Sunday, March 23, 2014

የሃይማኖተኞችና የፖለቲከኞች ሕገወጥ ጋብቻ የሚፈጥረዉ ችግር


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐቢይ ጾም የሚዉሉት እሑዶች እያንዳንዳቸዉ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተአምርን የሚያስታዉስ ስም አላቸዉ፡፡ ለምናገረዉ ታሪክ መነሻ የሆነዉ አራተኛዉ እሑድም መጻጉዕ ይባላል፡፡ በዚህም ጌታችን በምድር ላይ በሽተኞችን የፈወሰበት ተአምራት፣ 38 ዓመት ያህል አንድ አልጋ ላይ ተኝቶ መዳኑን ሲጠባበቅ ከኖረ በኋላ በጌታ በተፈወሰዉና በተለምዶ ‹‹ መጻጉዕ›› (በሽተኛዉ  ማለት ነዉ እንጂ  የመጠሪያ ስም  አልነበረም)  እየተባለ  በሚጠራዉ ሰዉ ታሪክ  መነሻነት ይታሰባል፡፡  በወንጌል እንደተጻፈዉ  ጌታ ወደ በሽተኛዉ ከደረሰ  በኋላ አስቀድሞ  ልትድን ትወዳለህን ሲል  ጠየቀዉ፡፡  መልሱን ከሰማ በኋላም ‹‹ ተነሣ አልጋህን ተሸክመህ ሒድ››  ሲል አዘዘዉና  በሽተኛ ወዲያዉ  ተነሥቶ ድኖ  አልጋዉን ተሸክሞ ሔደ፡፡ ታዲያ በዐብዮቱ ዋዜማ አካባቢ በነበረዉ የመጻጉዕ እሑድ እንዲህ ሆነ ይባላል /ዮሐ 51-10/ ፡፡  በዕለቱ ንጉሡም በተገኙበት ቅዳሴዉ ከተቀደሰ በኋላ በተነበበዉ ወንጌል ላይ የሚያስተምሩት እስካሁን የሊቅነትና የእዉነተኛ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት መለኪያ ተደርገዉ ከሚጠቀሱት እጂግ በጣም ጥቂት የሀገራችን ሊቃዉንት አንዱ የነበሩት  መልአከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ ‹‹ተንሥእ ወንሣእ ዐራተከ  ወሑር፤  ተነሥ አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› በሚለዉ ኃይለ ቃል መነሻነት ትምህርቱን ይሰጣሉ፡፡ በጊዜዉ ነበርን፤ የተደረገዉን አይተናል ሰምተናል የሚሉ ሰዎች እንደ ነገሩኝ ንጉሡ በዚህ ትምህርት በጣም ተበሳጭተዉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ‹‹ አልጋህን ተሸክመህ ተነሥና ሂድ›› የሚለኝ እኔን ነዉ ብለዉ በጊዜዉ ከነበረዉ የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም አራማጅ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ጋር አገናኝተዉ ስለተመለከቱት የተሰበከዉ በሙሉ ወንጌል ሳይሆን አዲሱ ፖለቲካ መስሏቸዉ ነበር ይባላል፡፡ መልአከ ሰላም ሳሙኤልም ብዙ ሳይቆዩ ስለሞቱ ለአንዳንድ ሰዎች  ትምህርቱን ለሞታቸዉ ምክንያት አድርገዉ እንዲናገሩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

