Tuesday, March 26, 2013

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስራቸውን ጀምረዋል

  • “እስከ አሁን ለሰራችሁት ስራ ቤተክርስቲን ታመሰግናለች ፤ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ትፈልጋለች ፤ ወደፊትም በዚሁ ቀጥሉ” ማኅበረ ቅዱሳን ራት ግብዣ ካደረገላቸው በኋላ የተናገሩት 
  •   የአንድ ቡድንን የእራት ግብዣ ፓትርያርኩ አልተቀበሉትም፡፡
  •  “ይህን ጉዳይ አላውቀውም ይቆይ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እነዲፈርሙ ለቀረበላቸው ሰነድ የሰጡት መልስ

(አንድ አድርገን መጋቢት 18 2005 ዓ.ም)፡- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከተመረጡ በኋላ  ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚህ በፊት ባሉ አባቶች ያልተለመደ ቃለ መጠይቅ ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ፕሮግራም ጋር አድርገው ነበር ፡፡ ፓትርያርኩን ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ ለጠየቃቸው በርካታ ጥያቄዎች ከአንድ አባት የሚጠበቅ ጥሩ መልስ መስጠታቸውን ብዙዎች የሚስማሙበት ነጥብ ሆኗል ፡፡ በርካቶች እንደ ‹‹አንደበታቸው ያድርግላቸው ሃሳባቸው እግዚአብሔር ያሳካላቸው›› በማለት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ ፤ ጥቂቶች ደግሞ ‹‹ትልቁ ነገር ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸው ፤ ከማንኛውም ፍትሀትና ስጋት ያለመሸበባቸው ነው›› በማለት አስተያየታቸውን የሰጡም አልጠፉም ፤ አንድ አንዶች “እጅግ የመርህ ሰው መሆናቸውን ያመላከተ ቃለ መጠይቅ ነበር” ብለዋል ፡፡ በተጨማሪም በባለፈው አስተዳደር የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በጎጥና በቋንቋ የሚግባቡ ሰዎች የተወረረ ቢሆንም ጥበባዊ እና መንፈሳዊ በሆነ አካሄድ ተጠቅመው ቤተክርስቲያኒቱ የሁሉ መሆኗን የሚያሳይ ከጎጥ ፤ ከብሄር ፤ ከቋንቋ እና መሰል ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክሏትን ነጥቦች ወደ ኋላ በማድረግ ዘመናዊ ስልጡን አስተዳደር ይዘረጋሉ ብለው የሚያምኑ  ሰዎች አልጠፉም፡፡

ከዚህ በፊት ጋዜጠኞች አባቶችን ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ አባቶች መናገር የማይፈልጓቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ከሚሰጡት ቃለ መጠይቅ ማወቅ ይቻላል ፡፡ መንካት የማይፈልጉትን ቦታ ጥያቄው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ቢመጣ መመለስ አይፈልጉም ፤ ብዙዎቹ ለጋዜጠኞች ቃል ለመስጠት ፍቃደኝነት አይታይባቸውም ፤ ፍቃደኝነት ቢኖራቸው እንኳን እውነት የሚናገሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግን ከዚህ በፊት ካላቸው ስብዕና እና በቅርቡ ካደረጉት ቃለ መጠይቅ በመነሳት ከእንደዚህ አይነት ፍርሀት ነጻ የሆኑ አባት ይመስላሉ፡፡ 

ፓትርያርኩ በቃለ መጠይቃቸው ስለ ምርጫው ፤ ስለ ቀድሞ ፓትርያርክ ሃውልት ፤ ስለ ነጭ ልብሳቸው ፤ ስለ እርቀ ሰላም ፤ ቀጣይ ሲኖዶሱ ምን መምሰል እንዳለበት ፤ ወደፊትም ቤተክርስቲያኒቱ በሕግና በሕግ ብቻ መመራት እንዳለባት ፤ እግዚአብሔር ቢረዳቸው ስለ ስብከተ ወንጌል ማስፋፋት እና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት 26 ደቂቃ የቆየ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡፡ 

አሁን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ብጹዕ አቡነ ማትያስ ስድስተኛ ፓትርያርክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ጠጋ የሚሉ ሰዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ነው ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ በእጅጉ ሥር እንደሰደደ የሚነገርለትን በዘመድ አዝማድ መሳሳብ፣ በወንዝ ልጅነት መጓተት ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራርና የሥልጣን እርከን ላይ ስውር በሆነ አካሄድ መሰባሰብና የቀድሞውን ብልሹ አሰራር አሁንም ዱካውን ሳይለቅ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ አቡነ ማትያስ ወደ ፕትርክና ከመምጣታቸው በፊት በጥቅማ ጥቅም የተሳሰረው የቤተክህነቱ አስተዳደር በተለያዩ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝባቸው አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ የሚነሱ ሰዎችንና የሚቀመጡ ሰዎችን ምደባ በማስተካከል አዲሱ ፓትርያርክ ሲመጡ ለማጸደቅ ስራውን አጠናቅቆ ነበር፡፡ ፓትርያርኩም ተሹመው ጥቂት ቀናት እንዳስቆጠሩ ቀድሞ ከእሳቸው በፊት የተሰራው ሹም ሽር ሰነድ ለፓትርያርኩ እንዲቀርብና እንዲጸድቅ ለማድረግ መሞከራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም እንዲፈርሙበት የቀረበላቸው ደብዳቤ በመመልከት “ይህን ጉዳይ አላውቀውም ይቆይ” በማለት  መመለሳቸውንም ማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ቡድን ፓትርያርኩን ራት ግብዣ እንደጠራቸው እርሳቸው ግን ግብዣውን እንዳልተቀበሉትም ከውስጥ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከእራት ግብዣ ጋር በተያያዘ ማኅበረ ቅዱሳን የእራት ግብዣ ለቅዱስነታቸው እንዳደረገላቸው እሳቸውም ግብዣውን በመቀበል በቦታው በመገኝ ከእራት በኋላ “እስከ አሁን ለሰራችሁት ስራ ቤተክርስቲያን ታመሰግናለች ፤ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ትፈልጋለች ፤ ወደፊትም በዚሁ ቀጥሉ” የሚል አጭር ቃል ማስተላለፋቸውን ታውቋል፡፡

ቸር ሰንብቱ

5 comments:

  1. Egziabiher yimesgen. Melkam neger mesmat joroyen nafqot neber. Ahunim Medhanialem Kirstos Abatachinin be Menfes Kidusu yimralin, yitebiqilin, tsegawunina mastewalun yabzalachew. Tewahido hoy, ayzosh!!!

    ReplyDelete
  2. EGZIABEHERE ke erso gar yehun

    ReplyDelete
  3. Bereketen keEGZIABEHER yemenekebelebet abat yadergo ersonem yerdawot !!!

    ReplyDelete
  4. Can you please post Patriarch Mathias interview with VOA

    ReplyDelete
  5. ayne be enba new yetemolaw.misegana le AMLAKACHEN.ersone be tsome tselote yatgawote.egnam berson bekidesena yemenbark yadergen

    ReplyDelete