(አንድ አድርገን ሚያዚያ 4 2004 ዓ.ም)፡- የልጅነት እድሜ ስማቸው
ናዚር ጋይድ ሩፋኤል ፤ የጉልምስና እድሜ የሶሪያ አባ አንቶኒዮስ በኋላም ጵጵስናን ሲቀቡ ሺኖዳ ሳልሳዊ ተባሉ፡፡ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሺኖዳ
ሳልሳዊ የልጅነት የጉልምስናና የእርጅና ዘመናቸው ያለ ድካም አገልግለው በ88 ዓመታቸው ጉልበታቸው ደክሞ ፤ ጤናቸው ታውኮ ህልፈታቸው
ሆነ፡፡ በህልፈታቸው የአሌክሳንድርያ ኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ብቻ አይደለም ያዘነው ፤ የግብጽም ህዝብ ብቻ አይደለም
ያዘነው ፤ የክርስትያን እምነት ተከታይ ብቻ አይደለም ያዘነው በአቡኑ ሞት ዓለም ሁሉ አዝኗል፡፡ ጌታችን በወንጌል ‹‹በኋላዬ ሊመጣ
የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።›› የማርቆስ ወንጌል 8፥34 እንዳለ ይህን ቃል መሰረት በማድረግ ህይወት ዘመናቸውን በታማኝነት መስቀሉን ተሸክመው ተከትለዋል ፤ ‹‹ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን
ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥›› 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፤ 7-8 በማለት እኛን ልጆቻቸውን ከተለዩን ሳምንታት
ተቆጥረዋል ፤ በህይወት ዘመናቸው ሳሉ ያለፉበትን መንገድ ለእኛ አሁን ላለንበት ጊዜ ትምህርት ከሆነን ብዬ በማሰብ ዞር ብየ ለመቃኝት
ወደድኩኝ፡፡ ቤተክርስትያናቸው ፈተናዋን እንደ አባትነት ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት መወጣት እንደቻሉ ከእኛ ጋር በጥቂቱ በማቆራኝት
ፅፌአለሁ፡፡
ናዚር ጋይድ ሩፋኤል በላዕላይ ግብጽ በምትገኝው አስዩት እ.ኤ.አ በ1923
ነሀሴ 3 ቀን ነው የተወለዱት የቤተሰባቸው ስምንተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነበሩ፡፡ እናታቸውን በልጅነታቸው በሞት የተነጠቁት ናዚር ከልጅነት ዕድሜአቸው አንስቶ ከቤተክርስትያን ጋር
የጠበቀ ትስስር አላቸው፡፡ ‹‹በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ።›› ወደ ዕብራውያን3፤18 በሰንበት
ትምህርት ቤት ንቁ ተሳታፊ ከመሆን ባሻገር በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በታሪክ ትምህርት መስክም ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን
አጠናቀው ከወጡ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዘኛና የማህበራዊ ጥናት ትምህርት አይነቶች አስተምረዋል፡፡
መጽሀፉ ‹‹ በወጣትነትህ ዘመን እግዚአብሔርን አስብ›› እንዳለ ናዚር
ጋይድ ሩፋኤል መምህር ሆነው እያገለገሉ በኮፕት ስነ መለኮት ትምህርት
ቤት የማታ የትምህርት ጊዜ የጀመሩትን የስነ መለኮት ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ 1949 አጠናቀው የሀዲስ ኪዳን ጥናት አስተማሪ ለመሆን
በቅተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የህይወት መስመራቸው አቅጣጫውን ቀይሯል፡፡
እ.ኤ.አ
በ1954 ዓ.ም በወርሀ ሐምሌ ወደ ሶርያ ያመሩት ወጣቱ
ናዙር ህይወታቸውን በገዳም ለማሳለፍ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በሶርያ ገዳምም አባ አንቶንዮስ የሚለው ስማቸው ለማግኝት በቅተዋል፡፡
ሶርያ ውስጥ በነበራቸው የሰባት ዓመት የገዳም ቆይታ በጸሎት ፤ በትምህርት መቅሰምና ትምህርት በመስጠት የነበራቸው አገልግሎት ከፍተኛ
ነበር ፡፡ በኋላም ላይ በገዳም ቆይታዎች ባበረከቱት አገልግሎትና በቀሰሙት ትምህርት ቤተክርስትያንን አና ህዝበ ክርስትያኑን በእውነት
