Tuesday, March 12, 2013

ታሪክን የኋሊት “አቡነ ማትያስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡት አቤቱታ”

 • ብዙ መከራ ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኝው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሲኖዶሳዊ ፍትሕ ርትዕን ትጠብቃለች፡፡
 • የእግዚአብሔር ባለ አደራ መሆን ቀላል ስላይደለ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፤ በታሪክና በሃይማኖት በምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን፡፡ ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስን “ለዐይኬ አባግዕ” በማለት እየደጋገመ አደራ ያለው ምግብናውን በቀላሉ እንዳያየውና ቸልተኛ ሆኖ አደራውን እንዳይዘነጋ ነው፡፡
 •   ፓትርያርኩ በተቃራኒ መንገድ በመጓዝ ምን አይነት ጥቅምና የኅሊና ደስታ እንደሚሰጣቸው በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡
 •  ቆቡ እንደው አንድ ጊዜ ከተሰቀለ በኋላ በቀላሉ የሚወርድ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” (የጳጳሳትን ሹመትን በተመለከት ለቅዱስ ሲኖዶስ ያሳሰቡት)
 •  በስመ ሲኖዶስ  የሚጠቀሙት ባለስልጣኖች ሲኖዶሱን ባያሰድቡ መልካም ነው፡፡
 •  አንድ ወታደር በቂ የሆነ ትጥቅና ስንቅ ሳይሰጠው የጀነራልነት ማዕረግ ብቻ አሸክመው ወደ ጦር ሜዳ ቢልኩት ከጠላት ጋር ተፋልሞ የአገር ዳር ድንበር ማስከበር አይችልም፡፡ (ዝኒ ከማሁ) መንፈሳዊ ወታደርም ከዚህ የተለየ አይለም፡፡
(አንድ አድርገን መጋቢት 3 2005 ዓ.ም)፡-  በአሁኑ ሰዓት ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጋ ቤተክርስቲያን የሾመቻቸው አባት ከአመታት በፊት የሰሜን አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱ በርካታ አስተዳደራዊ ግድፈቶችን ተመልክተው ማለፍ ያልቻሉት አቡነ ማትያት ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚደርስ 20 ገጽ ደብዳቤዎችን ከበርካታ አባሪ ማስረጃ ደብዳቤዎች ጋር ለወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሀፊ ለብጹዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ጥቅምት 12 1992 ዓ.ም አድርገው ልከው ነበር፡፡ ይህ የተላከው ሰነድ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮበት ውሳኔ እንዲሰጥበት መሆኑን አቡነ ማትያስ ይገልጻሉ ፡፡ ነገር ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈት ቤት ያገኙት መልስ ቢኖር “አልደረሰንም” የሚል ነበር፡፡ ይህ በሴራ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዳይቀርብ የተደረገው ደብዳቤ የግል ጋዜጦች እንዲያወጡትን በፓትርያርኩ እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች  እያደረጉ ያለውን ነገር ህዝቡ እንዲያውቅ ለማድረግ በአስቸኳይ የፖስታ አገልግሎት በወቅቱ ህትመት ላይ ለነበረው “ኢትኦጵ” መጽሄት ዋና አዘጋጅ ለአቶ ተስፋዬ ተገኝ ከተላከው ሰነድ እና በጊዜው ለህትመት ከበቃው ጋዜጣ ላይ መለስ ብለን አቡነ ማትያስ ምን አይነት ስሞታዎችንና ቅሬታዎችን ለሲኖዶስ እንዳቀረቡ ለማየት እንሞክራለን፡፡

     
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርዕሰክሙ ወኩሉ መራዕየ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመትርዐዩ ቤተክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥርያ በደሙ፡፡” ዮሐንስ 20፤28
ይህ ጽሁፍ በቤተክርስቲያናችን የበላይ ባለስልጣኖች በኩል በየጊዜው የሚደርሱብንን የአስተዳደር ፈለግና ሥነ ሥርዓት ያልተከተሉ የካህናት ጥሪዎችንና ልዩ ልዩ አግባብ የሌላቸው የአስተዳደር ጣልቃ ገብነትን የሚመለከት ሆኖ ይህን በተመለከተ ሰፋ ያለ መግለጫ እና ማስረጃዎችን ይዘዋል፡፡