በርግጥ እንዲህ ዓይነት ነገር  የተጀመረዉ በዐጼ ኃይለ  ሥላሴ  ዘመን  አይደለም፡፡ ጌታችን  ራሱ በሔሮድስም  የተሳደደዉ በዚሁ ምክንያትም ብዙ ሕጻናት ያለቁት የርሱን መንግሥት የሚቀማዉ ስለመሰለዉ ነበር፡፡ ከዚያም  በኋላ አይሁድ ጌታን የከሰሱት ነገሩን ከፖለቲካ ጋር አያይዘዉ ነበር፡፡ ለመንግሥት ግብር አትክፈሉ ይላል ፣ በመንግሥት  ላይ  ዐመጽ  ያነሳሳል ፣…..  ምን  ያልተባለ  ነገር አለ ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ  በሁለት  ሺሕ  ዐመታት የክርስትና  ጉዞአችን ዉስጥ እዉነተኛዎቹ የሃይማኖት አባቶች ድርጊታቸዉ ሁሉ መንግሥትን መቃወም  ተደርጎ ስለሚቆጠር  አንዳንድ ጉድለት ያለባቸዉ ሆድ አምላኮች ከመንግሥታት ጋር ተለጥፈዉ በሚሠሩት ብዙ  ተንኮል ብዙ ደም ፈስሷል ፤ ብዙ ግፍም ተፈጽሟል፡፡ የሚያሳዝነዉ ከሁለት ሺሕ ዐመታትም በኋላ መንገዱ  ሳይለወጥ ይሔዉ እንገፋፋበታለን፡፡  ችግሩ ግን የፖለቲካና የሃይማኖት ግጭቶች ሳይሆን የሃይማኖተኞችና  የፖለቲከኞች  ሕገወጥ  ጋብቻ የሚፈጥረዉ ችግር ነዉ፡፡

 ፖለቲካ በየትኛዉም ርእዮተ ዓለም ይሁን ሕዝብን የማስተዳደርና ሀገርንና የሀገርን ጥቅም የማስጠበቂያ መንገድ  ነዉ፡፡ የርእዮተ ዐለም ልዩነትና ብዛት ሀገርንና ሕዝብን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚካሔድ የአስተሳሰብ ልዩነት፣ የፍልስፍና ልዩነት ሁሉ ለኔ እንደ ትራንስፖርት ልዩነት ነዉ፡፡ ሁሉም የራሱ ጠንካራ ጎንም ደካማ ጎንም አለዉ፡፡  አንድ ዐይነት አንኳ ብቻ ቢሆንም እንደ ሾፌሮቹ ፣ እንደ አብራሪዎቹ ወይም እንደ ነጂዎቹ አቅም ፣  እዉቀት ፣ ክህሎት  እና ሥነ ምግባርም ጭምር ይለያያል፡፡  እነዚህ ሁሉ በሰዉ ለሰዉ የተሰሩ በሰዉ የሚመሩ፣ የሚነዱ  ናቸዉ፡፡ በራሳቸዉ ፈቃድና ስሜት መሔድ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ፖለቲካም አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም  ፍልስፍና ስለሆነ ማደሪያዉም የሰዉ ጭንቅላት ነውና በግዘፍ አንየዉ አንጂ ልክ እንደ አዉሮፕላኑ፣ ባቡሩ፣ መርከቡ መኪናዉ ሁሉ በሰዉ ለሰዉ የተፈጠረ በሰዉም የሚመራ የተለያየም ሆነ ተመሳሳይ እንደየመሪዎቹ ሁኔታዉ  የሚለዋወጥ፣ የሚፈጠር፣ የሚያድግ፣ የሚሻሻል፣ የሚጠፋ የሚሞት፣ የሚጠቅም፣ የሚጎዳ ሐሳበ ሰብእ ብቻ  እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ስለዚህ የሚፈጥሩት ሰዎችም አንዳንዶቹ ከሃይማኖት፣ አንዳንዶቹ ከአለማመን፣ አንዳንዶቹ  ከፍልስፍና፣ አንዳንዶቹም ከምጣኔ ሀብታዊና ከመሳሰሉት ተነሥተዉ መሆኑ የታወቀ ነዉ፡፡  ስለዚህ  ፖለቲካ  ‹‹ፖለቲካ›› በተባለ ኮረጆ የተጠረቀ ወይም በዚህ ስም የምንጠራዉ ርእዮተ ዓለሙ ምንም ይሁን ምን ዓላማዉ  ሰዎችን በተስማሙበትም ይሁን በተለያዩበት በምድር ላይ ማስተዳደር የሆነ ሥርዓተ መንግሥት ነዉ፡፡ ፖለቲከኛም ሥራዉ በአመነበትና በተቀበለዉ ርእዮተ ዓለም መንግሥት መሥርቶ ሰዎችን በምድር ላይ  ተመችቷቸዉ  እንዲኖሩ  የሚቻለዉን  ሁሉ  ማድረግ ነዉ፤ ቢሳካለትም ባይሳካለትም፡፡

ሃይማኖት ደግሞ ሰዉ በተረዳዉና በአመነዉ መንገድ ከሞት በኋላ ያለዉን ሕይወት እያሰበ በምድራዊ ሕይወቱ የሚተገብረዉና ከአምላኩ የሚኖረዉ መንፈሳዊ ግንኙነት (እምነትና አምልኮነዉ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ደግሞ የመገለጥ ሃይማኖት ነዉ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አንደኛ በጊዜ ቦታ የማይወሰን (beyond  space-time)  ዳግመኛም በሁሉም ቦታ ያለ  (Omnipresent)  ረቂቅ መንፈስ ስለሆነ ሰዉ ሊያየዉ አይችልም፡፡ ለዓለም መፈጠርም ብቸኛዉ አድራጊ (ultimate cause)  እርሱ ስለሆነ ሊደረስበት የሚችል(discoverable)  አይደለም፡፡  ስለዚህ ልናዉቀዉ  የምንችለዉ እርሱ  ራሱ ስለራሱ የነገረንን ያህል ብቻ ነዉ፡፡  መጽሐፍ  ቅዱስም እግዚአብሔር  በተገለጠላቸዉ  ነቢያትና በሥጋ በተገለጠ ጊዜ  በአስተማራቸዉና በሾማቸዉ  ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት  በሰዉ ቋንቋ የተጻፈ መለኮታዊ ሐሳብ፣ ትምህርት፣ ምክር፣ ምሥጢረ ሃይማኖት ነዉ፡፡ ዓላማዉም ሰዎችን ከሞት  በኋላ ስላለዉ ዘላለማዊ ሕይወት በዚህ ምድር እያሉ እግዚአብሔር በገለጠዉ መንገድ ብቻ ማዘጋጀት ነዉ፡፡  በርግጥ  በምድራዊ ሕይወታችንም  ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነትም ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም ይሕ  ግንኙነታችንና  አኗኗራችን  ለሰማያዊ ሕይወታችንም መሠረት ስለሆነ፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት መሪ የሆነ አንድ ክህነት  ያለዉ  ሰዉም ዓላማ በሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ሰዎችን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ማዘጋጀት ብቻ ነዉ፡፡

በአጭሩ ሃይማኖት ሐሳበ እግዚአብሔር ፖለቲካ ደግሞ ሐሳበ ሰብእ፤ የሃይማኖት ዓላማዉ ሰዎችን ለመንግሥተ  ሰማይ ማዘጋጀት የፖለቲካ ደግሞ ሰዎችን በምድራዊ ሕይወታቸዉ እንዲመቻቸዉ ማድረግ ሲሆን የሃይማኖት አባት ስለ  እግዚአብሔር መንግሥት በምድር የሚሠራ የእግዚአብሔር ወኪል ሲሆን አንድ ፖለቲከኛ ደግሞ ስለቆመለት ምድራዊ  መንግሥት እየሰበከ ሕዝብን ለማስተዳደር የሚሠራ የመንግሥት ወኪል ነዉ፡፡ ስለዚህ ሃይማትና ፖለቲካ ሳይጣሉና ሳይጋጩ  ነገር ግን ሳይገናኙና ሳይዋሐዱም እንደ ትይዩ መስመሮች (parallel lines) የራሳቸዉን መም  ጠብቀዉ  ሊኖሩ የሚችሉ  ነገሮች ናቸዉ፡፡  ይህ ማለት  ግን ፖለቲከኞች  ክርስቲያን አይሆኑም ሃይማኖተኞችም  ስለሚያስተዳድራቸዉ  መንግሥት  ስሜትና ምላሽ  አይኖራቸዉም  ማለት አይደለም፡፡

