Sunday, August 26, 2012

ድህረ አቡነ ጳውሎስ ሰዎች ምን ይላሉ?


  • “ስለ ሁሉም ግን መስማትና ማመዛዘን የሚችል አባት እንዲሰጠን ጸሎት ይዘናል” የተሀድሶ አቀንቃኝ ፊት አውራሪ 
  •  “ሞት ርስታችን ነው ፤ ጉዳዩ የቅደም ተከተል ነው ፤ የአቡነ ጳውሎስ ሞት ባያስደስተኝም  እግዚአብሔር ግን ይችን ቤተክርስትያን አሳረፋት” አንድ ሊቀ ጠበብት አባት

(አንድ አድርገን ነሐሴ 21 2004 ዓ.ም )፡- ባሳለፍነው ሳምንት በተከሰቱት ሁለት ትልልቅ ክስተቶች ላይ ሰዎች ትንሽ የመደናገጥ ስሜት ተፈጥሮባቸው ተስተውለዋል ፤ አንዱ ክስተት የአቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ነበር ፤ የፓትርያርኩ ሞት ከተሰማ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ወደ አዲስ አበባ ገብተው ነበር ፤ የፓትርያርኩን ስንብት ላይ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን 3 ሊቃነ ጳጳሳት ፤ 2 የግሪክ ኦርቶዶክስ  ሊቃነ ጳጳሳት ፤ በተጨማሪ በአሜሪካ ኒውስተን ዩኒቨርሲቲ 4 ተወካዮችን ጨምሮ የግብጽ ኮፕት ቤተክርስትያን 10 ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ከህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን 5 አባላት ያሉት ቡድን ፤ የአለም አብያተ ክርስትያናት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ኦላቭ እና 3 ሊቀ ጳጳሳት ፤ የአፍሪካ አብያተክርስትያናት ጸሀፊ  ዶ/ር አንድሪ ካራቫጋ እንዲሁም የዓለም ሀይማኖት ለሰላም 4 ሊቀጳጳሳት የአቡነ ጳውሎስ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመታደም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  ተገኝተዋል፡፡


በቤተክህነት አካባቢ አንድ የ”ሰንደቅ ጋዜጣ” ዘጋቢ ቤተክህነት አካባቢ ያየውን ነገር ፤ ያነጋገራቸውን ጥቂት አባቶች እና የተሀድሶ አቀንቃኝ ሰዎችን ስለ ወቅቱ ሁኔታ እና ስለ ቀጣዩ ፓትርያርክ በማንሳት ትንሽ ጽሁፍ በጋዜጣው ላይ አውጥቶ ነበር ፤ እኛም ጽሁፉን ለናንተው ለማቅረብ ወደድን፡፡

ወትሮ ይኽን ጊዜ ለሹመትና ደጅ ጥናት የሚመላለሱ ፤ ገንዘብ ወይም ወሬ የሚያቀብሉና የሚያቀባብሉ በሥጋ ዘመዶች ደርቶ ይውል የነበረው ቤተክህነት በተለይ በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤት አካባቢ ጭር ብሏል፡፡  መነኮሳት ከሌላው ጊዜው ይልቅ ሰሞኑን ሁለትና ሶስት ከዚያም በላይ ሆነው በለሆሳስ ሲነጋገሩ ይታያል፡፡ ሲፈልጉ በልምጫቸው ሲሻቸው በግፍትሪያ አጠገባቸው ሰው እንዳይደርስ ይከላከሉ የነበሩት የቅዱስነታቸው አጃቢዎች አሁን ጥቁር ካፖርት ደርበው ወጪ ወራጁን በዝምታ ይቃኛሉ፡፡