በቅድሚያ ቅዱስ ሲኖዶሳችን ኃይል መንፈሳዊና የመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዳይለየው እግዚአብሔር ለኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችን ጽንአትንና ብርታትን እንዲሰጣት የርቱዓነ ሃይማኖት አባቶቻችን ጸሎትና ረድኤትም እንዳይለየን የዘወትር ጸሎታችን መሆኑን እንገልጻለን፡፡ይህ ማመልከቻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ እንዲታይና ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥበት በታላቅ ትህትና አጥብቀን እናሳስባለን፡፡

ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ በነበሩብን ችግሮች ላይ ችግርን እየጨመሩብን የቆዩትና አሁንም በመቀጠል ላይ የሚገኙት ሕግንና ስርዓትን  ያልተከተሉ አሰራሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ ግለሰቦች የሚተላለፉ የቃል ፤ የቴሌፎን ጥሪዎችና የጽሁፍ ትዕዛዞች ሁሉ እንዲቆሙ ተደርጎ ከበላይ የሚተላለፉ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች በሙሉ የአስተዳደርን ፈለግ ተከትለው በአገረ ስብከቱ አስተዳደር ስር እንዲተላለፉ እንዲደረግልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ 

ከነበሩብን ሌሎች ከባድ ውጥረቶች አንጻርና ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል በሚል ተስፋ በትዕግስት ለአመታት ተሸክመነው ቆየን እንጂ የዚህ አይነቱ አሰራር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እያተራመሰ በአስተዳደራችንና በዕለታዊ ተግባራችን ላይ መሰናክልና ቀውሶችን እያስከተለ ሲያስቸግረንና ሲያስጨንቀን ኑሯል፡፡ በመንፈሳዊነት ፤ በቅንነት በሐቅ በሰላምና በመተማመን  በአንድነት ተሰልፈን  ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ፍሬ የምታፈራበትን ሥራ በመስራት በመፋጠን ፈንታ ፤ ፓትርያርኩ በተቃራኒ መንገድ በመጓዝ ምን አይነት ጥቅምና የኅሊና ደስታ እንደሚሰጣቸው በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡

“በዚህ ባለንበት በአሜሪካ አገር በታሪካችን ታይተው የማይታወቁ የዘርና ፖለቲካ ልዩነቶች በአብያተክርስቲያናት ውስጥ ሰርገው ገብተው የምዕመናንን አዕምሮ እየበጠበጡ እና እየከፋፈሉ ባስከተሉብን ጸዋትወ መከራዎች ምክንያት ወሰንና መለኪያ በሌለው ችግር ተወጥረን እንደምንገኝ እየታወቀ ቤተክርስቲያኒቱ ከእንዲህ አይነት የታሪክ ጠባሳ የምትወጣበት ፈሊጣዊ መንገድ በመቀየስና በመረዳዳት ፈንታ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ  እጅግ የበጠበጠን ጉዳይ ቢኖር  በትልቁም በትንሹም  ማለትም በጣም አነስተኛ ጥቃቅን  በሆኑ ጉዳዮች  ላይ ሳይቀር ፤ በአገረ ስብከቱ የሥራ ድርሻዎች  ላይ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶችና የቀውስ ስራዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ የሚሰራው የሰሜን አሜሪካ አገረ ስብከቱ ሳያውቃቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ስም የሚተላለፉ ትዕዛዞች የሚጻፉት ደብዳቤዎች የሚለወጡት ውሳኔዎችና ፤ ድንገተኛ የቴሌፎን ጥሪዎች ከአሁን በኋላ መቆም ይገባቸዋል፡፡ የአስተዳደር መስመር በመስበር በየጊዜው የተፈጸሙት ቅጥ የለሽ ተግባሮች ዝርዝር መግለጫዎች ከነማስረጃዎቻቸው ከዚህ በታች ይተነተናሉ፡፡” በማለት አቡነ ማትያስ ከአቤቱታቸው  ጋር በየጊዜው የተደረጉ ህገ ወጥ አሰራሮችን የሚያጋልጡ ኮፒ ሰነዶችን ለማስረጃት በማጣበቅ  በአባሪ መልክ አያይዘው ለቅዱስ ሲኖዶስ ልከው ነብወ፡፡

ሕገ ወጥ የካህናት ጥሪን የሚመለከት አቤቱታ
ጥር 17 1991 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቤተክህነት አንድ ስልክ ወደ አሜሪካ ይደወላል ፤ መልዕክቱም አንድን ካህን በአስቸኳይ አዲስ አበባ በሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲደርስ ነበር፡፡ አቡነ ማቲያስም ይህን ድርጊት በመቃወም ከዚህ በታች ያለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የእኛ ጥያቄ ለምን ተጠሩ አይደለም ፡፡ ጥሪው ለሹመት ከሆነ ይደልዎ ፤ እግዚአብሔር ያስችላቸው እያልን ከመጸለይ ጋር  ፤ ሹመቱን እንደግፋለን እንጂ ምንም አይነት ተቃውሞ የለንም፡፡ የእኛ ጥያቄ ?

 1.  ጥሪው አገረ ስብከቱ እንዲያውቀው ተደርጎ ለምን በሥነ ሥርዓት  በሕጋዊ መንገድ አልተፈጸመም ?
 2.   ባለንበት አገር ያሉት ካሕናት በጣም የተወሰኑ ስለሆኑ  አንድ ካህን ለአንድ ቤተክርስቲያን ብቻ እንጂ ትርፍ የሰው ኃይል የለንም፡፡ ይህንንም ችግር ፓትርያርኩ አሳምረው ያውቁታል  ፤ የኖሩበት አገር ነውና፡፡ ስለዚህ አንድ ካህም ለአጭርም ይሁን ለረዥም ጊዜ  ቦታውን ትቶ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ቤተክርስቲያን እንዳይዘጋና ምዕመናን እንዳይበታተኑ አሱን ተክቶ ቤተክርስቲያኗን የሚጠብቅ ካህን አስቀድሞ ማዘጋጀት ስለሚኖርብንና ካህናት ሲጠሩ አገረ ስብከቱ አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል፡፡
 3.    የተጠሩት አባት የሚያገለግሏቸው ምዕመናን ከእሳቸው በቀር ሌላ ቀድሶ የሚያቆርብ እንደሌለ እየታወቀ  በቅድሚያ መፍትሄ ሳይፈለግ በሚሄዱት ካሕን ሌላ አባ ሳይመደብ ያውም የሐምሌ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በተዳረሰበት ወቅት እሳቸውን በድንገተኛ ጥሪ ነጥቀው ሲወስዱ ለምዕመናኑ ምንም አላሰቡም፡፡ በዚህ ምክንያት ምዕመናኑ ተስፋ ቆርጠው ሊበተኑ ነበር፡፡ ደግነቱ ምንም እንኳን ስልጣነ ክህነት ኑሯቸው ማጥመቅና መቁረብ ባይችሉ ፤ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉት ውሉደ ክህነትና የወጣቶች ማኅበር ፤ ምዕመናኑን በማስተማርና በማበረታት ባደረጉት ጥረት በተለይ በሎሳንጀለስ የአቡነ አረጋዊ ካህናት በሳምንት አንድ ጊዜ የሁለት ሰዓት መንገድ በአውቶቡስ እየተጓዙ  እየመጡ በማጥመቅና በማቁረብ በኩል እንዲያገለግሉ በማድረግ በተወሰነ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ምዕመናኑን ከመበተን አድነዋል፡፡
 4. አሜሪካ ከኢትዮጵያ 10ሺህ ማይሎችን ያህል የሚርቅ ክፍለ ዓለም እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ነገር ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን የማይቻል መሆኑ ለማንም ስውር አይደለም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ጥሪ በሚደረግበት ጊዜ ለዝግጅት የሶስት ወር ያህል ጊዜን ይጠይቃል፡፡ ያለንበት የሰው አገር ነው፡፡ ካህን ለማስመጣት ረዥም ደጅ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አሜሪካን አገር የሚጠሩ ካህናትም ቢሆኑ  የአውሮፕላን ቲኬት በቅናሽ ለማግኝት ከ20 እስከ 30 ቀን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ካነሰ የቲኬቱ ዋጋ ሶስት አራት እጥፍ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ ዶላር ይደርሳል፡፡ እንግዲህ የትኛው ካህን ነው  ይህን ያህል  ከፍሎ በድንገት በሮ አዲስ አበባ መድረስ የሚችለው ? ይህን ሁሉ አስቀድሞ ማሰብ አስፈላጊ ነበር፡፡
 5. ጥሪው ለኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ከሆነም ደግሞ ኤጲስ ቆጶሳት ማለት የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ወሳኝ አካላት እንደመሆናቸው መጠን ፤ የምርጫ ሁኔታ በዕለታትና በሰዓታት የሚወሰን ሳይሆን ብዙ ወራትና አመታትን የሚወስድ ጥናት ፤ ምርምርና ማተዋልን የሚጠይቅ የቤተክርስቲያኒቱ አብይ ጉዳይ ነው፡፡ ለድንገት ሞት ድረስ እንደተባለ ነገር እንደዚህ በቅጽበት የሚሰራበት ምክንያት ምንድነው? ነገሩ በጣም የሚያስፈራና ለቤተክርስቲያናችንም የሚያሰጋ ጉዳይ ነው፡፡
በእውኑ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት እጥረት ኖሮባት ነው? ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ለተሾሙት ጳጳሳት የጵጵስና ክብራቸውንና ማዕረጋቸውን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ የተሟላ በጀት አላት? ወይስ እንዲሁ በባዶ ሜዳ ላይ በመጣል የቤተክርስቲያንን ክብር ለማዋረድ ሆን ተብሎ የሚሰራ ስራ ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ቆቡና መስቀሉ የቤተክርስቲያን አርማዎች እንደመሆናቸው ሌሎች አብያተክርስቲያናት የሚያደርጉትን ሁሉ መንፈሳዊ ክብራቸው መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ከማዕረጉ ጋር አብሮ የሚሄድ መንፈሳዊ  ክብሩን የሚጠብቅበት መሳሪያ ካልተሰጠው በቀር ብጹዕ ፤ ቅዱስ ተብሎ በስም ብቻ ቢከበር ምን ይጠቅማል? ምንስ ትርጉም ይሰጣል? አንድ ወታደር በቂ የሆነ ትጥቅና ስንቅ ሳይሰጠው የጀነራልነት ማዕረግ ብቻ አሸክመው ወደ ጦር ሜዳ ቢልኩት ከጠላት ጋር ተፋልሞ የአገር ዳር ድንበር ማስከበር አይችልም፡፡ (ዝኒ ከማሁ) መንፈሳዊ ወታደርም ከዚህ የተለየ አይለም፡፡ ተከታዩ ምዕመናንም ቢሆን ክብሩ የተጠበቀ  መንፈሳዊ አባት ማየት ይፈልጋል፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም”  ተብሏል፡፡ ቆቡ እንደው አንድ ጊዜ ከተሰቀለ በኋላ በቀላሉ የሚወርድ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ”

6.  ለዓመታዊ ሲኖዶስ ጉባኤ በፋክስ የሚደረግልን ጥሪም ሁል ጊዜ በዚሁ አይነት የመጨረሻዋ ደቂቃ ስትቀር ሲሆን ፤ ከዚህ በተጨማሪ “የመጓጓዣ ቲኬት ዋጋ አገረ ስብከቱ ይቻል” የሚል በመሆኑ  ጥሪው የግብር ይውጣ መሆኑን ብንረዳውም ሁኔታዎች ስላልተመቻቹና አቅምና ሁኔታ ስለማይፈቅድልን ለጊዜው መሳተፍ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የጥሪው ጊዜ አጠረ ረዘመ በማለት ምን አነታረከን  ? ብለን ሁል ጊዜ በትዝብት እናልፈዋለን፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው እኛ ያለንበት በሰዓትና በተወሰኑ ደቂቃዎች ፈጥኖ የሚደረስበት ቦሌ ወይም እንጦጦ አይደለም ፤ በብዙ ሺህ ማይልስ  ከአገር ርቀን ነው የምንገኝውና ይህ ሁሉ በቅድሚያ መታሰብ ይኖርበታል ነው የምንለው፡፡

አቡነ ማትያስ ለአንድ ተራ ግለሰብ ሲኖዶሱ የጻፈውን ደብዳቤ ተቃውመው የሰጡት መልስ
ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግ አውጪና የመጨረሻው አካል እንደመሆኑ መጠን እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር ተራና ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ  ይዘባርቃል ብለን ባናምንም ፤ በስመ ሲኖዶስ  የሚጠቀሙት ባለስልጣኖች ሲኖዶሱን ባያሰድቡ መልካም ነው ለማለት ያህል ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አርማና ማህተብ የሚበሩ ደብዳቤዎች እጅግ ከፍተኛ ለሆኑት ጉዳዮች ብቻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ነገሩ ሁሉ ጨዋታ መሆኑ ነው፡፡

“ምንም እንኳን አዲስ አበባ ለስብሰባ የተጠሩት ቄስ አንዳንድ ጊዜ ለካህናት ስብሰባ ተሳትፎ ብንጠራቸውም በእኛ በኩል ምንም አይነት ውክልና  ወይም ኃላፊነት ያልተሰጣቸው  በግል ሰርቶ አደርነት በራሳቸው የሚኖሩ ግላዊ ሰው ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በአገረ ስብከቱ ምንም ኃላፊነት ቦታ የሌላቸውን ግለሰቦች በቀጥታ ደብዳቤ መጻፍ ክብሩን ዝቅ ማድረጉ ብቻም ሳይሆን ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ምንም አይነት አስተዋጽኦ ለማያበረክት ግለሰብና ራሱን የቻለ ነጋዴ ደርሶ መልስ የመጓጓዣ ቲኬት ፤ አዲስ አበባ የሚቆዩበትን ጠቅላላ ወጪ በመሸፈን በሲኖዶስ ስም መክፈል ሃላፊነት የማይሰማውና አስተሳሰብ የጎደለው አሰራር አስመስሎታል፡፡ ነገሩ እንቆቅልሽ ሆኖብን ነበር ነገር ግን ቆይተን ስንመረምረው ጉዳዩ ከግል ጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ማስረጃዎች አመላክተውናል፡፡” በማለት በሲኖዶስ ስም ያለ አግባብ የሚወጡትን ደብዳቤዎች ስርዓት እንዲበጅላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰብ ችለው ነበር፡፡
ከሃይኖት ውጪ ለሆኑት  ካህናት ከሲኖዶስ የተላለፉ ደብዳቤዎችን በሚመለከት ያቀረቡት አቤቱታ
“በቅዱስ ሲኖዶስ አርማ ደብዳቤ ተጽፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ማህተብና የዋና ጸሀፊው ፊርማ አርፎባቸው ተመሳሳይ መልዕክት ይዘው በተመሳሳይ ቀን የተጻፉ አራት ደብዳቤዎች የልዩ ልዩ እምነት  ተከታይ ለሆኑት አራት ቀሳውስት በቀጥታ ሲላክላቸው እኛም በግልባጭ እንድናውቀው ተደርጓል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በእነዚህ ደብዳቤዎች አማካኝነት ቀሳውስቱን የሚጠይቀው ቲኔስ ኒውጀርሲ በሚባል ስቴት ላቋቋምነው አዲስ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ምዕመናን መጸለያ ቤተ መቅደስ እንዲለግሱን ነው፡፡ ቀሳውስቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ አይነት ደብዳቤ በቀጥታ ሲጻፍላቸው በጣም ሳይገርማቸውና ግራም ሳይገባቸው አልቀረም አንድም መልስ ሳይሰጡበት የቀሩት፡፡  እረ ለመሆኑ የወዴት አገር ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ነው ደረጃውንና ማዕረጉን ዝቅ አድርጎ በትምህርተ ሃይማኖት  በቀኖና ለማይመስሉት ያውም ለተራ ቀሳውስት በቀጥታ ደብዳቤ የሚፅፍ ? ተደርጎ የማይታወቅ ነገር ነው፡፡

እነዚህ ደብዳቤዎች የተጻፉት በማን ጠያቂነት እንደሆነ ባናውቅም ፤ ያመለከተ ግለሰብም ካለ ሀገረ ስብከቱ አውቆት ማከናወን የሚገባው ስራ ሆኖ ሳለ ፤ በትንሹም በትልቁም ጉዳዮች ላይ ያውም በሲኖዶስ ስም ጥልቅ እያሉ በመግባት ሀፍረትን መከናነብ ቤተክርስቲያንን ማዋረድ ምን ይጠቅማል? በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያስብበት ይገባል፡፡” በማለት በወቅቱ ሀገረ ስብከቱ ሳያውቀው ቀጥታ ለሌሎች እምነት ተከታዮች ቤተ መቅደስ እንዲለግሱን በማለት የተጻፈውን ደብዳቤ ተቃውመዋል፡፡

 ማጠቃለያ
ይህ ከዚህ በላይ በንኡስ አንቀጾች ተንትነን የቀረበው ስሞታና ዝርዝር መግለጫ ከላይ እንደተገለጸው  ሁሉ ከፓትርያርኩ የሚተላለፉ ቅጥ ያጡ ቅጽበታዊ ትዕዛዞች ፤ ከስነ ስርዓት ውጪ የሆኑ የቴሌፎን ጥሪዎችና ልዩ ልዩ ተጽህኖችን ፤ ለአስተዳደራችን ቀውስና  መሰናክል እየሆኑብን ስለተቸገርን ብንታገሰው በመሻሻል ፋንታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ ጉዳዩን ለሲኖዶስ ለማቅረብ ተገደናል፡፡

የቤተክርስቲያኒቱ እውነተኛ መጋቢ (አስተዳዳሪ) እግዚአብሔር ብቻ ቢሆንም ከእሱ በታች ቤተክርስቲያኒቱን እንድንመግብ ኃላፊነቱን ለእኛ ለውሉደ ክህነት ሰጥቷል፡፡ ሊዘነጋ የማይገባው አብይ ነገር የተቀበልነውን ምግብና የጸጋ እንጂ የባሕርይ ስላይደለ የሰጪው የእግዚአብሔር ባለአደራዎች መሆናችንን ነው፡፡ ይህንን በሚገባ ሳንረዳ ስልጣኑን የባሕርይ አድርገነው ከሆነ አጉል ቦታ ላይ ነው የተቀመጥነው ማለት ነው፡፡ ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስን “ለዐይኬ አባግዕ” በማለት እየደጋገመ አደራ ያለው ምግብናውን በቀላሉ እንዳያየውና ቸልተኛ ሆኖ አደራውን እንዳይዘነጋ ነው፡፡ስለዚህ የእግዚአብሔር ባለ አደራ መሆን ቀላል ስላይደለ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር በታሪክና በሃይማኖት የምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን፡፡   የተቀበልነውን ከባድ አደራ በሚገባ ለመወጣት ሰብአዊ ችሎታችንን በምንችለው ሁሉ መሞከር ይኖርብናል፡፡ አባቶቻችንስ በበኩላቸው “አደራ ጥብቅ ሰማይ ቁቅ ነው” ይላሉ፡፡

ስለዚህ እኛ የአሜሪካ ነዋሪዎች ብቻ ሳንሆን በዚች ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ስር የተጠለለ ሁሉ  ካህኑም ፤ ምዕመኑም በያለበት እውነተኛ መጋቢና ምግብና(ፍትሕ ርትዕን) ይጠብቃል፡፡ ይበልጡን ግን በብዙ መከራ ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኝው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሲኖዶሳዊ ፍትሕ ርትዕን ትጠብቃለች፡፡

“ወአምላክ ሰላም ይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እግሪክሙ ፍጡነ ጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ የሃሉ ምስሌክሙ” አሜን (ሮሜ 16፤20)  

  የአንድ አድርገን ሃሳብ
አቡነ ማቲያስ ቤተክህነቱን ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱንና ቅዱስ ፓትርያርኩ በጊዜው ያከናወኗቸውን ሕገ-ወጥነት መቃወም በመቻላቸው የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው፡፡ ማንኛውም ምዕመን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚካሄዱ ኢ-ሃይማኖታዊም ሆነ ብልሹ አስተዳደሮችን ተመልክቶ ዝም ብሎ ማለፍ እንደሌለበት አስተምረውናል ፡፡ ዛሬ በቀላሉ ስህተቱን ነግረን ማስተካከል የምንችላቸው ነገሮችን ነገ ችግሮቹን ለመፍታት የማይቻሉበት እጅግ ውስብስብ የሆነ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉም ማሰብ መቻል አለብን፡፡ ከምዕመኑ አንስቶ እስከ ቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አስተዳዳሪ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጭምር በደረጃ ሁሉም በአቅሙ ሕገ-ወጥነትንና ኢፍትሃዊነትን አጥብቆ የመቃወም ባህሉን ማዳበር ይገባዋል እንላለን ፡፡ ስብሰባ ረግጦ በመውጣት ተቃውሞን ብቻ በመግለጽ እውነታውን ለራስ ደብቆ ማቆየት ምዕመኑ ያሸከሙትን ሃላፊነትን መወጣት አያመለክትም ፡፡ ሰዎች ጥሩ ሲሰሩ ሊመሰገኑ ጥሩ ሳይሰሩ ሲቀሩ ደግሞ ስህተታቸውን በመንገር እና ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ አስተዋይነት ነው፡፡ አቡነ ማትያስ በጊዜው ችግሮቻቸው መፍትሄ ባያገኙም  ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እንዲህ ሞክረው ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ባለፉት አስተዳደሮች ጥያቄ ያልተሰጣቸው በርካታ ችግሮች በውስጥም በውጭም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሙስና ፤ ጎጠኝነት ፤ ሙሰኝነት ፤ የሰበካ ጉባኤ እና የምዕመና አለመስማማት ፤ የአንድነት ማጣት ችግር ፤ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ መልስ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች ፤ በአይን የማይታዩ ውስጣዊ አሰራር ችግሮች ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ደብዛቸው የመጥፋትና የተተኪ ችግር ፤ ገዳሞች በመናንያን የመራቆት ችግር ፤ ተመልካች ያጡ በየገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ አብያተክርስቲናት ላይ አገልጋይ የማጣት ችግርና ሌሎች መሰል ነገሮች ቤተክርስያኒቱን ከውስጥም ከውጭም ወጥረው የያዙበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡  እነዚህ ችግሮች አይናቸውን አፍጥጠው ጥርሳቸውን አግጥጠው እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ የለበትም፡፡ ወይም ችግሮቹ በፈጣን መልዕክት ተልከው የፓትርያርኩ ጽ/ቤት መድረስ አለባቸው ብለንም አናምንም ፡፡ የቀድሞውን አስተዳደራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ችግሮችና አቤቱታዎች ለመፍታት ወንበሩ ብቻውን ምንም አይሰራም ፤ ችግሮቹ እንደ ብዛታቸው የአፈታት ደረጃቸውም ሊለያይ ይገባል ፤ ከባለፈው አስተዳደር ተንከባለው የመጡ በቀላሉ መፍትሄ የሚሰጣቸው በርካታ ችግሮችና ጊዜ ፤ ገንዘብና የሰው ኃይልን የሚፈልጉ ችግሮችን በመለየት ቀላሎቹን በአፋጣኝ የመፍታት ፤ ከበድ ያሉትን ችግሮቹ ጊዜ ወስዶ ከሊቃውንት መክሮ  የሚፈቱበት መንገድ መቀየስ አለበት ብለን እናምናለን፡፡    አሁን ያለው አስተዳደር ከባለፈው የሚሻልበትን ነገሮች  በሚታይና በሚዳሰስ መልኩ ሰርቶ ለምዕመኑ ማሳየት መቻል አለበት ብለን እናምናለን፡፡

ከዚህ በፊት አንድ አድርገን አቡነ ማትያስ የቀድሞ መጽሄቶች ላይ ያደረጉት ቃለ መጠይቅ እና ስለ አቡነ ጳውሎስ ራሳቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡት አቤቱታ መጻፋችን ይታወቃል፡፡ አንድ አድርገን ላይ የወጣውን ጽሁፍ ቃል በቃል አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተሙ ከ7 ያላነሱ መጽሄቶች ላይ ወጥተው ለማንበብ ችለናል፡፡ መረጃው ሰዎች ዘንድ ተደራሽ ከመሆኑ አኳያ ደስ ቢለንም ምንጭ ከመጥቀስ አኳያ ከሁለቱ መጽሄቶች በስተቀር ሌሎቹ  መጥቀስ ተስኗቸው ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ መጽሄቶች ከተለያዩ ድረ-ገጾች የምትወስዷቻን መረጃች ምንጫቸውን የመጥቀስ ባህሉን ብታዳብሩ መልካም ነው እንላለን፡፡ 

(በሌላ ጊዜ ያለ በቂ ምክንያት ካናዳ ከዩናይትድ ስቴትስ ሀገረ ስብከት ስለመከፈሉና ሌሎች ደብዳቤዎችን አስፈላጊ ከሆኑ ለማየት እንሞክራለን)

ቸር ሰንብቱ

1 comment:

 1. ይህችንም የኋሊት ታሪክ ጨምሩባት

  http://www.youtube.com/watch?v=PKrImyDjxUw

  ReplyDelete