አሁን እነዚህን ሁለቱን የሚያገናኟቸዉ ሰዎች ናቸዉ፡፡ ሊያስማሟቸዉም ሊያጣሏቸዉም የሚችሉት እነርሱ ናቸዉ፡፡  ምክንያቱም ሁለቱም የሚያድሩትም የሚኖሩትም በሰዎች ኅሊና ዉስጥ ነዉ፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትንም ሆነ ፖለቲካን በኅሊናቸዉ ያሳደሩት ሰዎች የተረዱና ሌላ ርካሽ ጥቅምን የማይፈልጉ እውነተኞች ከሆኑ ሁለቱም ሰዉን በምድር  ሊጠብቁትና በሰላም ሊመሩት ለሰማዩም እንዳመነበት ሃይማቱን ይዞ ሊያኖሩት ይችላሉ፤ ይገባቸዋልም፡፡  ፖለቲከኞች ርቱዕ ሃይማኖተኞች በሚሆኑበት ጊዜ ዉክልናቸዉ እግዚአብሔራዊ ጠባይን  ስለሚይዝ ፍትሕ ርትዕ  አያጓድሉም፡፡  ምክንያቱም የሚያምኑት እግዚአብሔር ለሚያምንበትም ለማያምንበትም፤ ለኃጥኡም ለጻድቁም  ፀሐይን እንደሚያወጣዉ ፣ ዝናምን እንደሚያዘንመዉ፣ መግቦቱንም እንደማያጓድለዉ ልክ እንዲሁ ፈሪሃ  እግዚአብሔር ያለዉ መሪም በመንግሥታዊ አስተዳደሩ ዉስጥ ላሉት የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን  የእርሱን የፖለቲካ  ርእዮተ ዓለም ለማይከተሉም ጭምር ያለ አድሎ እንደ እግዚአብሔር ያስተዳድራል፡፡ ሌላዉ  ቀርቶ መሪዉ አድልቶ ሌሎቹን በሃይማኖታቸዉ ምክንያት ቢበድል ይህ ለመሪዉ ለራሱ ኃጢኣት  ይሆንበታል እንጂ በእግዚአብሔር የሚያስመሰግነዉ የሃይማኖት ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ እንግዲህ ሃይማኖት ለፖለቲካዉ  ሊያደርገዉ የሚችለዉ ትንሹ አስተዋጽኦ ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ ሃይማኖተኛ ፖለቲካን የሚርቀዉና የሚፈራዉ ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ የሚያስኮንነዉም ፖለቲከኛ መሆኑ ሳይን ፖለቲከኛ ሆኖም ሆነ ሳይሆን የሚሠራዉ ሥራ ነዉ፡፡ ሥራዉ ንጹሕና ትክክል እስከሆነ ድረስ ግን እንዲያዉም ፖለቲከኛ ሆኖ ሀገሩን ማገልገሉ የበለጠ ጽድቅ ይሆንለታል እንጂ የሚያስወቅሰዉ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ፖለቲከኞች እንዲህ ዓይነቱን ርቱዕነት ስለሚፈሩት  ሃይማኖትን በምልዓት ሊሰሙት ይፈራሉ፡፡

ልክ እንዲሁ የፖለቲካን አስፈላጊነት በአግባቡ የተረዱ የሃይማኖት መሪዎች መኖራቸዉ ጠቀሜታዉ እጂግ ብዙ ነዉ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዉስጥ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች በርዕዮተ ዓለም አንድነት እንደሚገናኙ ሁሉ ልክ  እንዲሁ ደግሞ የተለያየ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ያላቸው ሰዎች በሃይማኖት አንድነት ምክንያት አንድ የሃይማኖት  ተቋም ውስጥ ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ቤተ ከርስቲያኒቱ የሁሉም እናት ናት፡፡ መልካም እናት ገበሬውንም ፣ ነጋዴዉንም፣ የተማረዉንም ያልተማረውንም ልጇን አኩል እንደምትወድና በኑሮ ምርጫ፣ በሥራ፣  … ቢለያዩ በእናትነት አንድ አድርጋ አገናኝታ ቢጣሉም ዳኝታ እንደምታኖራቸዉ ቤተ ክርስቲያንም ለፖለቲከኞች እንዲሁ ናት፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡና ሲገቡ (በእኛጫማቸዉን አውልቀዉ እንዲገቡ እንደምታደርገው ሁሉ  እንደዚሁ ፖለቲካዊ አሳባቸዉን ትተዉበዚያ ለመቀስቀስና የራሳቸዉ ደጋፊ ለማድረግ እንዳይሠሩ እየተቆጣጠረችበእርሷ እንዲስተናገዱ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ በሃይማኖት ሥርዓቷ ጠበቅ አድርጋ የምትጠብቃቸዉ ከሆነማ ዐመጻና ክፋትን ስለሚያርቁ መሠረታቸዉም ማገልገል እንጂ የራስን ጥቅም ማካበት ስለማይሆን በተለያየ የፖለቲካ  ፓርቲ ውስጥ እንኳ ቢሆኑ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ታስችላቸዋለች፡፡ ይህ መሆን ቢችል ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሥራ ሳትሠራ ፖለቲከኞችን በማስተካከል ሀገርንም ሕዝብንም ጠቀመች ማለት ነዉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት መመጋገብና መጠባበቅ የሚገኝበት ቢሆን ኖሮ ቀጣፊዎች፣ ለመጣዉ ሁሉ አራጋቢ የሆኑና  ያልተፈጠረዉን ፈጥረዉ ተናግረዉና አጣልተዉ ጠቃሚ መስለዉ የሚኖሩ አጭበርባሪዎች ቦታ አይኖራቸዉም ነበር፡፡ ፖለቲካም እንደ ጭራቅ የሚፈራ፣ እንደ ኃጢአትም ያስኮንናል የማይባል፣ የሌቦች፣ የተንኮለኞች፣ የክፉዎችና የጨካኞች ተደርጎ አይታሰብም ነበር፡፡  ሃይማኖትንም ጥላና ጥግ አድርገዉ ለመጠቀም የሚያስቡ የሃይማኖት ለምድ የለበሱ ፖለቲከኞች አይቀልዱበትም  ነበር፡፡

