Wednesday, April 30, 2014

‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታችሁን ለመታደግ በሃይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ›› አለቃ አያሌው ታምሩ

 ‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታችሁን ለመታደግ በሃይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ››  አለቃ አያሌው ታምሩ ሚያዚያ 23 ቀን 1983 የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአል በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በሚከበርበት ጊዜ በቦታው ተገኝተው ያስተማሩት ትምህርት፡፡

(አንድ አድርገን ሚያዝያ 23 2004 ዓ.ም )-  የዛሬ 22 ዓመት መንግሥትና ቤተክህነት ሁለቱም የተሳሳተ ጎዳና ላይ ሳሉ አለቃ አያሌው ታምሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ አውደ ምህረት ላይ ያስተማሩትን ትምህርት እንመልከት:: 

1983 ዓ.ም ደርግ በህዝቡ ላይ ሲሰራ የነበረው ግፍ ሁሉ ዘንግቶ ከመጣበት የውድቀት ጥሪ ለመዳን በከፍተኛ ደረጃ በተፍጨረጨረበት ዓመት ነበር ።። በቀደሙትዓመታት ሙልጭ አድርጎ ሲሰድባቸው የነበሩት ቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታት ይልቁንም እነ አጤ ቴዎድሮስን ፡ እነ አጤ ዮሐንስን ፣ አጤ ምንይልክን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እያነሳ የህዝቡን ወኔ መቀስቀሻ እና የዘመቻ ማዘጋጃ ዘዴ ብሎ ይዞ ነበር።። ነጋ ጠባ ስለ እነዚህ ቀደምት ነገስታት ጀብዱና ሀገር ወዳድነት አትንኩኝ ባይነት ብዙ ይባል ነበር። ሚያዚያ 23 ቀን 1983 የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአል በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በሚከበርበት ጊዜ አለቃ አያሌው ታምሩ በቤተክርስቲያኑ ተገኝተው እንዲያስተምሩ ተጋብዘው ነበር። እሳቸው ስለ ሰማዕቱ ተጋድሎና በሃይማኖት ስላገኝው የድል አክሊል ዘርዝረው እንዲህ ብለው አስተማሩ።


‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታችሁን ለመታደግ በሃሃይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ ፡ የቴዎድሮስ ነኝ የምንሊክ ነኝ የዮሐንስ ነኝ ማለት ጉራ መንዛት አያዋጣም። እነርሱ በጊዜአቸው መስራት የሚገባቸውን ሰርተው የማይጠፋ ስም ተክለው ሄደዋል። ዛሬም እናንተ የራሳችሁን ግዴታ መወጣት አለባችሁ፡፡ ቤተመንግሥትና ቤተክህነት ተባብረው የካዱት እግዚአብሔር ፡ በድለውናል ጨቁነውናል ብለው ያንቋሸሿቸውን ነገሥታትን ስም ዛሬ የጦርነት ነጋሪት መጎሸሚያ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም ፡ እናንተም እነሱ የሚሏችሁን ተከትላችሁ ራሳችሁንና ሌላውን ወገናችሁን መጨረሻ ወደ ሌለው እልቂት መክተት  የለባችሁም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከግራ ከቀኝ የሚጎሰመው የጦር ነጋሪት አገራችንንም ራሳችንንም ወደ ማያባራ ተጨማሪ መከራ የሚያስገባ ነው ። ንስሀ አልገባችሁም የበደላችሁትን እግዚአብሕርን ይቅርታ አልጠየቃችሁም ፡፡  ባለፈው 17 ዓመት የተሰራው በደል ከባድ ነው፡ እግዚአብሔር ጨርሶ የለም ተብሎ ተክዷል መንግሥት ህዝብም ተባብረው ካዱት ፤ መንግሥት ‹አሮጌዋ ቤተክርስቲያን ትውደም ፡ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ የለም› ብሎ በካድሬዎቹ አማካኝነት ሰበከ ፤ ብዙ ህዝብም እግዚአብሔርን ክዶ በሶሻሊዝም ጸበል ተጠመቀ። በለውጥ ስም ልጆች ወላጆቻቸውን ፡ ወንድም ወንድሙን ገደል ። እናቶች የልጆቻቸውን እርም በሉ ብዙ እልቂትም በሀገሪቱ በሞላ ተካሄደ ። ቤተ ክርስቲያን በራሷ ካህን ተዋረደች ። ካህናት የፖለቲካ ካድሬዎች፣ የአብዮት ጠባቂዎች ሆነው ሰሩ። በእጃቸው የወገኖቻቸውን ደም አፈሰሱ ። ደም ባፈሰሱበት እጅ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የወልደ እግዚአብሔርን ስጋው ደሙ አቀረቡበት ። ጳጳሳት መምህራን ሶሺያሊዝምና ክርስትና አንድ ናቸው ፤ ማርክስ እንዲህ አለ ፤ ሌኒን እንዲህ አለ ብለው በእግዚአብሔር እና በቤተ ክርስቲያን ላይ አፌዙ ከግፈኞች ጋር በአደባባይ በየፖለቲካ ሸንጎ ተሰልፈው የግፍ ድግስ አድናቂዎች ሆኑ ፤ በቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ በስመ ማርክስ ኤንግልስ ወሌኒን እየተባለ ፌዝ ተነገረበት ። እግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ አዘነ ። የህዝቡም የመንግሥትም ልብ ባለመመለሱ አሁንም ወደ ተከታይ አዘቅት እየወረድን እንገኛለን። ስለዚህ እዘኑ ፣ ልባችሁን በፍጹም ንስሀ ሀዘን ለእግዚአብሔር ስጡ›› በማለት ነበር ያስተማሩት፡፡

ጊዜውን የደረሳችሁበት ታውቁታላችሁ ፡  ህዝቡም ፤ ቤተክህነቱም ሆነ መንግሥት አንድ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ያመጹበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በመላው ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በመቶ ዓመት ተከስተው የማያውቁ በርካታ ነገሮች በ17 ዓመት ተከናውነዋል፡፡ አሁንም በቤተክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለው ተጽህኖ ከሰዎች ጆሮ የማይገባ እና የማይሰማ አይደለም፡፡ በእምነት ያለ ሰው ስለ ቤተ ክርስቲያን ብሎ መቃወም ያለበትን ነገር መንግሥትን ሳይፈራ መቃወም መቻል አለበት የሚል እምነት አለን። አቡነ ሺኖዳ ከ30 ዓመት በፊት የማርቆስ መንበር ላይ ከተሰየሙ በኋላ ከግብጽ መንግሥት ጋር ከፍተኛ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ አቡነ ሺኖዳ በጊዜው የግብጽ መንግሥት በቤተክርስቲያናቸው ላይ እያደረገው ያለውን ነገር በግልጽ ተቃውመዋል፡፡ ይህ አካሄዳቸው ያልተመቸው የወቅቱ የግብጽ መሪ አንዋር ሳዳት ከፓትርያርክነት ወንበር  አንስቶ አሁን የተቀበሩበት ገዳም በግዞት እንዲቀመጡ አድርገዋቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ስለሚጠብቋቸው ህዝበ ክርስትያንና ስለ ቤተ ክርስቲያን ብለው ግዞቱን በደስታ ተቀብለውታል፡፡ ይህ የሚያሳየን ከአምላክ የተሰጣቸውን የበጎች ጠባቂነታቸውን ማንንም ሳይፈሩ እንደተወጡ ነው ። አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ በዚያን እሳት ዘመን ፡ ካድሬዋች የሰውን ነፍስ ከዶሮ ነፍስ አሳንሰው በሚመለከቱበት ወቅት ፣ አይደለም ሰው ከአንደበቱ ቃል ተናግሮ አስበሀል ተብሎ ተዘቅዝቆ በሚገረፍበት በግፍ በሚገደልበት ሰዓት ፣ በዚያን አስቸጋሪ ወቅት በአውደ ምህረት ላይ ቆመው ህዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት ማንንም ሳይፈሩ ማንንም ሳያፍሩ ስለ አምላካችን ክብር ብለው ትክክለኛውን ቃል ምዕመኑን አስተምረዋል ።

