Friday, March 29, 2013

ቅርሶቹ የት አሉ ?




  • ቅርሶቹን እና የደረሰብኝን ጉዳት በተመለከተም ማስረጃዎች በእጄ የሚገኙ በመሆኑ እያዘጋጀሁት ባለሁት መጽሐፍ ላይ ይፋ አደርገዋለሁ፡፡”  ቀሲስ ምትኩ

(አንድ አድርገን መጋቢት 20 2005 ዓ.ም)፡- መርጡ ለማርያም ገዳም የሚገኙት ቅርሶች ከዚህ በፊትም በገዳሙ ሰበካ ጉባኤ እና በሕዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ አርዕስ እንደነበር ይታወቃል ፡፡ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መኖራቸውን ሲጠራጠሩ የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ ደግሞ መኖራቸውን ምንም ሳይሆኑ መቀመጣቸውን ሲናገር ነበር፡፡ አሁን ግን አንድ አባት ቦታውን እና የቅርሶቹን ሁኔታ በአግባቡ አውቃለሁ አብዛኞቹ ቅርሶች ሸሽተዋል ወይም ጠፍተዋል በማለት ማስረጃ እንዳላቸውና ጥያቄውን ለሚመለከታቸው አካላት ቢቀርብም መልስ ስላልተሰጣቸው ያለመኖራቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እጄ ላይ ስለሚገኝ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም ለሕዝብ ይፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ ከሳምንት በፊት እኝህን አባት ቆንጆ መጽሔት አነጋግሯቸው ነበር፡፡



“ቀሲስ ምትኩ እባላለሁ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 19/20 ነዋሪና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ/ዓ/ስ/ቅ/ኪዳነ ምህረት ቅዱስ ጊዮርጊስና የቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን የሕግ ክፍል ነኝ” በማለት ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ እኝህ አባት ቀጥለውም ቀደም ሲል በመርጡ ለማርያም ገዳም አለ ተብሎ ከተመዘገቡት በርካታ ቅርሶች መካከል አስርቱ ቃላት የተጻፈበት ትልቅ የቅድስት ድንግል ማርያም ታቦት ፤ የወርቅ ሳጥንና ሙዳይን ጨምሮ ከ20 በላይ የሚሆኑ ቅርሶች በአሁኑ ወቅት የሉም ፡፡ የጠፉና የተዘረፉ ቅርሶችንም አሉ በማለት ሽፋን ለመስጠት የሚሞክሩ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች መኖራቸውን ቀሲስ ምትኩ ይናገራሉ፡፡

 ቀሲስ ምትኩ ከዚህ ቀደም በ1995 ዓ.ም በሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን አለሙ ተዘጋጅቶ ለማኅበረ መነኮሳት ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ በሰበካ ጉባኤው እንዲታተም ተወስኖ ለህትመት በበቃው የመርጡ ለማርያም ገዳም ታሪክና በዝርዝር ከቀረቡ ቅርሶች የመጽሀፍት ህትመት ላይ የተዘረዘሩ ቅርሶች በአሁኑ ወቅት ያለመኖራቸው ነው የሚያስረዱት፡፡
 
ጥያቄ፡- በአሁኑ ወቅት መርጡ ለማርያም ገዳም ስላለው ሁኔታ አስረዱን ?
ቀሲስ ምትኩ ፡- “ገዳሟ የረዥም ዓመት ታሪክ ያላት ናት፡፡ ብዙ ቅርሶች ከቀደሙት ነገስታትና መኳንንት ተበርክቶላት በዚያው በቤተክርስቲያኒቱ ግምጃ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በፊት ያለው ቅርስ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የተገለጸበት  ሁኔታ አልበረም፡፡ በቅርቡ ግን በወረቀት ተጽፎ እና ተመዝግቦ በ1996 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ ላይ ቅርሱ ተጠብቆ እንደሚኖር ያረጋግጣል፡፡ መጽሐፉ በመላው ዓለም ስለተሰራጨ ያነበበው ሁሉ እነዚያ ቅርሶች መኖራቸውን አምኖ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ቅርሶቹን የታሉ? ተብሎ ሲታይ የሉም፡፡  ቅርሶቹ ላይኖሩ የቻሉበት ምክንያት የታወቀ ነገር የለም፡፡ እንግዲህ ጠፍተውም ይሁን ተሽጠው ፤ ተለውጠውም ከሆነ በሀገሪቱ ሕግ እስካለ ድረስ በሕግ እንዲጤን ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ቅርሶቹ ከአጼ ዘርያዕቆብ የተሰጡና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንዳሉ ቢገለጽም አብዛኞቹ ግን የሉም፡፡”
 
