Monday, December 19, 2011

ልዩ ፍርድ ቤት!!( በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)


(By Gebregziabher Kide)ሰላሙና ፍቅሩ እንዲሁም ቸርነቱ መግለጽ ከምንችለው በላይ አብዝቶልን ስለ ቃሉ እንድንነጋገር የፈቀደልን ጌታ ስሙ ለዘላለም የተመሰገነ ይሁን!!አሜን፡፡ 

ዛሬ እግዚአብሔር እንደወደደ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ “ልዩ ፍርድቤት” ያስተምረናል፡፡ መስማትን እንሰማ ዘንድ አምላክ ይርዳን፡፡ 

የብዙዎቻችን ከንፈሮች ለሐሜት የተከፈቱ ናቸው፡፡የራሳችንን ግንድ ትተን ከሰዎች ጉድፍን ለማውጣት እንዳዳለን፡፡በወንድሞቻችንም ላይ እንፈርዳለን፡፡ተጠንቀቁ!! የፍርድ ዙፋን ያለው ከእርሱ ጋር ብቻ ነውና የወልድን ሥልጣን እናንተው አትያዙት፡፡ 

መፍረድ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያስ ምንም የማያስወቅስና በጣም ብዙ ጥቅም ያለው የፍርድ ችሎት አለላችሁ፡፡አጥብቃችሁ በሕሊናችሁ ላይ ለመፍረድ ተቀመጡ፡፡ከዚያም በደላችሁን ከፊታችሁ በመዝገብ አስቀምጡት፤ የነፍሳችሁም ወንጀል በሙሉ ፈትሹት፤ ተገቢውንም ፍርድ አስቀምጡና ነፍሳችሁን “ይህንና ያንን ያደረግሺው ለምንድነው” በሏት፡፡ከዚህ ፈቀቅ ብላ የሌሎችን ሰዎች ጉዳይ መፈለግ ከጀመረች “የተከሰስሽበት ጉዳይ የእነዚያ አይደለም፣ አንቺም የመጣሽው ስለነዚያ ሰዎች ለመሟገት አይደለም፡፡ስለምንድነው ክፋትን የሰራሽው? ስለምንስ ነው ያንንና ይህን ጥፋት ያጠፋሽው? የራስሽን ተናገሪ እንጂ ሌሎችን አትውቀሺ” በሏት፡፡ሁል ጊዜም ይህን አስጨናቂ ፈተናን እንድትመልስ አቻኩሏት፡፡ተሸማቅቃ ምንም የምትመልሰው ነገር ከሌላት አስፈላጊውን ቅጣት ወሱንባት፡፡ይህን ልዩ ፍርድቤት ሁል ጊዜ የምትቀመጡ ከሆነ የእሳት ሸሎቆው፣ መርዘኛው ትልና ሊመጣ ያለውን ስቃይ በአእምሮዋችሁ እንዲቀረፅ ያግዛችኋል፡፡


ሁልጊዜም “እሱ ወደ እኔ መጥቶብኝ ነው፤ እሱ ሸውዶኝ ነው፤ እሱ ፈትኖኝ ነው” እያለች ከዲያብሎስ ጐን እንድትሰለፍና ከእንግዲህም ወዲህ ሐፍረት የለሽ ንግግሮችን እንድትናገር አትፍቀዱላት፡፡ይልቁንም “አንቺ ፍቃደኛ ባትሆኚ ነው እንጂ እነዚህ ሁሉ ካንቺ ጋራ ምንም ጉዳይ የላቸውም” ብላችሁ ንገሯት፡፡ “እኔ እኮ ሥጋ ለባሽ ነኝ፣ የምኖረውም በምድር ነው” ካለቻችሁ “ይህ ሁሉ ሰበብና ምክንያት ነው፡፡ብዙዎች አንቺ የለበስሽውን ሥጋ ለብሰው በዚህች ምድር ኑረው ጸድቀዋል፡፡ አንቺ ራስሽ አንዳንድ ጊዜ መልካም ስታደርጊ ይኸን ሥጋ ይዘሽ ነው” በሏት፡፡ይህን ሁሉ ስትሏት በጣም ካመማት እጃችሁን አታንሱባት፡፡ምክንያቱም ስትቀጧት ከሞት ታድኗታላችሁ እንጂ አትገድሏትም፡፡ምክንያት ስታበዛባችሁም “እባብ አሳተኝ” ብላ ከተጠያቂነትና ከፍርድ ያላመለጠችውን የመጀመርያዋ ሴትን ንገሯት፡፡ 

የነፍሳችሁን ኃጢአት ስትመረምሩ ከአጠገባችሁ ማንም አይኑር፤ ማንምም አይረብሻችሁ፡፡ይልቁንም ዳኛ በፍርድ ወንበር ላይ እንደሚቀመጥ እናንተም በፍርድ ወንበር ፈንታ በምቹ ጊዜና ቦታ በጸጥታ ተቀመጡ፡፡እራት በልታችሁ ከተነሳችሁ በኋላና ወደ መኝታ ክፍላችሁ ስትሄዱ ይህን የፍርድ ወንበር ይዛችሁት ሂዱ፡፡ይህ ቦታና ጊዜ ከሁሉም በላይ ተስማሚ ነውና፡፡ነቢዩም ያዘዘን ይህንኑ ነው፡- “በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ የምታስቡት ይታወቃችሁ /መዝ.4፡4/፡፡” ይህን ዕለት ዕለት የምታደርጉ ከሆነ በዚያ በአስፈሪው የፍርድ ወንበር ያለፍርሐት ትቆማላችሁ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ የጠራ ነበረ፤ እንዲህ በማለትም ተናግሮአል “እኛ በራሳችን ብንፈርድ ኖሮ ባልተፈረደብም ነበር /1ቆሮ.11፡31/፡፡” 

እኛ ግን ተቃራኒውን እንጂ እንዲህ አላደረግንም፡፡ወደ መኝታ ክፍላችን ከገባን ጀምሮ የምናስበው በዚህ ዓለም ስላለው ጉዳያችን ነው፡፡አንዳንዶቻችንማ ቆሻሻ ሐሳባችንን፣ ለሌሎች አራጣን ስለማበደር እንዲሁም ስለ ዓለማዊ ምቾቶቻችን ብቻ ነው የምናሰላስለው፡፡ 

ድንግል የሆነች ሴት ልጅ ብትኖረን እንዴት በጥንቃቄ እንደምናያት እናውቀዋለን፡፡ከዚህች ልጃችን በላይ በጣም ውድ የሆነችውን ነፍሳችንን ግን በብዙ ክፉ ሐሳቦችን አስተኝተን እንድታመነዝርና እንድትረክስ እናደርጋታለን፡፡በቅናት፣ በቅንጦት፣ በለዛ ቢስ ስብስቦች፣ በቁጣና የትኛውም ወደ አእምሮአችን የመጣውን ቆሻሻ ሐሳብ በመውደድ በራችንን ክፍት በማድረግ ወደ ውስጥ እንዲገባ ጋብዘን ነፍሳችን በትርፍ ጊዜዋ ያረክሳት ዘንድ እንረዳዋለን፡፡ከሁሉም በላይ ውድ የሆነች ነፍሳችንን በብዙ ዘማውያን ስትጎዳና እስኪረኩ ድረስ ከሚረባረቡባት አመንዝራዎች ከማየት በላይስ ምን ነፍሰ በላ ተግባር አለ? ፈጽሞ አይኖርም፡፡ስለዚህም ነው የእንቅልፍ ሰዓታችን ሲደርስ ብቻ ከእሷ ተለይተው የሚሄዱት፡፡እንደውም አንዳንድ ጊዜ በሕልምም ሊቀጥል ይችላል፡፡ቀን ሲመጣም እንዚህ ምናቦች ነፍስ እውን ወደ ማድረግ ትሸጋገራለች፡፡ 

የአቧራ ቅንጣት ወደ ዐይን ብሌናችሁ ስትገባ ትንሽ እንኳን መታገስ እያቃታችሁ የታላላቅ ኃጢአት ክምር በነፍሳችሁ ሲከማች ሳታስተውሉት ታልፋላችሁን? ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር የሚተኛው ይህን ቆሻሻስ የምናጸዳው መቼ ይሆን? እሾኩን የምንቆርጠው መቼ ይሆን? እስኪ ንገሩኝ!! የሚያደክመው መጥፎ ምግባር ነው ወይስ መልካም ምግባር? እሺ! ሁለቱምስ ያድክሙ ብያንስ ጥቅም ያለውን ድካም እንኳን አትመርጡምን? እንደውም እኮ አንዳንድ መልካም ምግባራት ምንም ልፋት የለባቸውም፡፡እስኪ አለማማትን፣ አለመዋሸትን፣ አለመማልን፣ አለመቆጣትን ምን ዓይነት ልፋት እንዳላቸው ንገሩኝ? አድካሚው ለጭንቀትም የሚዳርገንስ የእነዚህን ተቃራኒ ስናደርግ ነው፡፡ 

እነዚህ ቀላል ነገሮች እንኳን የማንፈጽም እኛ የሚደረግልን ይቅርታ ምን ዓይነት ይሆን? ራሰችንን ከስንፍናና ከግዴለሽነት ስናርቅ አድካሚ ተግባራት ሁሉ ከእኛ ስለሚርቁ ይህ ሁሉ ቀላል ነው፡፡

በቸርነቱና ሰውን እንዲሁ በሚያፈቅረው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ ዓለምና በሚመጣው ዓለም መልካሙን እንወርስ ዘንድ ራሳችንን በልዩ ፍርድ ቤታችን እየተቀመጥን ከክፉ ሁሉ እንራቅ፤ መልካሙንም እንያዝ፡፡ክብርና አለቅነት ለእርሱ ይሁንለት ለአላለሙ አሜን!!! 

(ምንጭ፡John Chrysostom Homily on the Gospel of St. Mathew)

4 comments:

  1. የአቧራ ቅንጣት ወደ ዐይን ብሌናችሁ ስትገባ ትንሽ እንኳን መታገስ እያቃታችሁ የታላላቅ ኃጢአት ክምር በነፍሳችሁ ሲከማች ሳታስተውሉት ታልፋላችሁን?

    ReplyDelete
  2. ርብቃ ከጀርመንDecember 19, 2011 at 4:52 AM

    ቃለሂወትያሰማልን በጣሙን እኔን የሚመለከት ሆኖአግኝቸዋለሁና እራሴን በልዩ ፍርድቤት እንድመረምርና እንዳስቀምጥ የድንግል ማርያምልጅ ይርዳኝ አሜን!

    ReplyDelete
  3. እስከ ዛሬ ድረስ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተለይ ደግሞ "በተሃድሶ" ዙርያ ጥሩ ነገር ዘግባችሃል::
    ግን ግን አይብዛ የሰው ስም ደግሞ አትጥሩ ትኩርታችሁ ጽንጸ ሀሳቡ ላይ መሆን አለበት::
    በርቱ በርቱ.......

    ReplyDelete
  4. So touching preach from the Holy Father. God help me to judge myself not others!

    ReplyDelete