አባታችን ሲያስተምሩ ‹‹ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሃይማኖታችሁን ለመታደግ በሃይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ›› ብለው ደርግ ሊንበረከክ ኢህአዴግ መንበሩን ሊይዝ ሲል አስተምረዋል፡፡ ቀጥለውም ‹‹ቀደምት አባቶቻችን ስራቸውን ሰርተው አልፈዋል አሁን ያለነው ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት መቻል አለብን››ም ብለዋል ፡ ይህ ለዛሬ 22 ዓመት አማኞች ብቻ የተነገረ ብቻ ሳይሆን አሁን ላለነው ምዕመናን የሚስማማ መስሎ ይታየናል፡፡ ፈተናችን ሲከብድ እንጂ ሲቀል ለማየት አልቻልንምና ፣ ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው ፈተና ቢበረታብንም ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ሆነን የምዕመንነታችንን ሓላፊነት መወጣት መቻል አለብን ።

በወቅቱ አለቃ አያሌው ‹‹ንስሀ አልገባችሁም የበደላችሁትን እግዚአብሔርን ይቅርታ አልጠየቃችሁም ፡ባለፈው 17 ዓመት የተሰራው በደል ከባድ ነው።›› በማለት ተናግረዋል፡፡ አዎን ይህን ወደ እኛ ዘመን ብናመጣው ባለፉት 22 ዓመታት በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የተሰሩት ስራዎች በደሎች ብናስባቸው ጆሮ የሚያስይዙ ፤ ለማየት የሚከብዱ ነገሮች ተከናውነዋል፡፡ እግዚአብሔርም ምህረቱ የበዛ አምላክ ስለሆነ ፡ ለቁጣ የማይፈጥን አምላክ ስለሆነ ዝም ብሎ ይማራሉ ይስተካከላሉ ንስሀም ይገባሉ ብሎ አልፎናል፡፡ እኛም ንስሀ ገብተን ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለመቻላችን ፈተናችንን ከቀን ቀን እያባሰው ይገኛል ። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ደግሞ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? ብለው የሚጠይቁ ሰዎች እየበዙ ይገኛሉ ፣ የእኛም ጆሮዎች መልካም ያልሆኑ ነገሮችን መስማትን ተለማምደዋል፡፡

አለቃ አያሌው እንዲህም ብለዋል ፤ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በራሷ ካህን ተዋረደች›› ይህ አሁንም ምናየው ነገር ነው ፣ ጠላቶቻችን ከሩቅ የሚመጡ ሆነው አይደለም ፣ እዚህው አጠገባችን ያሉ ክደው ለማስካድ የተቃረቡ ሰዎች ናቸው፡፡ ለዘመናት ታይቶ የማይታወቅ ከስርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ የሆነ ሀውልት ፡ እኛን በመሰሉ ሰዎች ተሰርቶ የቀረበልን ጊዜ ፡ምዕመን በመንፈሳዊ አባቶች ላይ እምነት ያጣበት ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚ የማይሆንበት ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ጥቅማቸው በተነካ በጋሻ ጃግሬዎች የተገረሰሰበት ፣ ከብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ይልቅ የሌሎች ድምፅ ጎልቶ የሚሰማበት ፤ ያለ አግባብ የቤተ ክርስቲያኗን የጥምቀት ቦታ ያለ አግባብ የሚሸጥበትና ሌሎች ነገሮች እየተከናወኑ ያሉት ካህን ብላ ባስቀመጠቻቸው ሰዎች አማካኝነት ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን እየተዋረደች ያለችው ከሀገር ውጪ የጦር መሳሪያ ታጥቆ በመጣ ጦር አይደለም ፣ ስለዚህ የአባታችን ምክር በዚህ ዘመን የምንገኝ ምዕመናንም የሚመለከተን ይመስለናል ።