ለማገልገል ቅስና ተቀብለዋል፡፡
አባ አንቶንዮስ በቀሰሙት ትምህርት በሶርያ ቅስናን ከተቀበሉ በኋላ በግብፅ
ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እ.ኤ.አ 1959 ጵጵስናን የተቀበሉት ጳጳስ ሲሪል
ስድስተኛ ለአባ አንቶንዮስ አቡነ ሺኖዳ የሚለውን ስም ሰጥተው የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ሥነ መለኮት ሴሚናር ዲን ሆነው እንዲያገለግሉ
ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፡፡ በአቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እንዲመራ የተደረገው የስነ መለኮት ትምህርት ቤት በርካታ መሻሻሎችን ማሳየት ችሎ
ነበር፡፡ እርሳቸው ቦታውን ከያዙት በኋላ የሚቀበላቸው የተማሪዎች ቁጥርም በሶስት እጥፍ አሳድጓል፡፡
አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ በትምህርት ቤቱ ለውጥ ቢያመጡም አንዳንድ ጫናዎች
ነበሩባቸው፡፡ ይህም ጫና በኋላ ላይ ከስራ እንዲታገዱ አድርጓቸው ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች እና
አቡኑ ያላቸው ጠንካራ ወዳጅነት አቡኑም ሆኑ ተማሪዎቻቸው አንድ አይነት አቋም እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡ በሁለቱ የሀይማኖት መሪዎች
አማካኝነት የተቀሰቀሰው ጠብ በሰከነ መንፈስ በተካሄደው ውይይት ሊፈታ
ችሏል፡፡ ይህ ነገር ለእኛም ትምህርት ሊሆነን ይገባል በአባቶች መካከል ምንም አይነት ጠብ በመካከላቸው ቢፈጠር ሌላ ሶስተኛ ወገን
ሳይገባ በፈሪሀ እግዚአብሔር ተነጋግረው ተማምነው ችግሮቻቸውን መፍታት መቻል አለባቸው ፤ በአቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ እና በተማሪዎቹ ሲነሱ የነበሩ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ
አግኝተዋል፡፡ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ የአሌክሳንድሪያ 117ኛ ርዕስ ሊቃነ ጳጳስ ሆነው በተሾሙበት እ.ኤ.አ 1971 ዓ.ም የ48 ዓመት
ጎልማሳ ነበሩ ፡፡ በጊዜውም ሁሉም ምዕመን በታላቅ ደስታ ነበር የተቀበሉት ፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት መጋቢት
17 ቀን 2012 ድረስ በታማኝነት በመልካም እረኝነት የተሰጣቸውን መክሊት በመጠበቅ ምዕመኑን አገልግለዋ፡፡
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሲሪል ስድስተኛ በሞት ከተለዩ ከ9ወር በኋላ የተደረገ
የቅዱስ ሲኖዶስ ምርጫ አማካኝነት ‹‹ ሺኖዳ ሳልሳዊ የተሰኙት አቡኑ ከቀኖና ውጪ የተቀቡ ናቸው›› በሚል በአንዳንድ
ወገኖች በኩል ትችት ሲዘነዘርባቸው ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን 40 ዓመት መርተዋል፡፡
አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ለሀገራቸው ግብጽ ያላቸው ፍቅር እጅግ የተለየ ነው፡፡
‹‹ግብጽ በውስጣችን የምትኖር እንጂ የምንኖርባት አይደለችም›› በሚለው የዘወትር አባባላቸው ይታወቃሉ፡፡ ቅስና ከመቀበላቸው በፊትም
ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኝነት አሳይተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በነበራቸው የስራ ሀላፊነት ተጠቅመው በግብጽ ሙስሊሞች
እና ክርስትያኖች መካከል ጠንካራ ወዳጅነት እንዲፈጠር ማድረግ በመቻላቸው በሁሉ ወገን በፍቅር የሚወደዱ ሰው ለመሆን የበቁ ነበሩ
፡፡ ሙስሊሞች የሚያዘጋጇቸው ጉባኤዎች ላይ በክብር እንግድነት በመገኝት ከቁርአን እየጠቀሱ ንግግር ያደረጉበት ወቅትም ነበር፡፡
