Sunday, March 10, 2013

“ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ ሆና አታውቅም” ዲያቆን ዳንኤል ክብረት





  • መንግሥት ሙስናን ለመቀነስ የባለስልጣናትን ንብረት እንደመዘገበ ሁላ ቤተክርስቲያኒቱ የጳጳሳቱን ንብረት መመዝገብ ይኖርባታል፡፡
  • እስከ አሁን ብዙ ንብረት  በመያዝና በማስቀመጥ ክስ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡
  • ታምራት ላይኔ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተናገረ የተባለውን ነገር እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ለመውሰድ በግሌ እቸገራለሁ፡፡ ይህንን ካደረገ ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ መጠየቅና ለተፈጠረው ቀውስም ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡
  • የ6ኛ ፓትርያርክ ምርጫው ከመንፈሳዊነት ወጣ ባለ መልኩ የምረጡኝ አይነት የምርጫ ቅስቀሳዎች ነበሩ፡፡
  • እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት አትችልም፡፡
  • እርቀ ሰላሙ እንዲጀመር መንገድ የጠረጉት አቡነ ማትያስ ናቸው ፤ አቡነ ጳውሎስንና አቡነ መርቆሪዎስን ብቻቸውን ለማገናኝት እቅድ ነበራቸው ፡፡

 (አንድ አድርገን መጋቢት 2 2005 ዓ.ም)፡- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከወቅቱ የቤተክርስቲያን ጉዳይን በሚመለከት ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102 ጋር አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ቆይታው ይህን ይመስላል…. ያንብቡት

ላይፍ፡- የፓትርያርኩ ምርጫ ለማከናወን 800 ሰዎች ድምጽ እንዲሰጡ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዴት ተመረጡ ? አንተስ ከመራጮቹ አንዱ ነበርክ ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- የተደረገው ነገር መራጮች በአገሪቱ ካሉት ሀገረ ስብከቶች እንዲመጡ ነው፡፡ እኔ ከመራጮቹ አንዱ አልነበርኩም፡፡ ምክንያቱም ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ፍላጎቴ ሂደቱን መታዘብ እንጂ መራጭ መሆን አልነበረም፡፡ ሂደቱ ውስጥ በመግባት አንተ ራስህ አካል ስትሆን ምርጫውን በደንብ ለመመልከት አትችልም፡፡ የምርጫ ሂደቱ በጎም ይን መጥፎ ነገሮች የተስተዋሉበት ነበር፡፡ በተለይ ከሂደቱ በፊት የነበሩ ነገሮች ደስ የማይሉ ነበሩ፡፡ ከመንፈሳዊነት ወጣ ባለ መልኩ የምረጡኝ አይነት የምርጫ ቅስቀሳዎች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ በአንድ ወይም በሁለት አባቶች ላይ ሳይሆን ከዚያም ከፍ ባሉት ከዘር ጋር በተገናኝ የቡድንተኝነት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ መንግስት እንዲህ ብሏል የሚሉ ነገሮች መደመጣቸው ሂደቱ ላይ ጥላ አጥልተውበት ነበር፡፡ ችግሩ የተፈጠረው አድራጊዎቹ እንዲህ ለማድረግ በመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን ሕጉም ክፍተት ስለነበረው ነው፡፡ ለምሳሌ ለምርጫ ድምጽ እንዲሰጡ የተመረጡ ሰዎች ከአንድ ሀገረ ስብከት 13 መሆናቸው እንጂ እነዚህ ሰዎች እንዴት እንደሚመረጡ ሕጉ አይገልጽም፡፡ ስለዚህ ሊቀ ጳጳሳቱ የፈለጉትን ሰው እንዲመርጡ እድል ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ እኔ ሌሎች አገሮች ላይ አምስቱንም ኦሪየንታል ቤተ ክርስቲያናት አይቻለሁ፡፡ እነርሱ ጋር አጥቢያዎች በወረዳ ደረጃ ተሰብስበው የሚወክላቸውን መራጭ ይመርጣሉ፡፡ ውክልና የሚመጣው ከታች ወደ ላይ ነው፡፡ ደግሞም ለአንድ አገረ ስብከት 13 ሰው መባል የለበትም ፡፡ ድሬደዋ እና መቀሌ እንደገና ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ፤ ሰሜን ሸዋን እኩል ማድረግ አይቻልም፡ ድሬደዋ እና መቀሌ ያሉት አንድ አንድ አገረ ስብከቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ሁሉንም በአንድ በመጨፍለቅ በ13 ሰው እንዲወከሉ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ሌላው ለፓትርያርክነት በእጩነት የሚቀርበው አባት ያለው ስብዕና በእኛ ሁኔታ የሚመዘንበት መንገድ የለም፡፡ግብጽን ብንወስድ ለምርጫ የሚቀርቡት አባቶች በመጀመሪያ በፖሊስ አሻራቸው እንዲመረመር ይደረጋል፡፡ በዚህም ሰውየው ወንጀል ሰርቶ መሆኑንና አለመሆኑን እንዲጣራ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ፓትርያርክ ከሆነ በኋላ ከስልጣኑ ስለማይወርድ ማጣራት ይደረጋል፡፡ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት ጥሩ አባት ለማግኝት ጭምር ነው፡፡

ላይፍ፡- ቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርኳን ለመሾም ምርጫ ውስጥ መግባቷን እንዴት ትመለከተዋለህ ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምርጫ ውስጥ መግባቷ ወንጀል አይደለም ፡፡ በእርግጥ አለማዊ ባለመሆኑ መንፈሳዊነትን መላበስ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ምረጡኝ በማለት የቀሰቀሱ አባቶች የነበሩትን ያህል እኮ ከእኔ ይልቅ ሌሎች ቢመረጡ  ይሻላል ያሉም ነበሩ፡፡ ከዚህ ቀደም አባት ይሁኑን  ተብለው ከገዳም ታስረው የመጡ አባቶች ነበሩ፡፡ እንዲህ አይነት ታሪክ የነበራት ቤተክርስቲያን እዚህ ደረጃ መድረሷ ያሳዝናል፡፡ በእኔ እምነት ትልቁ ችግር የነበሩት ምርጫ ላይ የቀረቡት አባቶች ሳይሆኑ በእነርሱ ዙሪያ ተሰብስበው ነገ እንጠቀም ይሆናል ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ርቀት ሄደው አከሌን ምረጡ ሲሉ የነበሩ ሰዎች እነዚህ ናቸው፡፡


ላይፍ፡- የፓትርያርኩ ሹመት ከምርጫ ካርድ የመነጨ መሆኑ መንፈሳዊነቱን አያደበዝዘውም ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ሰዎች ከምርጫ ካርድ ይልቅ በዕጣ ቢሆን መንፈሳዊነትን ይላበስ ነበር በማለት ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ለቤተክርስቲያናችን አባቶችን በምርጫ መሾም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የኦሪየንታል አብያተክርስቲያናት ልምድ ከተመለከትን የምናገኝው ሁለት ነገር ነው፡፡ ግብጾች በእጣ ያምናሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አባቶቻውን በካርድ ይመርጣሉ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ታሪክ ፓትርያርክን በካርድ መምረጥ የተጀመረው  ከአቡነ ተክለሃይማኖት ጀምሮ ነው፡፡ከድምጽ ውጪ የተመረጡ አባቶች አቡነ ባስልዮስና አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው፡፡ የእጣውም ይሁን የድምጹ ትክክለኛ መስመር ይዘው እስከተከናወኑ ድረስ ስህተት አይሆኑም፡፡

ላይፍ፡- በምርጫው ሂደት አሸናፊ ሆነው የወጡት አባት ምርጫው ከመከናወኑ አስቀድሞ የፓትርያርክነቱን መንበሩን እንደሚይዙ ይነገርባቸው ከነበሩ አባት ከመሆናቸው አንጻር የምርጫ ሂደቱን አጠያያቂ አያደርገውም?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምርጫው ግልጽ ነበር አልነበረም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በምርጫው ሂደት ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች የሚሰጡትን ምላሽ መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የተጠበቀው ውጤት ብቻ መምጣቱ ምርጫው ነጻ አልነበረም አያሰኝውም፡፡ አቡነ ማትያስ ከኋላ የነበራቸውን ታሪክ መለስ ብለን ከተመለከትን ይህንን ለማለት የሚያስችል ነገር አናገኝም፡፡ ነገር ግን ሂደቱን ካየን አስገራሚ ነገር እናገኛለን፡፡ አቡነ ጳውሎስ በቤተክህት ፖለቲካ ውስጥ ወይም ቅራኔ የነበራቸው ሰው አለመሆናቸው በምርጫው ማሸነፍ ችለዋል፡፡ እነዚህ ነገሮችን ስታይ ከቤተክህነቱ ራቅ ብሎ የቆየ አባት የመመረጥ እድሉ ሰፊ መሆኑን ትመለከታለህ፡፡ አቡነ ማትያስም እንደ አቡነ ጳውሎስ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በውጭ ሀገር ነው፡፡   በፓትርያርክነት ቦታ ተገምተው የነበሩ ብቸኛ አባት አቡነ ማትያስ ብቻ አልነበሩም፡፡ እንዲያው የሚበዙት ጠብቀው የነበሩት ሌሎችን ነው፡፡