በቅርቡ በቅዱስ ፓትርያርኩ በዓለ ሲመት በብዛት ታትመው የተሰራጩ ፖስተሮች ግቢ ውስጥ ባሉ ግድግዳዎችና በየቢሮ መግቢያ እና መውጫ ላይ ተለጥፈዋል፡፡ከሌሎች አገልጋዮች የሚለዩ የደብሩ ጸሀፊዎችና ሒሳብ ሹሞች ስለመጪው እድላቸው ዝግ እያሉ ያወራሉ ፤ ባሳለፍንው ሳምንት ግብዓተ መሬት የተፈጸመላቸው አቡነ ጳውሎስ አሁን ላይ ሆኖ እንዲህ ነው ማለት መልካም ባይሆንም ሰዎች ምን ምን እንደሚሉ ከተለያየ አቅጣጫ ለማስዳሰስ አሰብን፡፡  አስተያየት ለመስጠት ካነጋገርኳው ካህናት አስከ ብጹአን አባቶች ድረስ ያሉት የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ እንዳሉ ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ራሳቸውን የቅዱስ ፓትርያርኩ ደጋፊ በማድረግ በሌሎች አገልጋዮች ላይ ነገር ሲሰሩ የባጁና በአንዳች ጥቅም መጓደል ወይም ፍትሀዊ ያልሆነ አሰራርን በመቃወም በየጋዜጣው ዝግጅት ክፍል መረጃ ይሰጣሉ የተባሉ ቡድኖች ግራና ቀኝ ተፋጠዋል፡፡ መጪው ፕትርክና የእነእገሌ አካባቢ ነው ሊባል በማይቻልበት ሁኔታ ግምቶች ከወዲያ ወዲያ ይመላለሳሉ ፤ ሙት ወቃሽ ላለመሆን በመፍራት ቅዱስነታቸውን በማመስገን አስተያየት የሰጡኝ አንድ ቆሞስ ከሁሉም በላይ የስብከተ ወንጌል መስፋፋት የአቡነ ጳውሎስን ጥንካሬ ያሳያል ባይ ናቸው ፡፡ በጥቂት የገዳማትና አድባራት የመጽሀፍ መምህራን ብቻ  ተይዞ የነበረው የወንጌል ትምህርት አሁን ግን በመላው አዲስ አበባና በየክልሉ ጭምር በወጣት ሰባኪያን አማካኝነት ምዕመኑ ስለ እምነቱ መሰረታዊውን ትምህርት ያገኝው በዚሁ በቅዱስነታቸው ዘመነ ሲመት መሆኑን አጥብቀው ይናገራሉ፡፡

መልአከ ሰላም ፍሬው ዝና የተባሉ የሰአሊተ ምህረት ማርያም ቤተክርስትያን አገልጋይም “ለዚች ቤተክርስትያን አስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ጽናቱን ይስጠን” ሲሉ ስለ ቅዱስነታቸው ዋና ዋና ተግባራ ያትታሉ ፤ “እነዚህ በደርግ ዘመን ተወርሰው የነበሩ የቤተክርስትያኗ ቤቶች እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ፤ ከ50 በላይ ጳጳሳት ሹመው ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋታቸውን ፤ ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር ለሚገኙ ካህናት ፤ ዲያቆናት ልዩ ልዩ ሰራተኞች ከፍ ያለ የደመወዝ ጭማሪ የተደረገው በአቡነ ጳውሎስ አባታዊ አመራር ነው ፤ በዘመኑ ቋንቋ “ልማታዊ ፓትርያርክ” ነበሩ ብላቸው ይቀለኛል” በማለት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ 

 ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ፤  ስሜን ከማውጣት ታቀብ ያለኝ  የቅድስት ስላሴ ካቴድራል አንድ አገልጋይ  “አቡነ ጳውሎስ ተመስጋኝም ተኮናኝም የሆኑበት አንድ ነገር አለ” ይላል፡፡ በእርሱ አስተያየት የአቡነ ጳውሎስ ትልቁ ስህተታቸው  ወደ ውስጥ አለማየታቸው ነው፡፡ ፓትርያርኩ የብዙ ዓለም ቋንቋዎች ተናጋሪ በመሆናቸው ውጭ ውጭ ሲሉ ከውስጥ ግን አስተዳደራቸው በአስከፊ ሙስና መዘፈቁን እያወቁ አያውቁም ማለት እንደማይቻል ይናገራል፡፡

