Tuesday, April 8, 2014

የኒቆዲሞስ ክርስትና


ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
henoktsehafi@gmail.com
ኒቆዲሞስ የሚለው ስም በዮሐንስ ወንጌል ብቻ ከተጻፉ ስሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን ሰው ባነሣበት ሥፍራ ሁሉአስቀድሞ በሌሊት የመጣውየምትል ቅጽል ያስቀድማል፡፡ ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ ነው፡፡ በሀብቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ባለጸጋ በሹመቱ የአይሁድ ሸንጎ /Sanhedrin/ አባል በትምህርቱ ደግሞ ጌታችን ራሱ እንደመሰከረለትየእስራኤል መምህርየሆነና አዋቂ ነው፡፡ የአይሁድ አለቃ የእስራኤል መምህር ኒቆዲሞስ ጌታችን ራሱ በቃል ምልልስ እያናገረ ጥያቄያቸውን እየመለሰ ካስተማራቸው ጥቂት ዕድለኛ ሰዎች አንዱም ነው፡፡ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘንበትን ምሥጢረ ጥምቀት በጥልቀት እና በዝርዝር የተማረው የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ በዚህ ትምህርትም ኒቆዲሞስ ባቀረበው ጥያቄ ከውኃና ከመንፈስ ዳግመኛ ስለ መወለድ ጌታችን በምሳሌ አድርጎ ያስተማረው ሲሆን አላምን ብሎ ሲከራከር ደግሞ ገሥጾታል፡፡ ዛሬም ድረስ ኒቆዲሞስ የተከራካሪዎች ምሳሌ ሆኖ በሊቃውንት ይጠቀሳል፡፡ እመቤታችን የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት በመቀበሏ በምናመሰግንበት ጊዜእንደ ዘካርያስ ሳትጠራጠሪ እንደ ነቆዲሞስ ሳትከራከሪ ቃሉን የተቀበልሽእያልን መሆኑ ይህን እውነታ ያጎላዋል፡፡ ኒቆዲሞስ ወደ ክርስትና ከመጣበት መንገድ ጀምረን በዮሐንስ ወንጌል ስንከተለው ቀስ በቀስ እያደገ የመጣ የመንፈሳዊነት ደረጃን እናገኛለን፡፡ የኒቆዲሞስ እንደ ወጣኒ እንደ ማዕከላዊና እንደ ፍጹም በሦስት ደረጃዎች ላይ የሚታይ ክርስቲያናዊ ሕይወት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡


ወጣኒው ኒቆዲሞስ 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ተአምር ተመልክተው ብዙ ሰዎች በስሙ አምነው ነበር፡፡ ወቅት ጌታችን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት ውኃን ወይን ያደረገበትና በቤተ መቅደስ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ገሥጾ ያስወጣበት ነበር፡፡ ይህንን ምልክት ተከትለው ካመኑበት ብዙ ሰዎች አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በጌታችን ቢያምንም ባመነበት ወቅት እምነቱን በልቡ ብቻ ይዞ አቆይቶ በማታ ወደ ጌታችን መጣናመምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለንአለው፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታችንን እግዚአብሔር በረድኤቱ ተአምራትን እንዲያደርጉ ከሚያስችላቸው ጻድቃን እና ነቢያት ለይቶ አላየውም ነበር፡፡ ንግግሩም ከእርሱ ጋር ምልክቱን አይተው አምነው ከነበሩት ሰዎች ቁጥር መሆኑን በሚያሳይ መንገድእናውቃለንየሚል የብዙዎች ወኪልነት ንግግር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው አምላካችን በዝርዝር ያስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስን እንዲህ በሌሊት ያስመጣው ምንድር ነበር? በቀን በአደባባይ ሊያናግረው አይችልም ነበር? እሱ እንደሆነ በሔደበት መንገድ የሚለቀቅለት የአይሁድ አለቃ ነውና ጌታችንን ለማግኘት ሰዎች አገዱኝ ሊል አይችልም፡፡ ይህ እንግዲህ የኒቆዲሞስ የመጀመሪያው የክርስትና ደረጃ ነበር፡፡ እሱ አምላካችንን ስላደረገው ተአምር ሊያደንቀው ፈልጓልእግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውብሎ አመስግኖታል ሊከተለው ግን አልፈለገም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጌታችን ጋር ሆኖ ሰዎች እንዲያዩት አልፈለገም፡፡ የጌታ ተከታይ ደቀመዝሙር ሆኖ መታሰብ አልፈለገም ጉዳዩ ክብሩን የሚነካበት መሰለው፡፡ የተማረ ነውናገና ይማራል እንዴብለው እንዳይንቁት ለክብሩ ሳሳ በዚያ ላይ ደግሞ ጌታችን በአይሁድ ሹማምንት ዓይን የተናቀ ነበር፡፡ እርሱግንበኞች እንደናቁት ድንጋይነበር፡፡ ‹‹የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።›› ይላል ነቢዩ፡፡ /ኢሳ. ፶፫፥፫/ ታዲያ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ መታየት በዚያን ወቅት የሚያስከብር ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ፈራ ተባ እያለ በጨለማ መጣ፡፡ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመጣ ሰው ፈተናው ይኼ ነው፡፡ ክርስትናችን በሰዎች ፊት የታወቀ እንዲሆን ፈቃደኞች የማንሆን ብዙዎች ነን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሰው ተብሎ ላለመታየት የሚሸሹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማዕተብ ማድረግ በቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሲያልፉ መሳለም በአበው ትውፊት ጽዋዕ መጠጣት ወዘተ ማድረግ የሚከብዳቸው የሚጨነቁና የሚያፍሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት አካባቢ ስለ ሃይማኖታቸው ባይታወቅ የሚመርጡ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔዳቸው ባይሰማ ደስ የሚላቸው ኒቆዲሞሶች ብዙኃን ናቸው፡፡ የኒቆዲሞስ ችግር በክርስትናው ማፈሩ ብቻ አልነበረም፡፡ ክርስትና የሚያመጣበትን መዘዝ መፍራቱም ጭምር ነው፡፡ አይሁድ ‹‹እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኩራብ ይውጣ›› የሚል ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ (ዮሐ. ፱፥፳፪) በዚህ ሕግ ምክንያት በጌታችን አምነው እንኳን ስለ እርሱ ለመመስከር የሚፈሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።›› (ዮሐ. ፲፪፥፵፪) ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጥቶ መማሩ እንዲታወቅ ያልፈለገውም ለዚህ ነበር፡፡ ለክርስትናው ምንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ለማድነቅ እንጂ መከራን ለመቀበል አልተዘጋጀም፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ሌላው የክርስቲያናዊ ሕይወት ፈተና ነው፡፡ ሐዋርያው የክርስትናችንን ዓላማ ሲገልጥ ‹‹ስለ እርሱ ደግሞ መከራን ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፡፡›› ብሏል፡፡ (ፊል. ፩፥፳፱) ብዙዎቻችን ክርስትናችንን እንፈልገዋለን ሆኖም በክርስትናችን ምክንያት ቅንጣት መከራ እንኳን እንዲነካን አንፈልግም፡፡ በእግዚአብሔር በማመን ውስጥ ፈተናም አለ፡፡ ራሳችንን በእውነት ክርስቲያን ነኝ ብለን ለመጠየቅ ብንፈልግ አብረን መጠየቅ ያለብን በእውነት መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ወይ ማለት ጋር ነው፡፡ በእግዚአብሔር በማመናችን ምክንያት ምን የከፈልነው ዋጋ አለ? ለእርሱ ብለን የተውነው ነገር ምንድን ነው? ለእሱስ ብለን ያጣነው ነገር ይኖር ይሆን? ምንም ነገር ከሌለ ክርስትናችን ገና ያልጠነከረ ነው ማለት ነው፡፡

ማዕከላዊው ኒቆዲሞስ 
ፈሪሳዊያንና የካህናት አለቆች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘውት እንዲመጡ ሎሌዎች ላኩአቸው፡፡ እነዚህ ሎሌዎች ጌታችንን ይዘው እንዲመጡ ቢላኩም በጌታችን ጣዕመ ትምህርት ተደንቀው ተመስጠው ሲማሩ ውለው ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፡፡ አይሁድያላመጣችሁት ስለ ምንድን ነው?›› ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹እንደዚህ ሰው ከቶ ማንም ተናግሮ አያውቅም›› ብለው መለሱ፡፡ ይህን ጊዜ አይሁድ ተቆጥተው ሎሌዎቹን ‹‹እናንተ ደግሞ ሳታችሁ? ከአለቆች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእርሱ ያመነ ሰው የለም፡፡ ሕዝቡም ያመነበት ሕግ የማያውቅ ርጉም ስለሆነ ነው›› ብለው ገሠጹአቸው፡፡ እናንተ ያመናችሁት ባለማወቃችሁ ነው ከእኛ ከአዋቂዎቹ ማን በእሱ አመነ? ብለው ሊያሸማቅቋቸው ሞከሩ፡፡ ይህን ሁሉ ሲሆን የማታው ተማሪ የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ እዚያ ቆሞ ነበር፡፡ ከአለቆች መካከል በጌታ ያመነ የለም ሲባል እየሰማ ነው፡፡ አሁን ክርስትናው ልትፈተን ነው፡፡ ደፍሮ እኔ አምኜአለሁ ብሎ መናገር ባይችልም ፈራ ተባ እያለ እንዲህ አለ ‹‹ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።›› እነሱ በተናገሩት ብቻ ለምን ትፈርዳላችሁ? እሱን ሳትሰሙ መፍረድ ተገቢ ነው ወይ? ማለቱ ነበር፡፡ አይሁድ እንደ ሎሌዎቹ ሁሉ ኒቆዲሞስን ማቃለል እንዳይችሉ የተከበረ መምህር ሆነባቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።›› ጌታችን ከገሊላ ናዝሬት መምጣቱን በመጥቀስ መሲህ ከገሊላ አይነሣም ብለው ሊያስተባብሉ ሞከሩ፡፡ ይህ ግራ መጋባት በሐዋርያው ናትናኤልም የታየ ነበር እርሱ ‹‹ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?›› ብሎ የጠየቀው መሲሁ ከይሁዳ ቤተ ልሔም እንደሚነሣ የተነገረውን ትንቢት በማየት ነበር፡፡ ጌታችን የተወለደው ከቤተ ልሔም ነው ያደገው ግን በገሊላ ናዝሬት በመሆኑ ነው ይኼ ሁሉ ውዥንብር፡፡ ኒቆዲሞስ ክርስትናውን በሌሊት ፈርቶ ጀመረ፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ነኝ ብሎ መመስከርና መግለጥ ባይችልም ቢያንስ አይሁድ ከአለቆች ማን በእርሱ አመነ? ብለው ሲዘብቱ ቢያንስ ድምፁን ለማሰማት ሞከረ፡፡ በጥያቄ አስጨንቆም በዚያች ዕለት ስብሰባውን በተነው፡፡.

ፍጻሚው ኒቆዲሞስ 
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል መከራ ዓለምን የማዳን ሥራውን ፈጸመ፡፡ በዚህ የመከራ ወቅት በዋለበት የዋሉ ባደረበት ያደሩ ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር በፍርሃት ተበተኑ፡፡ ነፍሱን ከሥጋው ተለይቶ ከመስቀሉ ሲወርድም አንድም ሐዋርያ አብሮት አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅት ኒቆዲሞስ እንደ ቀድሞው ሌሊት እስኪሆን አልጠበቀም፡፡ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ ከአርማትያው ዮሴፍ ጋር ሆነው የጌታችንን ሥጋ ወሰዱ፡፡ እንደ አይሁድ የአገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት፡፡ ሲገንዙት እያለቀሱ ነበር ‹‹ሞትከኑ መንሥኤሆሙ ለሙታን ደከምከኑ መጽንኤሆሙ ለድኩማን›› ‹‹ሙታንን የምታስነሣ ሆይ ሞትክን? ደካሞችን የምታጸናቸው ሆይ ደከምክን?›› እያሉ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ጌታችን በመለኮቱ ሕያው እንደመሆኑ አነጋገራቸው፡፡ በነገራቸው መሠረት ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት…›› የሚለውን በኪዳን ወቅት የምናደርሰውን ዓለም አቀፋዊ ጸሎት እያደረሱ ገነዙት፡፡ ኒቆዲሞስ ሲፈራ ቀስ እያለ ሲናገር የነበረውን ክርስትናውን በአደባባይ ገለጠ፡፡ ‹‹ልቡ ለጻድቀ ውኩል ከመ አንበሳ›› ‹‹ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ሳይፈራ ይኖራል ›› እንዲል ጠቢቡ በጌታ የደረሰ መከራ ቢደርስብኝ ሳይል ሥጋውን ተሸክሞ ገነዘ፡፡ ከምኩራብ ያስወጡኛል ብሎ የፈራው ኒቆዲሞስ ቤተ ክርስቲያን እንዳለች ስለተረዳ በድፍረት ክርስትናውን መሰከረ፡፡ ከሦስቱ የኒቆዲሞስ ክርስትና ደረጃዎች እኛ በየትኛው ላይ ነን? ስለ ሃይማኖታችንስ በየትኛው ደረጃ እንመሰክራለን፡፡ በጨለማ ነው? ፈራ እያልን ነው ? ወይንስ ያለ ፍርሃት




1 comment:

  1. Qalehiywet yasemalin egnanim kefitsumu niqodimos yidemiren

    ReplyDelete