ላይፍ፡- አቡነ ማትያስ ወደ አሜሪካ ካቀኑ በኋላ ዜግነታቸውን መለወጣቸው ይታወቃል፡፡ አንድ አባት የግል ጥቅሙን  በማሰብ ዜግነቱን እስከመቀየር ከደረሰ በኋላ ዜግነቱን የጣለበት ሀገር በፓትርያርክነት እንዲመራ ተመረጠ መባሉ እንግዳ ነገር አይሆንም ? የቤተክርስቲያኒቱ ሕግ በዚህ ዙሪያ ምን ይላል ?
ዲ/ን ዳንኤል፡-  ዜግነትን በተመለከተ የቤተክርስቲያን ሕግ የሚለው ነገር አለ፡፡ ለእኔ የቤተክርስቲያኒቱ አባት ዜግነት የፈለገው መሆኑ ጽድቅ ወይም ሃጥያት አይደለም፡፡ በደብረ ሊባኖስ ታሪክ  ወእጨጌ ከተባሉ ጳጳሳት  ከግብጽ በመለጠቅ  ገዳሙን ይመራ የነበረው  አቡነ እምባቆም የመናዊ ነበር፡፡  አቡነ ማትያስ  ምርጫው ከመድረሱ በፊት አቡነ ጳውሎስ በህይወት እያሉ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዜግነታቸውን አልመለሱም ይላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በማስረጃ ቀርበው እስካላየን ድረስ ለመፍረድ እንቸገራለን፡፡

ላይፍ፡- አቡኑ መለስኩ ማለታቸው በራሱ ኢትዮጵያዊነትን በመተው የአሜሪካ ዜግነት ለማግኝታቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አቡኑ ላይ ትችት ለሚሰነዝሩ ወገኖች ነገሩ በር አይከፍትም?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ሰማያዊና ምድራዊ ዜግነት ይለያያል፡፡ ለቤተክርስቲያን መሪነት የሚያስፈልገው መንፈሳዊነት ነው፡፡ በግሌ ዜግነቱ ምንም ቢሆን ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል ፤ እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት  ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ  እንደ ችግር አልታየም፡፡

ላይፍ፡- ከምርጫው በፊት አሜሪካ የሚገኝው ሲኖዶስ ጋር እርቅ ለማውረድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር ፤ በግልጽ የእርቁ ደጋፊ ነበር ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርቅ እደግፋለሁ፡፡ ሁለቱ አባቶች በአንድነት ሆነው ስድስተኛውን ፓትርያርክ ቢመርጡ ደስ ይለኝ ነበር፡፡  ነገር ግን መርቆሪዎስ በህይወት እስካሉ ድረስ ሌላ አባት መምረጥ አይገባውም ከተባለ ግን ከሶስት ነገር አንጻር አያስኬድም፡፡ አንደኛ በትክክል በእኒህ አባት መፍረድ ከባድ ቢሆንም መንበሩን ትተው ሄደዋል፡፡  ወደ መንበሬ መልሰኝ በማለት ሲጸልይ የነበረ አባት ሳይሆኑ በ1985 ዓ.ም በሜሪላንድ ሕግ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ የተመሰረተበት ሕግ ከአምስቱ ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት  የሚቆጠር ስድስተኛ ቤተክርስቲያን ለመመስረት እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ወደ መንበር የመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለፉት 20 ዓመታት ይችን ቤተክርስቲያን ወደድንም ጠላንም  ፓትርያርክ ሾማ ሕይወት ቀጥላለች፡፡ ጥፋት ጠፍቷል የሚሉ ሰዎች ወደ ኋላ መመለስ አለብን እያሉ ነው፡፡  ነገር ግን ሁል ጊዜ የተሰደደ ሰው ብቻ እንደ ጀግና ለምን እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ ጀግና  ሀገር ውስጥ ያለውን መከራ የተቋቋመ ወይስ ጥሎ የተሰደደ ሰው ነው? ችግርና ጥፋቱ የጋራ ነው መባል የነበረበት እናንተ አጥፍታችኋልና እኛን ወደ ቦታችን መልሱን ሳይሆን ሁላችንም አጥፍተናል ከአሁን በኋላ ለዚች ቤተክርስቲያን ሲባል በጋራ ምን እናድርግ ? ነበር ማለት የነበረባቸው ፡፡ እርቁ የተጀመረው በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ነው፡፡ በእሳቸው ጊዜ እርቁ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ምን ሊኮን ነበር?  ለምንድነው የአንድን ሰው ሞት እንደ መልካም አጋጣሚ የምንቆጥረው ? የሞቱት እኮ በመቅሰፍት አይደለም፡፡ የቫቲካኖች መሪ ስልጣን አልፈልግም እናንተ ተስማምታችሁ ስሩ በማለት መንበራቸውን ተሰናብተዋል፡፡ እኔ ከመጀመሪያ የነበረኝ አቋም እርቁ እንዲፈጸምና በተቻለ ፍጥነት ተተኪው ፓትርያርክ እንዲመረጥ ነበር፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ በፓትርያትክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ በማለት አቡነ ጳውሎስን መውቀስ ከብዙ ነገር አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡ አቡነ ጳውሎስ በሰሩት ስራ ትክክል ነበሩ? ወይም አልነበሩም? ማለት ሌላ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቀኖናዊ ነበሩ፡፡

ላይፍ፡- የአሜሪካው ሲኖዶስ ወይም አቡነ መርቆሪዎስ ባወጧቸው መግለጫዎች ጥያቄያቸው የፓትርያርክነት መንበር ይሰጠን ሳይሆን እርቅን ማስቀደም እንደሆነ ደጋግመው ገልጸዋል፡፡
ዲ/ን ዳንኤል፡- ጥያቄያቸው አንድና አንድ ነው፡፡ ወደ መንበራችን እንመለስ የሚል፡፡ ያወጧቸው መግለጫዎች በእጄ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ይህንኑ ማሳየት እችላለሁ፡፡

ላይፍ፡- አቡነ መርቆሪዎስ በፖለቲካ ጫና አገር ጥለው ለመሰደዳቸው በእሳው ወገን ያሉ ሰዎች ከሚሰጡት መግለጫ በተጨማሪ በቅርብ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔና ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አቡኑ በፖለቲካ ጫና መንበራቸውን ስለመልቀቃቸው ተናግረዋል፡፡ አንተ ደግሞ ከአሁን በኋላ አልሰራም ማለታውን ግላዊ ታደርገዋለህ፡፡
ዲ/ን ዳንኤል፡- ታምራት ላይኔ ይህን ተናግረዋል በማለት የምቀበለው በትክክል እዚህ ተገኝቶ በይፋ ይህንን አድርጌአለሁ በማለት 40 ሚሊየኑን የቤተክርስቲያኒቱን አማኝ ይቅርታ ሲጠይቅ ነው ፤ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተናገረ የተባለውን ነገር እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ለመውሰድ በግሌ እቸገራለሁ፡፡ ይህንን ካደረገ ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ መጠየቅና ለተፈጠረው ቀውስም ሃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ቤተክርስቲያን ከፖለቲካው ጫና ነጻ ሆና አታውቅም፡፡ አሁንም ይሁን ከዚህ በፊት ጫናዎች ነበሩ፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ጫናውን በመቋቋም እዚህ ደርሰዋል፡፡እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መፍጠር አትችልም፡፡ ዋልድባን መርዳት የማይችል ሲኖዶስ አሜሪካ ውስጥ መፈጠሩ ምንም አይጠቅምም፡፡

ላይፍ፡- በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ተጀምሮ የነበረው እርቅ የተቋረጠው የአሜሪካው ስልጣን በመጠየቁ ሳይሆን የመንግሥት ፍላጎት ባለመሆኑ ነው የሚሉ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ የቀድሞ የሕወሓት አመራር አቶ ስብሃት ነጋ ለላይፍ መጽሄት  በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህንኑ በማንጸባረቅ “ለእርቅ ቄሶቹን የላኩ ሰዎች መሰቀል ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ ይህንን እንዴት ትመዝነዋለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አቦይ ስብሃት የተናገሩት የመንግሥት አቋም በማድረግ ለመውሰድ እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁን እሳቸው በመንግሥት ስልጣን ላይ አይገኙም፡፡ እኔ የምወስደው የግላቸው አቋም በማድረግ ነው፡፡ የግላቸው አቋም ቢሆንም ትክክል ነው ብዬ አልወስደውም፡፡ ከሃይማኖትም ከሕግም አንጻር ንግግራቸው ትክክል አይደለም፡፡ ለእርቅ የሄደ ሰው በሕግ ይሰቀል አይባልም፡፡ የደርግ ባለሥልጣናት እንኳን ከእስር ቤት እንዲወጡ ያደረገች አገር ለእርቅ የተነሳሱ ሽማግሌዎችን ትሰቅላለች የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሃይማኖትም “የሚያስታርቁ ብጹአን ናቸው” ነው የሚባለው፡፡ ለእርቅ የሄዱ ሰዎች ይመሰገኑ ይሆናል እንጂ አይወገዙም፡፡ እርቅ ሂደት ውስጥ ስህተት ሊኖር ይችላል፡፡ እኔም የማልቀበላቸው ነገሮች አሉ፡፡ በነገራችን ላይ የእርቁን ሂደት የጀመሩት አሁን የተሸሙት አቡነ ማትያስ ናቸው ፡፡ ይህን ስለተሾሙ ብቻ የምናገረው አይደለም፡፡ አሜሪካ በሄድኩ ጊዜ አግኝቻቸው ብዙ ዶክመንቶችን ሰጥተውኛል፡፡ ማንም ባላሰበበት ወቅት እዚህ ድረስ በመምጣት ሲኖዶስ እርቅ እንዲፈጽም ተማጽነዋል፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ደብዳቤ በመጻፍ እርቅ እንዲወርድ ሲማጸኑ ነበር፡፡ እንዲያውም አቡነ መርቆሪዎስንና አቡነ ጳውሎስን ብቻቸውን የማገናኝት እቅድ ነበራቸው፡፡ ይህ ያልተሳካው አንድ አንድ አቡነ መርቆሪዎስን ይቀርቡ የነበሩ አባት እንዴት እኔ ሳልሰማ ይህ ይሆናል? በማለት አቡነ መርቆሪዎስ እንዳይሄዱ በማገታቸው ነው፡፡ ሁለቱ አባቶች ኒውዮርክ ላይ ለመገናኝት ፈቃደኞች ሆነው ነበር፡፡ ሁለቱ አባቶች ተገናኝተው ተያይተው አያውቁም፡፡ ምክንያቱም አቡነ ጳውሎስ በቦሌ ሲገቡ አቡነ መርቆሪዎስ በሞያሌ በኩል ወጥተዋል፡፡ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ሰዎች አቡነ መርቆሪዎስን በማምጣት ችግሩ እንዲፈታ አስበው ነበር፡፡ 

ላይፍ፡-  አሁን እርቁን ሲመኙ የነበሩት አባት ወደ መንበሩ በመምጣታቸው  በቀጣዩ የተቋረጠው እርቅ  ድርድር ቀጥሎ ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ ይሆናሉ ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ በጣም ተስፈኛ ነኝ ፡፡ እርቁ ጥሩ የሚሆነው መንበሩ ላይ ፓትያርክ ከተቀመጠ በኋላ ነው፡፡  ፓትርያርኩ ካለ እኔን አስቀምጡኝ? የሚል ጥያቄ ስለማይነሳ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ላይፍ፡- በአቡነ ጳውሎስ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች አዲሱ ፓትርያርክ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ለህዝብ በመግለጽ ገቢ ያደርጋቸዋል ብለህ ታስባለህ? ከሃብታም ነጋዴዎች ያልተናነሰ ሀብት ያካበቱ ጳጳሳት እንዳሉም እየሰማን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ወደ ግብጽ በሄድኩበት ሰዓት ከተማ ውስጥ ያገኝኋቸው ሁለት መነኮሳትን ብቻ ነበር፡፡ እነዚህም መነኮሳት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ሌሎች መነኮሳት የሚቀመጡት በገዳም ነው፡፡ በዋልድባ ስንት መነኩሴ አለ ? በአራት ኪሎስ ? ለከተማ የቀረቡ መነኮሳት ደግሞ በከተማ ስርዓት መጠመዳቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያን ጳጳሳቱ ምን ያህል ንብረት እንዳላቸው የምታውቅበት መንገድ የላትም፡፡ ቤተክርስቲያን ሲሆን ለመንግሥት አርዓያ መሆን ይገባት ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ከመንግሥት ልትማር ይገባል፡፡ መንግሥት ሙስናን ለመቀነስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሀብት እመዘግባለሁ ብሏል፡፡  ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ይህን ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ገዳሞቻችን በመነኩሴ እጥረት እየተራቆቱ ነው፡፡ እኔ ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታች መሰራት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ጳጳሳቱ ንብረት አፍርተው ይሆናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን እንዲህ አይነት ንብረት ነበረኝ ለቤተክርስቲያኒቱ ሰጥቻለሁ ማለት መጀመር መቻል አለባቸው፡፡  የቤተክህነቱን ጸባይ ሳውቅ ግን እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ረገድ እሰከ አሁን ብዙ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ምናልባት ዘመዶቻቸው ረድተው ይሆናል ካልተባለ በቀር ብዙ ንብረት የላቸውም፡፡





ዲ/ን ዳንኤል ካደረገው ቃለ መጠይቅ እኛን ይመለከታል ያልነውን ብቻ ወስደናል ፤ የተቀረው ቃለ መጠይቅ የጊዜው የሁሉ እጉርጎሮ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሀፍ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ን ይመለከታል …. እሱንም ማንበብ ለምትፈልጉ በpdf ብሎጋችን ላይ እናስቀምጥሎታለን፡፡


32 comments:

  1. woy Daniel Kibret....

    ReplyDelete
  2. እንግዲህ ነገሮችን ከሚያውቀውና ግንዛቤ ካለው ሰው መስማት ምን ያህል እውነተኛነቱና ትክክለኛ መረጃነቱን ከዚህ ትምህርት ማግኘት ይቻላልና በዚሁ ቀጥሉበት። ዲ/ን ዳንኤል የሰጠው ቃለ ምልልስ በጣም ጠቃሚና ወቅታዊ ነው። የተናገራቸው ሁሉ ትክክለኛነቱን ብዙዎቻችን የምናውቀው በመሆኑ ይበል ብያለሁ። ምን ይሁን ምን የተመረጡት ርእሰ አበው ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሰላማዊና ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን አክባሪና አስከባሪ በመሆናቸው መንፈሳዊው ጉዞው በበለጥ እንዲሰምር ምእመናን በጸሎት እንዲራዱ የሚያስፈልግበት ጊዜ ስለሆነ ሌላውን ትቶ በዚሁ በጸሎት ላይ መጠንከሩ መፍትሄ ይሆናል የሚል ትልቅ ግምት አለኝና እግዚአብሔር ይርዳን።

    ReplyDelete
  3. I am waiting for the pdf. about Pr Mesfin

    ReplyDelete
  4. ay Daniel amusing person, I feel sham about u!I like profesor,he show ur boundary,realy u and daniel who preach on stage r the same?,no u r "asmesay" robber!

    ReplyDelete
  5. benegerachin layi diakon daniel eyekeshefe yale sew new. tenegro ayisemam. yerasun hasab bicha new yemianitsebarikew. bilt newu.

    ReplyDelete
  6. This interview clears out a lot of things. Thanks for sharing it. Dn Daniel, have stayed very positive, reserved to be judgemental quickly. We don't know exactly what the new Patriach will do, so we have to give time for him.

    Stay positive, let us just focus to create conducive environment in duties we are assigned. If we try our best in our circles, we can make change at large in our church, our country.

    ReplyDelete
  7. Dn. Daniel, you will be judged because you have judged beyond the limit,
    You are living in an area which is like a zoo, or a sandbox, because you are constrained from getting information as a free person.
    Your internet is censored, the books that you read are only those books allowed in the realm of Ethiopia,
    you don't have the actual information and capacity to judge
    So God forgive you

    ReplyDelete
  8. “በእኔ እምነት ትልቁ ችግር የነበሩት ምርጫ ላይ የቀረቡት አባቶች ሳይሆኑ በእነርሱ ዙሪያ ተሰብስበው ነገ እንጠቀም ይሆናል ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ብዙ ርቀት ሄደው አከሌን ምረጡ ሲሉ የነበሩ ሰዎች እነዚህ ናቸው፡፡”

    አበጀህ ዳንኤል:: ስለነዚህ ቡድኖች ሰፋ አርገህ ትንታኔ ብትሰጥበት ብዙዎቻችንን ታስተምራለህ:: እግዚአብሔር ይስጥልን::

    “አቡነ ማትያስ ምርጫው ከመድረሱ በፊት አቡነ ጳውሎስ በህይወት እያሉ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዜግነታቸውን አልመለሱም ይላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በማስረጃ ቀርበው እስካላየን ድረስ ለመፍረድ እንቸገራለን፡፡ እነዚህ ነገሮች በማስረጃ ቀርበው እስካላየን ድረስ ለመፍረድ እንቸገራለን፡፡”

    አንድ ለጵጵስና የቀረበ አባት እና ለጵጵስና የሚመለምል የቅዱስ ሲኖዶስ አካል እንዲሁም የክርስቶስን ቅዱስ ስጋ ክቡር ደም የተቀበለ የቤተ ክርስቲያኑዋ አስመራጭ አካል አማስረጃቸውን በግልጽ አለማቅረብ መቻሉ ወይም መሻቱ በራሱ ማስረጃ ተደርጎ አያስቆጥረው ይሆን

    “በግሌ ዜግነቱ ምንም ቢሆን ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል ፤ እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ ችግር አልታየም፡፡”

    “ነገር ግን ሁል ጊዜ የተሰደደ ሰው ብቻ እንደ ጀግና ለምን እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ ጀግና ሀገር ውስጥ ያለውን መከራ የተቋቋመ ወይስ ጥሎ የተሰደደ ሰው ነው?”

