉ መደብደባቸውን የተናገሩት የዋልድባ አብረንታንት መነኮሳት÷ በተለይም ከነሐሴ 18 ቀን 2004 ዓ.ም በሚፈጸምባቸው ድብደባ በርካታ አባቶች መጎዳታቸውን፣ ከተሰደዱት 6 መነኮሳ መካከል አባ ገብረ ማሪያም ጎንዴ እና አባ ገብረ ጊዮርጊስ የተባሉ አባቶች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ (ደጀሰላም)
ይህን
ሁሉ የመከራ ገፈት የሚቀምሱት መነኮሳት በገዳሙ ውስጥ እያሉ ባሳለፍነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ቤተክርስትያኒቱ
ምንም አይነት ተቃውሞ በዋልድባ ገዳም ላይ እንደሌላት የሚያትት ጽሁፍ አስገብተው በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲወጣ
መደረጉ የግንቦት ወር ትውስታችን ነው፡፡ አሁን ይህን የመሰለው መሰሪ አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተጠራርጎ
ከቤተክህነቱ የሚወጣበት ጊዜ ይሆናል የሚል እምነት አለን ፡፡
አለቃ አያሌው በ1976
ዓ.ም ጥቁር አንበሳ አካባቢ የቆመውን ኃውልት በማስመልከት “የሀገሪቱ መሪዎች የሀውልት መታሰቢያ ለማቆም የሚያበቃ
አንድም የረባ ነገር ሳይሰሩ ምስላቸው ያለበትን ሀውልት ማቆማቸው ከናቡከደነጾር ስራ ጋር የሚመሳሰል ነው ፡
ምእመናን ለዚህ ሀውልት ሳይሆን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ብቻ ክብርን ስጡ” በማለት የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ሀውልት በግልጽ በአደባባይ ተቃውመው ትምህርት ለምዕመኑ ሰጥተዋል፡፡ አለቃ አያሌው የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ሀውልት በአደባባይ ተቃውመዋል ፤
መንግስት
በአደባባይ የሚሰራቸውን ስህተቶች ቤተክርስትያን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ መቻል አለባት ፤
በቤተክርስትያኒቱ የውስጥ አሰራር ላይ ጣልቃ እንዳይገባ በሩን ከመዝጋት እንስቶ በብጹአን አባቶች አማካኝነት በቃልም መናገር
ያስፈልጋል ፤ የሳለፍነው 20 ዓመት 40 ሆኖ እንዳይመጣ ቤተክርስትያኒቱ መናገር ባለባት ጊዜ መናገር መቻል
አለባት ብለን እናምናለን ፤ እንደ በፊቱ መንግስትን በመፍራት የሚደረግ ተግባር የወደፊቱን ጊዜ ከባለፈው ይልቅ
ስለሚያጨልመው መጠንቀቅ ግድ ይላል ፤
በስልጣን
ላይ የተቀመጠ መንግስት በአደባባይ የሚሰራቸውን ስህተቶች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እርምት እርምጃ
እንዲወስድ የምትጠይቅበት ጊዜ ሩቅ መሆን አይገባውም ፤ ዋልድባ ላይ የሚሰራው ስራ ትክክል አይደለም የገዳሙን
ህልውና ያናጋዋል ብላ ለገዥው መንግስት ጥያቄ ኦፊሻሊያዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ አለባት ፤ በየአድባራቱ በጥቅም
ፈላጊዎችና በመንግስት ባለስልጣናት አማካኝነት የሚደርሰውን አስተዳደራዊ በደል የተቃውሞ ድምጿን ማሰማት አለባት ፤
በተለያዩ አድባራት ያሉትን መሬት ነክ ጉዳዮች ከቤተክርስቲያኒቱ ላይ ለመንጠቅ እና ለሌላ አላማ ለማዋል የሚራወጡትን
ግለሰቦችና የመንግስት አካላትን ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ ፊት ለፊት መጋፈጥ አለባት ፤ እኒህን እና መሰል
ቤተክርስቲያን ወንጌልን ለትውልድ እንዳትሰብክ ምእመኑን በእግዚአብሔር ቃል እንዳታንጽ እንቅፋት የሆኑባትን መሰረታዊ
ችግሮች ለመቅረፍ ከችግሮቹ እና ችግር ፈጣሪዎቹ ጋር ፊት ለፊት በመቆም ተሟግታ የምትረታበት ጊዜን ማየት እኛን
ይናፍቀናል፡፡ እነዚህን ለማድረግ አሁን ላይ የሚከናወነው የፓትርያርክ ምርጫ ለወደፊት ረዥም ርቀት ለመጓዝ
የመጀመሪያና ወሳኝ መነሻ ይመስለናል፡፡
ጥንታዊቷንና
ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስትያን በነቢያት ትንቢት በሃዋርያት ትምህርት የታነጸች ፤ በደም
ከእርሱ የተመሰረተች አማናዊት ቤተክርስቲያን ናት ፤ ይህ እውነታ በቅዱሳን መጻህፍት ምስክርነት በታሪክ መነጽርነት
የተረጋገጠ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን በታሪክ እርከን የገጠማትን ፈተና በመንፈሳዊ ጥበብ በጾም በጸሎት ድል ነስታ በሰማዕታት ቅዱሳን አጽም ታጥራ የኖረች ወደፊትም የምትኖር ቤተክርስትያን ናት ፤ ስለዚህ መለኮታዊ አደራና ኃላፊነት ቤተክርስትያንን ለማገልገል ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁ ብጹአን ቅዱሳን አባቶቻችን የምንወዳትና የምንሳሳላት ቤተክርስትያናችን መለያ ምልክቷ ሰላም ፍቅር አንድነት ስለሆነ
ይህም ለዘመናት ከሷ ጋር አብሯት የነበረ ዓላማዋ ስለሆነ በትክክለኛ መንገድ ማይሄዱትን ፤ ለእድገቷ እና
ለእርምጃዋ እንቅፋት የሚሆኑትን ፤ ትውልድ ተሸጋጋሪነቷ ላይ ጥላ የጣሉትን የመንግሰትም ሆነ የግል አካላት
በመቃወመወ በግልጽ ከፊት ትቆሙላት ዘንድ ፤ ለችግሯ የመፍትሄ መነሻ ሃሰብ ትሆኑላት ዘንድ እናተን መርጣ ሹማችዋለች ፤ ሁሉም ነገር በስርአተ ቤተክርስትያ ይከናወን ዘንድ መልእክታችን ነው፡፡
ቸር ሰንብቱ
ሰላምአንድ አድርጎች እንደምን ከረማችሁ ስላቀረባችሁልን ቤተክርስቲያናችን አሁን ያለችበትንሁኔታና ወደፊትም ስለሚጠብቃት መልካምም ሆነ አስቸጋሪ ፈተና መዳሰሳችሁ በጣም አስፈላጊነው:: ምክንያቱም ያሁኑ የሽግግርወቅት የወደፊቱን ሁኔታ ሊያጣምመውም ሊያቃናውንም ይችላልና የምንጥለው መሰረት ወሳኝነት አለው ብየአምናለሁኝ ::ግን ያልገባኝ አንድነገር አለ በተደጋጋሚ ስለ6ኛው የቤተክርስቲያን መሪ ምርጫ ሲነገር (ሲጻፍ) አያለሁኝ ግልጽያልሆነልኝ ነገር ቢኖር አሜሪካ ያለሁት የቀድሞው ፓትያሪክ መመለስ የማችሉበት ሁኔታ ሳይረጋገጥ ስለምጫ ማውራት መቸኮል አይመስላችሁም ምክንያቱም ተገደው መንበራቸውን እንደለቀቁ ስለሚወራ አሁን ግን ለመመለስ የሚያግዳቸው ነገር ያለ አይመስለኝም ምንአልባት አሁንም የመንግስት ጣልቃገብነት ካልተጨመረበት በቀር ለዚህ ደግሞ ቅድመሁኔታውን ካሁኑ ማስተካክል የቁዋሚሲኖዶሱ እና የሁሉንም ምእመናን ድጋፍ የሚያስፈልግ ይመስለኛል ባይሆን አንድስጋት አለኝ አቡነ መርቆሪወስ የሚመለሱበት ሁኔታ ከተስተካከለ የሚቀጥለው ጥያቄ የሚሆነው ባሜሪካ እያሉ የሾሙቸው ፓፓሳት ጉዳይ ነው ምክንያቱም ባብዛኛው ሰያዋቸው ዘመናዊነት የሚያጠቃቸውና ወደ ፕሮቴስታንት (ተሀድሶ)የገቡና በጉዞላይ ያሉ ናቸው:: እና እርሳቸው ከመጡ የሚታየኝ አደጋ እኒህን ፓፓሳትና ካህናት እንቀበላቸው ከተባለ ቤተክርስቲያናችን ላይ የሚመጣው ፈተና እንዲህ በቀላሉ የምንወጣውነው ብየ አላምንም :: ስለዚህ በዚህነገር ላይና ባዲሱ ምርጫላይ ግልጽየሆነ ውይይት ማድረግ ብንችል ሳይቃጠል በቅጠል ይሆናል ነገሩ ላማንኛውም ለነዚነገሮች መልስሊሰጠኝ (አስተያየት)የሚችል
