Saturday, March 8, 2014

ፓትርያርኩ የአመራርና ውሳኔ ሰጭነት አቅማቸው አጠያያቂ ኾኗል ተባለ


  • ‹‹ቅዱስነትዎም ከሥራ ጓደኞችዎ ጋር ከየት መጣህ ሳንባባል በአንድነት እየተመካከርን ነው ማገልገል ያለብን  ፤ ከዚያ ወርደን መገኝት የለብንም›› አቡነ ኤልሳ ለአቡነ ማትያስ ከተናገሩት የተወሰደ
(ፋክት የካቲት 29 2006 ዓ.ም)፡- ከዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ተኛ ፓትርያርክ ኾነው የተመረጡበት አንደኛ ዓመት በዓለ ሢመት ፤ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም የተከበረላቸው ብጹዕ  ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሕገ ቤተክርስቲያን ከሚታወቀው አስተዳደራዊ መዋቅር ውጪ ለአማካሪነት አቅርበዋቸዋል በተባሉት አካላትና ግለሰቦች ማንነት ሳቢያ በአንድ በቅዱስ ሲኖዶስ አባል ትችት ተዘነዘረባቸው፡፡
 
የፓትርያርኩ የመጀመሪያ ዓመት በዓለ ሢመት በተከበረበት ዕለት ማምሻውን በጠቅላይ ቤተ ክህነት በተዘጋጀ የራት መርሐ ግብር ላይ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙት የሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳ ‹‹እርስዎ ከማን ጋር ወርደው ነው እተማከሩ ያሉት?›› ሲሉ ፓትርያርኩን መጠየቃቸውና የምክር ቃል መለገሳቸው ታውቋል፡፡የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ዘመናቸውንና ቀራቢ ወንድማቸው መኾናቸውን ያወሱት አቡነ ኤልሳ ፤ አቡነ ማትያስ ከረዥም ጊዜ የውጭ ዓለም ቆይታ እና አገልግሎት በኋላ ለፕትርክና ክብር መብቃታቸው በይበልጥ እርሳቸውን ደስ እንደሚያሰኛቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ፓትርያርክ ከማን ጋር ነው ምክሩ?››  በማለት ወንድማዊ ነው ያሉትን ምክራቸውን የቀጠሉት ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማትያስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት የተቀበሉትን ታላቅ ኃላፊነት ከቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ጋር  በቅርበት እየተመካከሩ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ከዚያም ሲያልፍ ከቋሚ ሲኖዶስና አስፈላጊም ከሆነም የቅ/ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት መምከር እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡


‹‹ምክርዎት ከሌላ ጋር ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል›› ሲሉ ያሳሰቡት አቡነ ኤልሳ ፤ ፓትርያርኩ መዋቅሩንና ደረጃውን ጠብቀው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከመምከራቸው ባሻገር በአመራርነታቸውና ውሳኔያቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳረፈ ነው የሚባለውን የብሄርተኝነት ከበባም የሚያመላክት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ፓትርያርኩ በዓለ ሢመት የተከበረበት ዕለት የጻድቁ አቡነ ተክለሃ ማኖት መታሰቢያ መኾኑን ያዘከሩት አቡነ ኤልሳ ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ ከውጭ ከመጡ ሌላው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በመላው ሀገሪቱ እየተዘዋወሩ ሲያገለግሉ ‹‹ከየት መጣህ አልተባባሉም ፤ ዘር ጎጥ አልተጠያየቁም ፤ ቅዱስነትዎም ከሥራ ጓደኞችዎ ጋር ከየት መጣህ ሳንባባል በአንድነት እየተመካከርን ነው ማገልገል ያለብን  ፤ ከዚያ ወርደን መገኝት የለብንም››  በማለት ምክር አዘል ትምህርታቸውን አጠቃለዋል፡፡


የሊቀ ጳጳሱ ምክር አዘል ትምህርት ወቅታዊና ተገቢ መኾኑን ለፋክት የተናገሩት የበዓለ ሢመቱ ተሳታፊዎች ፤ ፓትርያርኩ በአማካሪ አቅርበዋቸዋል የተባሉት ግለሰቦች በስም በመጥቀስ ፤ እርሳቸው በንግግር ከሚታወቁበት መልካም አስተዳደርን የማስፈን ለሙስናና ብክነት  የተጋለጡ ብልሹ አሰራሮችን  በወሳኝ መልኩ የመቅረፍና የማድረቅ ጥረት ጋር የሚጣጣም ማንነት ጨርሶ እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡  ከወራት በፊት የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ‹‹እጅግ አስቸኳይ›› በሚል አቡነ ማትያስ ሲጠቀሙባቸው የቆዩት አነሳሽ ቃላት አሁን አሁን እየተዘነጉ የለውጥ እንቅስቃሴውን ለመምራትና ለማጠናከር የሚጣጣሩ ጳጳሳትንና ባለሙያዎች በአማካሪነት ከተጠጉት ግለሰቦች ጋር በተሳሰሩ የለውጡ ተቃዋሚዎች  በፓትርያርኩ ፊት በግልጽ የሚዘለፉበት ኹኔታ መኖሩን ጠጠቁሟል፡፡


የቤተ ክርስቲያኒቱ የተቋም ለውጥ ጥረቶች የፓትርያርኩን የላቀ የአመራር ክህሎትና የውሳኔ ሰጭነት አቅም  የሚጠይቁ እንደሆኑ የጠቆሙት ምንጮች ፤ ከጽናትና አረዳድ ሁኔታ ይታይባቸዋል በሚባለው በተፈላጊው አቋም ሁኔታ አለመርጋትና የአቅም ውስንነት ሊቃነ ጳጳሳቱና የመንግሥት አካላት ጭምር ጥያቄ ማንሳት መጀመራቸውን አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ኤልሳም ያልተጠበቀ ግልጽ ምክር ከዚህ ጥርጣሬ ሊመነጭ እንደሚችልና በቀጣይም በቅ/ሲኖዶስ መነጋገሪያ ሳይሆን እንደማይቀር በአስተያየት ሰጪዎቹ ተመልክቷ፡፡  
 የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። . . ." የሐዋሪያት ሥራ ፳ ፥ ፳፰

1 comment:

  1. Are we still with nationality? We thought Abune Matias will work to unite the Church! This is a dangerous experience for the church. "Dimet menkusa...." mehon yelebetm! "Zeregnenet yitfa!" Don't say, i am for "Apulon" or "Peter" or "Paul"....We are one! You divisive fathers "please see everyone as one". We are for one church!

    ReplyDelete