 ችግር እየሆነና ግጭቱን የሃይማኖትና የፖለቲካ ያስመሰለው ግን ይህ አይመስለኝም፡፡ ቀደም ብየ በመግቢያየ እንደገለጽኩት የሃይማኖት አባቶችን ያህል ተሰሚነት የሌላቸዉ የፖለቲካ ሰዎች ሕዝቡን የሚያጡትና ሌሎች የሚጠቀሙበት ሲመስላቸዉ ፍርሃታቸዉ ያይላል፡፡ በርግጥ የፍርሃታቸዉ ምንጭ ይዘዉት በሚመሩበት የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ወይም በመሪዎቹ ላይ የሕዝባቸዉ አመኔታ ማጣት፣ ወይም ከሥልጣን ጥም የተነሣ ረጂም ዘመን እንኖርባቸዋለን  ብለዉ የመረጧቸዉ መንገዶች አዛላቂነት አለመኖር ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በሆነ ዘዴ ይህን ኃይል ለመጠቀም ያስባሉ፡፡ 
 ብዙ ጊዜ ሃይማኖቱን ጠብቆ ከሚኖረዉ አብዛኛዉ እነርሱን የሚቃወም ይመስላቸዋል፤ በዚህ ጊዜ በሃይማኖት  መሪዎች  በኩል  ሕዝቡን ለመያዝ ይሞክራሉ፡፡ ልክ እንደዚሁ ደግሞ ሃይማኖትን ሰውን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ማዘጋጃ መሆኑን ረስተው ከሃይማኖት ተቋማት የግል ጥቅማቸዉን ሊያጋብሱ የሚሯሯጡ ቀሳጥያን አይጠፉም፡፡ እነዚህኞቹም የሚመሩት የሃይማኖት ተከታይ ሲነቃባቸው ደግሞ የመንግሥትን ድጋፍ በማግኘት ያለ ሃሳብ  የሚፈልጉትን እያደረጉ ለመኖር ያስባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም ይሳሳቡና በሕጋዊና ርቱዓዊ መንገድ ከመረዳዳት ይልቅ ሁለቱም የቆሙለትን ዓላማ ትተዉ ጥቅምን፣ የሥልጣን መባለግንና የመሳሰሉትን ከወሸሙ በኋላ እንደገና ሁለቱ ሕገ ወጥ ጋብቻ ይፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካና ሃይማኖት ሳይጋቡ ፖለቲከኛዉና ሃይማኖተኛዉ በሚፈጽሙት  የተሳከረ የአስተሳሰብ ወሲብ ሕዝባቸዉን ሲያሳዝኑ የቆሙለትንም ዓላማ ሲያዋርዱ ይኖራሉ፡፡ 