በመጽሀፈ ምሳሌ 13፤15 ‹‹መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል ›› ይላል ለአባታችን አቡነ ሺኖዳም እውቀታቸው ሞገሳቸውም ጭምር ነበር
ያላቸው የቁርአን እውቀት ላቅ ያለ በመሆኑም ከሙስሊም ወዳጆቻቸው ጋር
ተገናኝተው በሚጨዋወቱበት ወቅት ቁርአን ጥቅስ እየጠቀሱ ወጋቸውን ማሳመራቸውና በሰው ልጆቸች መካከል ያለውን የሀይማኖት ልዩነት
ለመከባበር እንቅፋት እንደማይሆን ማመናቸው በሁሉም ወገን ተወዳጅ እንዲሆኑ መንገዱን ጠርጎላችዋል፡፡ የአቡነ ሺኖዳ ከሙስሊሞች ጋር
የጠበቀ ወዳጅነት መፍጠር በክርስትያን ወገኖች ላይ ሲደርስ የነበረው በርካታ አደጋ ማስቀልበስ ችለዋል፡፡ ዘወትር ረቡዕ የሚያስተላልፉት
ትምህርት ህዝቡ ሰላማዊ እንዲሆንና ለሚደርስበት በደል ብቀላን እንዳያስቡ ይሰብኩ ነበር፡፡በአቡነ ሺኖዳ ዘንድ ብቀላ ዋጋ የለውም፡፡
‹‹ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤
በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።›› ወደ ሮሜ ሰዎች 12 ፤19 በማለት ክርስትያኖቹ የሚደርስባቸውን በደል መሰረት አድርገው አጸፋወን በበቀል እንዳይነሱ አበክረው ያስተምሩ ነበር፡፡
አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ እስር ቤተ ቀምሰዋል ፡፡ ከሀላፊነት ተነስተው ለስደት
ተዳርገዋል፡፡ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር ያደረጉት
የካምና ዴቪድ ስምምነትና በአገሪቱ እያደገ የመጣው እስላማዊ አክራሪነትን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ ችላ ማለታቸውን አቡነ ሺኖዳ አንዋር
ሳዳት ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ለበርካታ ጊዜያት በተደጋጋሚ እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጓ፡፡ በኋላም
በንትሪያን በርሃ ውስጥ ወደሚገኝ ገዳም ተሰደዋል፡፡በገዳምም ለ3 ዓመት ያህል እንዲቆዩ ተደርጓል ፤ እርሳቸው ግን ወደ ገዳም በግዞት
ሲወስዳቸው ደስ እያላቸው ነበር ወደ ገዳም ያመሩት ፤ ‹‹ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ
መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥
ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።›› 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች10፤13 ‹‹ይህም
ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን
ደግሞ እንመካለን፤›› ወደ ሮሜ ሰዎች 5፤3 የሚለውን የመጽሀፍ ቅዱስ ቃልን መሰረት በማድረግ የገጠማቸውን ፈተና ከቁብ ሳይቆጥሩት
አብዝተው ሲጾሙ ሲጸልዩ እንደነበር ከእረፍታቸው በኋላ የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ ፤ ‹‹ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ
እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤›› ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 11፤29 ተብሎ እንደተጻፈ አቡነ ሺኖዳ
ስለ ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ብለው በርካታ መከራ ሊቀበሉ ችለዋል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።›› መዝሙረ ዳዊት
34፤15 በገዳም ሳሉ ግዞት የላካቸው አንዋር ሳዳት ከተቃዋሚዎች ዘንድ በተጠመደ ቦንብ መሞቱ ተሰማ፡፡ ከአቡነ ሺኖዳ ጋር መስማማት ያልቻለው
ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት ግድያ እንደተፈጸመባቸው በእግራቸው ተተክተው ሀገሪቱን መምራት የቻሉት ፕሬዝዳንት ሁስኒ ሙባረክ አቡነ
