(አንድ አድርገን መጋቢት 23 2005 ዓ.ም)፡- ትላንት ለዛሬ ታሪክ ነው ፤ ዛሬ
የተጻፈውም እውነት ለነገው ትውልድ ታሪክ ሆኖ ይቀመጥለታል ፤ የዛሬ ታሪክን የኋሊት ፅሁፋችን ከአስራ አራት ዓመት በፊት በወርሐ ሐምሌ 1991 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
በኢየሩሳሌም በነበሩበት ወቅት ከ‹‹ጦቢያ መጽሔት›› ጋር ያደረጉት
ቃለ መጠይቅ ይሆናል ፡፡
- አቡነ ሺኖዳ ‹‹ዴር ሡልጣን በእጃችን እስካልተመለሰና የፍልስጤም መንግሥት ተመስርቶ እየሩሳሌምን እስካልገዛ ድረስ ኢየሩሳሌምን አልሳለምም›› ብለው በይፋ በጋዜጣ ላይ ጽፈዋል፡፡
- ግብጽ በመንግሥት ደረጃ ጉዳዩን ይዛ ሽንጧን ገትራ በዲፕሎማሲያዊ መስመር ከፍተኛ ትግል ስታካሂድ ኢትዮጵያ ግን በመንግሥት ደረጃ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብታ ባለመከራከሯ በእጃችን ገብቶ የነበረውን ፍትህ እንድናጣ ሆኗል፡፡
- የግብፅ መንግሥትና የግብፅ ቤተ ክርስቲያን በዴር ሡልጣን ጉዳይ እንቅልፍ የላቸውም፡፡ ግብጾች በጉዳዩ ክርክር ያደርጉ የነበረው ‹‹የአገር መሬት ነው የተወሰደው ፤ ሁኔታው የክብር ጉዳይ ነው›› ብለው ነበር፡፡
- ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስት ነው፡፡ ይህንን በአገር ውስጥም በውጭ ያሉትም ኢትዮጵያውያን ማወቅ ይገባቸዋል፡፡
- የእስራኤል መንግሥትም እንደ ግብፅ መንግሥት ሁሉ በጉዳዩ ላይ ክርክር ሆነ ውይይት እንዲደረግበት የሚፈልገው በመንግሥት ደረጃ እንጂ በቤተ ክርስቲያን ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይደለም፡፡
- የጎሳ በሽታው ከዚሁ ከአገር ቤት እንደ ተስቦ ወደ ኢሩሳሌም የተዛመተ ነው ማለት ይቻላል፡
ጦቢያ ፡- ብፁዕ አባታችን እርስዎ በአሁኑ ወቅት በኢየሩሳሌም ያሉት
የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ እንደመሆንዎ ኢትዮጵያ የእነዚህ ገዳማት
ባለቤት የሆነችው መቼና እንዴት እንደሆነ ሊያብራሩልኝ ይችላሉ ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ይሄ በመሠረቱ
መጠየቅ ያለበት ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ቦታው ክርስትና ከመግባቱ በፊት የኢትዮጵያ ይዞታ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እና የኢየሩሳሌም ግንኙነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከንግስት ሳባ ጀምሮ ጸንቶ ያለ ነው፡፡ በባህላችን
መሰረትና መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚነግረን የኢትዮጵያ ንግሥት የነበረችው ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ሄዳ ተሳልማ ስትመጣ ከወቅቱ ኢየሩሳሌም ንጉሥ ሰሎሞን ጋር ተገናኝታለች፡፡
ያን ጊዜ ድንኳኖቿ የተተከሉበትና ሰራዊቶቿ የሰፈሩበት ቦታ የጎሎጎታ አካባቢ ነው፡፡ በእኛ እምነትና ታሪክ የተጠቀሰው ቦታ ከዚያን
ጊዜ ጀምሮ ይዞታችን ነው፡፡ ሌላው የሚለውን አላውቅም፡፡ ከዚያ ሲያያዝ መጥቶ ከክርስትና እምነት መከሰት በኋላ ኢትዮጵያ ለኢየሩሳሌም
ቅርብ ሆና ነው የቆየችው፡፡ ብዙ አባቶች ጎለጎታ ለመሳለም ጌታ ትንሳኤ ያደረገበትንና የተወለደበትን ቦታ ለመሳለም ወደ ኢሩሳሌም
ይጓዙ ነበር፡፡ እዚያ ሲሄዱ የሚያርፉት አሁን ከጠቀስኩት ስፍራ ነው፡፡ ይዞታው በአጠቃላይ ዴር ሡልጣን ይባላል፡፡ ቃሉ አረብኛ
ሲሆን ትርጉሙ የነገሥታት የመሳፍንት ገዳም ማለት ነው፡፡ በተለይም የክርስትና እምነት ከተመሠረተ ከ5ኛው ክፍለ
ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ገዳም እየሄዱ ይቀመጡ ነበር፡፡ ገዳሙ በጣም ረዥም ታሪክ ያለው ነው፡፡
ጦቢያ ፡- እነዚህ ገዳማት ያሉበት መሬት ተገዝቶ ነው ወይስ በስጦታ
የተገኝ ነው ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ገዳማቱ ያሉበት ቦታ ከሰሎሞን
ጊዜ ጀምሮ ለኢትዮጵያ በስጦታ የተሰጡ ናቸው፡፡ እዚያ የሚገኙ ግሪኮችና
አርመኖችም ቦታ ያገኙት ገዝተው ሳይሆን በስጦታ ነው፡፡ ለእኛ ደግሞ የሃይማኖት ርስታችን ነው፡፡ ከዴር ሡልጣን ውጪ የተገዙ ሌሎች ቦታዎች
አሉን፡፡ ደብረ ገነት የምትባል ታላቅ ገዳም አለች፡፡ ቦታዋ ተገዝቶ ነው፡፡ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱ የተሰራችው፡፡
በታሪክ እንደሚታወቀው አፄ ዮሐንስ
በምፅዋ ፤ በኩአቲትና በዶግአሊ የሀገራችን ድንበር ለመድፈር ከመጡ
ባዕዳን ወራሪዎች ጋር ከፍተኛ ጦርነት አካሂደው ድል አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ጦርነቱን ያሸነፍሁ እንደሆነ ኢየሩሳሌም የሚገኝው ለጎሎጎታ
ገንዘብ እልካለሁ ብለው ተስለው ነበርና ድል ስለቀናቸው በምርኮ ባገኙት ገንዘብ ቦታው ተገዝቶ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲታነጽና በእመቤታችን
ስም እንዲጠራ አደረጉ፡፡
አጼ ምኒልክም አጼ ዮሐንስን ተከትለው
ሕንጻ ገዝተው ለገዳማቱ መተዳደሪያ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃን ሲባሉ የነበሩት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም እንዲሁ ህንፃ ገዝተው
ለገዳማቱ መተዳደሪያ አድርገዋል፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱም እንደ አባታቸው ለገዳሙ መተዳደሪያ ሕንፃ አሰርተው አበርክተዋል፡፡
ከአጼ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ ይዞታው ለገዳማቱ
ሳይገባ እስከ አሁን በኢትዮጵያ መንግስት እጅ ይገኛል፡፡ከዚህ ታላቅ ሕንፃ በአሁኑ ጊዜ ሰባት አፓርታማ ለገዳሙ ተመልሶለታል፡፡
ሌሎችም ታላላቅ አባቶችና መሳፍንቶች ታላቁ ጀግና ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ትልቅ ቤት ስጦታ አበርክተዋል፡፡ እነ ወ/ሮ አማረች
፤ እነ ወ/ሮ አልታዬ ፤ እነ ራስ ወልዱ ፤ እነ አፈንጉሥ ነሲቡ የመሳሰሉት እንዲሁ በበኩላቸው ለመነኮሳቱ መተዳደሪያ እያሉ ቤት
እያሰሩ ሰጥተዋል፡፡
ጦቢያ፡- የዴር ሡልጣን ገዳማት ባለቤትነት ጉዳይ ግብጽን ለዘመናት
ሲያወዛግብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? የግብጽ ጥያቄስ በምን ላይ የተመሰረተ ነው ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- እርግጥ
ነው የገዳማቱ ጉዳይ ለዘመናት ሁለቱን ቤተ ክርስቲያናት ሲያወዛግብ ቆይቷል ፤ አሁንም እያወዛገበ ይገኛል፡፡ ግብጾች “ዴር ሡልጣንንና አካባቢው የእኛ ነው መረጃ አለን” እያሉ ነው
የሚናገሩት ፡፡ እኛ ደግሞ ‹‹ገዳሙ ይዞታችን ለመሆኑ እጅግ በርካታ
ማስረጃዎች አሉን›› ነው የምንለው፡፡
በሃይማኖት ወልድ ዋህድ በማለት
አንድ ስለነበርን ግብጻውያኑ እዚያ እና ገዳም እየገቡ ከኢትዮጵያውያኑ
ብዙዎች የዐረብኛ ቋንቋ ስለማይችሉ መሬቱን እያታለሉ እንደወሰዱባቸው ነው የተመዘገበው፡፡ በዚህ ዓይነት ዘዴ ግብጾች ብዙ መሬት
ቆርሰው ወስደውብናል፡፡ አሁን በእጃችን የቀረው በጣም ጥቂት ቦታ ነው፡፡ ያቺን የቀረችዋን ይዞታችንን ለማሳጣት እንደገና እንወስዳለን
እያሉ ይህው ውዝግቡ 300 ዓመት በላይ ፈጅቷል፡፡ አሁን በክርክር ላይ ነው የምንገኝው ጉዳዩ በእስራኤል መንግሥት እጅ ተይዞ ነው
ያለው፡፡
ግብጾች የራሳቸው የሆነ ሰፊ መሬት
እዚያው አጠገባችን አላቸው፡፡ ይህ ቦታ ራሱ በጥንት ታሪኩ መሠረት ከሆነ የእኛ ይዞታ የነበረ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም
በቃን ስላላሉ በይዞታችን ሥር የቀረውን ለመጠቅለል ነው ሃሳባቸው፡፡ እኛ ደግሞ ‹‹ትክክል አይደላችሁም የወሰዳችሁት ራሱ የእኛ ነበር
፡፡ አሁን በእጃችን ያለውን ግን የፈለገው ነገር ቢመጣ እንሰጥም›› ብለን በመከራከር ላይ ነው የምንገኝው፡፡
ገዳሙ በአሁን ጊዜ በክርክር ላይ
ስላለና የማን መሆኑ ስላለየለት ምንም ነገር መስራት አልቻልንም፡፡ በዚህ ምክንያት መነኮሳቱ የሚኖሩት ተራ በሆኑ ጎጆዎች ውስጥ
ነው፡፡ ለእስራኤል መንግሥት ክብር ይግባውና ቁልፉን አስረክቦናል፡፡ የገዳሙ መግቢያ በር ቁልፍ ያለው በእጃችን ነው፡፡ በውስጡም
የመድኃኒዓለምና የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደሶች አሉ፡፡ ቦታው ጎለጎታ ደጃፍ ላይ በመሆኑና እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው ግብጾች
አይናቸውን ያሳረፉበት፡፡
ጦቢያ ፡- የእስራኤል መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው አቋም ምን ይመስላል?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የእስራኤል
መንግሥት ስለ ዴር ሡልጣን ያለው አቋም እንዳለፈው የዮርዳኖስ መንግሥት ነው፡፡ የዴር ሡልጣን ጉዳይ የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ የርስት ጉዳይ ነው፡፡ የቀድሞ የዮርዳኖስ መንግሥት
ሁኔታው በከፍተኛ ሁኔታ ነበር ሲመለከተው የቆየው፡፡ ክርክሩ ከቱርክ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ በቱርክ ጊዜ ዳኞችም ቱርኮች ነበሩ
፤ ኢትዮጵያውያንና ግብጾች ይከራከሩበት ነበር፡፡ ፍርዱ አንዳንዴ ወደ ኢትዮጵያውያን ያዘነብላል ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ግብጾች ያጋድል
ነበር፡፡
ዮርዳኖስ በንጉሥ ሁሴን ዘመነ መንግሥት
እ.ኤ.አ 1960 ዓ.ም በቀረቡት ማስረጃዎች ተመርምሮ መሬቱና ይዞታው
የኢትዮጵያ ነው ተብሎ ተፈርዶልን ነበር፡፡ ይሁንና ፍርዱን ተፈጻሚ የሚያደርግ አካል ለማግኝት አልተቻለም፡፡ ለአስፈጻሚው ዋናው
መሰናክል በወቅቱ በመካከለኛው ምስራቅ ታዋቂ የነበሩት የግብጹ ፕሬዝዳንት ጋማል አብዱልናስር በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሬታችን ተወርሷልና ገላግሉን
ብለው ያቀረቡት ተማጽኖ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ አቤቱታውን ተቀብለው ጉዳዩን ለመላው የአረብ መንግሥታት በማቅረብ ተጽህኖ በማሳደራቸው
ፍርዱ እንዲቀለበስ ተደረገ፡፡
ፓትርያርኩና ሲኖዶሱ የተቻላቸውን
ያህል ተረባረቡ ፤ ሳይሰሙ ቀሩ፡፡ ፕሬዝዳንት ጋማል አብዱል ናስር በዚያን ጊዜ ተሰሚ ሰው ስለነበሩ ለዮርዳኖስ ንጉሥና መንግሥት
ለአረብ ሊግ ባቀረቡት ይግባኝ የተሰጠው ፍርድ ተቀልብሶ ክርክሩ እንዲቀጥል ተደረገ ፡፡ ይህ እጅግ የሚያሳዝን ፍርደ ገምድል ውሳኔ
ሲተላለፍብን በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት የግብጽን ያህል ትኩረት ሰጥቶ የሠራው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡
ግብጽ በመንግሥት ደረጃ ጉዳዩን
ይዛ ሽንጧን ገትራ በዲፕሎማሲያዊ መስመር ከፍተኛ ትግል ስታካሂድ
ኢትዮጵያ ግን በባለስልጣናት ወይም በመንግሥት ደረጃ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብታ ባለመከራከሯ በእጃችን ገብቶ የነበረውን
ፍትህ እንድናጣ ተደረግን፡፡ ለዚህ የበቃው ጉዳይ የሃይማኖት ነው ተብሎ ሲሆን ግብጾች ግን ክርክር ያደርጉ የነበረው ‹‹የአገር መሬት ነው የተወሰደው ፤ ሁኔታው የክብር ጉዳይ ነው›› ብለው
ነበር ትኩረት ሰጥተው በመሟገት ውሳኔውን ያስለወጡት፡፡ ይህ ሁኔታ በዚያን ጊዜ ብቻ በተደረገ ክርክር አላበቃም፡፡ የግብጽ መንግሥት
የዴር ሡልጣንን ጉዳይ አሁን ድረስም ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየተከታተለው ይገኛል፡፡ እኔ እንደተገነዘብኩት የእስራኤል መንግሥትም
እንደ ግብፅ መንግሥት ሁሉ በጉዳዩ ላይ ክርክር ሆነ ውይይት እንዲደረግበት የሚፈልገው በመንግሥት ደረጃ እንጂ በቤተ ክርስቲያን
ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይደለም፡፡
ጦቢያ፡- በአንድ ወቅት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ የዴር ሡልጣን ጉዳይ በመንግሥት
ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ጥረቱ አሁን ቀዝቅዟል ማለት ነው?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- እንደተባለው
አምባሳደር ቆንጂት በጣም ጠንካራ ዲፕሎማት ስለሆኑ እዚያ ሳሉ ጉዳዩን በከፍተኛ ደረጃ አንቀሳቅሰውት ነበር፡ እንዲያውም የቀድሞ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት የዴር ሡልጣንን ሁኔታ እንዲገነዘቡ በማድረግ ጉዳዩን ከእስራኤል
መንግሥት ጋር እንዲነጋገሩበት እስከማድረግ አድርሰውት ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው ወደ ሌላ ስፍራ ሲቀየሩ ጉዳዩ አልቀጠለም፡፡
ሁኔታው ያዝ ለቀቅ አይነት ነገር ሆኖ ብልጭ ብሎ በኋላ ደግሞ ድርግም አለ፡፡ በወቅቱ በቀጣይ ጉዳዩን የሚከታተል ዐብይ ኮሚቴ በመንግሥትና
በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ቢሰየም ኖሮ ዛሬ አንድ ለውጥ ይታይ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ አሁንም የአገር ቅርስና ይዞታ መሆኑ ታውቆ
ከመንግሥትና ከቤተ ክርስቲያኑ የተወጣጣ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሊከታተለው ይገባል፡፡
እኔ ባለብኝ ሃላፊነት ሁኔታውን
በቅርቡ ለተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቤ ጉባኤው ተወያይቶበት የሚመለከታቸው የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን አካላት ያሉበት ኮሚቴ
አቋቁሞ ጉዳዩን መከታተል እንዳለባቸው የሚያሳስብ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ችግሩን ቤተ ክርስቲያን ብቻ ተከራክራ የማትዘልቀው ስላልሆነ
እንደ ግብጽ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጎን ቆሞ ግፊቱን መቀጠል እንዳለበት ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስት ነው፡፡ ይህንን በአገር ውስጥም
በውጭ ያሉትም ኢትዮጵያውያን ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ ግብፆች እንዲህ በዋዛ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ጳጳሳቱ ሆነ መንግሥቱ ገዳማቱን በተለያዩ
ዘዴዎችና ብልጣ ብልጥነት በእጃቸው በማስገባት በከፍተኛ ደረጃ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ሊለው
ይገባል፡፡ እነሱ እንቅልፍ የላቸውም፡፡
እዚህ ላይ አንድ የሚከነክነኝና
የሚያሳዝነኝ ነገር ስላለ ሕዝብም ማወቅ ስላለበት ሳልናገረው አላልፍል፡፡ የግብጽ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ “ዴር ሡልጣን በእጃችን እስካልተመለሰና
የፍልስጤም መንግሥት ተመስርቶ እየሩሳሌምን እስካልገዛ ድረስ ኢየሩሳሌምን
አልሳለምም” ብለው በይፋ በጋዜጣ ላይ የጻፉ መንፈሳዊ አባት መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ለመናገር የተገደድኩት ግብጾች
ምን ያህል እርቀት እንደሄዱና ዴር ሡልጣንን ለመያዝ ያላቸው ጽኑ ፍላጎት ለማሳየት ብዬ ነው፡፡ ይህን አቋም ከእኛ ጋር ስናወዳድረው የሰማይና የመሬት ያህል
ይራራቃል፡፡ ባጭሩ ብዙ አልታሰበበትም ማለት ይቻላል፡፡
ጦቢያ ፡- ከዚህ ሁሉ ክርክር መካከል የእስራኤል መንግሥት የወሰዳቸው
ገንቢ ርምጃዎች የሉም ?
የእስራኤል መንግሥት ምንም እንኳን
በዮርዳኖስ የተፈረደልን ፍርድ በግብጽ መንግሥት ተጽህኖ ግፊት ተቀልብሶ ክርክሩ እንዲቀጥል ማስለወጥ ባይቻልም ታላቅ ውለታ አድርጎልናል፡፡
ቀደም ሲል በእጃችን ያልነበሩትን የገዳማቱን መግቢያ በር ቁልፎች እ.ኤ.አ በ1972 ዓ.ም አስረክቦናል፡፡ በአሁን ጊዜ ቁልፎቹ
በእኛ እጅ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በኩል ባለውለታችን ቢሆንም ግልጽና የማያሻማ ፍትህ በማገኝቱ ረገድ ገና በመሆኑ ይህንን ካሉን በቂ
ማስረጃዎችን አኳያ ተመልክቶ ሚዛናዊ ፍርድ ይሰጠናል ብለን በከፍተኛ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ እስከ አሁን እንዳየነው
ከእኛ መንግሥት በኩል በቂ እገዛ ካገኘ የእስራኤል መንግሥት አመለካከት ጥሩ ነው፡፡ የዮርዳኖስ መንግሥትም ምንም እንኳን በግብጽና
በሌሎቹም ዐረቦች ግፊት ፈርዶልን የነበረውን ፍርድ ቢቀለብሰውም በወቅቱ በገዳማቱ ያሉት መነኮሳት መብራትና ውሃ አጥተው ሲሰቃዩ
መኖራቸውን በመገንዘብ እ.ኤ.አ 1960 ዓ.ም መብራትና ውሃ ያስገባ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡
ጦቢያ ፡- ዴር ሡልጣን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኤርትራም ይገባኛል የሚል
ጥያቄ አንስታለች እየተባለ ይወራል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው ? ከቃላት ባሻገር የገዳማቱን የዕለት ተዕለት ሥራ ለማደናቀፍ
የሚደረግ ሙከራስ አለ ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ይሄን
ነገር ከዚህ ቀደም አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተም የግል ጋዜጣም ዘግቦት ነበር፡፡ ይህ ነገር በተንኮል የሚነገር ነው የሚመስለኝ፡፡ እሰከ አሁን የኤርትራ መንግሥትም ሆነ የኤርትራ
ካህናት ዴር ሡልጣንን በተመለከተ በይፋ ያቀረቡት ጥያቄ አላጋጠመኝም፡፡ ዴር ሡልጣን በታሪክ የሰፈረው የኢትዮጵያ (አቢሲኒያ) ገዳም
ተብሎ እንጂ የኤርትራ ተብሎ ስላልሆነ የሚጠይቁበት መሰረት የላቸውም፡፡
እነሱ ኢትዮጵያ የሚለውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 40 ጊዜ የተጠቀሰውን ቃል ተጠይፈው ስለሆነ የተገነጠሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ተጋሪ
ሊሆኑም ሆነ ይገባናል ጥያቄ ሊያነሱ አይችሉም፡፡ እዚህ ላይ መጽሐፉ የሚለው ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ሐበ እግዚአብሔር›› እንጂ ኤርትራ ወይም አሜሪካ አይደለም፡፡ በመሆኑም ጥያቄውን
በአሉባልታ ደረጃ ፖለቲካ የሚያራምዱ ግለሰቦችና ወይም መንግሥቱ ለታክቲክ ይጠቅመኛል ብሎ አናፍሶት ይሆናል፡፡ እኔ እስከማውቀው
ድረስ ግን የተባለው ጥያቄ እሰከ አሁን መንግሥትም ሆነ በሃይማኖት አባቶች በይፋ አልቀረበም፡፡
ጦቢያ፡- የጎሣ ፖለቲካው በአንድ ወቅት ከአገር ቤት አልፎ በኢየሩሳሌም ገዳማት ተዛምቶ መነኮሳቱን እያናቆረ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ሁኔታው በም ደረጃ ላይ ይገኛል?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የጎሳ
በሽታው ከዚሁ ከአገር ቤት እንደ ተስቦ ወደ ኢሩሳሌም የተዛመተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እዚህ ያሉት መነኮሳትም ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ በተለያዩ ምክንያት እዚህ ሲመጡም
ሆነ ወደዚያ ምዕመናን በሚሄዱበት ጊዜ የተስፋፋ ጉዳይ ነው፡፡ በአገራችን ይህ ችግር አሁን የተከሰተ ሳይሆን እንዲህ እንደአሁኑ
በይፋ አይሰራጭ እንጂ በአጼ ምኒልክ ዘመንም እንደነበር ብጹዕ አባታችን አቡነ ማቴዎስ ‹‹ዴር ሡልጣን›› በሚል መጽሐፋቸው ውስጥ
በዝርዝር ታሪኩን ጽፈውታል፡፡ በገዳማቱ ያን ጊዜም አማራ ፤ ትግሬ እየተባባሉ መነኮሳቱ ይጨቃጨቁና ይከራከሩ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ
ደዌና ልናስወግደው የሚገባ በሽታ ነው፡፡ በመነኮሳቱ መካከል በጎሳ ምክንያት ቁርቁስ መኖሩ ባይካድም ለድብድብ የደረሰ አምባጓሮ
ግን አልተፈጠረም፡፡
እኔ የዴር ሡልጣንን ሁኔታ ከስድስት ዓመታት ጀምሮ በቅርብ ስከታተል የቆየሁ ከመሆኔም ሌላ ከሶሰት አመታት ወዲህም ወደዚያ ተሹሜ የሄድኩት ይህንን የጎሳ ውዝግብ ለማጥፋት
ነው፡፡ እግዚአብሔር ከረዳኝ እያስተማርኩ ያለሁት የካህናትና ይልቁንም
በመነኮሳት መካከል የጎሳ ልዩነት መኖር የለበትም እያልኩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በየጊዜው የተለያዩ ኮርሶችን ሴሚናሮችንም እያካሄድን
ስለሆነ ወደፊት የዚህ አይነቱ አመለካከት ከገዳማቱ ጨርሶ ይጠፋል የሚል ጽኑ እምነት ነው ያለኝ፡፡ የወደፊቱን ባላውቅም በአሁኑ ጊዜ የዚህ ዓይነቱ አዝማሚያ እየጠፋ በመሄድ
ላይ ነው፡፡
ጦቢያ ፡- በእስራኤል የሚገኝው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የገዳማቱን አስተዳደርና
የመነኮሳት ግንኙነት ምን ያህል የጠበቀ ነው ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ቀደም
ሲል የጠቀስኳቸው አምባሳደር ቆንጂት ከዲፕሎማቲክ ሥራቸው በተጨማሪ ለዴር ሡልጣን ገዳማት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩ ሁሉ
በእሳቸው እግር የተተኩት አምባሳደር ዘውዴ ኦቶርሞ ጥሩ ስራ እየሰሩ
ነው የሚገኙት፡፡ በተለይ ከእኛ ጋር ጥሩ የመቀራረብና የሥራ ግንኙነት አላቸው፡፡ የኦርዶክስ ሃይማኖት ተከታይም ስለሆኑ አንዳንድ
ችግሮች ሲገጥሙን ሁሉ እሳቸውን ነው ትብብር የምንጠይቀው አለበለዚያ ከእሳቸው ጋር በኢምባሲው ውስጥ የሚሰሩትን ወንድሞቻችንን እንዲተባበሩን
እየጠየቅን እንደራሳችን ቢሮ ነው የምንገባውና የምንወጣው፡፡ በገዳሙ አስተዳደርና እዚያ ባለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ መካከል ምንም
አይነት ችግር የለም፡፡ ይህን በሚገባ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
ጦቢያ ፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- እኔ አጠንክሬ
የማስተላልፈው መልዕክት በራሳችንና በታሪካችን እንድንመካ ነው፡፡ ይህ በጎሳ መከፋፈል እንዲጠፋም ነው የምፈልገው ፡፡ እኔ በጎሳ
መከፋፈሉ በጣም ነው የሚያሰጋኝ ፤ እኔ በኦሮሞ አካባቢ በምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ሆኜ ለ3 ዓመታት ያህል ሠርቻለሁ ፤ ከኦሮሞዎችና
ከትግሬዎች ጋር ነበርኩ ፤ ሌላው ቀርቶ ኤርትራም ኖሬአለሁ፡፡ የጎሳ መለያየት ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡‹‹
እንደ አንድ ልብ ሀሳቢ እንደ አንድ ልብ ተናጋሪ ሆነን›› መስራት አለብን ብዬ ነው አደራ የምለው፡፡ ከተለያየን ግን ሀገራችን
ትጠፋለች ፤ አንድነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ኢትዮጵያ ሆና የኖረችው በአንድነቷ ጸንታ በመቆየቷ እንጂ በመገነጣጠሏ
በመከፋፈሏ አይደለም ፡፡ስለዚህ ሕዝቡ አንድነቱን እንዲያጠናክር አደራ እላለሁ፡፡ እኔም ጠንክሬ የምጸልየው ስለዚህው ስለ አንድነታችን
ነው፡፡
ቸር ሰንብቱ
No comments:
Post a Comment