ReplyDeleteካለ በደስታ እጠብቃለሁኝ በግሌግን አንድነገር አስባለሁኝ ዝምብለን ወደላይ ማመልከት እርሱ እራሱ የማያዳግም መልሰ ለቤተክርስቲያናችን እንዲሰጣት ማመልከት ብቻነው እላለሁኝ እስኪ ከኔየተሻላችሁ እውቀቱና ብስለቱ ያላችሁ ወገኖች ሀሰሳባችሁን ለግሱን::
ድንግልማርያም በምልጃዋ አትለየን አሜን!
Anid Adirgen Tebareku Hulgize Yemitakerbut Yeteshale neger new Awkalehu Deje Selam-Ahat Tewahedo Yerasachihu endehone Gin yeteshale Neger yemtasayun Bezihi lay New Beteley Yesewn Sim matsifat yelebetim Yastemral
ReplyDeleteAbune Merkorewos Bemelesu yishalal yemil Asteyayet Yemisetsu Alu Bezemenachew yeserutn Gifina Mekera Enawkalen Egiziabher Yelem Yemilewn Derg Barkew Yelekeku Poletkega -Kelela Hager Sew Yegonder Dingay Yishalal Yalu zerega -Bete kihinetun -lideta Lemaryamin -Kidist Silasen -Arada Giyorgisin Legonder Kahinat Yasirekebu -Letsornet Genzeb Siredu Yenoru -Dergi siwedik Lesgachew Adiltew Wede Gedam Sayihon Wede Ameica Yekobelelu-Kediga Besteker Moya Yelelachew -Rediete Egiziabher yeteleyachew Kifu Zerega Mehonachewn Zerzirachihu Giletsu Shimgilnaw Ydereg Gin Haymanot Yelelachew Alu Abune Meleke Tsedek yemtarekut keman gar new yenesun neger lemezegeb yemtiferut lemindinew ?Benesu Zemen Yeteserawn Bedel Ahun Masawk Neberebachihu -America Gebtew Yeserutin Tawkalachihu
Abune Pawlos Yeserut Melkam Sira Ale Yatsefut Degimo Bizu Neger Ale Hulunim Zerzirachihal Ahun Bemekabir Alu Yibekal Meneger Yalebet rasachewn Melkam Yeseru Asimesilew Tsornet ethiopia lay yasfelgal bilew lemiyawjut Abune Melkesedekina Abune Mekaryos Zecanada yetebalutin sewch Guday new
i agree!!!!
DeleteGirum new Egziabher yistachihu, engedih joro yalew yisma!!!
ReplyDeleteከብጹእ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በስተቀር ማንም ፓትርያርክና ጳጳስ መንግስትን አጥፍተሀል ተመለስ ያለ አልነበረም፡፡ አሁንም የለም፡፡ can you tell us this history it could be a good motivation. Thanks
ReplyDelete