ለአቅመ ሃይማኖት ያልደረሱ ፖለቲከኞችና ለአቅመ ፖለቲካም ያልደረሱ ሃይመኖተኞች የሚፈጽሙት የጋብቻ ዉል በቤተሰብ ሕጉ በወንጀልነት ያልተካተተ ቢሆንም በተፈጥሮና በፈጣሪ ሕግ የሚያስቀጣ ሕገ ወጥ ብቻ ሳይሆን ያላቻ ጋብቻም ነዉ፡፡  ይህ ጋብቻ ደግሞ ልጅ የሚያስገኝ ሳይሆን ለብዙዎቹ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ የሞተ  ጋብቻም ነዉ፡፡እነዚህ ያላቻና ሕገ ወጥ ጋብቻዎች ቢቆሙ ሃይማኖትና ፖለቲካ በመሠረተ ሐሳብ እንደ ትይዩ  መስመር የሚጓዙ በሕዝቡ ሕይዎት ደግሞ አንዱ ያጎደለዉን ሌላዉ የሚሞላበት (complimentary) ይሆኑ ነበር፡፡ በአምዱ ውሱንነት ምክንያት ያልዘረዘርኳውን ጠቀሜታዎችም ሊያስገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን በድብቅ እንደሚካሄድ የዚህ ዓለም ወሲብ ባለተገባ ግንኙነት ሰክረዉ ይቀራሉ፡፡ ፍች የተከለከለዉና የማይጠቅመዉም ለባልና ሚስት ነዉና እባካችሁ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ  ሆናችሁ ከመንግሥታዊም ሆነ ከከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ሕገወጥና ያላቻ ጋብቻ የፈጸማችሁ የሃይማኖት አገልጋዮች በተለይ መሪዎቹ ተፋቱልን፡፡ ሰዉን ሥጋዉንና ደሙን አቁርባችሁ አንድ ለአንድ አጋቡ ተባላችሁ እንጂ እናንተዉ በጥቅምና በሥልጣን ብልግና ቆርባችሁ ከፖለቲከኞች ጋር ተጋቡ  አልተባላችሁም፡፡ በዚህ መፋታት ይቻላልና እባካችሁ ተፋቱልን፡፡  እናንተ ስትፋቱ እኛም በሕይወት እንኖራለን፡፡  

5 comments:

 1. Oh! how impressing message it is?! Yes, if they can, it would have been better if they divorced. But, I don't think, they couldn't. I believe that they are merged in one or another way. If one asks to be isolated, the other will oppose and bring a sward. Unless and otherwise one of them passed accidentally, like Meles Zenawi and Abine Pawlos, they couldn't be isolated. The only good message cold be new engagements are recommended no to be started among politicians and religious leaders. Time will definitely come to end they intimacy. Both groups do not knowing they are playing with fire.
  Tesfa alegn from hageremariam

  ReplyDelete
 2. እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

  ክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ በ፲፱፻፱ ዓ.ም. “ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ” ብለው ከጻፉት ላይ ልጥቀስ፥

  “በእውነትና በሚገባ ነገር ሁሉ ይሉኝታ አትፍራ። በመንግሥት ሥራ ካልሆነ በቀር ፖለቲከኛ አትሁን።”

  ከኛ በፊት ኢትዮጵያ ብዙ ብልሆች ነበሩባት። በብልህነታቸው ነፃነቷ፣ ኃይማኖቷና አንድነቷ ተጠብቆ ለረጂም ጊዜ ቆየ። አሁን ባለንበት ዘመን ግን እንቧይ እንደሎሚ፣ እንክርዳድ እንደ ስንዴ፣ የገደል ማሚቶነት እንደ ጠቢብ ምክር ሲቀርብልን እናያለን። ጥበብ በመካከላችን እንዲኖር የአዜብ ንግሥት እንደሻተችው አድርገን ጥበብን ልንሻ ይገባል።

  ካላይ “የኃይማኖተኞችና የፖለቲከኞች ህገወጥ ጋብቻ” በሚል አርእስት የቀረበው ምክር ለኔ እንደሚገባኝ ከውጭ መጥቶ በየማእዘኑ የሚነፋልን ጥሩንባ ያነሰ ይመስል በተጨማሪ የሚያስተጋባ የገደል ማሚቶ ነው። ጽለ ኢትዮጵያ የሞጽፍ ሰው ኢትዮጵያ ምንድን ናት ብሎ እራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ይህስ ዴሞክራሲ የሚባለው ምንድን ነው። ኢትዮጵያዊ ነው? ካልሆነስ ማን አመጣው? ለምን መጣ? ፓርቲስ ምንድን ነው> ፓርቲዎች የሚሠሩት ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ምን ነበርች? ምን አጋጠማት? የት ደረሰች? አሁንስ የት ናት? የትስ ትሄዳለች። አሁን በኢትዮጵያ “ፖለቲካ” የሚባለው ምንድን ነው? አንድ ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ነበር በምጮት ያለስጋት መጠቀም ይችላል። ሰው አይን አለው ሊያይበት ይገባል። ሰው ጆሮ አለው ሊሰማበት ይገባል። እግዚአብሔር ውኃን አቅርቧል ዉኃ መጠጣት መልካም ነው። ነገር ግን ውኃ ሲጠጣ የኖረን ኢትዮጵያዊ የውጭ ሰው መጥቶ፣ ለምን ውኃ ትጠጣለህ። ውስኪ እየጠመቅህ ጠጣ እንጂ ውኃንማ አፍህ አይንካው ሲለው ኢትዮጵያዊው ሊያስተውል ይገባዋል። ለጊዜው ውስኪው ከውኃ ሊጣፍጥ ይችላል መጨረሻው ግን አያምርም።

  ይህ ጸሃፊው “ፖለቲካ” እያሉ ያቀነቀኑለት የውጭ አገር ሰዎች ያጠጧቸውን ውስኪ “ሴኪዩላር መስተዳድርን” ነው። ጸሐፊው ከውጭ አገር ሰዎች የሚሰሙትን ሁሉ እንደወረደ ከሚያስተጋቡልን ይልቅ መጀመሪያ የኛኑ ታሪክ በጥናት ቢያኝኩት ኖሮ እሳቸውም ብልሃቱን ያውቁና እኛም ያልፍልን ነበረ። መኮረጅ ማንንም አሳልፎለት አያውቅም። ያገሩን በሬ ባገሩ ሠርዶ እንዲሉ እኛ እራሳችንን እንጂ ሌሎችን መኦን አንችልም።

  ሴኪዩላሪዝም ምእራባዊ ነው የመነጨውም ማርቲን ሉተር ከተባለው አመጸኛ (protestant) አመለካከት ነው:: በመጀመሪያ ምእራባውያን የፈጠሩት “ሴኪዩላሪዝም” እራሱ (ሲፈጠር መስሎ ባይቀርብም) እምነት አልባነት ወይም (atheism) ነው። ኤቲይዝም ደግሞ በተራው በራሱ መንገድ ሌላው ጠፍቶ እምነት እራሱ ብቻ ሆኖ መቅረት የሚፈልግ “ኃይማኖት” ነው። ሴኪዩላሪዝም ፍልስፍናው ዴሞክራሲ ነው ሲባል በመዳረሻው በተለይ ክርስትናን ያጣፋል። በርግጥ ነው በቀጥታ ክርስትና ይጥፋ ላይል ይችላል ነገር ግን ክርስትና እንዳይኖር የሚያደርጉ የጥፋት መሠረቶችን ድምጹን በጩኸት ሳያሰማ ይጥላል። በተለይ ኢንላይትመንት የተባለው የምእራባውያን ጉዞ ሴኪዩላሪዝምን ያደራጀው ክርስትናን እንዲያጠፋ በማሰብ ነው። በተለይ ደግሞ ምእራባውያን የሌሎች አገሮችን መልካዓ ምርድርና የክርሰ ምድር ኃብት በቀላሉ ለመውሰድ ወይም ለመንጠቅ ሴኪዩላሪዝምና ዴሞክራሲን ሌሎች ህዝቦች የተሳሰሩበትን አንድነት መበተኛ መሣሪያ አድርገው ነው የተጠቀሙባቸው። ርካሽ ሸቀጦቻቸውን ለመጣልና ውድ ሃብቶችን ለመመጥመጥ ሴኪዩላሪዝም አይነነተኛ መሣሪያቸው ነው።