ጊዜው 1976 ዓ.ም የታህሳስ ገብርኤል በዓል በሚከበርበት ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የመንግሥቱ ኃ/ማርያም ምስል ያለበት ሐውልት ተሰርቶ ቆሞ ይታያል። አለቃ አያሌው በብስራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው እንዲያስተምሩ ተጋብዘው በዚያም ተገኝተው ነበር ። ቅዳሴ እና የታቦት ዑደት ከተፈጸመ በኋላ በቦታው ለተገኝው ብዙ ህዝብ ትምህርት መስጠት ጀመሩ ። ስለ በአሉ ታላቅነት አስተማሩ ከዚያም ቀጥለው ወደ ህዝቡ የእለት ህይወት በመግባት ፡ በጊዜው የነበሩ የሀገሪቱ መሪዎች የሀውልት መታሰቢያ ለማቆም የሚበቃ አንድም የረባ ነገር ሳይሰሩ ምስላቸው ያለበትን ሀውልት ማቆማቸው ከናቡከደነጾር ስራ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ፡ ምእመናን ለዚህ ሀውልት ሳይሆን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ብቻ ክብርን ሊሰጡ እንደሚገባ የሚገልጽ ቅኔ ለበስ ተግሳጽ ይናገራሉ። ይህ ከሆነ በኋላ መንግሥት ይዟቸው እንዲህ አይነት ነገር በአውደ ምህረት ላይ እንዳይናገሩ ማስጠንቀቂያም ተጨምሮላቸው ሊለቀቁ ችለዋል፡፡ እሳቸው ግን በጊዜው የተሰራውን ሀውልት በግልጽ አውግዘዋል ፤ የሰሩት ስራ ሳይኖር ሀውልት ማቆማቸው ተገቢ አይደለም ብለውም አስተምረዋል ፤ እኛም ሁሌም ማድረግ ያለብን ነገር ጊዜው ሳያልፍ በጊዜው ከስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የሆነን ነገር መቃወም መቻል አለብን ፡፡ ገዳሞቻችንን ሲነኩብን መቃወም መቻል አለብን ፣ እጃቸውን ቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ሲያስገቡብን መቃወም መቻል አለብን ፣ ስርዓተ ቤተክርስቲያን በውስጥም ሆነ በውጭ ሰዎች ሲናድ ስንመለከት መቃወም መቻል አለብን ፤ በጠቅላላ ቤተክርስቲያንና የቀደሙ አባቶቻችን ካስቀመጡልን መስመር የሚያስወጣ አካሄድ ስናይ ስንመለከት ስንሰማ ሁሌም ስለ አንዲት እምነታችን ብለን መቃወም መቻል አለብን ፤ ዝምታ ግን መስማማትን ይወክላልና ዝም ማለት የለብንም ፣ ዛሬ ዝም ብለን ያሳለፍነው ጉዳይ ነገ አድጎ እና ተመንድጎ መልኩን ቀይሮ ሲመጣ ‹ወይኔ የዛኔ ብቃወም ኖሮ› ብንል ‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኽ› ነው የሚሆነው ። አባታችን አለቃ አያሌው በወቅቱ የማይደፈረውን የመንግሥቱ ኃ/ማርያምን ሀውልት ነበር የተቃወሙት ፡ አሁን እኛ ቤተመንግሥትና ቤተክህነት ስህተት ቢሰሩ ፣ ሁለቱም በተሳሳተ ጎዳና ላይ ቆመው ብንመለከታቸው እኛም የእነሱ ተባባሪ መሆን መቻል የለብንም ።

ግብዓት ፡- ከአለቃ አያሌው ታምሩ የሕይወት ታሪክ


1 comment: