Tuesday, March 5, 2013

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንትን በማነጋገር ስራቸውን ጀመሩ(አንድ አድርገን የካቲት 27 2005 ዓ.ም)፡- ባሳለፍነው ሳምንት ዕለተ ሀሙስ በ500 ድምጽ የተመረጡት በእለተ ሰንበት ሲመተ ፕትርክናቸውን ያገኙት 6ተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ይፋዊ ስራቸውን ትላንት የኢፌዲሪን ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን  በቤተመንግሥት በማነጋገር  መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል አምስት ያህል አባቶች ከአዲሱ ፓትርያርክ ጋር በብሔራዊ ቤተመንግሥት በመገኝት በርካታ ጉዳዮችን ከፕሬዝዳንቱ ጋር መነጋገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ፓትርያርኩ ከውጭ ከሚገኙ አባቶች ጋር እርቀ ሰላሙ እንደሚቀጥል ፤ ቤተክርስቲያኒቱ በሀገሪቱ ላይ እያደረገች ያለችውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል ለፕሬዝዳንቱ ገልጸውላቸዋል፡፡ እንደ ቅዱስነታቸው ገለጻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሀገሪቱ ባለፈም በአለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ተናግረዋል፡፡ በስተመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጀመረቻቸውን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንደምትቀጥል ተስፋቸው እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ቅዱስነታቸው የስራቸውን መጀመሪያ ከላይ መጀመራቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በርካታ አመታትን ውጭ እንደመቆየታቸው አንጻር ፈጣን የሆነ ለውጥ ከአመራራቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ መጠበቅ ባይቻልም እግዚአብሔርን በማስቀደም ብቁ የሆኑ አባቶችን ከበታቻቸው በአማካሪነት በማድረግ በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ስራዎች ላይ በሂደት የሚታይ እና የሚጨበጥ ለውጥ እንደሚያመጡ በቅርበት የሚያውቋቸው ሰዎች አንደበት እየተሰማ ይገኛል፡፡ 


በባለፈው አስተዳደር የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በጎጥና በቋንቋ የሚግባቡ ሰዎች የተወረረ ቢሆንም ጥበባዊ እና መንፈሳዊ በሆነ አካሄድ ተጠቅመው ቤተክርስቲያኒቱ የሁሉ መሆኗን የሚያሳይ ከጎጥ ፤ ከብሄር ፤ ከቋንቋ እና መሰል ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክሏትን ነጥቦች ወደ ኋላ በማድረግ ዘመናዊ ስልጡን አስተዳደር ይዘረጋሉ ብለው የሚያምኑ  ሰዎች አልጠፉም፡፡


ይህ ሁሉ መልካም ምኞት እንዳለ ሆኖ ከቀድሞ ስርዓት መታሰብና መዘንጋት የሌለበት ነገር ቢኖር በህይወት ያለፉት አምስተኛው ፓትርያርክ እንጂ  ከስራቸው ሆነው የሙስና ፤ የዘር ማንዘር ስርዓት በቤተክህነትና በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር  ውስጥ የዘረጉት እንዲዘረጉ ያደረጉ ሰዎች አሁንም በቦታቸው ላይ መሆናቸው ለአፍታ  መዘንጋት የለበትም ፡፡ ለውጥ ሲታሰብም ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ጋርና ከዘረጉት ስርዓት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥን የቀድሞ የግንኙነት መስመሩን መበጣጠስን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ በተለምዶ ግቢ ገብርኤል ተብሎ የሚጠራው ቤተክርስቲያን ላይ ሰበካ ጉባኤ አባላት ተደርገው በህዝብ የተመረጡ በማስመሰል ከወራት በፊት የቀድሞ ፓትርያርክ እያሉ ስራቸውን ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች የቤተክርስቲያኑ ህጋዊ መሳይ ማህተብ ያላቸው ፤ ከህዝብ ገንዘብ መሰብሰቢያ ህጋዊ መሳይ ደረሰኝ በተመሳሳይ ቁጥሮች ያሳተሙ ፤ የቅዱስ ገብርኤልና የእነሱ የሆነ በተመሳሳይ ስም ፤ ፊርማ እና ማህተም ያለው ሙዳየ ምጽዋት የሚያዞሩ ፤ በ800 ብር ደመዎዝ የ800ሺህ ብር መኪና የሚነዱ ፤ በህጋዊ መንገድ ለቤተክህነት ፈሰስ ከሚደረገው 15 በመቶ ወርሀዊም ሆነ አመታዊ ገቢ ላይ በተመሳሳይ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆን ፈሰስ ቦታውን ለሰጧቸው ስውር ለሆነው የቤተክህነት አስተዳደር ፈሰስ የሚያደርጉ ፤ በሰበካ ጉባኤ ምርጫ ሂደት ላይ  ሽጉጥ  ታጥቀው ቆባቸውን ደፍተው በአውደ ምህረት ላይ የሚቆሙ  ፤ ስጋወ ደሙ ባቀበሉበት እጃቸው የሰንበት ተማሪዎች ላይ ለመተኮስ ሽጉጥ የመዘዙ  ፤ ፍቅረ ነዋይ አይናቸውን ግንባር ያደረገባቸው ሰዎች እና ውስጣዊው የማይታየውን የቤተክህነት አስተዳደር የመረጃ መረቡን ለመበጠስ ፓትርያርኩ ቀላል ስራ ይጠብቃቸዋል ብለን አንጠብቅም፡፡ ይህ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጉዳይ በየሀገረ ስብከቱ ያለ የሚሰራበት በአንዳድን ቦታዎች ላይ ህዝቡም አቤት የሚልበት ቦታ አጥቶ እግዚአብሔር እንደሆነ ያድርገው ብሎ የተወው ጉዳዮችን መፍታት የቅዱስነታቸው ቀላል የቤት ስራ ይሆናል ብለን አንጠብቅም፡፡ (ተጨማሪ ምሳሌ በተለምዶ አዲሱ ሚካኤል የሚገኝው የሰበካ ጉባኤ እና የህዝቡ ፍጥጫ)


ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ቋሚ እና የማያሻማ ውሳኔ ለማሳለፍ በመጀመሪያ የችግሮቹን ብዛት ፤ ጥልቀት እና በምዕመኑ ላይ በአሁኑ ጊዜ ያሳረፉትን ተጽህኖ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስነታቸው የቤተክህነቱን የሚታይና የማይታይ አሰራር ሰንሰለት ለመረዳት በቀላሉ ይችላሉ ብለን አንገምትም ፤ በ20 ዓመት የተገነባውን ብልሹ አሰራር በ20 ቀን እንዲፈታም መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ተሀድሶያውያኑ አዲስ ፓትርያርክ ስለተሾመ በአንድ  ቀን ይወጣሉ ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው፡፡ ለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ከፊታቸው አድርገው ጉዞውን ከጀመሩ የማይወጣ ዳገት ፤ የማይገፋ መንገድ ስለሌለ ምዕመኑ መንገዳቸውን እግዚአብሔር እንዲያስተካክልላቸው በጸሎቱ ያስባቸው ዘንድ ግድ ነው፡፡ ከቤተመንግሥቱ የጀመሩትን የመጀመሪያ ውይይት  በቤተክርስቲያኒቱም በተዋረድ ይቀጥሉበት ዘንድ ምክራችን ነው፡፡


አምላክ መንገዱን ጠራጊ ያደርግዎ ዘንድ መልካም ምኞታችን ነው፡፡

1 comment:

 1. not only we believe in change, but also we want to
  see and touch what this election has brought. a few
  parochialists may stretch their hands to proceed

  carrying their sin made and evil painted hearts.
  how ever,God may send His hands to show them again
  what His power is invincible. i am afraid God may pay us all the wage of our sins committed in
  the past two decades.

  ReplyDelete