Monday, March 11, 2013

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝን አነጋገሩ


  • አቶ ኃ/ማርያም ለለቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካላት ተሰሚነት አንጻር በኢትዮጵያ እና በኤርትና መካከል ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን አስተዋጽኦ ታበረክት ዘንድ ጠይቀዋል


(አንድ አድርገን መጋቢት 2 2005 ዓ.ም)፡- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያኒቷ ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጋ ከሾመቻቸው በኋላ ስራቸውን በይፋ ከጀመሩ ዛሬ ስምተኛ ቀናቸው ይዘዋል ፡፡ አቡነ ማትያስ ከብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ባሳለፍነው ሳምንት የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስን በቢሯቸው ተገኝተው ስለ ወቅቱ የቤተክርስቲያኒቱ ሁኔታ እና ቤተክርስቲያኒቱ ለሀገሪቱ አየሰራቻቸው ያሉትን ማህበራዊ እና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ፕሬዝዳንቱን ማነጋገራቸው ይታወቃል፡፡ ቅዱስነታቸው በመቀጠልም የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን በቢሯቸው በመገኝት እንዳነጋገሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በንግራቸው ላይ አገሪቱ የያዘችው የልማት ጎዳና ማስቀጠል ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን  የምታካሂደውን ዘርፈ ብዙ  ልማት አጠናክራ እንደምትቀጥል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ቤተክርስቲያኒቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም  በአገሪቱ የሚካሄደውን ልማት  እንዲቀጥል የበኩሏን አስተዋጽ ታደርጋለች ብለዋል፡፡ በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ አማኞች ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር  በመተባበር በልማት ስራዎች እንዲሳተፉ እና ለሀገሪቱም እድገት አሻራቸው እንዲጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸውም ቤተክርስቲያኗ በተለያዩ ዘርፎች ያበረከተችውን የልማት ሥራዎች በማድነቅ ወደፊትም በቅዱስነታቸው መሪነት አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች ወደ አረብና ወደተለያዩ አገራት በመሄድ የሚደርስባቸው አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ችግር ቤተክርስቲያኗ ተገቢውን ትምህርት በመስጠት በአገሪቱ በሚካሄደው ልማት ተሳታፊ እንደሆኑ ማድረግ ይገባታል ብለዋል፡፡ 


እንዲሁም አቶ ኃ/ማርያም ለቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካላት ተሰሚነት አንጻር ከሌሎች የሃይይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ እና በኤርትና መካከል ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን አስተዋጽኦ ታበረክት ዘንድ ጠይቀዋል፡፡በመጨረሻም የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ያለምንም ችግር በሰላም በመጠናቀቁ አቶ ኃ/ማርያም ቅዱስ ሲኖዶስን ማመስገናቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡


ብጹዕ አቡነ ማትያስ ከ10 ዓመት በፊት የሰሜን አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ እንዲፈጽሙ ሀሳቡን ከማንሳት አንስቶ ብዙ ርቀት የተጓዙ መሆናቸው በየጊዜው የቅዱስ ሲኖዶስ የጻፉት ደብዳቤዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን የሚፈልጉት የወቅቱ ጥያቄዎች አንዱ እና ቀዳሚው እርቀ ሰላም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቅዱስነታቸው ሊቀ ጳጳስ ሆነው ራሳቸው የጀመሩትን ሃሳብ እግዚአብሔርን በማስቀደም በፕትርክና ዘመናቸው ዳር ያደርሱታል የሚል ከፍተኛ ተስፋ በሰዎች ዘንድ ማደሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
   

No comments:

Post a Comment