  የኢትዮጵያ አስተዳደርስ ምን ይመስል ነበር? የኢትዮጵያ አስተዳደር የተዘጋጀው በእግዚአብሔር ነበር። ነገሥታቱን የምትቀባው ቤተክርስቲያን ነበረች። ቤተክርስቲያን ያልቀባችው (እግዚአብሔር ያልቀባው) ንጉሥ ሊያስተዳድር አይችልም። ክፉ የሚሠራ ንጉሥ የሚጠየቀው በእግዚአብሔር ህግ ነው። እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ የምትተዳደርበትን ህግ ያወጣቸው ቤተክርስቲያን ናት። የኢትዮጵያ ህዝብ ክብር የመጣው መንግሥቷ የእግዚአብሔር ስለሆነ ነበረ። አሁን ምእራባውያን አዝለው አምጥተው እምነት የሌላቸውን ገዚዎች ስለጫኑብንና ኢትዮጵያንም ስለቆራረጡ በዚህም አወዳደቅ ምክንያትና በሚደረገው የመንገድና ህንጻ መሥሪያ የዶላር ችሮታ ምክንያት ብዙዎች አስተውሏቸው ስለተዛባ አሁን ጉልበት የያዘው አስተሳሰብ ትክክል መስሎ ይታያቸዋል። ይህ ስህተት ነው። ሴኪዩላሪዝም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የምትጠፋበት መንገድ ነው። ኢትዮጵያም ልትበታተን ትችላለች። አያዋጣም። ለኢትዮጵያ እግዚአብሔር ያዘጋጀው በአንድ ንጉሥ መመራትን ነው። አሁን በኢትዮጵያ የንጉሥ አስተዳደርን ማንም ሰው መልሶ ሊያመጣ አይችልም ነገር ግን በእግዚአብሔር የማይቻል ነገር የለም። የንጉሥ አስተዳደር ካለ ብላቴን ጌታ ኅሩይ እንዳሉት በመንግሥት ሥራ ካልሆነ በቀር ብዙዎች ፖለቲከኛ መሆን አያስፈልጋቸውም። ይህ ጊዜ ሩቅ አይደለም።

  ከላይ እንዳየነው ሲኪዩላሪዝም ሌሎችን አጥፍቶ ብቻውን መቅረት የሚፈለግ “ ኃይማኖት” ነው። ሴኪዩላሪዝም አሁን በኢትዮጵያ ነግሷል። እስልምናን ብንወስድ ደግሞ እንደሚታወቀው ሌሎቹን አጥፍቶ እራሱን ብቻ ማስቀረት የሚፈልግ “ኃይማኖት” ነው። እንግዲ አሁን አለንላችሁ የሚሉን ሊቃውንት ከላይ ጽሁፉን እንደከተቡልን አይነት ከሆኑ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሌሎቹን አንግሳ እርሷን ማጥፋት የምትፈልግ ታይታም ተሰምታም የማትታወቅ ኃይማኖት ሆነች ማለት ነው። አስደንጋጭ ጉዳይ ነው። እነሆ ባዷችን ቀርተናልና ጥበብ በመካከላችን እንዲኖር እንለምን።

  እግዚአብሔር ይመስገን።
  ኃይለሚካኤል።

  ReplyDelete
 3. Amlak Yibarkih!!!!! I have no word. right and timely message.

  ReplyDelete
 4. Dear Second Anonymous, please wake up and see the reality. We are no longer in the 20th Century. The Monarchy era will never come back. You better challenge the writer based on the reality than fantasy.

  With respect.

  ReplyDelete
 5. ሰዉን ሥጋዉንና ደሙን አቁርባችሁ አንድ ለአንድ አጋቡ ተባላችሁ እንጂ እናንተዉ በጥቅምና በሥልጣን ብልግና ቆርባችሁ ከፖለቲከኞች ጋር ተጋቡ አልተባላችሁም፡፡ በዚህ መፋታት ይቻላልና እባካችሁ ተፋቱልን፡፡ እናንተ ስትፋቱ እኛም በሕይወት እንኖራለን፡፡

  ReplyDelete