Thursday, April 10, 2014

በለንደን ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ተፈጥሮ ለነበረው ችግር ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ‹‹ቄስ›› ብርሃኑ ብስራትን ከስልጣነ ክህነት መሻሩን አስታወቀ



  • ‹‹ቄስ›› ብርሃኑ የሚመሩት ቡድን ‹‹ፕሮቴስታንታዊ›› ዓላማ  እና አወቃቀር ያለው ‹‹መተዳደሪያ ደንብ›› አርቅቆ የቤተክርስቲያኗን ሃይማኖታዊ ልዕልና በሚጋፋ መልኩ ከእንግሊዝ ሀገር ምግባረ ሰናይ(Charitable Trust) ተቋም ምዝገባ አውጥቶ ሕንጻ ቤተክርስቲያኑን በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ(Private Limited Company) አስመዝግበው ለመቆጣጠር ሙከራ አድርገው ነበር፡፡


    • ‹‹ቄስ›› ብርሃኑ የሚመሯቸው ግለሰቦች በጠበቃቸው አማካኝነት ብጹዕ አቡነ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ ወደ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መጥተው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሰጡና በቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ እንዳይታዩ ለማድረግ የፍርድ ቤት እግድ አውጥተው ኢ-ክርስቲያናዊ የሆነ ሙከራ እንዳደረጉ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ 
    • ‹‹ካህኑ ኤጲስ ቆጶሱን አልታዘዘው ቢል(ቢንቀው) ፤ ብቻውን ቤተመቅደስ ቢሠራ ፤ ኤጲስ ቆጶሱም ሦስት ጊዜ ቢጠራው ትዕዛዙን ተቀብሎ መልስ ባይሰጥ፤ እሱ ከማዕረገ ክህነቱ ይሻር ፤ ተከታዮቹም ይሻሩ››(ፍመ ምዕራፍ 6 ፤ አንቀጽ 228 ፤ 3ኛ ረስጠብ 22)
(አንድ አድርገን 03/08/2006 ዓ.ም)፡-  የዛሬ 40 ዓመት ገደማ የርዕሰ አድባራት ለንደን ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በአውሮጳ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በብጹ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ መልካም ፍቃድ በአባ አረጋዊ ወልደ ገብርኤል(ቆሞስ) በኋላ በብጹ አቡነ ዮሐንስ አስተዳዳሪነት ለረጅም ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችውና ቀጥሎም በእንግሊዝ ሀገር እና በመላው ዓለም የሚገኙ የጽዮን ወዳጆች ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የዘወትር ጸሎት ፤ የጉልበትና የገንዘብ አስተዋጽኦ በአንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ሺህ የእንግሊዝ ገንዘብ በለንደን ከተማ ማዕከላዊ በሆነ ቦታ የራስዋ የሆነ ህንጻ ቤተክርስቲያን ገዝታ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የተሟላ አገልግሎት በመስጠት  ላይ ትገኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሕንጻው ክፍያ ከጠናቀቀ በኋላ ጥቂት ግለሰቦች ቤተክርስቲያኑን ከቅዱስ ሲኖዶስ ማዕከላዊ አስተዳዳር ፤ ከቃለ ዋዲው መመሪያ እና ትዕዛዝ አስወጥተው በግለሰቦች አደረጃጀት ሕንጻውን በግል ይዞታ ለመቆጣጠር ባወጡት የተሳሳተ ዕቅድና ዓላማ ምክንያት ችግር ተፈጥሮ መንፈሳዊ አገልግሎቱ በግፍ ተቋርጦ ቤተክርስቲያኒቱ ለዘጠኝ ወራት በላይ ያለአግባብ ተዘግታ ካህናት ምዕመናን በከፍተኛ ደረጃ ሲያሳዝናቸውና ሲያስለቅሳቸው ቆይቷል፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረው መንፈሳዊ እና ክርስቲያናዊ መንገድ ያልተከተለ ፤ ከመጠን ያለፈ እና መረን የለቀቀ ረብሻ እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በአብዛኛው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቦ በዓለም ላይ ያሉትን የቤተክርስቲያናችን ተከታዮች ሁሉ ያሳዘነ ፤ በስደት የሚገኝውን ማኅበረሰባችንን ገጽታ ያበላሸ አሳዛኝ ታሪክ ሆኖ የተዘገበ ተግባር ሲሆን ቄስ ብርሃኑ አስራት የዚህ ሕገ ቤተክርስቲያንን የጣሰ ፤ በቃለ ዓዋዲ የማይመራ የአመጽ ቡድን አስተባባሪና መሪ በመሆን ለችግሩ ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ በመሆናቸው መንበረ ጵጵስናውን እንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ያደረገው የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ‹‹ቄስ›› ብርሃኑ ብስራትን ከስልጣነ ክህነት መሻሩን አስታውቋል፡፡


ስልጣነ ክህነትን በሚሽረው ደብዳቤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የበላይ አካላት ፤ ሁሉም አህጉረ ስብከት ፤ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ፤ ካህናት ፤ ምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በግልብጭ ተላልፏል ›› በማለት መልዕክቱን ለሁሉም አስተላልፏል፡፡


ሙሉ መረጃውን ይህን በመጫን ያንብቡ ደብዳቤ 1 ደብዳቤ 2

2 comments:

  1. minale moyalem iyemetachu indi ayinet lebochin ina yebetekrstiyak zerafiwochin bitawardulin......are gif beztual bik beluln

    ReplyDelete
  2. እጅጉን ከእውነት የራቀ አርስዕስተ ዜና ነው።ለሕዝብ የተበተነው የመወያያ ረቂቅ ደንቡ ላይ የተጻፈው (Charitable Company Limited By Guaranty) የሚል ሆኖ ሳለ ያልተጻፈ ነገር(Private Limited Company) ብሎ ጽፎ ማውጣቱ ትክክል አይደለም እና እርማት ሊሰጠው ይገባል።

    ReplyDelete