- ዓላማው ግብረ ሰዶማዊነትን በአፍሪካ ማስፋፋት ነው
- መንግሥት ስብሰባው በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ አልተከላከለም
ስብሰባው በተመድ የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ አዘጋጁ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡ ቀደም ሲል ስብሰባው እንደሚካሄድበት የተነገረው ጁፒተር ዓለምአቀፍ ሆቴል በበኩሉ፤ የተጠቀሰው ስብሰባ ፈጽሞ በሆቴሉ ውስጥ እንደማይከናወን አስታውቋል፡፡
ምንጮቻችን እንዳረጋገጡት፣ መቀመጫቸውን በ13 አፍሪካ አገሮች ያደረጉ 15 ግብረ ሰዶማዊነትን እንደ በጎ ምግባር የሚያንጸባርቁ ድርጅቶች ያዋቀሩት በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ አምሸር/AMSHeR(The African Men for Sexual Health and Rights) ተብሎ የሚጠራ የጋራ ድርጅት፤ ከጥቅምት መግቢያ ጀምሮ ከ25 አገራት የተውጣጡ በአይካሳ ስብሰባ የሚሳተፉ ግብረ ሰዶማውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እና ከስብሰባው አስቀድሞ ለሚደረግ የቅድመ ዝግጅት ስብሰባ የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽና ማረፊያ ቦታ በኢሜል ሲያፈላልግ መቆየቱ ታውቋል፡፡ ፍላጎቱ እንዳሰበው ያልተሳካለት ድርጅቱ፤ ወኪሎቹን አዲስ አበባ በመላክ ማረፊያ ቦታ አፈላልጎ እንግዶቹን ማሳረፉን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
“Claim,Scale-up and sustain”(የራስ ማድረግ፣ ማሳደግ እና ቀጣይነት) በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ25 አገራት የተውጣጡ 200 ግብረ ሰዶማውያን የሚሳተፉበት ስብሰባ ዓላማም፤ “ግብረ ሰዶማዊነት ሕጋዊ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ አፍሪካዊ ምላሽና ነጸብራቅ ማሳየት፤ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ ግብረ ሰዶማዊነትን ሕጋዊ ማድረግ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በመለየት ለተግባራዊነቱ አቅጣጫን መቀየስ፣ በአፍሪካ የወንድ ለወንድ ግብረ ሰዶማዊ ግንኙነቶችን - MSM and HIV(Men who have sex with Men) እውን የማስደረግ ጉዳይ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ ትኩረት እንዲያገኝ ማስቻል” መሆኑን አምሸር የተባለው ድርጅት በድረ ገጹ ላይ አስፍሮታል፡፡
በድረ ገጹ የሰፈረው ጹሑፍ አያይዞም፣ “ስብሰባው ለግብረ ሰዶማውያኑ አዲስ ትብብር ለመፍጠር እና ለማቀናጀት፣ ልምድን ለማዳበር፣ ምርጥ ተመክሮዎችን ለማስፋፋት እና ለሚቀጥለው ትውልድ ይህንኑ ዘይቤ ለማስተላለፍ ለየት ያለ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመንበታል” ይላል፡፡
በውይይቱ ላይ የ(ICASA)ን ተወካይ ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት የኤች.አይ.ቪ ዋና ዳይሬክተር ሚሼል ሲዲቤ፣የግሎባል ፈንድ ፀረ የኤች አይቪ፣ቲቢ፣ የአባለዘር በሽታዎችና ወባ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ደብረወርቅ ዘውዴ፤ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ አስተባባሪ አምባሳደር ኤሪክ ጎስቢ ፣የተከበሩ ሬኔ አላፒኒ ጋንሱ የቀድሞ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ሊቀመንበርና የወቅቱ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖችና ይበልጥ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ መብት አስከባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር የዕለቱ ተጋባዥ ተናጋሪዎች እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡
ስብሰባው የሚካሄደው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል መሆኑ በአምሸር ድረ ገጽ ላይ ከወጣ በኋላ በርካቶች ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን ጉዳዩን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የሆቴሉ ም/ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ያየህይራድ ለአዲስ አድማስ ሁኔታውን እንዲህ አስረድተዋል፤‹‹ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ከአገር ውስጥም ሆነ ከተለያዩ ዓለማት ለሚመጡ ደንበኞች ዓለም አቀፍ የሆቴል አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ነው ፡፡በዚህም የተነሳ በተለያዩ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚመጡ እንግዶችን በሚገባ ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡ በቀጣይም በሚገባ ለማስተናገድ ጥረት እያደረግን ነው ፡፡ እንደ አሠራር የሆቴላችንን አዳራሾች ለስብሰባ ስንጠየቅ የምናረጋግጠው ስለ ድርጅቱ ሕጋዊነቱን እንጂ ስለ ስብሰባው አጀንዳ አይደለም፡፡የተባለውን ድርጅት በሚመለከት እኛ ምን እንደሚሠራ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ አምሸር የተባለ ድርጅት ተቀማጭነቱ ደቡብ አፍሪካ መሆኑን - በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ በሚደረግ ኮንፍረንስ ላይ የሚሳተፉ አባላት እንዳሉት፣ ይህንንም በሚመለከት ስልጠናን ጨምሮ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንደሚያደርግና ቦሌ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ከኅዳር 20 እስከ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ከ40 እስከ 45 ሰው የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ ከምሳና ከሻይ ቡና ጋር እንዲሁም ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም ደግሞ ለ200 ሰው የስብሰባ አዳራሽ ከምሳና ሻይ ቡና ጋር እንድንይዝላቸው በኢሜል ጠየቁን፡፡በስልክም አነጋገሩን፡፡እኛም 200 ሰው በአንዴ የሚይዝ አዳራሽ ስለሌለን በአጋጣሚም በተጠቀሰው ጊዜ በሙሉ በሌሎች ተሰብሳቢዎች የተያዘ በመሆኑ ቦታ እንደሌለን ጠቅሰን ይቅርታ ጠይቀን መልስ ጻፍንላቸው፡፡በኋላ ላይ ግን ስብሰባው በጁፒተር ሆቴል ይካሄዳል የሚል ነገር ሁላችሁም እንደሰማችሁት እኛም ሰማን፤በመጀመሪያ እንዲህ ያለ ስብሰባ በእኛ ሆቴል እንደማይካሄድ ስንገልጽ ቆይተን በኋላ የድርጅቱን ስም ከተላከልን ኢሜል ጋራ ስናስተያየው አንድ ሆነ ፣ድርጅቱም ስብሰባውን በእኛ ሆቴል እንደሚያካሂድ በድረ ገጹ ላይ እንደጠቀሰ ጥቆማ ስለደረሰን የተባለው ስብሰባ በእኛ ሆቴል እንደማይካሄድ እየታወቀ ስማችን መገለጹ አግባብ ያለመሆኑን ጠቅሰን ስማችንን ከድረ ገጹ ላይ እንዲያነሱ አሳሰብናቸው፡፡እነሱም አንስተው ስብሰባው በተመድ የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ አስፍረዋል፡፡››በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አያይዘውም፤‹‹በዕለቱ ሌላ ስብሰባ እንጂ የተጠቀሰው ስብሰባ ፈጽሞ አይካሄድም፤ይህን ማረጋገጥ የፈለገ ሰው በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት ወደ ሆቴሎቻችን መጥቶ ማየት ይችላል፤››ብለዋል፡፡
ቦታ ቢኖራችሁ ኖሮ ታከራዩአቸው ነበር ወይ? በሚል የተጠየቁት አቶ ያየህይራድ፤ ‹‹በአገር ደረጃም ይሕ ነገር በኢትዮጵያ ሕግ የተከለከለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ቦታ ቢኖረን ኖረና ሳናውቅ አዳራሻችንን አከራይተን ቢሆን ኖሮ እንኳን ጉዳዩን እንዳወቅነው መሰረዛችን አይቀርም ነበር፡፡ ነገር ግን ቀድሞውኑ ቦታ ባለመኖሩ ምክንያት ለእነሱ ያከራየነው አዳራሽ የለም፡፡››ብለዋል፡፡
‹‹የግብረ ሰዶማውያን የህይወት ዘይቤዎች በሳይንሳዊ ምርምር ለትውልድ ጠር፤ለአገር ዕድገትም እንቅፋት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ግብረ ሰዶማዊነትን እንዴት ማስፋፋት ይቻላል? የሚል ስብሰባ እኛ አገር ላይ መደረጉ በጣም አደጋ ነው›› የሚሉት በስነተዋልዶ ጤና አተኩሮ ትምህርት የሚሰጠው “ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ድርጅት ዳይሬክተር እና የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ስዩም አንቶኒዮስ ናቸው፡፡