    “እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መፍጠር አትችልም፡፡ ዋልድባን መርዳት የማይችል ሲኖዶስ አሜሪካ ውስጥ መፈጠሩ ምንም አይጠቅምም፡፡”

    ውስጣቸው ባዘሉት እውነታ ብስማማም፥ ተሰደደ የተባልውን ሲኖዶስ ባልድግፍም ከላይ ተመራማሪ ዳንኤል የዘረዘራቸው እውነታዎች ለተመራማሪው እርስ በርሳቸው የሚጋጩበት ይመስለኛል:: አንደኛ የተሰደደ ሲኖዶስ ችግር መፍታት አይችልም በሎ የሚያምን ተመራማሪ ተገልብጦ ከመሰደድ አልፎ ዜግነቱን የለወጠ እና ሃገረ ስብከትንና በሃገር ዜግነት ክብር የካደ አባት ቸግር አይታየኝም ለማለት መሞከር የሞራል ጥያቄም ያስነሳል:: ሁለተኛ ከላይ ያስቀመጥኩዋቸውን ሶስት የዳንኤል አባባሎች ጎን ለጎን ሲቀመጡ የሚያሳዩት መደነቃቀፍ ለተመራማሪው ለራሱ ግልጽ ይመስሉኛል::

    “ነገር ግን መርቆሪዎስ በህይወት እስካሉ ድረስ ሌላ አባት መምረጥ…”

    ቢያንስ “አባ” የምትለዋን ቃል ከሁዋላ መርሳት የጽሁፍ ግርፈት ወይስ የወስጥ ስሜት ነጸብራቅ: የጽሁፍ ግድፈት ከሆነ እሰየው::

    “አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው፡፡”

    መስከረም ፪፰ ቀን ፩፱፰፬ ዓም ቅዱስ ሲኖዶስ የጻፈውን ደብዳቤ ተመራማሪ ዳንኤል አላየው ይሆን ወይስ ይህ ደብዳቤ የውሸት ይሆን (http://www.facebook.com/photo.php?fbid=10200894844752962&set=a.1210551623509.2032933.1220307524&type=1&theater)?

    ReplyDelete
  9. i think Daniel forget one thing, i read one letter from his blog, he attached one letter about Abune Merkorios written by Tamirat Laine.

    ReplyDelete
  10. According to my view Daniel is not neutral on the view of Synodos. He opposes American Bishops. He is saying that Abune Merkorios is not forced by TPLF shame on him.

    ReplyDelete
  11. ዲያቆን ዳንኤል የሰጣቸው ትንታኔዎች መልካም ናቸው። ሆኖም ግን ዜግነትን በተመለከተ የሰጠውን አስተያየት ስመለከት የተዋህዶን አንኳር እና የቅዱሳን መጻህፍትን ሚስጢር እንዳልደረሰባቸው ተገነዘብኩ። እስኪ እግዚአብሔር ይግለጥለት።

    ዜግነትን በመሃላ መቀየር ቀላል ነገር አይደለም። ሩት እስራኤልን ብትመርጥ ቦዔዝን አገባች። ኢዮቤድንም ወለደች። ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ። ይህ የተቀደሰው መንገድ ነው። ዘጠኙ ቅዱሳን ከተለያዩ ዓለማት ዜግነት መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ በቅድስና ኖሩ። ሁሉም የኖሩት በኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ቃልኪዳን ነው። የክርስትና ቃልኪዳን ነው። ኤሳው ለሆዱ ሲል ብኩርናውን ለወጠ። የኤሳው መንገድ መልካም መንገድ አልነበረም። ዲያቆን ዳንኤል ምእራባዊ ስነ-አመክንዮን በመጠቀም ሁለቱን አንድ አድርጎ ተመልክቷል። ስህተት ነው።

    አንድ ካህን በመሃላ “እኔ ከዛሬ ጀምሮ ለማንም መንግሥት፣ ሃገርና ኃይል የነበረኝን ተአማኒነትና አገልጋይነንት ክጃለሁ፣ ከዛሬ ጀምሮ ህጎቿንና ምግባሮቿን የኔ ናቸው ብየ በመቀበል አሜሪካዊ እሆናለሁ፣ አሜሪካ የምትሰጠኝን የሲቪል ሥራም ሆነ ወታደራዊ ግዴታ በሙሉ ልብ እፈጽማለሁ፣ ይህንንም በማሃላ በእግዚአብሔር ስም አጸናለሁ” ብሎ ዜግነቱን ከቀየረና አሜሪካ በቅዱሳን ላይ የፈጸመችው በደል ካለ ይህ ካህን የበደሉ ተባባሪ ሆኗል። ለምሳሌ የወሎው ወይም የሰሜኑ ድርቅ ሰው ሠራሽ ሆኖ ቢገኝ እና ድርቁን ፈጻሚ አሜሪካ ሆና ብትገኝ ይህ ካህን በድርቁ ለሞቱት ሚሊዮኖችና እና በድርቁ ያለቁ ካህናትና ዲቆናትም ካሉ ለነሱ ጥፋት ተባባሪ ሆኗል። በተለይ ኢትዮጵያዊነትን ትቶ ሌላ ዜጋ መሆን እጅግ በጣም ከባድ እርምጃ ነው። ያውም ለካህን። ሆኖም ግን ብጹእ አቡነ ማትያስ በእርግጥ እሳቸው እንዳሉት ዜግነታቸውን መልሰው ከሆነ እግዚአብሔር የሚጻጸትን ሰው በጣም ይወዳልና፣ ይቅርታም ያደርጋልና እኛ ፍርድ ልንሰጥ አይገባም።

    ሆኖም ግን ዜግነቴን መልሻለሁ ያሉት “ማን ሄዶ ይመረምረዋል፣ እባክዎን መልሻለሁ ይበሉ” ተብለው በመንግሥት ተገፋፍተው ከሆነ ትልቅ ችግር አለ። በተለይ ሁለት ፈተና ከፊታቸው ቆሟል። አንደኛው የዋልድባ ጉዳይ ነው። በተለይ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ቅርበት ተጠቅመው ዋልድባን ከመታርስ ያድናሉ ወይ? ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ለንስሃ ያነሳሳሉ ወይ? እንዚህን ሁለቱን የማይፈጽሙ ከሆነና ያሜሪካ ዜግነቴን መልሻለሁ ያሉት እውነት ካልሆነ ሁላችንም ከፊት ለፊታችን የመከራ ቀን እንዳለብን አውቀን እንዘጋጅ። ሃይማኖቱን የለወጠ/የካደ መሪ (ጠቅላይ ሚኒስትር) እና ሃገሩን የካደ የሃይማኖት መሪ ባንድ ላይ መምጣት የትልቅ ጦስ ቅድመ ምልክት መሆኑን ተረድተን ካሁኑ እያለቀስን እግዚአብሔርን ይቅርታ ብንለምነው ይሻላል።

    ዲያቆን ዳንኤል በውጭ አገር ስለሚገኙት ጳጳስት የሰጠው አስተያየት ትክክል ነው።

    ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይታረቃት።

    ኃይለሚካኤል

    ReplyDelete
    Replies
    1. ከላይ አስተያየት ሰጪው እንደጠቆሙት ዓይነት አመለካከት ያላቸው ጥቂቶች አይደሉም:: ዛሬ የተፈጠረም አይደለም:: ወዳጆች ሀገራችንን እንደ ሀገር እንወዳታለን ከሌሎች ዓለማት ተለይታም የምትታወቅባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ምስክሮች ነን:: ይሁን እንጂ ከኛ በላይ የምንልበት ጉዳይ ግን ያለ አይመስለኝም:: ይህ አመለካከት በበርካታ አገሮች ላይ ይታያል:: አረቦች ያለ መካ እንደሚይሉት ዓይነት ነው:: በነገራችን ላይ የዚህ አመለካከት ጥግ የት እንደሚደርስ ታውቃላችሁ? "ዓለም ሁሉ ሲያልፍ ኢትዮጵያችን ግን ሀገረ ገነት ሁና ትቀጥላለች" እስከሚለው ጽንፍ:: ታዲያ ይህ እብደት ካልሆነ ምን ትሉታላችሁ? መውደዳችንን የምንገልጥበት የሀሰት ቃል ለሀገር ምን ይበጃል:: የዳቦ ቅርጫት ታሪኳ እንደ ብሉይ አልፎ አዲሱ ታሪኳ እኮ ሕዝቦቿን መመገብ ያልቻለች የሚል እኮ ነው::
      በሀይማኖት ከተለየን ደግሞ እኛ ለምናምነው እምነት የመጀመሪያዎቹም የመጨረሻዎቹም ልንሆን አንችልም:: አይደለንምም:: ዜግነት ሥጋዊ ሀሳብ ብቻ ነው:: መንፈሳዊ ዜግነት ይልቃል:: በኢትዮጳያዊነታችን ከማንም እንደማናንስ ከማንም አንበልጥም:: የመጨረሻው ነገር ማንም መሆን ፈልጎ የሆነ አለመኖሩ ነው:: ዜግነት የሕይወት ምርጫ አይደለም:: በመሆኑም ማንንም አያስወቅስም አያስከስስም:: ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ነገር ሲጽፍ እንዲህ ብሏል "እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና።" ይህንን እንዴት እንተርጉመውና የሥጋ አገራችንን ከመንፈሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት አንድ እናድርገው?
      በካሪቢያን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ላይ ያጠመቅናቸውን ሰዎች ዛሬም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እያልን የምንጠራቸው ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል:: ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን እንዲችሉ ደግሞ እነርሱም ጎጆ እንዲወጡ ማድረግ ብንችል ኖሮ የአሀት ሀገራትን ቁጥር ከፍ ከማድረግ አልፈን ለክርስትና መስፋፋት አስተዋጽኦአችንን ከፍ ባደረግነው ነበር:: ከክርስትናችን የሚበልጥ ዜግነት ምን ነበር? ጭራሽ ደግሞ በዜግነት ምርጫ እንከራከር በወንዝ በጎጥ መካሰሳችንን የማደጉ ምልክት ይሆን?
      ሀሳቦን በመረጃ ደግፈው ይከራከሩ? በመከባበር ሀሳብ መለዋወጥ ከቻልን ባለ ጦማሮቹን የምናስቸግር አይመስለኝም::

      Delete
    2. ሰላም ጤና ይስጥልኝ ስሞዎትን ማን ልበል ወዳጄ? እኔ ኃይለሚካኤል ነኝ።

      በፈረንጆች አፈ ታሪክ ድሮ በፍርድ ቤቶቻቸው አካባቢ ከጫማቸው ላይ የዶሮ ላባ ሰክተው የሚቆሙ ሰዎች ነበሩ ይባላል። የዶሮ ላባ ከጫማ ላይ መሰካት “የሃሰት ምስክር ከፈለጋችሁ እኔ አለሁ” ለማለት የሚጠቀሙበት ምልክት ነበር ይላሉ። የሃሰት ምስከር ፈላጊዎች ብር ከፍለው የሃሰት ምስክር በዚህ መልክ ያገኙ ነበር ይባላል። ታዲያ ዛሬ ዛሬ ፈረንጆቹ የዶሮ ላባን ጉዳይ ሃሳዊ ጥቅስን ለማመልከት እንደምሳሌ አድርገው በፍልስፍናቸው ይጠቀሙበታል። ሰው ያላለውን ነገር እንደተናገረ ተደርጎ የሚቀርብን የትችት ዲስኩር “የዶሮ ላባ ሃሳዊነት” ወይም በእንግሊዝኛ “ስትሮውማን ፋላሲ” ይሉታል።

      ወዳጄ ሆይ - ኣስተያየቱን የሰጠሁት ዲያቆን ዳንኤል ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መቀየርን በተመለከተ የሰጠው አስተያየት ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የማይስማማ መሆኑን ለትምህርት እንዲሆነን ለዲያቆን ዳንኤል ለማሳሰብ ነበር። እርስዎ የሰጡት መልስ ለየትኛው ጥቅስ እንደሆን አልገባኝም። መልስዎ ከማን እንደሆነም አልተናገሩም። “ከኛ በላይ ማን አለ” ያለ ሰው ካለ ይህን ያለው ሰው ባለበት ቦታ ሄደው ለሱ መልስ ቢሰጡ ይሻል ነበር።

      እርስዎ ያቀረቡት ክስ አዲስ ክስ አይደለም - ፕሮቴስታንቶች እና ተሃድሶዎች ዘወትር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚያቀርቡት ክስ ነው። የክሱ አላማ ምን እንደሆነም ግልጽ ነው። ከጥንት ጀምሮ አባቶቻችን “ኢትዮጵያ ሃገረ እግዚአብሔር” ማለታቸው ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ሰዎች በላይ ናቸው ማለታቸው አይደለም። የኛ ድርሻ እግዚአብሔርን ማገልገል ነው ማለት ዝቅ እንበል እንጂ ከሌላው በላይ ነን ማለት አይደለም። ክርስትና እኮ መስቀልን መሸከም ነው፣ መከራ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ያለ ሰው ዓለማዊ ኑሮን ትቶ ገዳም ሲገባ እራሱን ማዋረዱ እንጂ ከሰው በላይ ነኝ ማለቱ አይደለም። ፕሮቴስታንቶች በክፋት መንገድ ሃሳዊ ጥቅስ የሚጠቅሱት ተዋህዶን ለማዳከም ይረዳናል ብለው ስለሚያስቡ ይመስለኛል። ቀጣሪዎቻቸውም በዚህ ክስ እንዲገፉበት የሚያበረታቷቸው ትርፍ ስለሚያገኙበት ይመስለኛል። ተዋህዶ ከተዳከመ የበረታ የሃገር ፍቅርና አንድነት ስለማይኖር መልክአ ምድሯን ወይም በከርሰ ምድሯ ያለውን ሃብቷን በነጻ ለመዛቅ ለሚቋምጡ የውጭ ሰዎች የውኃ መንገድ ስለሚሆንላቸው ክሱን ይወዱታል።

      ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን እንድታገለግል የተሰየመች አገር መሆኗን ቅዱሳን መጻህፍት፣ የታሪክ መጻህፍት እንዲሁም ደግሞ ቅርሶቿና ታሪኳ ሁሉ ተባብረው ይመሰክራሉ። እርስዎ ይህን አላውቅም ካሉና ዝርዝር ማስረጃ ከፈለጉ የብሎጎትን ስም ይንገሩኝና በብሎግዎ የሚለጠፍ ትንታኔና ማስረጃዎቹን እግዚአብሔር በፈቀደ ትንሽ ጊዜ ወስጄ ኣጠናቅሬ ልልክልዎ እችላለሁ።

      “በካሪቢያን፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ላይ ያጠመቅናቸውን ሰዎች ዛሬም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እያልን” ጠራናቸው ብለው ለተቆጩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ቦታ እንጂ ሥጋ አይደለችም። ምነው አምታቱት። አገራቸው ደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ የሆኑ ካቶሊኮች “ሮማን ካቶሊክ” እየተባሉ ሲጠሩ አልሰሙም ወይ? ስዎቹ ሮማዉያን ናቸው ማለት እንዳልሆነ እርስዎም ያውቃሉ፤ ታዲያ ምነው ክስዎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ወንጀለኛ አደረገ? ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ኤጲስ ቆጶሳትና ዲያቆናት በምእራፍ ፫ ቁጥር ፫ የጻፈውን ጠቅሰዋል ትርጉሙ ግን የገባዎት አልመሰለኝም። ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ እንጂ በሥጋ አንመካ ማለቱ የኔን ማሳሰቢያ (ክርስቶስን እንጂ ስጋን አንሻ) ያጠናክራል እንጂ የእርሶን ለኢትዮጵያዊ ካህን አሜሪካዊ የመሆን ማበረታቻ አይደግፍም።

      እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም መልካም ልብ ይስጥ።
      ኃይለሚካኤል

      Delete
    3. "ዜግነትን በተመለከተ የሰጠውን አስተያየት ስመለከት የተዋህዶን አንኳር እና የቅዱሳን መጻህፍትን ሚስጢር እንዳልደረሰባቸው ተገነዘብኩ። እስኪ እግዚአብሔር ይግለጥለት።

      ዜግነትን በመሃላ መቀየር ቀላል ነገር አይደለም። ሩት እስራኤልን ብትመርጥ ቦዔዝን አገባች። ኢዮቤድንም ወለደች። ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ። ይህ የተቀደሰው መንገድ ነው። ዘጠኙ ቅዱሳን ከተለያዩ ዓለማት ዜግነት መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ በቅድስና ኖሩ። ሁሉም የኖሩት በኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ቃልኪዳን ነው። የክርስትና ቃልኪዳን ነው። ኤሳው ለሆዱ ሲል ብኩርናውን ለወጠ። የኤሳው መንገድ መልካም መንገድ አልነበረም። ዲያቆን ዳንኤል ምእራባዊ ስነ-አመክንዮን በመጠቀም ሁለቱን አንድ አድርጎ ተመልክቷል። ስህተት ነው።"
      Well said dear ኃይለሚካኤል

      Delete
    4. ወዳጄ ኃይለ ሚካኤል ሰላም ባለህበት? ከማንነቴ ይልቅ ሀሳቤ ላይ ማተኮሩን ስለመረጥሁ ለጊዜው ስሜን ተወውና አስተያየቶችህ ላይ አስተያየቴን ልስጥ:: የሀሰት ምስክር ላሉት እኔ የማምንበትንና እንደ ክርስትና መሠረታዊ ትምህርት መታሰብ ያለበት እንዴት እንደሆነ ለማመልከት ያለምኩ ምእመን እንጂ ሴረኛ አይደለሁም:: ሌላው ስለማይመጥነኝ እንዳላነበበ ትቼዋለሁ:: ነከሮችን በጥርጣሬ ብቻ የማየት አባዜ መች እንደተጠናወተን ባይታወቅም ብዙዎቻችን ግማሽ ዐይን ያለን መሆኑ አልዘነጋውም:: ያም ሆኖ ግን ሀሳብ ስለማከብር ሀሳብዎን በሀሳብ ለመቃወም ያህል ይህን ላነሳሎ እወዳለሁ:-

      ኢትዮጵያ???

      ኢትዮጵያን መውደድ እንደዜጋ መልካም ነው:: ሀገረ እግዚአብሔር ናት ስንል ግን ምን ማለታችን ነው? ከሌሎች ሀገሮች ጋር ስትወዳደር የምናቀርበው የልዩነት ማሳያ ምንድንነው? ለምሳሌ ሌላው ሁሉ ቀርቶ እንደው ባንዳንድ ነገሮች ከሚመስሉን አገሮች ጋር ስትነጻጸር እንኳ /እርሶ እንዳሉት ከሆነ ቅርስ አነሰም በዛም የሌለው አገር አይኖርም:: ለገዳም ሥርዓትና ሕልውናም እኛ መቼም የመጀመሪያዎቹ አይደለምን:: ያወረሱንና የወረሱ የተስፋፋባቸውም ሌሎች አገሮችም እንዳሉ ሊዘነጋ አይገባውም:: ልዩነቱ የቱ ጋር ነው? ኃይልዬ?/:: ይህንን እንዲያውቁ እወዳለሁ ለአገልግሎት የተለየች አገር የለችም:: ሁሉ የእርሱ ገንዘቦቹ ናቸው:: ብንበረታና ያለንን ብናስፋፋው ሌላው ቀርቶ አፍሪካችንን እንኳ ብናጠምቅ ያኔ የተለየ ክፍለ ዓለም ኖረው ማለት ነው? አይደለም ከዚያም በላይ መሥራት ይጠበቅብናል እንጂ:: እንደዚህ አይነቱ እምነት በኦሪት አይሁድ ለኢየሩሳሌም ይሰጡት የነበረ እና ኋላ ግን የተሻረ ነው::/ዮሐ.4፥21/:: እስላሞች ለመካ መዲና ያላቸው አስተሳሰብ ይህን የመሰለ ነው:: የርሶ ከዚህ በምን ይለያል?

