Thursday, April 17, 2014

በአዲስ አበባ ሊደረግ የታሰበው የፀረ ግብረሰዶማውያን ሰልፍ አሜሪካውያንን አስግቷል



(ሰንደቅ ሚያዚያ 08 2006 ዓ.ም) ፡- በአዲስ አበባ ግብረ ሰዶማውያንን በመቃወም ሊደረግ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የሚገኙ አሜሪካውያን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢምባሲው በድረ ገጹ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሳሰበ፡፡ ኢምባሲው ከሶስት ቀን በፊት ባወጣውና በድረገጹ በለቀቀው በዚሁ መግለጫው በአዲስ አበባ በሚገኙ ዜጎቹን ያስጠነቀቀው ሚያዚያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም የተቃውሞ ሰሰላማዊ ሰልፍ በሚደረግባቸው አካባቢዎ ላይ እንዳይገኙ እና ራሳቸውን ከማንኛውም ጥቃት እንዲከላከሉ ነው፡፡
ኢምባሲው ለማስጠንቀቂያው ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም የተባለው ተቋም ያተባብረዋል የተባለው ይኽው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ስሜታዊነት ሊንጸባረቅበት እና ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ሊኖር ይችላል ከሚል ስጋት የመነጨ ነው፡፡
ኢምባሲው ለዜጎቹ መረጃዎች ለመስጠት ድረገጽ ማዘጋጀቱ ያመላከተ ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎት የማያገኙ አሜሪካውያን የተለያዩ የስልክ ቁጥሮችን በአደጋ ወቅት እንዲጠቀሙ ጠቁሟል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የግብረሰዶማውያን መብት መከበር አለበት በሚል የምትሟገት ሲሆን በቅርቡ የዩጋንዳ መንግሥት ካወጣው የጸረ ግብረሰዶማውያን ጠንካራ ሕግ ጋር በተያያዘ በግልጽ  ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ  እስከማድረግ መዝለቋ  የሚታወስ ነው ፡፡የአዲስ አበባውን የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ በማድረግ ለዜጎቿ የሰጠችው ማስጠንቀቂያም ነገሩን ለማጦዝ ካላት ፍላጎት የመነጨ እንጂ በአዲስ አበባው ሰልፍ  አሜሪካውያንን ችግር ይገጥማቸዋል በሚል ስጋት አለመሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከወዲሁ እየተናገሩ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment