Monday, June 18, 2012

ቅ/ሲኖዶስ በተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅነት ያወገዛቸው 7 ድርጅቶችና 16 ግለሰቦች ውሳኔ ለአህጉረ ስብከት ተሰራጨ


·         መናፍቃ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያናችን የክህነት፣ የክብርና የማዕርግ ስም አይጠሩም
·         የቤተ ክርስቲያኒቱን የከበረ ስሟን በማጉደፍ ታሪኳንና ክብሯን በመዳፈራቸው በሕግ ይጠየቃሉ
·         መናፍቃ እና ድርጅቶቹ ላሰራጯቸው ኅትመቶች የማስተባበያ ጽሑፎች ይዘጋጃሉ
·         ሊቃውንት ጉባኤ ከማንኛውም አካል ለሚሰነዘረው ሃይማኖት የሚያጎድፍ ክብረ ነክ ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት በሚችልበት አኳኋን በጥራትና በስፋት ይጠናከራል
·         ከተወገዙት ድርጅቶች መካከል የ”አንቀጸ ብርሃን” ድርጅት መሥራች በኾነውና በእጅጋየሁ በየነ አቅራቢነት የፓትርያኩ መልእክቶች ጸሐፊ እስከመኾን ደርሶ በነበረው አሸናፊ መኰንን ላይ የተላለፈውን የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ ለመቀሠጥ የተደረገው የሸፋጮች ሙከራ ከሽፏል (ሙከራውን የሰነዱን ገጽ 38 እና 39፣ ተ.ቁ 16ን በማነጻጸር ይመልከቱ)
·         “አሁን የተሐድሶ መናፍቃኑ ዝናራቸውን ጨርሰው የአገልጋዮችን ስም ማጥፋቱን ተያይዘውታል፤ ያወገዝናቸው ስለጠላናቸው ሳይሆን ስለካዱ ነው፤ ሰውን ማስታመም የሚቻለው በምግባር ድክመቱ እንጂ በሃይማኖት ክሕደት አይደለምና፡፡” /ብፁዕ አቡነ አብርሃም የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለሀ/ስብከታቸው ሰባክያነ ወንጌል እና ምእመናን ይፋ ሲያደርጉ ከተናገሩት/
(ደጀ ሰላም፤ ሰኔ 9/2004 ዓ.ም፤ ጁን 16/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሃይማኖት ጉዳይ በተለይም ለምእመናን አንድነት ቅድሚያ በመስጠት፣ በጉዳዩ ላይ በስፋት በመነጋገር፣ ግንቦት 15 ቀን 2004 ዓ.ም፣ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና መጽሐፎቻቸው ላይ በአንድ ድምፅ ያስተላለፈውን የውግዘት ውሳኔ የያዘው ቃለ ጉባኤ ለመላው አህጉረ ስብከት ተሰራጨ፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሰኔ 7 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ 48 አህጉረ ስብከት ባሰራጨው ቃለ ውግዘት የተካተቱት መናፍቃን ድርጅቶች ሰባት ሲኾኑ የግለሰቦቹ ብዛት ደግሞ 16 ነው፡፡


ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ የተወገዙት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት የተለየ የኑፋቄ ትምህርት በመጽሐፋቸው፣ በመጽሔታቸው፣ በመጣጥፎቻቸውና በኤሌክትሮኒክስ የኅትመት ውጤቶቻቸው ሲያሰራጩ በመገኘታቸውና ይህም በማስረጃ በመረጋገጡ መኾኑን የገለጸው ቃለ ውግዘቱ÷ውሳኔው በይፋ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ መርሐ ግብር በማንኛውም መድረክ እንዳይሳተፉ፤ እስከ አሁን ሲጠሩበት በነበረው የክህነት እና የክብር የማዕርግ ስም እንዳይጠሩበት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ ለውሳኔው መሠረት የኾነው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና የሊቃውንት ጉባኤ ጥምር ኮሚቴ ሰነድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ዐዋቂዎች እና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከተመረመረ በኋላ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ የቤተ ክርስቲያኒቷን የከበረ ስሟን በማጉደፍ፣ ታሪኳን፣ ክብሯን በመዳፈር ላደረሱት በደል በሕግ እንደሚጠይቁ የውሳኔ ቃለ ጉባኤው አስታውቋል፡፡

መናፍቃን ድርጅቶቹና ግለሰቦቹ ላሰራጯቸው ጽሑፎች የማስተባባያ ምላሽ እንደሚዘጋጅና ዝግጅቱም በመጽሔት ጥራዝ መልክ ተዘጋጅቶ እንደሚወጣ የውሳኔው ማጠቃለያ አመልክቷል፡፡ በይቀጥላልም ጽሑፉን የማዘጋጀት ሓላፊነት የተጣለበት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ ከማንኛውም አካል የሚሰነዘረውን ሃይማኖትን የሚያጎድፍ ክብረ ነክ ጽሑፍ ተከታትሎ በጊዜው በቂ የኾነ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችለው ስፋት እና ጥራት እንደሚጠናከር አብሥሯል፡፡

በቃለ ውግዘቱ የተካተቱት ድርጅቶችና ግለሰቦች በበደላቸው ተጸጽተው የይቅርታ ደብዳቤ ጽፈው ይቅርታ ከጠየቁ የይቅርታ ጥያቄውን ለመመርመር እና ይቅርታ ጠያቂዎችን ለመቀበል ዝግጁ መኾኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጧል፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኒቂያና በቁስጥንጥንያ፣ እንዲሁም በአምስተኛው መቶ ዓመት በኤፌሶን በተደረጉ ጉባኤያት የተወሰኑትን ተቀብላ፣ አጽንታ በመያዝ የምታስተምር መኾኗን የገለጸው የውሳኔው መግቢያ÷ በዓለማችን በትምህርተ ሃይማኖት ሂደት ብዙ አስደንጋጭ፣ አስፈሪና አሳፋሪ ብዙ ክሥተቶች በየጊዜው በተለያየ ስምና ጠባይ መፈጠራቸውን አስታውሷል፡፡ ነቢያት በትንቢት፣ ሐዋርያት በስብከት፣ ሊቃውንት በትምህርት የተባበሩበት ትምህርተ ሃይማኖት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያው ያልተለወጠው፣ የማይለወጠው የጸና፣ የቀና እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚኖር በመኾኑ መናፍቃን ድርጅቶቹንና ግለሰቦቹን ማውገዙን አስታውቋል፡፡

ቃለ ውግዘትን ፈርቶ በተወገዙበት ጉዳይ ከልብ ተጸጽቶና ቃለ ካህንን አክብሮ ይቅርታ መጠየቅ፣ ራስን ከተሳሳተ ትምህርትና ከምግባረ ብልሹነት መጠበቅ አብዝቶ ይጠቅማል፡፡ እንደ መፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች ክህነትንና ግዝትን ንቆና ተደፋፍሮ ሌላውን ማደፋፈር ደግሞ ድርብ ጥፋት ነው፡፡ በሰማይ እና በምድር ሁሉን በተገባ ለማሰርና ለመፍታት ሥልጣን የተሰጣቸው ቅዱሳን ሐዋርያት መንበር ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በክህነታዊ ሥልጣኑ ያስተላለፈውን ውግዘት መናቅ በምንም መንገድ መንፈሳዊነት ሊኾን አይችልምና፡፡

ከተወገዙት ድርጅቶች መካከል “አንቀጸ ብርሃን”  በሚል ስያሜ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚያጭበረበረው ድርጅት መሥራች አሸናፊ መኰንን ይባላል፡፡ በእጅጋየሁ በየነ አስተዋዋቂነት በመንበረ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት “የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት” የተሰኙ ጽሑፎችን እስከማዘጋጀት መድረሱ ይነገርለታል፡፡ ወደ ልዩ ጽ/ቤቱ ከመቅረቡ በፊትም ይኹን በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የቅዱስ ሲኖዶስን ቃለ ጉባኤ ከሚይዝ አንድ ግለሰብና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና መዝገብ ቤት ሓላፊ ከኾነችው ወ/ሮ ዐጸደ ግርማይ ጋራ ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ተገልጧል፡፡

ኑፋቄን፣ ስድብንና ሽንገላን፣ ሽሙጥንና ትችትን፣ ክሕደትን የተመሉ ስድስት መጻሕፍቱ፣ 10 መጽሔቶቹ እና ሌሎችም መጣጥፎቹ ተመርምረው ዳንኤል ተሾመ ከተባለ ሌላ ግብረ አበሩ ጋራ እነርሱም፣ ድርጅታቸውም ጽሑፎቻቸውም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘው አሸናፊ÷ ገና ጉዳዩ ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ በመታየት ላይ ሳለ በወይዘሮዋና በፓትርያርኩ ተጽዕኖ ውሳኔውን ለማስቀየር ያደረገው ብልጠት ሳይሠራለት ቀርቷል፡፡

አሸናፊ ግን ቁርጡን ዐውቆ በህልውና ሥላሴ፣ በጌታችን አምላካዊ ክብር፣ በሃይማኖታችንና በኢትዮጵያዊ ወኔያችን ላይ ሲዳክርበት የኖረውን ጥፋቱን አላመነም፡፡ የመጨረሻ ነገር ግን አሳፋሪ ሙከራ አደረገ፡፡ ለዚህም የቅዱስ ሲኖዶስን ቃለ ጉባኤ ከሚይዙት የጽ/ቤት ሠራተኞች የአንዱን÷ በአንዳንድ ምንጮች ጥቆማ ግለሰቡ የ”አንቀጸ ብርሃን” የቆየ አባል እንደ ኾነም ተጠቁሟል÷ (ስሙን ብናውቅም ከመጥቀስ ተቆጥበናል) ሸፍጥ ይጠቀማል፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንደሚያስረዱት ይኸው የአሸናፊ ሸፍጠኛ የቅዱስ ሲኖዶሱ የውሳኔ ቃለ ጉባኤ ተተይቦና ተባዝቶ በሚጠረዝበት ወቅት÷ በገጽ 38 ላይ በስም ተራ ቁጥር ከሚዘረዝራቸው 16 ውጉዝ ግለሰቦች መካከል÷ በተራ ቁጥር 16 ላይ የተጠቀሰው የአሸናፊ መኰንን ስም አብሮት ከተወገዘውና በተራ ቁጥር 4 ላይ ከተጠቀሰው ዳንኤል ተሾመ በመነጠል በመጨረሻ ላይ እንዲሰፍርና እንዲገደፍ በማድረግ የ15 ሰዎችን ስም ዝርዝር ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቅርቧል፡፡ ሰነዱን በጥንቃቄ የመረመሩት ብፁዕ ዋና ጸሐፊውም ግለሰቦቹ 16 መኾናቸውንና የአሸናፊ መኰንን ስም አለመካተቱን በመጥቀስ ቀልቡን ይገፉታል፡፡