      ዜግነት???

      ለመልካም አርአያነት አባቶች ሊኖራቸው ከሚገባ ምሳሌያዊነት የተነሳ እንጂ የዜግነት ጥያቄ መቼም የጽድቅ ጉዳይ ሆኖ እንደማይነሳ ልቡናዎ ይመሰክርልዎታል:: ያን እያወቁም ቢሆን ግን እየተከራከሩነው:: ለምን? የዲ/ን ዳንኤልም የመከራከሪያ ሀሳብ የመነጨው ከዚህ ይመስለኛል:: የዜግነት ጉዳይ የሥጋ ጉዳይ ነው:: ከመንፈሳዊነት ጋር ትይይዝ የለውም:: በመሆኑም ጥቅምና ጉዳቱን ለይተን የምንገባበት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ነው:: ለምሳሌ የትኛውንምዜጋ ወደንና ፈቅደን የማግባት መብት የሰውነት ነው:: እንደማኅበረሰብ ባሕልና ወግ ነውር ሊሆን ይችላል:: እንደ እምነታችን ሥርዓት ደግሞ የምንጠየቀው ያመነ/ች ስለመሆናቸው ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም:: ሌላ ጥያቄ ልታነሳም አትችልም:: ባጠቃላይ ዜግነት መንፈሳዊ ጥያቄ ሊሆን አይችልም::

      ስብከታችን ምንድን ነው?
      ቤተ ክርስቲያናችንን ለዘመናት ቀንበር የሆነባት አንድ ጉዳይ ነበር:: የጵጵስናና የፕትርክና ጉዳይ:: የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን በምንኮንንበት አንደበት ግን ራሳችንን መቅጣት አልቻልንም:: ስብከታችን ምንድንነው? የሚል ጥያቄም እንዳነሳ ያስገደደኝ ይኽው ነው:: ባንተ ላይ ሊደረግ የማትሻውን አታድርግ አይደለም? ታዲያ ለምን? እንዲሆኑ የምንፈልገው ክርስቲያን ነው ኢትዮጵያዊ? የእስልምናውና የፕሮቴስታንቱን ክፍል ዓለም የሚንኮንነው በምንድን ነው? እነዚያ አረባዊነትን ሲሰብኩበት የወዲያኞቹ ደግሞ ምዕራባዊነትን የሚያስፋፉበት መሳሪያ በማድረጋቸው አይደለል? እኛ እንዲሆኑ የምንፈልገው ምንድንነው ማለት አግባባዊ ጥያቄ ነው:: እያጠመቅን ምን እናድርጋቸው? ኬንያዊ ዲያቆን፣ ጃማይካዊ ቄስ፣ አሜሪካዊ ጳጳስ እንዴት እናፍራ? ብዙ ባልኩ በወደድኩ ነገርግን ለመረዳዳት በቂይመስለኛል::

      የት? አለ ዘበርጋ

      የዘበርጋን ጥያቄ ያስታውሱታል መቼም? የትኞቹ መጻሕፍት ናቸው አገራችንን ለይተው ያጸደቁልን? ቅዱሳንን በማፍራት ከሆነ የኛ ሥራ /ተልእኮ/ በዚህ የሚወሰን አይደለም:: በብዙ ምክንያቶች ተይዘን እንጂ ብንበረታ ከላይ እንዳልኮ ዓለምን ሁሉ ለቅድስና የመጥራት ተልእኮ ነው የያዝነው እንጂ በዚህች ትንሽ አገርና 50 ቢልየን በማይሞላ ሕዝብ ልንኮፈስ አይደለም:: ያም ሆኖ ግን የት የምትለዋን ጥያቄ መጠየቄን አልተውም:: በማን ገድል? በየትኛው የታሪክ ክፍል?

      የእመቤታችን የአሥራት አገር ናት ማለት ፈልገው ከሆነ እኔም አምናለሁ:: ያ ማለት ግን ምን ማለት ነው? ጋራና ሸንተረሩ እኮ አይደለም:: ለእኛ ለተዋህዶ ልጆች የተሰጠ ነው:: ያ ደግሞ ድርብ ዜግነት በመያዝ አይሰረዝም:: ይህን ካሉ ያብራሩልኝ ዘንድ እለምናለሁ?
      የሮም ካቶሊክን ያነሱበትን አግባብ አልወደድሁትም:: ለዚህ ነገርም ምሳሌ የምትሆንም አይመስለኝም:: የኢትዮ ካቶሊክን ግን ስላላት መዋቅራዊ አንድነት ሮማዊት እንላት ካልሆነ በቀር የሮማ ካቶሊክ ተብላ ስትጠራ ሰምቼ አላውቅም:: በዚህ መንገድ የሚጠሩ ሌሎች አቢያተ ክርሲቲያናት መኖራቸውን ባውቅም የኢትዮ ቤተ ክርስቲያን በምታካሂደው የወንጌል አገልግሎት የምታገኛቸውን ነፍሳት ጎጆ እንዲወጡ እንዲሰፉ ካደረገች በኋላ ደሞ ወደሌላ ትሄዳለች እንጂ በስሟ እየተጠሩ እንዲኖሩ ማስገደድ አለባት ብዬ አላምንም:: የደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን፣ የጃማይካ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአሜሪካ . . . ማየት ይናፍቀኛል::
      ሃይማኖታችንን ያስፋልን

      Delete
    5. ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋሉ። ስምዎን ጠርቼ ሰላምታ እንዳላቀርብልዎት መናገር የምፈለገው ተደብቄ ነው አሉኝ። አሳሳች መናፍስት በድብቅና በተለያየ አስመሳይ አቀራረብ (ለምሳሌ በስንዴ መካከል እንክርዳድ ሆነው) እየመጡ ቤተክርስቲያናችን እና አገራችን እነሆ እስካሁን ድረስ ለረጂም ጊዜ ስላወኳት ለምን አንሰጋ? ቅዱስ መጽሐፍ “ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው” እያለን እርስዎን እንመን ወይስ ቅዱስ መጽሓፉን?

      ዲያቆን ዳንኤል መንፈሳዊነት አለው ብየ ስለምገምት እንዴት የኢትዮጵያ ዜግነትን በመሃላ የመቀየርን ጉዳይ ሳያውቅ ቀረ ብየ በመገረም ነበር ለሱ አስትያየት የሰጠሁት። አረማውያን የቅዱሳን መጻሕፍት መንፈሳዊ ሚስጢራት ለምን አልገባቸውም ብየ አልገረምም። የበገና ዜማ ለእርያ ይገባዋልን? ለአህያስ ማር ይጥማታልን?

      የጻፍኩሎትን ነገር አንዱንም አልጨበጡትም። ቤተክርስቲያን አንዲት ናት። በውንም አንድ ነበረች። አሁን እርስዎ ያነሱትን ጥያቄ የሚመስል የጥርጣሬ እንክርዳድ የሚዘሩ በየዘመኑ እየተነሱ ምእመኗን ነጣጠቁ። ክፉው መንፈስ እንኳን ሌላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳን ሳይቀር በአርባ ጾም ሊፈትን አልቀረበም? ይታይዎት በአርባ ጾም! ድሮ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ኢትዮጵያዊ ካህን የእግዚአብሔር ቃል እንጂ ዜግነቱን መቀየር አልነበረም ዳቦ የሚሆነው። ወርደ ብዙ የሆነውን የኢትዮጵያን መንፈሳዊ ገጽታ እግዚአብሔር በፈቀደ እንዳቀርብልዎት የብሎጎትን አድራሻ ይስጡኝ ብልዎትም አይሻኝም ብለዋል። ትምህርት እንጂ ድርቅና እና ንትርክ ምን ፋይዳ አለው? ትምህርት እንድንለዋወጥ ከፈለጉ ሜዳውን ያቅርቡ። ግንዛቤ የጎደለው የድርቅና ጥያቄ መወራወር ለሁላችንም አይጠቅምም።

      እንዳየሁዎት የእርስዎ ስልት አላየሁም ብሎ የመካድ ነው። ሮማን ካቶሊክ የሚባል አላየሁም ስላሉ እነሆ ይህን ይመልከቱ። http://dioceseofbrooklyn.org/roman-catholic-diocese-of-brooklyn/

      በተረፈ እግዚአብሔር ለሁላችንም ልቦና ይስጠን።
      ኃይለሚካኤል።

      Delete
  12. ዳንኤል በዚህ ወቅት ዘለፋና ጫናውን ሳትፈራ ቤተክርስቲያንህን አስበልጠህ እውነት መናገርህ በእውነት ትልቅ መሰዋእትነት ነው ።
    ትልቁ እና ዋናው የቤተክርስቲያናችን ችግር ዘረኝነት እና ፖለቲካ ነው ፡ ብዙዎች ሃሳብ የሚሰጡት እነዚህን ሁለት ነገሮች በማስቀደም ነው ። በየብሎጉ ስንት የነፍስ ነገር መማማር የምንችልበትን ከኛጋር ያልሆኑ ሾልከው በመግባት ለራሳቸው ሀሳብ ማራመጃ እያደረጉት ነው ይህ ደግሞ ብዙ የቤተክርስቲያን ልጆችን በርዞብን አደጋው ቤተክርስቲያንን እየጎዳ ነው ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠቃሽ ቤተክርስቲያንዋ የራስዋ ሚዲያ አለመኖሩ በስድብ እና ለራሳቸው ሀሳብ መጠቀምያ እያደረጉ ነፃሚዲያ እየተባለ የቤተክርስቲያንዋ ዋልታ የሆኑትን አባቶቻችንን ለስድብ አልፎም ቤተክርስቲያናችንን እያዋረድን ነው ። ሰለዚህ ቤተክርስቲያናችን የራስዋ ሚዲያ ቢኖራት ሀገር ውስጥ ካልተቻል በውጭም ቢሆን እላለሁ።
    እግዚአብሄር በቸርነቱ ይጎብኘን
    አባታችሁ

    ReplyDelete
  13. D. Daniel as a comment it is a good idea.our problem is to figure out the wheat
    from the chaff.Where is the truth? we are perplexed.There are people who talk
    evil regarding the newly elected patriarch.The government says another thing.
    Who is faithful and loyal to the religion? D.please if can write a book that can
    reveal the fact.Every body blowing his or her trumpet to convince others.
    Who believes who?Every one says "I am the truth".In such devil driven air,how
    can one screen out the truth from the bags of lies? MAY GOD REVEAL THE TRUTH.

