Thursday, December 22, 2011

አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ! (በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!! አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 347 እስከ 407 .. የነበረና 398 እስከ 404.. የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ሆኖ ያገለገለ ታላቅ የቤተክርስቲያን አባት ነው፡፡ ይህ አባት ከሚያስተምረው የትምህርቱ ጣዕም የተነሣ አፈወርቅ፣ ጥዑመ ልሳን ተብሏል፡፡ በእርግጥም በትምህርቱ ሁሉንም መማረክ የሚችል፤ ለማንም የማያዳላ ይልቁንም ለድሆች ጠበቃ የሚሆንላቸው ፍትሕ አባት ነው፡፡ ትምህርቶቹም ዘመን ተሻጋሪና ክርስቲያናዊ ሕይወቱን መመዘን ለሚፈቅድ ሰው የማያዳሉ ሚዛኖች ናቸው፡፡ እስኪ ዛሬም በዚያ አንደበቱ ይናገረን፤ እኛም እንደ ሊድያ ልቦናችንን ከፍተን እንስማው፤ ከዚያም ራሳችንን እንመርምር፡፡


ወንድሞቼ ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ውድ ስጦታዎችን ይዛችሁ ስትመጡ አያለሁ፡፡ መልካም አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ስትመለሱ ደግሞ መበለቶችን፣ ደሀ አደጎችንና ሕጻናትን ስትበድሉ አያችኋለሁ፡፡ ታድያ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ምሥዋዕና ጽዋዕ ብታቅረቡ ምን ይጠቅማችኋል? ለምንስ መሥዋዕቱን ማክበር ስትፈልጉ አስቀድማችሁ ልባችሁን መባ አድርጋችሁ አታቀርቡም? ልባችሁ በጭቃ ተጨማልቆ ምሥዋዑ እንኳን ወርቅ ፕላቲንየምስ ቢሆን ምን ይረባችኋል? ምንስ ይጠቅማችኋል?

ተወዳጆች ሆይ! አመጣጣችን በወርቅ የተለበጠ መሠዊያ ለማቅረብ ሳይሆን ይኸን ከልብ በመነጨ ለማቅረብ ይሁን፡፡ ከልባችን የምናቀርበው ነገር ሁሉ ከወርቅ የበለጠ መባ ነው፡፡ ልብ በሉ! ቤተ ክርስቲያን የወርቅ ወይም የነሐስ ማቅለጫ ቦታ አይደለችም፤ ለቅድስና የተጠሩ ሁሉ እና የመላእክት ኅብረት እንጂ፡፡ ስለዚህ ከስጦታችሁ በፊት ልባችሁን ይዛችሁ ኑ፡፡ እግዚአብሔር እኮ ሥጦታችንን የሚቀበለው ደሀ ሆኖ ሳይሆን ስለ ነፍሳችን ብሎ ነው፡፡ ክርስቶስን ማክበር ትወዳላችሁን? እንግዲያስ ዕራቆቱን ስታዩት ችላ አትበሉት፡፡ እናንተ ወደ ቤተ መቅደስ ስትመጡ እጅግ ውድ በሆኑ ልብሶች አጊጣችሁ ስትመጡ እርሱ በብርድና በመራቆት ሊሞት ነውና ብያንስ ትንሽ እንኳን እዘኑለት፡፡ ቤተ መቅደስ ረግጣችሁ ቤተ መቅደስ አትምጡ፡፡ በቃሉ ይህ ሥጋዬ ነው ያለው ጌታ በተመሳሳይ ቃሉ ተርቤ ስታዩኝ አላበላችሁኝም፤ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ይለናል /ማቴ.254245/፡፡ በእውነት ይህ ምሥዋዕ ልብሳችሁን ሳይሆን ልባችሁን ነው የሚፈልገው፤ እነዚህ የተራቡት ግን ልብስም ምግብም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ክርስቶስ እርሱ እንደሚወደው ማክበርን እንማር፡፡ እከብር አይል ክቡር የሆነው እርሱ ደስ የሚያሰኘው ክብር እኛ ውድ ነው ብለን የምናቀርበው ሳይሆን እርሱ ሊቀበለው የወደደውን ስናቀርብለት ነው፡፡

