Friday, June 29, 2012

በባቦጋያ መድሃኒአለም የቦታ ጉዳይ 13 ሰዎች ላይ እያንዳንዳቸው ሰባት ወር ተፈረደባቸው


  • ከ400 በላይ ምዕመናን በእንባ ወደ እስር ቤት ሸኝተዋቸዋል፡፡
  • የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የበላይ አካል ተጽህኖ አለበት ፤

(አንድ አድርገን ሰኔ 22 ፤ 2004 ዓ.ም)፡- በፍርድ ቤቱ ውሳኔ በጣም አዝነናል ፤ ሲጀመር አንስቶ በባቦጋያ መድሃኒዓለም ቦታ እና በኩሪፍቱ ሪዞርት መካከል ያለው የቦታ ውዝግብ በየጊዜው ማቅረባችን ይታወቃል፤ አቅማችን በፈቀደው መጠን ጉዳዩን ሰዎች ዘንድ እንዲደርስ የመፍትሄ አካላት እንዲሆኑ ያላሰለሰ ጥረት አድርገናል ፤ ከወራት በፊት የቤተክርስትያኑን ቦታ በአካባቢው ምዕመናን ጉዳዩን ዳር እዲያደርሱ የተወከሉ ሰዎች በፍርድ ቤት “እናንተ መጠየቅ አትችሉም ቤተክርስትያኒቱ የወከለቻችሁ አካላት አይደላችሁም” በማለት ለኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት እንደተወሰነለት ገልጸን ፅፈን ነበር ፤ 


ከዚህ በኋላ ምዕመኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተስፋ ለማስቆረጥ ወደፊት ምንም ጥያቄ እንዳይጠይቁ ለማሸማቀቅ አቶ ጌታቸው ዶኒ ፤ የሪዞርቱ ባለቤትና የፍርድ ቤት ጠበቃቸው ከባቦጋያ መድኃኔዓለም ቤተክርስትያ አስተዳዳሪ ጋር በመሆን የሀሰት ክስ ማቅረባቸውን ይታወሳል ፤ ይህ በእንዲህ እያለ አቶ ጌታቸው ዶኒ የሀሰት ምስክሮችን አስመጥቶ ፍርድ ቤት በማቆም ማስመስከሩ ይታወቃል ፤ በዚህ የፍርድ ቤት የምስክር ሂደት የቤተክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ ፍርድ ቤት ውስጥ የሚሰሙትን ምስክርነት ለሶስተኛው ምስክር አሳልፈው ሲናገሩ በመያዛቸው ለ24 ሰዓት ታስረው በ2000 ብር ዋስ መፈታታቸው ይታወቃል ፤ ፍርድ ቤቱ እኝህን አስተዳዳሪ  አቃቢ ህግ ክስ እንዲመሰርት ቢያዝም አቃቢ ህግ ልብ አግኝቶ ይህን ሲያደርግ መመልት አልተቻለም ፤ ፍርድ ቤቱ የተቀመጠው ህግ ከባለስልጣናት ትዕዛዝ ሲበልጥበት መመልከት አልቻልንም ፤ አስተዳዳሪው ምስክሮቹ ቃላቸው አንድ አንዲሆን በማሰብ የውስጡን ለውጩ ምስክር አሳልፈው ምስክርነቱን ሲናገሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በዝምታ መታለፋቸው ሁሉን አስደምሟል ፤ በመሰረቱ ምስክርነት እየተሰማ ሳለ አይደለም መስካሪ የችት ታዳሚው ችሎቱን አቋርጦ መውጣት እንደሌለበት ያስቀምጣል ፤ ዳኛው  “ችሎትን በማወክ” በሚል አንቀጽ እዚያው ሌላ ፋይል ሳይከፍት የቅጣተኝነት ፍርድ ማስተላለፍ ይችል ነበር ፤

የት ሄደን አቤት እንበል? የትስ ሄደን ጉዳያችንን እናቅርብ? ይትስ ሄደን ድምፃችንን እናሰማ ? ማንስ ሚዛናዊ ፍርድ ይፍረድልን ? “የራሳችንን ቦታ አንሰጥም ፤ የሌሎችንም ቦታ አንፈልግም”  ብሎ ምዕመኑ በጠየቀ በሌላ አይን እየታየ ይገኛል ፤ ስለ ቤተክርስትያን ጥያቄ መጠየቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ፤ ለብዙ ጊዜያት ሲንከባለል የመጣው የባቦጋያ የመሬት ጉዳይ በአካባቢው የከተማ አስተዳደር ፤ በባቦጋያ ሪዞርት ባለቤት ፤ በአቶ ጌታቸው ዶኒ ሴራና በቤተክህነታችን ተባባሪነት 13 ሰዎችን እስር ቤት አውርዷል ፤  አይደለም ሰባት  ወር ይቅርና ሰባት ሰዓት እስር ቤት መግባት የሌለባቸው ሰዎች በተጽህኖ ስር በወደቀው የፍርድ ሂደት አማካኝነት ሰባት ወራት በእስር እንዲያሳልፉ ፈርዶባቸዋል ፤

ቦታው የመድኃኔዓለም ታቦት ማደሪያ ነው ያሉ ወንድሞች ምን ዓይነት ክስ እንደተመሰረተባቸው ፤ በምን ያህሉ የቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው እና በየትኞቹ ክሶች ደግሞ በነጻ እንደተሰናበቱ ለማየት እንሞክር፡፡

የቀረቡት የሐሰት የክስ አይነቶች
  1.     አንቀጽ 492 - መጋቢት 23/2004 አቶ ጌታቸዉ ዶኒ የቅዱስ ሲኖዶስ ዉሳኔ ነዉ በማለት ራሱ ጽፎ የቤተክህነቱን ማህተብ ያደረገበት ጽሁፍ  ለምዕመኑ በአውደ ምህረት ላይ በማንበብ ላይ ሳለ ፤ ማይክራፎን አጥፍተዋል በማለት / ሲሳይ ወንድሙና / ወግደረስ አመሃ የተከሰሱበት ሲሆን በቀረበዉ የሰዉና የቪዲዮ ማስረጃዎች ነጻ ወጥተዉበታል፡፡
  2. 2.    አንቀጽ 492- አቶ ሐብታሙ ታዬ  “የኢትዮጵያ ሲኖዶስ እኛን አያስተዳድረንም የአሜሪካዉ ሲኖዶስ  እንጅ”  ብሏል በማስባል ክስ መስርተው ነበር ፤ በዚህ ክስም ጌታቸው ዶኒ እና መ/ር ኃይለእየሱስ በሀሰት ቢመሰክሩበትም ባቀረበው የቪዲዮ ማስረጃ አማካኝነት አቶ ሃብታሙ ታዬ ነጻ ሊወጣ ችሏል ፤

በጣም የሚገርመው ከአንድ ወር በፊት  “የፍትሕ ሳምንት” በተከበረት ወቅት በየጊዜው በፍርድ ቤቶች የሚቀርቡት ሰዎች የሚያቀርቧቸው የሀሰት ምስክሮች አማካኝነት ህዝቡ እደተመረረ እና በዚህ ሁኔታም በመጀመሪያው ክስ  በእነ አቶ ጌታቸው ዶኒ አማካኝነት የተቀነባበረውን የሀሰት ምስክርነት ለባለስልጣናቱ ያስረዱበት ሁኔታ የተፈጠረ ሲሆን የክልሉ ኃላፊዎችም ይህን ችግር እንደ ችግር በማየት ወደፊት እንደሚስተካከል ፤ በዚህ ምክንያት በሀሰት የሚቆሙትንም ሰዎች ህጉ ባስቀመጠው ስርዓት አማካኝነት እንደሚጠየቁ ያስገነዘቡ ቢሆንም ቃላቸውን ሲጠብቁ ግን ህዝቡ መመልከት አልቻለም ፤
 
3. አንቀጽ 492/1-ምድዋይ - ምጽዋት ገልብጠዋል ተብለው በሀሰት ቢከሰሱም ይህ ነገር ሆነ ብለው ለፍርድ ቤት ያረዱበት እና ከምስክሮች አፍ የተሰማው ቃል አንድ ባለመሆኑና ፤ ተከላካይ ምስክሮች ሁኔታውን የተከሰሱት ሰዎች በቦታው እንዳልነበሩ ሁሉም ተፈጸመ በተባለበት ጊዜ ከከተማ ውጭ መሆናቸውን ስላስረዱ ከክሱ ነጻ ሊወጡ ችለዋል፡፡



4. አንቀጽ 436/1ሐ-ያለአግባብ ስልጣናቸዉን በመጠቀም ቤተክርስትያን አስተዳደሩ ተብለዉ በተከሰሱበት ክስ እያንዳንዳቸው ሰባት ወር ጽኑ እስራት በ13ቱም ሰዎች ላይ ሲፈረድባቸዉ በዲ/ን ሲሳይ ና ወግደረስ አስፈራርተዋል በማለት 400ብር ቅጣት ተጨማሪ ተፈርዶባቸዋል፤፤

ይህ ሁሉ የሀሰት ክስ አንድ ጊዜ እጃቸው የተነካካበትን የቦታ ጉዳይ መና ለማስቀረት እና እነርሱም ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚያደርጉት ዘመቻ መሆኑ እሙን ነው ፤ እኛ አቅም አጥተን ፍርድ ተዛብቶብን ተገቢውን ፍትህ ማግኝት ባንችል እንኳን እግዚአብሔር ግን በጊዜው ሁሉን እንደየስራው እንደሚከፍለው እናምናለን፡፡


በሐሰት የተከሰሱ ሰዎች
1.
አበጀ እንደሃብቱ
2. 
ሰለሞን ከበደ
3. 
ሙላቱ እንግዴ
4. 
ይጥና አጎናፍር
5. 
ሰናይት /መስቀል
6. 
እሸቱ በቀለ
7. 
ሲሳይ ወንድሙ
8. 
ወግደረስ አመሃ
9. 
ግርማ በጅጋ
10. 
ሐብታሙ ታዬ
11. 
ደሱ ሮቢ
12. 
አፀዱ ተገኝ
13. 
ብርሃኑ ደገፎ
እነዚህው ስለ ቤተክርስትያን ቦታ ብለው ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎች ወደ ጣቢያ ከገቡ በኋላ የሚበላ ምግብ ፤ ጎናቸውን የሚያሳርፉበት  ፍራሽ እንዳይሰጣቸዉና ከቤተሰቦቻቸዉና ጠበቃቸዉ ጋር እንዳይገናኙ የተደረገ ሲሆን ፤  በጾታ ሳይለዩ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ 19/10/2004  በአንድ ቤት አሳድረዋቸው ፤ በነጋታው  ወደ አዳማ ሲወሰዱ ከ400 በላይ ሕዝብ  በእንባ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝቶ ሸኝቷቸዋል ፤ ህዝቡ በሁኔታው ክፉኛ ልቡ ደምቷል ፤ ይህን ፍርድ ያስተላለፈው ዳኛ ፍርዱን ያስተላለፈው በጫና ነው ብለው ብዙዎች የምናሉ ፤

የባቦጋያ መድኃኔዓለም ሁኔታ ምን ያህል ፍትህ የሌለበት ፍርድ የሚጓደልበት ሀገር እየኖርን እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ፤ ከዚህ በፊት እነዚህው ተከሳሾች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ ቢቀርብባቸውም በጊዜው የነበረው ዳኛ ሁለት ተከሳሾች ላይ የ200 መቶ ብር ቅጣት በማስተላለፍ ሌሎቹን “መብታቸው ነው መጠየቅ ይችላሉ” ብሎ በነጻ ማሰናበቱ ይታወቃል ፤ ይህ ዳኛ ይህን ፍርድ ካስተላለፈ በኋላ በተደረገው የውስጥ ግምገማ አማካኝነት “እንዴት ይህን ውሳኔ ታስተላልፋለህ?`` በማለት ከበላይ አካላት ዛቻ ማስፈራሪያ እና ቅጣት ደርሶበታል ፤ ይህም ዳኛ “ህጉ ያስቀመጠውን ነው ያደረኩት ፤ ለማንም ብዬ ያደላሁት ነገር የለም” በማለት በወቅቱ ሞግቷቸው ነበር ፤ ከዚያ በኋላ በተካሄደ የውስጥ ስብሰባ አማካኝነት “በመጀመሪያው ክስ ወቅት አስተማሪ የእስር ውሳኔ ቢተላለፍባቸው ኖሮ ዛሬ እንዲህ አይነት ጥያቄ ባላነሱ ነበር” በማለት በቂም በቀል ተነሳስተው ህጉ የማይፈቅደውን ነገር በአሁኑ ሰዓት ሊያደርጉ ችለዋል ፤ እነዚህን ህገወጦች ማነው ፍርድ ቤት የሚያቆማቸው ?

በተጨማሪ ይህ የመሬት ህገወጥ ሽያጭ ከቤተክህነቱ ሰዎች አንስቶ እስከ ከተማው መስተዳድር ድረስ ያሉ ሰዎችን የሚያነካካ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት  እየተደረገ ያለው የሚደረገው ነገር አግባብ ያለመሆኑ ተገልጾ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አስታራቂ መፍትሄ እንዲያመጣ ቢጠየቅም “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ዝም ማለቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በጣም አሳፋሪው ነገር ግን  ከደብረዘይት 4 ኪሎ ቤተክህነት ድረስ የሚመጡ ሰዎች ጠቅላይ ቤተክህነት ገብተው ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ሲሞክሩ በር ላይ ያሉ ዘቦች “ከባቦጋያ የሚመጡ ሰዎችን እንዳታስገቡ” ተብለናን በማለት አጭር መልስ ስለሚሰጧቸው መዝለቅ እና አቤቱታቸውን መዋቅሩን በጠበቀ መልኩ ፓትርያርኩ ዘንድ ማቅረብ አለመቻላቸው ስናውቅ በቤተክህነቱ በጣም አዝነናልም አፍረናልም ፡፡

ይህ ጉዳይ ለኦሮሚያ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከነ ሙሉ መረጃው የደረሰው ሲሆን ኮሚሽኑ የደረሰውን መረጃ መሰረት በማድረግ የከተማው አስዳደር እና ቤተክርስያኒቱ ላይ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረቡ ተሰምቷል ፤ ከዚህ በተጨማሪ የተፈረደው ፍርድ አግባብ አለመሆኑን በመቃወም ይግባኝ የሚጠይቅ አካል በመምከር ላይ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡በቅርቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በተነሳው የቦታ ችግር ምክንያት የሁለት ሰው ህይወት ማለፉንና በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ይታወቃል ፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን

3 comments:

  1. betam asafari asafari....

    ReplyDelete
  2. አልፎ አይቼውJune 29, 2012 at 5:32 PM

    የአንጋፋው ይድነቃቸው አባት ነጋድራስ ተሰማ እሽቴ ከአጼ ሃይለ ስላሴ እጅ መኪና ይሽለማሉ፡: ከታች ያሉት ታዲያ ድክም ያለችዋን ይሰጧቸዋል። በዚህ የተበሳጩት ነጋድራስ ቀን ሲጠብቁ አንድ ቀን ንጉሱ ወደ ደብረ ዘይት መሄጃ ሰዓታቸውን ጠብቀው መኪናቸውን ይይዙና ከፊት ይቀድማሉ። ትንሽ እንደሄዱ የንጉሱ መኪና ብቅ አለ። የዚህን ጊዜ ቶሎ ብለው መኪናው ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ውረዱና መኪናውን ግፉ ይሏቸዋል። እሳቸው ከውስጥ ፍሬኑን ይዘውታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የንጉሱ መኪና ደረሰ። የንጉሱ ባለሟሎች እና ወታደሮች ወረዱ። መኪናዋ አትንቀሳቀስም። የዚህን ጊዜ ነጋድራስ ጮክ ብለው ግፉ ግፉ ግፉ ገና ነው። ንጉሱ ማነው ምንድነው በማለት ሲጠይቁ ነጋድራስ እንደሆኑና ግፉ ገና ነው እያሉ መሆኑን ነገሯቸው። ንጉሱ ነገሩ ገብቷቸው ይህን አሮጌ መኪና ሰጥታችሁ ነው የምታሰድቡኝ በሉ ቀይሩለት ብለው አዲስ ተሰጣቸው።
    መንገዱን ዘግቶብን ቆሟል መኪናው፡
    ወይ አዲስ አልገዛን በሽታ የሌለው፡
    ግፉ በዝቶብናል መፈታተኛው ፡
    አንድ እንሁንበት እናስወግደው።

    ReplyDelete
  3. መቼም እግዚአብሔር የናቡቴን ዋጋ እንደሚከፍላቸው አንጠራጠርም:: ክርስትና ዋጋ የሚያሰጠው በዚህ ፍርድ በሌለበት ወቅት ነውና በሃይማኖታችን እንጽና :: በሃሰት ለተፈረደባቸውም እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጥልን:: እኛም ከበረከቱ ተካፋይ እንሆን ዘንድ በዚህ መክንያት ቤተሰቦቻቸው እንዳይችገሩ፣ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰብ የባንክ ቁጥር አሳውቁንና 7 ወር አብረን ተቸግረን እናሳልፈው :: እግዚአብሔር በሃይማኖታችን ያጽናን

    ReplyDelete