በድጓ ሊቅነታቸው የተመሰከረላቸውና የአንድ ደብር አስተዳዳሪ የሆኑ አንድ አባት ያለፈውን ሳይሆን መጪው ጊዜ  የቤተክርስትያኗ እድል የሚወሰንበት እንደሆነ ይናገራሉ ፤ ስለዚህ ምዕመኑ በጾም በጸሎትና በሱባኤ ስለ ደግ አባት መምጣት እግዚአብሔርን መለመን እንዳለበት ያምናሉ ፡፡ በቅኔ እና በሌሎች የቤተክርስትያኒቷ ከፍተኛ ትምህርት ረዥም ጊዜ ያሳለፉት  አንድ ሊቀ ጠበብት “ሞት ርስታችን ነው ፤ ጉዳዩ የቅደም ተከተል ነው ፤ የአቡነ ጳውሎስ ሞት ባያስደስተኝም  እግዚአብሔር ግን ይችን ቤተክርስትያን አሳረፋት” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እኝህ ሊቀ ጠበብት አስተያየት  ከሆነ “ሊቃውንተ ቤተክርስትያን አሁንም ስፍራ አላገኙም ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችና መምህራኑ ተበትነው ፤ ጥንታዊያን ገዳማትና አድባራት ተበዝብዘው የሰው ያለህ እያሉ ነው” በማለት በምሬት ይናገራሉ፡፡ “መላ ዘመናቸውን በቤተክርስትያን ትምህርትና በአገልግሎት የጨረሱት ሊቃውንት ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ጸሀፊዎችና ሂሳብ ሹሞች የሚተካከል ከቶውንም የሚነጻጸር ደመወዝ እንኳን የላቸውም” ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማስተማር ላይ ያሉ አንድ መምህር ደግሞ የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትምህርታዊ ብቃት አይጠራጠሩም ፤ “ከሳቸው በፊት ከነበሩት አራት ፓትርያርኮች በተለየ ሁኔታ ለመንፈሳዊ ኮሌጆችና ደቀመዛሙርቻቸው የሰጡት ቦታ ይህንኑ ይገልጥ ይመስለኛል” ይላሉ ፤ “የቅዱስነታቸው ትልቁ  ችግር የማስተዳደር ችግር ነው ፤ ቤተክርስትያኗ በዘመኗ አይታ የማታውቀው ገንዘብ ውስጥ ትገኛለች ፤ ነገር ግን ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ ሙያተኞች ባለመኖራቸው የቤተክርስትያኗ ሀብት በጥቂት ጎረምሶች እየባከነ ይገኛል” ሲሉ መስክረዋል፡፡

“ፓትርያርኩ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ ያደረጉት ጥረት ያስመሰግናቸዋል” ያሉት እኝህ መምህር ጥለውት የሄዱት ከቶውንም ደግሞ በልዩ ልዩ ጥቅም መሳሳብ ከፍተኛ ባለጠጋ የሆኑ ጸሀፊዎችና አስተዳዳሪዎች የቢዝነስ ኢምፓየር መኖር የቤተክርስትያኗ ቀጣይ ራስ ምታት ሆነው እንደሚቆዩ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ብርቱ በሆነ ሀዘን ውስጥ ያገኝኋቸው ከሰበታ ቤተ-ደናግል ማህበር ከመጡ በርካታ መነኮሳይት መካከል ከሁለቱ እንደተረዳሁት በቅዱስነታቸው ድንገተኛ ዕረፍት የተጎዳው ቤተ-ደናግሉና ማህበራቸው ነው፡፡ መነኮሳይቱ እንዳሉት ቅዱስነታቸው ባልተጠበቀ ጊዜ እንደሚጎበኟቸው ፤ ማህበሩ ከ300 በላይ እናትና አባታቸውን ያጡ ህጻናት እንደሚያስተዳድርና ለዚህ ደግሞ የቅርብ እገዛ ሲደረግ የቆየው በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደሆነ ተናግረዋል ፤ ለሀዘንተኛ ቆሎና ዳቤ ሲያቀርቡ የነበሩት እኝህ መነኮሳይት በለቅሶ ብዛት ድምጻቸው ሰልሎ ፤ አይናቸው ቀልቶ አሁንም አሁንም እንባቸውን ያረግፉታል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ ከተፈቀደላቸው ሰባክያን ወንጌል ውጪ ማንም ማስተማር አይችልም ፡፡ በተሀድሶ እንቅስቃሴያቸው በተጨባጭ መረጃ የተገኝባቸው ሰዎች ፤ ሲኖዶሱ “እኛ አናውቃቸውም” የተባሉ ወገኖችን ለማነጋገር ሞክሬአለሁ፡፡  “ማስተማር አትችሉም” ከተባሉትና ሰባኪያን የሚታወቅ አንድ አገልጋይ እንደ እርሱ አስተያየት የተሻለ እንደሚመጣ ተስፋ አለው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን በውጭ ሀገር ያሉ አባቶችና ሲኖዶሳቸው ወደ ሀገር መጥቶ እርቅ የሚወርድበትና የፕትርክናው ምርጫ ፍጹም ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ተመኝቷል፡፡

“የኛ ጉዳይ ቀላል ነው ፤ የጉልበት ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ እንደ አባቶቻችን ብሒል በልዩነቶቻችን ላይ ፊት ለፊት ብንነጋገር ይህው ልዩነት ይፈታል”  ባይ ነው፡፡ ሌላው በተሀድሶነት ከተፈረጁትና ከማህበራቱ የአንዱ አመራር  በመሆን የሚታወቀው ሰው “ስለ ሁሉም ግን መስማትና ማመዛዘን የሚችል አባት እንዲሰጠን ጸሎት ይዘናል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የአንድ አድርገን ሀሳብ
ከተሀድሶያውያን ጋር የሚያብር አባት ከአሁን በኋላ ይመጣል ብለን አንገምትም ፤ ተስፋም የለንም ፤ ከተሀድሶያውያን ጋር ተነጋግረን የምንስማማበት ነጥብ አይኖረንም ፤ ባይሆን በሰሩት ስራ ተፀፅተው ንስሃ ገብተው ይመለሱ ይሆን እንጂ ወደፊት አጀንዳ ይኖረናል ብለን አናስብም ፤ ይህ እንዳይሆን የአንድ ሰው አምባገነንነት ዳግም እንዳይከሰት ቅዱስ ሲኖዶስ እየሄደበት ያለው መንገድ ይበል የሚያስብል ነው ፤ ቅድሚያ አቃቢ መንበር መምረጡ እና ቋሚ ሲኖዶሱን የማጠናከር ስራ መስራቱ ደስ ያሰኛል ፤ ቀጣዩ ምርጫ መከናወን ያለበት ከእርቀ ሰላሙ በኋላ ቢሆን መልካም ነው ፤ ሀገር ውስጥ ያሉት ምዕመናን ፤ የደብር አስተዳዳሪዎችና በተለያየ የስልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ የቤተክርስትያኒቱ አገልጋዮች  በተጨማሪ ከሀገር ውጭ ያሉት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚቀበሏው አባት ለመምረጥ ያስችል ዘንድ እርቀ ሰላሙ ቢቀድም መልካም ነው ፤ በዘመናችን ሁለት የሆነችውን ቤተክርስትያን አንድ የምናደርግበት ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ ወደፊት የምናገኝ አይመስለንም ፤ ለሁሉም በጸሎት አምላክን መጠየቅ ይገባል እንላለን፡፡
       
ቸር ሰንብቱ

4 comments:

  1. 2 የግሪክ ኦርቶዶክስ ሊቃነ ጳጳሳት ተብሎ የተጻፈውን ነው ተዋህዶ ብለህ ያነበብከው ወይስ ሌላ ቦታ የተጻፈ አግኝተሃል ፡፡

    ReplyDelete
  2. አንድ አድርገኖች በጣም አርፍ ስራ ነው በርቱ..ከተሃድሶ ጋር መተባበር አይሰራም..keep on writing!!

    ReplyDelete
  3. Dear Andadrgen

    Where is the topics "" Kit Yataw Hazen"" Yet aderegachihut. It is true why u take it off from the site I have read it that is true. Your view is excellent.
    Keep it up a good work. May GOD bless u all Andadrgen.

    ReplyDelete
    Replies
    1. ጽሁፉ በኢትዮጵያ ለመነበብ የሚችል አይደለም ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማንኛውንም ዓይነት ኢንፎርሜሽን የማግኘት ነጻነት ስለሌለ ነው ፡፡ ይህም ማለት በእነሱ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል /ምን አለፋህ ሊታገዱ ምክንያት ይሆናል/፡፡ ባናሞግስም ፊት ለፊት መጋፋቱ የአገልግሎት ዕድሜን ያሳጥራልና ፣ እንደዛ ዓይነት ጽሁፍ ከመውጣቱ በፊት የሚያመጣው ውጤት ቢመዘን የሚል አመለካከት ለማጋራት ነው ፡፡ ከሌሎቹ ጐራ ሆነህ ከሆነ ይህን ጥያቄ የምታቀርበው ፣ እንዲጠፉ ትፈልጋለህ ማለት ነው ፡፡

      Delete