ሺኖዳ ሣልሳዊ ከስደት እንዲመለሱ በመወሰናቸው ዳግም ወደ ቅዱስ ማርቆስ መንበር ተመልሰው መቀመጥ ችለዋል፡፡ ይህ የመጀመሪያ መንግስት
ውድቀት ነው፡፡
የቀድሞ የግብጽ ፕሬዝዳንት ዘመነ ስልጣን አቆጥቁጦ የነበረውና የእስልምና
አክራሪነት ውስጥ ውስጡን ስር ሰዶ በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣናቸው
በወረዱት ፕሬዝዳንት ሁስኒ ሙባረክ ዘመነ ስልጣን አስደንጋጭ ጭፍጨፋ ደርሰ ፡፡ በእለተ ሰንበት የፈረንጆች ሚሊኒየም በገባ በሁለተኛው
ቀን የኮፕቲክ ክርስትያኖች መንደር በሆነችው ኮሽን በሳላፊስቶች አማካኝነት ዘግኛኝ ጭፍጨፋ ተካሄደ ፤ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት ክርስትያናቹ
የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶሰን ልደት በዓል አክብረው ከቤተክርስትያናቸው እንደወጡ ቀድሞ በተጠመደ ቦምብ ከ30 በላይ
የንጹሀን ክርስትያኖች ደም በአውራ ጎዳና ላይ ፈሰሰ፡፡
ክርስትና እና ኮፒቶች
በግብጽ ሀገር የሚገኙ ክርስትያኖች ከሙስሊሞች ፈተና ሲያጋጥማቸው ሁሉም
ክርስትያን ወደ ችግር ወደ ተፈጠረበት ቦታ በነቂስ ነው የሚወጡት ፤ አባቶቻቸው ችግራቸውን ቤታቸው ቁጭ ብለው በቁጭት ማሳለፍን አላስለመዷቸውም ፤አሁን በእኛ እጅ ያለው ዋልድባ ገዳም የግብጾች ቢሆን ኖሮ
አንድም ክርስትያን ቤቱ አታገኙትም ነበር ፤ ሁሉም በቦታው ላይ ሰፍረው ታገኟችዋላችሁ ፤ ብዙዎቹ ፈተናቸው በመኖሪያ አካባቢ ፤
በትምህርት ቤት ፤ በመስሪያ ቦታ እና በተለያዩ ቦታዎች ስለሆነ በመዳፋቸው ላይ የመስቀል ምልክት ተነቅሰው ይታያሉ በሀይማኖታቸው
ማንኛውም በገር ቢያደርሱባቸው መጀመሪያ የተነቀሱትን መስቀል ነው የሚያሳዩት ይህ ማለት ‹‹ እኔ ክርስትያን ነኝ በሀይማኖቴ ከመጣ ምንም አልፈራም ››
ለማለት ነው፡፡
ከደረሰው አደጋ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 89 ሰዎች
በቁጥጥር ስር ቢውሉም ኋላ ኋላ ያለዋስትና መለቀቃቸው አቡነ ሺኖዳ ከሁስኒ ሙባረክ አስተዳደር ጋር ግጭት ውስጥ ከተታቸው፡፡ በአደባባይም
‹‹ አሁን ያለው ስርዓት ታግለን ፍትህ ማስፈን ይኖርብናል›› ብለው በመግለጽ በክርስትያኖች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ ፍትህ ለማግኝት
ወደ ፍርድ ቤት ዳግም ላለመሄድ መወሰናቸውን ተናገሩ፡፡ በወቅቱም
ፍርድ ከፈጣሪ እንጂ ከሰዎች እንዳልሆነ ገልጸው አሳሰቡ ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ፍትህን ፍለጋ የመንግስት ሀላፊዎችን የፍትህ መስሪያ
ቤቱን ቢሮ ማንኳኳት አልፈለጉም ፤ ‹‹ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና››ኦሪት ዘዳግም 1፤17 በማለት ውስጣቸው በደረሰው አደጋ ክፉኛ
አዝኖ ቀጥታ ከአምላካቸው መልስ ለማምጣት ፤ ወደ ገዳም ለሱባኤ ገቡ፡፡ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።›
›የያዕቆብ መልእክት 5፤ 16 እንደሚለው ‹‹እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ…›› ሰቆቃው ኤርምያስ 3፤49-50 በማለት መልስ ከእግዚአብሔር እስኪሰጣቸው ድረስ
በገዳም ቆዩ ፤ መሀል ላይ አደጋው ከተፈጠረ ከቀናት በኋላ ከካይሮ ምድር አንድ ወሬ ተሰማ ፤ ህዝብ በመንግስት ላይ አመጸ ፤ ይህን
ቢሰሙም እርሳቸው ከሱባኤያቸው አልወጡም ነበር ፤ አቡነ ሺኖዳ ከገዳም የወጡት እግዚአብሔር እንዲህ ሲላቸው ነበር ‹‹ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥
እንባህንም አይቻለሁ›› ፡፡ትንቢተ ኢሳይያስ 38፤5 ክርስትያኖች ላይ ለደረሰው አደጋ ፍትህን ያጓደለባቸው 30 ዓመት ያህል ግብጽን