    ReplyDelete
  14. ዉድ ዳኒኤል, እውነተኛ እርቅ ሊመጣ የሚችለው በሃቅ ላይ የተመረኮዘ ውይይት ሲደረግ ነው:: በኔ እይታ የችግሩ መነሻ የ አቡነ መርቆሪዮስ ክመንበራቸው በግፍ መባረር ነው:: አንተ ይሀን እውነት ክደሃል!
    1. አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ላልከው የታለ ደብዳቤው?????? በ52 ገጽ የታተመው አሳፋሪ ሰነድ ላይ አንተ ያልከው ደብዳቤ የለም::
    2 (ጥገኝነት ለመጠየቅ ተናገረ የተባለውን ነገር እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ለመውሰድ በግሌ እቸገራለሁ፡፡):: ላልከው ይህ ተግባሩ ጥገኝነት ያስከለክለው ይሆናል እንጂ ጥቅም የሚሰጠው አይመስለኝም:: በመሰረቱ ሰውየው ጥገኝነት ለማግኘት ብዙ ሌላ ምክንያት አያጣም::
    በአንጻሩ ግን አቡነ መርቆሪኦስ በግፍ ከመንበራቸው በግፍ እንደተነሱ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ: 1.አቡነ ዜናማርቆስ የጻፉት 'መንበረ ፓትሪያርኩን ልቀቁ' ደብዳበ, 2.የአቡነ መርቆሪኦስ ንግግር "...ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበልነውን መለኮታዊ አደራ ለመወጣት እየሰራን ሳለን ከውስጥ ቢጽ ሃሳዊያን ከውጭ የዚህ አለም ባለስልጣናት ተቃውሞ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖብናል..." 3. ታምራት ላይኔ የሳቸው መንግስት ከአቡነ መርቆሪኦስ ጋር ለመስራት እንደሚቸገር የሳፈው ደብዳቤ በሬዲዮ ላይ ሲነበብ የተሰማ ወዘተ
    ታዲያ እኛ ቁጭ ብለን የመጣልንን መረጃ አንተ እመራመራለው, አነባለው መረጃ ለማግነት የተሻለ እደል አለን የምትል ሰው እንዴት ላትሰማው, ላታየው, ላትመዝነው ቻልክ? እባክህ እንቅፋት አትሁን ለማጥቃለል
    -የችግሩ ስር መሰረት : የሃገሪቱ የፖለቲካ ምስቅልቅል
    -የችግሩ መነሻ: የፓትሪያርኩ በግፍ መባረር
    -ችግሩን ያባባሰው: የፖለቲካ ሃይሎች ፍላጎት
    -ችግሩን የመፍቻ መንገድ; ሃቅ ላይ የተመሰረተ ንግግር
    -የችግሩ ጊዜአዊ መፍትሄ; ይቅር ለእግዚአብሄር
    -የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ; ብሀራዊ እርቅ

    ReplyDelete
  15. ዳንኤል በዚህ ወቅት ዘለፋና ጫናውን ሳትፈራ ቤተክርስቲያንህን አስበልጠህ እውነት መናገርህ በእውነት ትልቅ መሰዋእትነት ነው ።
    ትልቁ እና ዋናው የቤተክርስቲያናችን ችግር ዘረኝነት እና ፖለቲካ ነው ፡ ብዙዎች ሃሳብ የሚሰጡት እነዚህን ሁለት ነገሮች በማስቀደም ነው ። በየብሎጉ ስንት የነፍስ ነገር መማማር የምንችልበትን ከኛጋር ያልሆኑ ሾልከው በመግባት ለራሳቸው ሀሳብ ማራመጃ እያደረጉት ነው ይህ ደግሞ ብዙ የቤተክርስቲያን ልጆችን በርዞብን አደጋው ቤተክርስቲያንን እየጎዳ ነው ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠቃሽ ቤተክርስቲያንዋ የራስዋ ሚዲያ አለመኖሩ በስድብ እና ለራሳቸው ሀሳብ መጠቀምያ እያደረጉ ነፃሚዲያ እየተባለ የቤተክርስቲያንዋ ዋልታ የሆኑትን አባቶቻችንን ለስድብ አልፎም ቤተክርስቲያናችንን እያዋረድን ነው ። ሰለዚህ ቤተክርስቲያናችን የራስዋ ሚዲያ ቢኖራት ሀገር ውስጥ ካልተቻል በውጭም ቢሆን እላለሁ።
    እግዚአብሄር በቸርነቱ ይጎብኘን
    አባታችሁ

    ReplyDelete
  16. "Absence of evidence is not evidence of absence" ሰው ሳይችል ሲቀር ዝም ማለትና ራሱን ማግለል ይችላል። ለራሱ ተምታቶበት እያለ ግን ራሱን ተመራማሪ ብሎ ሰይሞ የሃገሪቱንም ሆነ የቤተክርስቲያኒቱን ተረካቢ ወጣት ትውልድ የማነሁለል/የማፍዘዝ/ ስራ መስራት በምን መልኩ መንፈሳዊንት እንደሚባል ሊገባኝ አልቻለም። እንዳንተ ያለው ሃያ ዓመት ሙሉ አውቃችሁም ይሁን ያለዕውቀት ሰውን በመንፈሳዊነት ስም አንገት ደፊ ባታደርጉት ኖሮ ሃገሪቱም ቤተክርስቲያኗም ነጻ በወጡ ነበር። ለአባ ጳውሎስ ከገንዘብ ንኪክ ንጹህ መሆን ዋናው ማስረጃህ ብዙ ስለማይወራባቸው ነው፤ ከእርሳቸው በብልጠት በዘመዶቻቸው ሥም መገንባት ያንተ በጓንት የሰረቀ ነጻ ነው መደምደሚያ እንዴት እንደሚያበሳጭ ማን ይንገርህ? የዊክሊክስ መረጃ ለአረብ አብዮት /ጠቅሟል አክስሯል የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ/ መነሳት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ቁልፍ መረጃ ነው። እንዴት ትናንት ቤተክርስቲያን ነጻ አልነበረችም ተብሎ ዛሬም ፖለቲካ አብሮ ግብቶ ይፈትፍት ይባላል? አሁን ታምራት ላይኔና ሃይለስላሴ ቤተክርስቲያንን እኩል በድለዋታል ልንል ነው? አባ መርቆሬዎስ ለምን አልተሰውም ብለህ የለፈፍከውን ያህል ነፍጠኞቹ ለምን በ21ኛው ክፍለዘመን ለምን መነኩሴ መግደል እንደሚፈልጉ ልትሞግታቸው አልፈልግክም። አይ አንች ኢትዮጵያ 85 % ሕዝብሽ ያልተማረ ፣ ABCD ከቆጠረው አብዛኛው የተማረ ማኅይም/አድር ባይ/፣ ጥቁሩን ነጭ የሚል ሰበነክ ሊቃውንት/Prostitute Intellectual/

    ReplyDelete
    Replies
    1. I could not have said it better.

      Delete
  17. ዲ/ን ዳንኤል ካደረገው ቃለ መጠይቅ እኛን ይመለከታል ያልነውን ብቻ ወስደናል ፤ የተቀረው ቃለ መጠይቅ የጊዜው የሁሉ እጉርጎሮ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሀፍ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ን ይመለከታል …. እሱንም ማንበብ ለምትፈልጉ በpdf ብሎጋችን ላይ እናስቀምጥሎታለን፡፡

    When?

    ReplyDelete
  18. "...ዳንኤል ካደረገው ቃለ መጠይቅ እኛን ይመለከታል ያልነውን ብቻ ወስደናል ፤ የተቀረው ቃለ መጠይቅ የጊዜው የሁሉ እጉርጎሮ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን መጽሀፍ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ን ይመለከታል …. እሱንም ማንበብ ለምትፈልጉ በpdf ብሎጋችን ላይ እናስቀምጥሎታለን፡፡"
    Thank you for waht you did.
    When are you going to post the rest of the interview.

    ReplyDelete
  19. ...ERE BEYETIGNAWU HAGERE SIBIKET MIRCHAWU WUST LEGEBA NEBER....EWUNETEGNA MEHON TIRU NEWU...

