Monday, April 14, 2014

ርግብ ሻጮቹ

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
 ጌታችን ወደ ቤተ መቅደስ ከገባ በኋላ ሻጮችንም ሆነ ገዥዎችን አባርሯል፡፡ ወደ ርግብ ሻጮቹ መቀመጫ ከደረሰ በኋላ ግን  ገበታቸውን ገልብጦ ‹‹ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት›› ብሏል፡፡ በዚህም ንግግሩ ወንበዴዎች ያላቸው ‹‹ርግብ ሻጮች›› መሆናቸው ታውቋል፡፡
 
ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደተረጎሙት ‹‹ ርግብ›› የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ስለሆነች ‹‹ ርግብ ሻጮች›› የተባሉት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ሀብተ ክህነትን ለምድራዊ መኖሪያ ብቻ የሚገለገሉበት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ገበታቸውን ደርድረው በቤተ መቅደሱ አካባቢ ሲሸጡ ይኖራሉ፡፡ ክህነታቸውን፣ የተሰጣቸውን ጸጋና የቤተ ክርሰቲያን ኃላፊነት ሁሉ ለገንዘብና ለገንዘብ ብቻ የሚጠቀሙት ሁሉ የዘመናችን ርግብ ሻጮች ናቸው፡፡የእነዚህን ሰዎች ገበታ ጌታ ይገለብጠዋል፤ ያባርራቸዋልም፡፡ ‹‹ እውነት እውነት እላችኋለሁ አላውቃችሁም ›› ይላቸዋል፡፡


በርግጥ ይህ ነገር አገልግሎት ፈጽመው ከቤተ ክርስቲያናቸው ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ የሚቀበሉትን የሚመለከት እንዳልሆነም ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ‹‹ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሠር ›› ተብሎ የተጻፈላቸው አገልጋዮች ናቸውና አይመለከታቸውም፡፡ ዋናው ጉዳዬ ስለ ሻጮቹ  ስለሆነ ወደዚያው ጉዳይ ልመለስ፡፡

ርግብ ሻጮቹ እነማን ናቸው?በፈውስና በተአምራት ስም የቤተ ክርስቲያኒቱን ዐውደ ምሕረት ይዘው ንግዳቸውን የሚያጧጡፉትን አይደሉምን? በመንፈሳዊ ዛር ከብረው ሰውን ሁሉ በቅቻለሁ እያሉ ባለትዳሩን እያፋቱ፣ ዕጮኛሞቹን እየለያዩ በሀብተ መንፈስ ቅዱስ ስም የሚነግዱትን አይደሉምን? ቤተ ክርስቲያን በማሠራት፣ ገዳማትን በመርዳትና በመሳሰሉት ሰበብ አስባቦች እያሰባሰቡ የራሳቸውን ቤቶች የሚገነቡትን፣ ንግዳቸውን የሚያጧጡፉትን አይደለምን? በክህነትና በአገልግሎት ሰበብ ፖለቲካቸውን የሚቸረችሩትን አይደለምን ?በቤተ ክርስቲያን ልማት ሰበብ ራሳቸውን የሚያለሙትን አይደለምን? እኔን እግዚአብሔር ያመለክተኛል፤  እኔ በማዘዝህ ብቻ ሥራ እያሉ ከባለጸጎቹ ተጠግተው ቤት አሠርተው የቤተሰቡ የጸሎት አባት እየተባሉ በሀብተ መንፈስ ቅዱስና በበቁት ቅዱሳን ስም የሚነግዱትን የአንዳንድ ባለጸጎች የግል ጠንቋዮችን አይደለምን? የሰውን አለማወቅ ተጠቅመው ለንስሐ እንኳ ትልልቅ ገንዘብ የሚሰበስቡትን አይደለምን? በአገልግሎት ሰበብ የየራሳችንን ግዛት እያስፋፋን የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሰዎች የምናጠበውን አይደለምን? እስኪ ዛሬ በክህነቱ የማይነግድባት የተባረከው ማን ይሆን? የተሰጠችውን ትንሽ ጸጋ ሳይቀር ለጥቅሙ የማያመቻቻትስ? እረ ለመሆኑ ዛሬ በእኛ ዘመን ሰዎች በእጅጉ የሚከፋቸው መቼ ነው? በውኑ የቤተ ክርስቲያን ክብር ሲዋረድ ወይስ የእነርሱ ትንሽ ሲነካ? የእኛ ጥቅም የሚቆም ሲመስለን ወይስ የቤተ ክርስቲያን? ማን ይሆን ዛሬ ርግቡን የማይሸጥ? በየሰበካው ያሉት ጠቦች ምክንያታቸው ምን ይሆን? አንዱ ተባርሮ አንዱ የሚመጣበትስ ምክንያቱ?

ርግብ ጸጋ እግዚአብሔር እንደዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን የሚሸጥበት ዘመን ይኖር ይሆን? እኔ እንጃ! በርግጥም የርግብ ሻጮች ዘመን፡፡ ለዚህ ነው ጌታ በዚህ የተጠመዱትን ሁሉ የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ያለው፡፡ ምክንያቱም ሰዎቹ ወንበዴዎች ቢሆኑም የሚፈጸመው ተግባር መንፈሳዊ የሚያሰኝ የሚያስመስልም ቅባት ስለተቀባ ደግሞ ሕዝቡ አይለይምና ‹‹ ዋሻ ›› መደበቂያ፣ ማታለያ ለመሆን በቅታለች፡፡ ስለዚህ ዋሻ ያላት ግብራችሁ የወንበዴ ቢሆንም አንደኛ ክህነታችሁ ከእግዚአብሔር ስለሆነ እውነተኛ መስላችሁ ትኖራላችሁ ለማለት ነው፡፡አሁንም እየሆነ ያለው ይኸው ይመስላል፡፡ ጌታ ጅራፉን ገምዶ በሚመጣ ጊዜ ግን የሚቆመውን እንጃ፡፡


እርሱም ይህን አውቆ ይመስላል፤ ‹‹ እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም አብራችሁ እንዳትነቅሉ ተውት እስከ መከር ጊዜ አብሮ ይቆይ›› ሲል ያዘዘው፡፡ ልክ ነው ሁሉም እስከ እርሱ መምጣት በትዕግሥት ይጠብቃል፤ እንክርዳዱን ከስንዴው፣ ምርቱንም ከገለባው የሚለየው ባለመንሹ  እርሱ ነውና፡፡ልክ ነው እርሱ ገበታቸውን እስኪገለብጥ ድረስ ርግብ ሻጮቹ በቤተ መቅደሳችን ይኖራሉ፤ የዋሐን ምእመናንንም እግዚአብሔርን ያገኙ እርሱንም ያገለገሉ እየመሰላቸው ርግብ ሻጮቹን ሲያከብሩ ይኖራሉ፡፡ ወይ ርግብ ሽያጭ!!! ንግድ ፈቃድ የሌለበት፤ ግብርም ቫትም የማይከፈልበት፣የዘመናችን ምርጥ ንግድ ሆኖት አረፈ፡፡ ባካችሁ ርግብ ሻጮች! እረ እባካችሁ  ዋጋውን እንኳ ቀለል አድርጉልን? ደግነቱ ገበታችሁን ጌታ ይገለብጠዋል፡፡ ያኔ ማን ያድናችሁ ይሆን? በእውነት የምንሸጥ ሁሉ ወዮልን፡፡

6 comments:

 1. "በክህነትና በአገልግሎት ሰበብ ፖለቲካቸውን የሚቸረችሩትን አይደለምን? በቤተ ክርስቲያን ልማት ሰበብ ራሳቸውን የሚያለሙትን አይደለምን?... እረ ለመሆኑ ዛሬ በእኛ ዘመን ሰዎች በእጅጉ የሚከፋቸው መቼ ነው? በውኑ የቤተ ክርስቲያን ክብር ሲዋረድ ወይስ የእነርሱ ትንሽ ሲነካ? የእኛ ጥቅም የሚቆም ሲመስለን ወይስ የቤተ ክርስቲያን?"

  ድንቅ መልእክት! ዓምና ይኸን ጊዜ ገደማ ክብራቸው ትንሽ እንዳትነካ ሲሉ ቤተ ክሲያናችንን ለሸጧት ለነአባ እንቶኔ፤ ጥቅማቸው እንዳይቆም ብለው ላሻሿጧትም ለነጋሼ እንትና ትድረስ! ምናልባት ቢጸጸቱ እና የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለው ቤተ ክሲያናችንን ቢያስመልሱልን!

  ReplyDelete
 2. ርግብ ሻጭ ማቅ ነው ነጋዴ ነውና

  ReplyDelete
 3. Dn. Birhanu qale hiwot yasemalin,

  I wonder our Christianity. I usually read most of blogs, when there is something 'alemayi' 'alubalta' 'were' you can see a lot of responses and even argument about every single word. However, when the the message is Gospel, 'menfesawi timihirt,' there is no response at all.

  Gobez!!! which one is better for us????

  ReplyDelete
 4. kale hiewot yasemalin enidezih yalu wonidimoch yabizalin

  ReplyDelete
 5. God Bless you!!!
  Gin rigib shachochu yanebbut yihon? Geta hoy ayinachewun gilet.

  ReplyDelete
 6. በክህነትና በአገልግሎት ሰበብ ፖለቲካቸውን የሚቸረችሩትን አይደለምን

  ReplyDelete