Sunday, March 30, 2014

ሾልከው የወጡ መረጃዎች




(አንድ አድርገን መጋቢት 22 2006 ዓ.ም)፡- የዛሬ ሳምንት ገደማ በቤተክህነት አዳራሽ የማኅበረ ቅዱሳን ተቃዋሚዎች ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀውን የአስተዳደር መዋቅር ተቆጣጥሮ ለፖለቲካ ጥቅም ሊያውል ይፈልጋል›› በማለት የሚቃወሙ የአዲስ አበባ የደብር አስተዳዳሪዎች  ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ባደረጉትም ስብሰባ የስብሰባው የድምጽ ቅጂ ለጋዜጠኛ ተመስገን ለፋክት መጽሔት መድረሱን ተናግሯል፡፡ የስብሰባውን ሙሉ ክፍል በመቃኝት አንኳር ነጥቦች ፋክት መጽሔት ተሰብሳቢዎቹ ማኅበሩን በሚመለከት ያወጡት  የአቋም መግለጫ  በመጋቢት 21 እትሟ መሰረት እንዲህ አቅርበዋለች፡፡
  • የዋንኛ የመራሮቹ የባንክ አካውንት ይመርመር፡፡
  • የማኅበሩ ሒሳብ መንግሥት በሚመድበው የውጭ ኦዲተር ይመርመር፡፡
  • ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹን( ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸው ቀላልና ከባድ መኪናዎቹ ሳይቀሩ) ወደ ቤተክህነቱ ይዘዋወሩ፡፡
  • የንግድ ተቋማቱ (ትምህርት ቤት ፤ ሬስቶራንቶቹ ፤ ንዋየ ቅድሳት ማምረቻ እና ማከፋፈያውን) ያስረክብ፡፡
  • ከምዕመናን በቀጥጣም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚቀበለው አስራት እየፈረጠመበት ስለሆነ እንዳይቀበል ይከልከል፡፡
  • የግቢ ጉባኤ (በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) እርሱ በሚቀርጸው ትምህርት እንዳይወስዱ መስራት፡፡
  • ተጠሪነቱ ከዋና ሥራ አስኪያጅ ተነስቶ ፤ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ስር አንዱ ንዑስ ክፍል ይሁን…
  • ሌሎችም….
የባንክ ሒሳብ ይመርመር ብሎ መንግሥት በሚፈልጋቸው ሰዎች ላይ ከተነሳ ተጠርጣሪዎች ራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች ማዘጋጀት መቻል አለባቸው፡፡ እኛ እስከምናውቀው የሒሳብ ደብተሩ እንዲመረመር የሚፈለግ ሰው በሕይወት ዘመኑ ደብተሩ ውስጥ ተገኝቶ የማያውቅ ብር በአካውንቱ ገቢ ይደረግለታል ፤ ሰውየው ምንጩ የማይታወቅ ሀብት በማካበት በሚል ይከሰሳል ፤ ከዚያ የሒሳብ አካውንቱ በፍርድ ቤት ብሎክ ይደረግና ክሱ መስመሩን እንዲስት ያሰቡትን አላማ ማስፈጸሚያ ያደርጉታል ፡፡   
ቤተ ክርስቲያኒቱን ከስሯ የመናድ ስራ መንገዱን ከጀመሩት እኛስ በያለንበት ቦታ ምን እየሰራን እንገኛለን? አባቶች ‹‹አይሆንምን ትተሽ…›› አይደል የሚሉት … ለመቃወም ሳይሆን የአፍራሽ ግብረ ኃይሉን ጡንቻ ለመመከት ሁሉም በያለበት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል ፤ ይህ የአንድ ማኅበር ጉዳይ ሳይሆን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን የማፈራረስ ስም አጠራሯን የማጥፋት ሴራ ነው፡፡

አቡነ ማቲያስ ከአቡነ ጳውሎስ ይብሱ ይሆን?
ጋዜጠኛው አገኝሁት ባለው ሙሉ የድምጽ መረጃ መሰረት ከዚህ ሤራ ጀርባ በተቀረፀው ድምፅ ላይ ፓትርያርኩና መንግሥ በትብብር መቆማቸውን የሚያሳየው ፣ የተቃዋሚዎቹ አስተባባሪ መሰብሰቢያ አዳራሹን ለመጠቀም የቻሉት በአቡኑ መልካም ፈቃድ እንደኾነ ከመግለጽ በዘለለ ‹‹ቅዱስ አባታችን በዚህ ተቃውሞ ምክንያት ከሥራ የሚባረር የለም ፤ አይዟችኹ አትፍሩ ብለውናል›› በማለት ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከዚህ ግቢ አቅም ኖሮት የሚያስወጣን የለም እንጂ ካስወጡን መንግሥታችን ቸር ስለኾነ ከእርሱ ቦታ ተቀብለን የራሳችንን ቤተ ክርስቲያን እናቋቁማለን›› እና ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት አገልጋዮች ማኅበር እንመሠርታለን›› እስከ ማለት መድረሳቸው ከአገዛዙ ጋራ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ያመላክታል፡፡ ተመስገን ቀጥሎም በስብሰባው እንዲሳተፉ ከተቀሰቀሱት 169 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው መካከል የተገኙት የስምንት አድባራት አስተዳዳሪዎችና 150 ሰራተኞች ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
……………….
ዕንቁ መጽሔትት በበኩሏ ‹‹መካሪ የሌለው መንግሥት?›› በማለት “ሥርዐቱ አሁን በያዘው መንገድ ማኅበረ ቅዱሳንን ማፍረስ የሚሸጋገር ከሆነ ያለምንም ጥርጥር የተቃውሞ ጎራ ይጠነክራል፡፡ ይህም አገሪቱን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የአውራ ፓርቲ ሥርዐት ለአርባና ኃምሳ ዓመታት እመራለው ለሚለው ገዥው ፓርቲ ግብዓተ መሬት አፋጣኝ ምክንያት ሊኾን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ማኅበሩ ትውልዱ ሃይማኖቱን ተረድቶ ፤ ቤተክርስቲያኑን አውቆ ፤ ማንነቱን እንዲገነዘብና  በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ብቁ ዜጋ ሥርዐቱን ከአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ደምሮ ማየቱ አይቀሬ ነው››  የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ከእስልምናው የተቃውሞ ጎራ ጋር ትይዩ የኾነ መቧደን በመፍጠር አገሪቱ ውስጥ ቀውስ ሊቀሰቀስ ይችላል ይላሉ፡፡ ስለዚህ መካሪ እንደሌለው የእብድ ሥራ ከመሥራት በፊት ነገሮችን ማጤን ለመንግሥት ይበጀዋል ብለው የሚመክሩ ብዙዎች ናቸው›› በማለት ሃሳቧን አስቀምጣለች፡፡

1 comment:

  1. Abune Matyas looks even much more dependent on TPLF. The Patriark looks with very low level of confidence to make decisions without consulting TPLF. That is the problem.

    ReplyDelete