በቤተ ክህነቱ የቆየ ሠራተኛ ለዚያውም የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባልደረባ በመኾኑ ጓደኛው አሸናፊ ከክፉ ግብሩ ተመልሶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊመክረው ሲገባ ቅሠጣው የተጋለጠበት ቀሣጢው ግለሰብም በድንጋጤ ነው ቢሉ፣ ለሌላ ተንኰል እንዲያመቸውም ነው ቢሉ የተቀሠጠው (የጎደለው፣ የጎመደው) የአሸናፊ መኰንን ስም በተራ ቁጥር 16 ላይ በእጅ ጽሑፍ እንዲገባ ያደርጋል (ገጽ 38 ይመልከቱ)፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው አቡነ ሕዝቅኤል ግን ውሳኔው ከተላለፈ ወዲህ እንኳ ስሕተቱን አምኖ በተከፈተለት የይቅርታ በር ከመጠቀም ይልቅ በጓሮ በር በሽምግልና ጭምር ሲያስቸግር የሰነበተው የአሸናፊ መኰንን ስም እጅ ጽሑፉ ብቻ ሳይኾን በታይፕም ተጽፎ (ገጽ 39 ይመልከቱ) በሁሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዳግመኛ እንዲፈረምበት በማድረግ ያከሸፉትን ቅሠጣ ለታሪክ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡ በተ.ቁ (7) ላይ ስብሐት ለአብ በሚል በአባቱ ስም ብቻ የተገለጸውቀንደኛው መናፍቅና የ”ማኅበረ በኵር” መሥራች መሠረት ስብሐት ለአብ ስምስ በምን ተንኰል በዚህ መልኩ እንደታለፈ አያጠያይቅም ለማለት አይቻልም፡፡

ይህ የከሸፈ የእነአሸናፊ ሸፋጮች ሙከራ ግን የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄው ትግል ቀጣይ የተጋድሎ ዐውድማ በሚኾነው በቤተ ክህነቱ ቢሮክራሲ ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በግልጽ የሚያመለክት እንደኾነ የጉዳዩ ታዛቢዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክህነቱን ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቅጥረኞች እና የእነርሱ መተላለፊያ ወደብ (harbor) ከኾኑት ሙሰኞችና ዘረኞች ለማጽዳት በይቀጥላል የሚደረገው ቢሮክራሲያዊ ትግል እስከአሁን ከተካሄደው የበለጠ ውስብስብ እንደሚኾን ከታሪካዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደማቅ ውሳኔዎች ማግስት አባ ጳውሎስ እንደ ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ካሉ አጋፋሪዎቻቸው ጋራ በእልክና በበቀል ጥማት የሚያሳዩት መወራጨት ምስክር ነው - የመጨረሻው ምሽግ መላላጥ (the last ditch effort) ይኾን?

ግሪኮች “ከዐዩ የወገን ድል በፊት ጠላት የሚያውጃቸው ትንንሽ ድሎች አሉ” ይላሉ፡፡ አባ ጳውሎስና እነኀይለ ጊዮርጊስ መንግሥትን ጭምር ሊያጨበረብሩበት የተዘጋጁበትና ከፈተናው በፊት ቀረር የሚያሰሙበት ሰሞናዊው “ጉባኤያቸው” የት ያደርሳቸው ይኾን? ብዙ እየተናገሩ ነው፤ እርስበስ ለማናተፍ ይረዳናል፤ ያሸማቅቅልናል ያሏቸውንና ከምናባቸው በቀር በዕውን የሌለ የጭቃ ጅራፋቸውንም በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎቻቸው እያጮኹ ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ግልጽ ሊኾንላቸው የሚገባው ግን ብፁዕ አቡነ አብርሃም ትናንት፣ ሰኔ 8 ቀን 2004 ዓ.ም እንደተናገሩት “በሽተኛ እና ጤነኛ በአንድ ቤት ማደር እንደማይችል” ነው፡፡

የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰባቱ መናፍቅ ድርጅቶች እና 16 ግለሰቦች ላይ ስላሳለፈው የውግዘት ውሳኔ÷ ትናንት፣ ሰኔ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በሐረር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በተጠራው የሀ/ስብከቱና የስድስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም የፀረ - ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት በተገኙበት ጉባኤ ላይ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ የግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ልበሱ” (ኤፌ.6÷11) በሚል ርእስ ትምህርት ሰጥተዋል፤ በውሳኔው አተገባበር ላይም አባታዊ ሪያና ምክር አስተላልፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተሐድሶ ጭፍሮች ዝናራቸውን ጨርሰው የቅዱሳኑንና የትጉሃን አገልጋዮቹን ስም ወደ ማጥፋት መዝቀጣቸውን ተናግረዋል፡፡ “ድርጅቶቹንና ግለሰቦቹን ያወገዝናቸው በሰውነታቸው ስለጠላናቸው ሳይኾን በሃይማኖት ስለ ካዱ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ሰውን ለማስታመም የሚቻለው በምግባር ድክመቱ እንጂ በሃይማኖታዊ ክሕደቱ እንዳልኾነ አስረድተዋል፡፡

በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በውሳኔው “የኑፋቄ ትምህርት አስተላላፊዎች እና ፀረ - ኦርቶዶክስ አቋም ያላቸው መናፍቃን” ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በተወገዙበት ማግስት ለውሳኔው መሠረት የኾኑ ማስረጃዎችን አጠናቅሮ በማቅረብ እልክ አስጨራሽ ተጋድሎ ያደረጉትን በሙሉ÷ በተለይ ማኅበረ ቅዱሳንን÷ ለማዳከም ከተሳካላቸውም ለማፈራረስ፣ ውሳኔው በተገቢው መንገድ ተጠንቶና ተመርምሮ ታላቅ ፍጻሜ ላይ የደረሰበትን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የአባ ጳውሎስን ሥልጣን በሚያጠናክር አኳኋን ለመለወጥና የቅዱስ ሲኖዶሱን ሥልጣን ለመፃረር፣ ከመወሰን እስከ ማስፈጸም ድረስ በየደረጃው ሓላፊነት የተጣለባቸውን ብፁዓን አባቶች፣ የሥራ ሓላፊዎች፣ ካህናት፣ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል ለመድፈቅ እየተራወጠ የሚገኘውን ስብስብ (የዐመፅ ቡድን) ተግዳሮቱ በሚጠይቀው መጠን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ገጥሞ ለማስወገድ አንድነታችንን እንድናጠነክር ደጀ ሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

የክህነትና የክብር ማዕርጋቸው ተሽሮ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ
በሰማይና በምድር የተወገዙት ድርጅቶች እና ግለሰቦች ዝርዝር
የሚከተለው ነው፤
ሰባቱ ድርጅቶች፡-
1. ከሣቴ ብርሃን
2. ማኅበረ ሰላማ
3. የምሥራች አገልግሎት
4. የቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር
5. አንቀጸ ብርሃን (ከድርጅቱ ጋራ አሸናፊ መኰንንና ዳንኤል ተሾመ)*
6. የእውነት ቃል አገልግሎት
7. ማኅበር በኵር
8. የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኅብረት/ኢመተኅ/ - (ተጨማሪ ማጣራት የሚደረግበት)

16ቱ ግለሰቦች፡-
1. ‹አባ› ወልደ ትንሣኤ አስገዶም
2. አቶ መስፍን
3. አጥናፉ መኰንን
4. ዳንኤል ተሾመ
5. ግርማ በቀለ
6. ሥዩም ያሚ
7. መሠረት ስብሐት ለአብ
8. ሰሎሞን መኰንን
9. ጽጌ ስጦታው
10. ደረጀ ገዙ
11. በዛ ሰፈርህ
12. አግዛቸው ተፈራ (አሁን የጮራ መጽሔት አዘጋጅ)*
13. ተስፋ ተገኝ
14. ብሥራት ጌታቸው
15. መ/ር ተስፋ ዓለም
16. አሸናፊ መኰንን

ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ “ትምህርተ ውግዘት” በሚል ርእስ ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ ከጻፉት የተወሰደ ነው፡፡ ስለ ውግዘት አጠቃላይ ግንዛቤ በሚሰጥ መልኩ እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
 ቸር ወሬ ያሰማን!!!!! አሜን

No comments:

Post a Comment