ጥያቄ፤- ጉዳዩን ለማሳወቅ የሚመለከተው አካል ጋር ሄደዋል ወይ?  
ቀሲስ ምትኩ ፡- በየደረጃው ያሉና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች ጋር ተንቀሳቅሻለሁ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ፤ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ፤ ለቅርስ ባለስልጣንና ለብሔራዊ ሙዚየም ጉዳዩን አሳውቄአለሁ፡፡በዚህ እንቅስቃሴ የደረሰብኝ ብዙ ጫና አለ ፤ ብዙ ጉዳት ደርሶብኛል ፤ በዚህ ጉዳይ ታስሬ እስከ ክፍለ ሀገር ድረስ የተወሰድኩበት ነገር አለ ፤ ቅርሶቹን እና የደረሰብኝን ጉዳት በተመለከተም ማስረጃዎች በእጄ የሚገኙ በመሆኑ እያዘጋጀሁት ባለሁት መጽሐፍ ላይ ይፋ አደርገዋለሁ፡፡ 

የእኔ ዋናው ጉዳይ ቅርሶቹ የት አሉ ? አሉ ከተባለም በሚመለከተው አካል ለህዝብ ይፋ ይሁኑ ፤ እኔ ግን ቅርሶቹ ያለመኖራቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎች በእጄ ይገኛሉ ፡፡ ዋናው ነገር እውነታው ይውጣ ነው የምለው ፡፡ እውነቱ ይውጣ የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡

ቀሲስ ምትኩ ደምሴ በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እነብሴ ወረዳ የመርጡ ለማርያም ገዳም ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት 27 በሚደርሱ ተሰብሳቢዎች የተፈራረሙበት የገዳሙ ቅርሶች የሉም በአንድም በሌላም መንገድ ተመዝብረዋል” ባይ ናቸው ፡፡ 

በመርጡ ለማርያም ገዳም ጌታን በስቅለቱ ጊዜ ያለበሱት ከለሜዳ ፤ መራራ ሃሞት ያጠጡበት ሰፍነግ ፤ ከርቤ ፤ የወርቅ ሳጥን ፤ መዳይ ወርቅ ፤ መክደኛው የወርቅ የሆነ ሳጥን ፤ በውስጥም በውጭም በወርቅ የተለበጠ ሳጥን ፤ አስርቱ ቃላት የተጻፈበት የቅድስት ድንግል ማርያም ታቦት ፤ የሃና አጽም ፤ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ አጽም ፤ የገላውድዮስ አጽም (ዘአንጾኪያ) ፤ የሐዋሪያው የበርተለሜዎስ አጽም ፤ የሳዊሮስ አጽም ፤ ሔሮድስ ያስፈጃቸው ህጻናት አጽም ፤ የያእቆብ ሐዋርያው አጽም ፤ የእስጢፋኖስና  የበርናባስ አጽም  ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ቀሲስ ምትኩ በጉዳዩ ላይ መልስ የሚሰጥ ወይም ቅርሶቹ አሉ የሚል አካል ካለ መልስ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ 

እኝህ አባት ያለ ምንም ማስረጃ የገዳሙን ሰበካ ጉባኤም ሆነ በየደረጃው የሚገኙትን ኃላፊዎች ይሞግታሉ ብለን አንገምትም፡፡ አንድ አድርገን የሚመለከተው የቤተክርስቲያኒቱ አካል ይህን ጉዳይ መልስ ይሰጥበታል ብላ ተስፋ ታደርጋለች፡፡


3 comments:

  1. keteteqesut qirsoch mekakel vatikan alugn yemitlachewu yigegnubetal wusit minalbat kezich gedamwosdewut yihon?

    ReplyDelete
  2. enante andadrgen egnhn abat endet amnachihuachew?????

    ReplyDelete
  3. Vatican alugn yemtlewu KEthiopia teshetolat kalhone aynoratem ahun yeteqomut Abat ewonetegna Mereja slealachewu newu. Manm maregaget yemichlewu neger newu yetenagerut. Edeme yestachewu Ethiopia yemilewu sem bcha eko newu yekeren alem yawqewu newu.

    ReplyDelete