ያስተዳደራትን ፕሬዝዳንት ሁስኒ ሙባረክ ከስልጣኑ ገርስሼልሀለሁ ሲላቸው ነው፡፡ ‹‹የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥›› 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፤12
‹‹አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው።›› መዝሙረ ዳዊት
119፤137 እውነት ነው እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነው ፡፡ትንቢተ ኢሳይያስ 25፤8 ላይ ‹‹ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን
ያብሳል፥›› ይላል ፤ በአቡነ ሺኖዳ ጸሎት በምእመኑ ለቅሶ በግፍ የተገደሉት ከ30 በላይ ክርስትያኖችን እንባ አብሶላቸዋል፡፡ ይህን
ጥቅስ ሳስበው ከመከራቸው እና ከመልሳቸው ጋር ሳገናዝበው ለራሴ ገርሞኛል ‹‹እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ
ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ›› የዮሐንስ
ራእይ21፤4፡፡ ይህ ደግሞ የሁለተኛው መንግስት ውድቀት ነው፡፡
አሁን እኛም መጮህ ያለብን ወደ እግዚአብሔር ነው ፤ ስለ ዋልድባ ገዳም ከመንግስትም ሆነ ከቤተክህነቱ መልስ
ባናገኝም ደግመን ደጋግመን መጮህ ያለብን ወደ አምላካችን መሆን መቻል አለበት ፤ የግብጽ ክርስትያኖችን አቤት ብሎ ሲሰማቸው
እያየን ነው ፤ እኛም ስለ ፈተናችን ብንጸልይ መልካም ነው ፤ ‹‹ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ
ጸልዩ ።›› የሉቃስ ወንጌል 22፤46 ነው የሚለው ፤ ቁጭ ብለን መፍትሄ የማይሆኑ ሰዎችን መጠበቅ ጊዜን ያለ አግባብ
ማሳለፍ ነው፡፡ የመንግስት አቋም በማያሻማ መልኩ ግልጽ ነው ፤ የቤተክህነቱም እንደዛው ፤ እነርሱ በአንድ ቤተክርስትያን
አንድ ሚሊየን ብር በ18 አብያተክርስትያናት 18 ሚሊየን ብር ለመቀበል ተዘጋጅተው ከመንግስት ላለመጣላት ፈርተው የተቀመጡ
ናቸው ፤ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል ፤ አሁን መፍትሄ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው በርትተን ሁላችን
ብንጸልይ ከአምላከ ዘንድ መልስ ይኖራል ብለን እናስባለን ፡፡
|
||||||
አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ጋር
የነበራቸው ወዳጅነት ለዓመታት ሻክሮ የቆየ ነበር፡፡ ከቤተክርስትያኗ ጋር ያላቸው ወዳጅነት የከረረው የደርግ መንግስት መምጣትና
ተከትሎ ብዙ እንግልት ደርሶባቸው በኋላም ለሞት በበቁት የአቡነ ቴዎፍሎስ ጉዳይ ነበር፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ በደርግ አስተዳደር ዘብጥያ
መውረዳቸው ለሞት እንዳበቃቸው ያምኑ የነበሩት አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ የሞታቸው መንስኤ ካልተጣራ በስተቀር የሁለቱ ቤተክርስትያናት
ወዳጅነት ወደ ነበረበት እንደማይመለስ ያስረዱ ነበር፡፡ በጊዜው ብጹእ አባታችን አቡነ ቶዎፍሎስ በደርግ ሲገደሉ ከቤተክህነት ከአስር
የሚበልጡ ጳጳሳት ግድያውን እንደግፋለን ብለው መፈረማቸው የሚታወቅ ነው ፤ ይህ የሆነ ነገር እንጂ የፈጠራ ወሬ አይደለም ፤ አቡነ
ሺኖዳ እውነተኛ አባት ስለሆኑ ሀገር ተሻግረው ድርጊቱን ሲቃወሙ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት እዚህ ያሉ ጳጳሳት ደግሞ መሞታቸውን
እንደግፋለን ማለታቸው ለሰሚ ከባድ ነው ፤ በጊዜው ወታደራዊ መንግስቱ ለፕሮፖጋንዳ ማስፈጸሚያ ሲባል ደብዳቤውን እንዲጻፍ ቢያስገድድም
፤ ከቤተክህህነት ግን ይህ ደብዳቤ መውጣት አለበት ብለን አናስብም ፤ የኛ የልጆች ሀሳብ አሁንም መንግስትን ፈርታችሁ ዳግም ሌላ
ስህተት እንዳትሰሩ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ነው የምንለው ፡፡ መጽሀፍ ቅዱስ የሚለው ‹‹ ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን
በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ።›› የሉቃስ ወንጌል 12፤4 ነው፡፡ ደርግ በፈቃደኝነትም ይሁን በእጅ ጥምዘዛ ያን ደብዳቤ ማስፈረም ችሎ የታሪክ ጠባሳ ትቶልን አልፏል ፤
አሁን በእናንተም ጊዜ ፈቅዳችሁም ይሁን ተገዳችሁ ተገቢ ያልሆነ ምእመኑን
፤ ቤተክርስትያንንና ፤ የዋልድባ ገዳም አባቶች የሚያሳዝን ተግባር ብትፈጽሙ ነገ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ
፡፡ ይህ ምክር ችግሩ የታየንን እና የተገለጸልንን መጠን ለሚመለከተው አካል ሁሉ የተላለፈ ነው፡፡ ‹‹እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም ።›› የሀዋርያት
ሥራ 4፤20 እንዳለ እኛም ስለዋልድባ ገዳም ያየነውን የሰማነውን ከመጻፍ ወደ ኋላ አንልም፡፡
አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ በሰሜን አሜሪካ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እንዲስፋፋ
ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡ እሳቸው ወደ ሃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት 4 ብቻ የነበረው የሰሜን አሜሪካ
የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቁጥር 200 በላይ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
ለሰው ልጅ ፍቅር ፤ እምነት አንድነትና መተሳሰብ መጎልበት ህይወታቸውን
የደከሙት አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ወደ ቀጣዩ ፤ ወደ ማይቀርበት ዓለም እ.ኤ.አ 2012 መጋቢት 17 አልፈዋል፡፡ ሞታቸው ዓለምን ሁሉ
አሳዝኗ ፤ አስክሬናቸው በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ልብሰ ተክህኗቸውን እንደተጎናጸፉ ለ3 ቀናት ሲታይ ቆይቶ በቅዱስ ፒሾይ ገዳም
አርፏል፡፡
Read this for additional information
ye egnaw Aba Pawulos yetignaw tarikachew yhon yemitsafilachew?????????
ReplyDeleteየመንግስት አቋም በማያሻማ መልኩ ግልጽ ነው ፤ የቤተክህነቱም እንደዛው ፤ እነርሱ በአንድ ቤተክርስትያን አንድ ሚሊየን ብር በ18 አብያተክርስትያናት 18 ሚሊየን ብር ለመቀበል ተዘጋጅተው ከመንግስት ላለመጣላት ፈርተው የተቀመጡ ናቸው ፤ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል ፤ አሁን መፍትሄ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው በርትተን ሁላችን ብንጸልይ ከአምላከ ዘንድ መልስ ይኖራል ብለን እናስባለን ፡፡ ..... libin behazen yemiwega.....ejig kifu neger
ReplyDeleteAndadrgen Ageliglotachhun Amlak besemay yesafilachu GOD bless u all
ReplyDeleteደርግ በፈቃደኝነትም ይሁን በእጅ ጥምዘዛ ያን ደብዳቤ ማስፈረም ችሎ የታሪክ ጠባሳ ትቶልን አልፏል ፤ አሁን በእናንተም ጊዜ ፈቅዳችሁም ይሁን ተገዳችሁ ተገቢ ያልሆነ ምእመኑን ፤ ቤተክርስትያንንና ፤ የዋልድባ ገዳም አባቶች የሚያሳዝን ተግባር ብትፈጽሙ ነገ የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ፡፡ ይህ ምክር ችግሩ የታየንን እና የተገለጸልንን መጠን ለሚመለከተው አካል ሁሉ የተላለፈ ነው፡፡
ReplyDelete