አምሸር የተባለው ድርጅት ስብሰባው የሚካሄደው በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሆነ በድረገጹ ካስነበበ በኋላ የሆቴሉ ኃላፊዎች ስብሰባው በሆቴሉ እንደማይካሄድ እንደገለጹላቸው ያረጋገጡት ዶ/ር ስዩም፤‹‹ግብረ ሰዶማዊነትን በሚመለከት የሚደረግ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው ይታወቃል፡፡ስብሰባው በቀጥታ የግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ ነው ቢሏቸው የሆቴሉ ባለቤቶች ፈቃደኛ እንደማይሆኑላቸው እና ቦታ አለን እንደማይሏቸው እገምታለሁ››ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤትን ጨምሮ የበርካታ አብያተ እምነት መሪዎችን በአባልነት የያዘው “የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባኤ”፤ የግብረ ሰዶማያኑን ስብሰባ በመቃወም ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ረቡዕ ዕለት ሊሰጠው ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም መግለጫው በሚሰጥበት ቦታ በድንገት ከተገኙ በኋላ መሰረዙ፣ጋዜጠኞች መግለጫው በሚሰጥበት ሥፍራ ተገኝተው ያነሷቸው ፎቶ ግራፎች በሥፍራው በነበረ አንድ የደኅንነት አባል እንዲጠፋ መደረጉ፣የት እንደሆነ ባይታወቅም ወደ 40 የሚጠጉ ግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ እንደሚያደርጉ እየታወቀ እንዲወያዩ መፈቀዱ፣ እንዲሁም አዘጋጁ ድርጅት በድረ ገጹ እንዳሰፈረው በዛሬው ዕለት የሚደረገው 200ዎቹ የሚሳተፉበት ስብሰባ አዲስ አበባ በሚገኘው የተመድ የስብሰባ ማዕከል (ECA) እንዲካሄድ መደረጉ፣የአይካሳን ተወካይ ጨምሮ አምስት ታዋቂ ሰዎች መሳተፋቸው መገለጹ፣ መንግሥት ይህ ስብሰባ እንዲካሄድ መፍቀዱን ወይም አለመከልከሉን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከኅዳር 24 እስከ 28 ቀን 2004 ዓ.ም የሚካሄደውን “16ኛውን ዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የአባላዘር በሽታዎች ጉባኤ በአፍሪካ” (ICASA) ማስተናገዷ የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ መድረክ ለመገንባት እና እያንዳንዱ ተሳታፊ በጉባኤው ላይ ለመታደም ይችል ዘንድ ለምዝገባ ከከፈለው በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር ጀምሮ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አኳያ ከፍተኛ ሽር ጉድ እየተደረገበት ቢሆንም ከልምድ በሚታወቀው የዚህ ዐይነቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎች ግብራዊ ጠባይዕ ላይ ጥንቃቄ አለማድረጉ ከሚያስከትለው “የባህል መበረዝ/ወረርሽኝ ጠንቅ” አንጻር ክፉኛ አስተችቶታል፡፡
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ መሰረት ግብረ ሰዶም ወንጀል ሲሆን መንግሥት ይህ ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ በመፍቀዱም ራሱ ያወጣውን ሕግ ራሱ ለመጣሱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል-አስተያየት ሰጪዎች፡፡
የአይካሳ የኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ሲሳይ ስለጉዳዩ በስልክ ተጠይቀው፣ የተጠቀሰው ስብሰባ ከአይካሳ ስብሰባ ጋር ግንኙነት ስለሌለው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጽ ለተጨማሪ ጥያቄና መልስ ‹‹ስልኩ አይሰማም›› በሚል ምክንያት ስልኩን ዘግተዋል፡፡ሌላ የስልክ ቁጥር በመቀየር በተደረገ ጥረት ተገኝተው፤በኢትዮጵያ ሕግ ክልክል የሆነው ግብረ ሰዶም በአይካሳ ስብሰባ ስም ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ አግባብ ነው ወይ? በሚል ለተጠየቁት ‹‹ግለሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በአይካሳ ስም ስለመሆኑ መረጃ ስታመጡ እንነጋገራለን››ሲሉ በቁጣ መልሰዋል፡፡
ድርጅቱ በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ ግን ስብሰባው የቅድመ አይካሳ ኮንፍረንስ ማነቃቂያ መሆኑንና በግብረ ሰዶማውያኑ ስብሰባ ላይ የአይካሳ ተወካይ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
ከአዲስ አድማስ የተገኝ
አሁንስ የት እንድረስ ልጆቻችንን የት እናሳድግ ብለው ብለው ደግሞ ይሄን አመጡብን መንግስት ቢያስብበት ጥሩ ነው ይህ ነው ዘርማጥፋት ወንወጀል ስንቱን እንታገል ኑሮውን ወይስ ደግሞ ስሙን አልጠራውም ስሙ ይጠፋ የዚችን ሀገር ከነህዝቡዋ አምላክ የጠብቅልን ሰዎች እናልቅስና አምላክን እንለምን እሱ አያሳፍረንም ፈጥሮናልል እና በስራአቱ አለሙን ሲፈጥር እኮ እንደ አልማዝና እንቁ ውብ ያድገው እሱ ነውና ከስርአት ውጭ መሆን ደግሞ ሞት የሞት ሞት አለበት ሀገርም ይጠፋል ‹‹ጌታ ሆይ ከሐይለኞችና ጨካኞች ተጽእኖ ጠብቀን መሪዎቻችንን መልካሙን ነገር አመልክታቸው አሜን››
ReplyDelete