ጴጥሮስ ጌታን ያከበረ መስሎት እግሩን መታጠብ እምቢ አለ፤ ይህ ግን በጌታ ዐይን ማክበር ሳይሆን ተቃራኒው ነበር፡፡ ስለዚህ ጌታን ማክበር ስትፈልጉ ገንዘባችሁን አስቀድማችሁ በድሆች ላይ አውሉት፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚፈልገው ወርቃማ ምሥዋዕን ሳይሆን ወርቃማ ነፍሳትን ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምላችሁ ግን መባ እንዳትሰጡ እየከለከልኳችሁ አይደለም፤ ይልቁንም ከዚሁ ጐን ለጐን እንደውም አስቀድማችሁ መመጽወትን እንድትለማመዱ ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለምሥዋዑ ያመጣችሁትን መባ ይቀበላል፤ ለድሆች የምትሰጡትን ደግሞ ከዚሁ በበለጠ ይቀበላችኋል፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ብታመጡ ተጠቃሚዎች እናንተ ብቻ ናችሁ፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ድሀውም እናንተም ትጠቀማላችሁ፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ስትሰጡ ውዳሴ ከንቱ ሊያመጣባችሁ ይችላል፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ርኅራኄንና ሰው ወዳድነትን ያመጣላችኋል፡፡ ጌታ ተርቦ ሳለ ምሥዋዑ በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ምን ጥቅም አለው? ከሁሉም በፊት ጌታ ተርቦ ስታገኙት አብሉትና ከዚያም ምሥዋዑን አስጊጡት፡፡ ነገር ግን እርሱ አንድ ኩባያ ውኃ እንኳን ሳያገኝ እናንተ ጽዋውን የወርቅ ጽዋ ታደርጉታላችሁን? እርሱ ገላውን የሚሸፍንባት ቁራጭ ጨርቅ እንኳን አጥቶ እናንተ ምሥዋዑን በወርቅ ልብስ ታስጌጡታላችሁን? ከዚሁ የምታገኙት መልካም ነገርስ ምንድነው? እስኪ ንገሩኝ! እርሱ የሚበላውን ዳቦ አጥቶ እናንተም ረሀቡን ሳታስታግሱለት ወደ ቤተ መቅደሱ መጥታችሁ ምሥዋዑን በብር ስታስጌጡት የሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን? ንገሩኝ እንጂ? የማይቆጣችሁስ ይመስላችኋልን? እንደገና አንድ ሰው ቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ብርድ ሲያቆራምደው እየተመለከታችሁ ምንም ልብስ ሳትሰጡት በቤተመቅደስ መጥታችሁ ይህ ሥጦታ ለጌታዬ ክብር ነው ብላችሁ ምሥዋዑን በወርቅ ብታስጌጡት ጌታ፡- “ፌዘኞች!ብሎ እንደሰደባችሁት የማይቈጥረው ይመስላችኋልን?

እርሱ መጠለያ ፈልጐ እንግዳና መንገደኛ ሆኖ ሲዞር እናንተ ግን ባለ ብዙ ክፍል ቤት እያላችሁ ችላ ብላችሁታል፡፡ ቤታችሁ በተለያዩ የመብራት ዓይነት አጊጦ ሳለ ክርስቶስ ግን በእስር ቤት ነው፤ ልታዩት እንኳን አልወደዳችሁም፡፡ ወንድማችሁ በጣም ተቸግሮ እያያችሁት እናንተ ግን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለማስጌጥ ትሮጣላችሁ፤ ነገር ግን አማናዊው ቤተ መቅደስ ከሕንጻው የበለጠ ወንድማችሁ ነበር፡፡ ወንድሞቼ! ልንገራችሁና እናንተም አድምጡኝ! ለሕንጻው ቤተ መቅደስ የምታመጧቸው ጌጣጌጦች አንድ ኢአማኒ ንጉሥ፣ ወይም ጨካኝ መሪ፣ ወይም ሌባ ሊዘርፋቸው ይችላል፡፡ ወንድማችሁ ሲራብ፣ እንግዳ ሆኖ ሲመጣ እና ሲታረዝ የምታደርጉለትን ማንኛውም ነገር ግን እንኳንስ ጨካኝ መሪ፣ እንኳንስ ጨካኝ ሌባ የጨካኞች አባት የሆነው ዲያብሎስም መውሰድ ይቅርና ሊያይባችሁም አይችልም፡፡ ገንዘባችሁ ሁሉ በአስተማማኝ ቦታ ይከማቻል፡፡ ምጽዋት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ትከፍታለች፡፡ ጸሎትህ እና ምጽዋትህ ለመታሰብያ እንዲሆን ዐረገ እንዲል /ሐዋ.104/፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ሁሉ የበለጠች መሥዋዕት ናት፡፡ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማውቅ እወዳለሁእንዲል /ሆሴ.66/፡፡ ምጽዋት ኃጢአትን ታነጻለች፡፡የሚወደድ ነገርስ ለምጽዋት ስጡ፤ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋልእንዲል /ሉቃ.1141/፡፡ እንግዲያስ አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግና የሚመጣውን ዓለም እንድንወርስ ሰውን በማፍቀር ሰው የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!


8 comments:

  1. "ወንድሞቼ ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ውድ ስጦታዎችን ይዛችሁ ስትመጡ አያለሁ፡፡ መልካም አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ስትመለሱ ደግሞ መበለቶችን፣ ደሀ አደጎችንና ሕጻናትን ስትበድሉ አያችኋለሁ፡፡ ታድያ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ምሥዋዕና ጽዋዕ ብታቅረቡ ምን ይጠቅማችኋል? ለምንስ መሥዋዕቱን ማክበር ስትፈልጉ አስቀድማችሁ ልባችሁን መባ አድርጋችሁ አታቀርቡም? ልባችሁ በጭቃ ተጨማልቆ ምሥዋዑ እንኳን ወርቅ ፕላቲንየምስ ቢሆን ምን ይረባችኋል? ምንስ ይጠቅማችኋል?" ቃለ ሕይወት ያሰማልን::

    ReplyDelete
  2. kalehiwot yasemalin

    ReplyDelete
  3. What I learned from this is that the most important of all is LOVE. If we love each other we can't do those we are not allowed to do like killing but we do what we are expected to do like feed the hungry, provide shelter and clothing for those who are in need, etc.
    So LOVE is the key word here. Thank you and God Bless you.

    ReplyDelete
  4. BETAM ASTEMARI NEW AMLAK ABIZITO YIBARIKLIN!!!

    ReplyDelete
  5. ቃለ ህይወት ያሰማልን !

    ReplyDelete
  6. አሜን የህይወትን ቃል ያስማልን

    ReplyDelete
  7. አሜን የህይወትን ቃል ያስማልን

    ReplyDelete