    ReplyDelete
  20. ዲያቆን ዳንኤል ይህንን ያልከውን ሁሉ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ስትጽፋቸው ከነበሩት ጽሁፎችህ ጋር ይጣረሳሉ፡፡ ለምሳሌ- አቡነ ጳውሎስ ያረፉ ሰሞን ያወጣኸው አንድ ጽሁፍ ላይ ከዚህ ቡሃላ ምን መደረግ እንዳለበት በነጥብ ባስቀመጥከው መሰረት የአቡነ ጳውሎስ ሃብት ተሰብስቦ ለቤተ ክርስቲያኗ ገቢ ይደረግ የሚልን ሃሳብ ነበር ያንጸባረከው፡፡ አሁን ምን ተገኝቶ እንደሆነ እግዜር ይወቀው፡- ‹ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ረገድ እሰከ አሁን ብዙ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡›

    ReplyDelete
  21. ዲያቆን ዳንኤል ድምጽህ ጠፍቶ ነበረ አሁን ብቅ ብለሃል ጥሩ ነው፥፥
    ብልጠትን በተሞላ ሁኔታ አዲሱን ፓትርያርክ ከሰማይ የወረዱ መላክ ለማረግ የጻፍከው ጽሁፍ ጥሩ ነው (ቀድመህ ጀመርክ ከዚያም መሀበረ ቅዱሳን ይቀጥላል )፥፥ በነገራችን ላይ አትርሳው ይህች ቤክ ለሁለት የተከፈለችው በ አዲሱ ፓትርያርክ ምክንያት ነው፥፥ በነገራችን ላይ የሆነ ስልጣን ብጤ አትጣም እና በዚሁ ቀጥል፥፥

    ReplyDelete
  22. ሃሳብ ሲበታተን እና ሲገጣጠም
    (ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንደማሳያ)

    “ምርጫው በድምጽና በቆጠራ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትና ትውፊታዊነትን በተላበሰ መልኩ በጸሎትና በዕጣም እንዲከናወን ቢደረግ፡፡” ዳንኤል ክብረት: ከፊታችን ያለው መንገድ: Thursday, August 16, 2012: http://www.danielkibret.com/2012/08/blog-post_619.html
    “ሰዎች ከምርጫ ካርድ ይልቅ በዕጣ ቢሆን መንፈሳዊነትን ይላበስ ነበር በማለት ያስባሉ፡ …የእጣውም ይሁን የድምጹ ትክክለኛ መስመር ይዘው እስከተከናወኑ ድረስ ስህተት አይሆኑም፡፡” ዳንኤል ክብረት: ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102: http://andadirgen.blogspot.ca/2013/03/blog-post_10.html
    ____________________________
    “አቡነ መርቆሬዎስና የአቡነ ጳውሎስ አመራረጥም አወዛጋቢና የሌሎች እጅ የነበረበት ነበር፡፡” ዳንኤል ክብረት: ፓትርያርክና ፕትርክና: Wednesday, August 29, 2012: http://www.danielkibret.com/2012/08/blog-post_29.html
    “አቡነ መርቆሪዎስ ከአሁን በኋላ አልሰራም በማለት ለሲኖዶስ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ ቦታውን ለመልቀቃቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ በፓትርያትክ ላይ ፓትርያርክ ተሾመ በማለት አቡነ ጳውሎስን መውቀስ ከብዙ ነገር አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡” ዳንኤል ክብረት: ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102: http://andadirgen.blogspot.ca/2013/03/blog-post_10.html
    __________________________

    “የካህናተ ደብተራ ሌላው ጠባይ ደግሞ ወተቱን ማጥቆር ከሰሉን ማንጣት ነው፡፡ እውነትን የሚመዝኗት ከጥቅማቸው አንፃር ብቻ ስለነበረ ኃጢአት ሲሠራ እያዩ ጽድቅ ነው፤ ግፍ ሲፈጸም እያዩ ቅድስና ነው ማለት ይወዱ ነበር፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ በበደል ላይ በደል እንዲጨምሩ ያደርጓቸው የነበሩትም እነርሱ ናቸው፡፡….. በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የእውነተኞቹ አባው፣ ሊቃውንትና ካህናት አገልግሎትና ትሩፋት ለቤተ ክርስቲያን ብልጽግና እንዳይሰጥ ሲያሰናክሉና ለእውነት ዕንቅፋት ሲሆኑ የኖሩት ካህናተ ደብተራ ናቸው፡፡” ዳንኤል ክብረት: «ካህናተ ደብተራ» Thursday, May 17, 2012: http://www.danielkibret.com/2012/05/225-197.html
    “…..የደብተራ ተንኮል……..” የዳንኤል ክብረት ክሽፈት ፕሮፌሰር መስፍ: ጥር 2005
    “ከስድስቱ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በህይወት የሚገኙት ፕሮፌሰሩና መንግስቱ ኃ/ማርያም ብቻ ናቸው፡፡ የዶክተሩን ስም መጥቀስ ያልፈለኩት ዶክተሩ በህይወት ስለሌሉ ነው፡፡ ይህንን መናገር ድብትርና የሚል ትርጓሜ አያሰጥም፡፡ እኔ ለድብትርና አልበቃሁም፡፡ ዮፍታሄ ንጉሴ የጻፈውን ካነበባችሁ ድብትርና ትልቅ ማዕረግ መሆኑን ትገነዘባላችሁ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይህን ሹመት የሚሰጡ በሆኑና በተቀበልኳቸው ደስታውን አልችለውም፡፡” ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102: http://andadirgen.blogspot.ca/2013/03/blog-post_13.html
    _________________________
    “ማንኛውም የፓትርያርኩ [የአቡነ ጳውሎስ] ንብረቶች ወደ ሌሎች ከመጓዛቸው በፊት በጥብቅ ይቀመጡ፡፡ የባንክ ሂሳቦች ይዘጉ፡፡” ዳንኤል ክብረት: ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዛሬ ሌሊት ዐረፉ Thursday, August 16, 2012: http://www.danielkibret.com/2012/08/blog-post_7924.html
    “ንብረት በመያዝና በማስቀመጥ ረገድ እሰከ አሁን ብዙ ያልተሰማባቸው አባት አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ምናልባት ዘመዶቻቸው ረድተው ይሆናል ካልተባለ በቀር ብዙ ንብረት የላቸውም፡፡” ዳንኤል ክብረት: ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102: http://andadirgen.blogspot.ca/2013/03/blog-post_10.html
    “አቡነ ማትያስ ምርጫው ከመድረሱ በፊት አቡነ ጳውሎስ በህይወት እያሉ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዜግነታቸውን አልመለሱም ይላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በማስረጃ ቀርበው እስካላየን ድረስ ለመፍረድ እንቸገራለን፡፡”

    “በግሌ ዜግነቱ ምንም ቢሆን ልዩነት አይፈጥርም፡፡ በጣም ብዙ አባቶች በፖለቲካም ይሆን በኢኮኖሚ ጫና ወደ አሜሪካ ሄደዋል ፤ እነዚህ አባቶች በዚያ የተሻለ ነገር ለማግኝት ሲሉ በሁኔታዎች አስገዳችነት ዜግነታቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ በቤተክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ ችግር አልታየም፡፡”

    “ነገር ግን ሁል ጊዜ የተሰደደ ሰው ብቻ እንደ ጀግና ለምን እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ ጀግና ሀገር ውስጥ ያለውን መከራ የተቋቋመ ወይስ ጥሎ የተሰደደ ሰው ነው?”

    “እሳት በተነሳ ቁጥር ቦታህን እየለቀክ ከተሰደድክ ለችግሩ መፍትሄ መፍጠር አትችልም፡፡ ዋልድባን መርዳት የማይችል ሲኖዶስ አሜሪካ ውስጥ መፈጠሩ ምንም አይጠቅምም፡፡”

    አራቱም የሚቃረኑ ጥቅሶች የተወሰዱት: - ዳንኤል ክብረት: ከላይፍ መጽሄት የመጋቢት ወር እትም ቁጥር 102: http://andadirgen.blogspot.ca/2013/03/blog-post_10.html

    ReplyDelete
    Replies
    1. በመንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ወድቆ ያገኘ አንድ ሰው ባጋጣሚ ሲገልጥ ማቴዎስ ሃያ ሰባት ቁጥር አምስት ላይ “ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።” የሚል ንባብ ያገኛል:: ገለጥ ያደርግና ደግሞ አይኑን ወርወር ያደርጋል:: ሉቃስ አሥር ቁጥር ሰላሳ ሰባትን ያነባል:: ምንባቡ “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ” ይላል:: በዚህ ምክንያት ለካ የጣሉህ በዚህ ተግባርህ ነው ብሎ ጠቃሚውን የሕይወት መጽሐፍ ጥሎት ሄደ:: ቃላት የሀሳብ መግለጫ ናቸው እንጂ በምልአት አንድን ሁነት የሚያሳዩ አይደሉም:: ምስል ከሳች አድርገን ብንጻጽፋቸው እንኳ ብዙ የሚያጎድሉት አላቸው:: የአንድን ጽሑፍ ዓረፍተ ነገሮች በመነጠል የምናየው ከሆነ ከአውድ ውጪ ይሆኑና ለግልብ ትርጉም የተጋለጡ ይሆናሉ:: በዚህ መንገድ የማይጋጨውን መጽሓፍ ቅዱስ እንኳ ልናጋጨው እንችላለን:: በዚህ መንገድ ስህተት የማይሆን ነገር ፈልጎ ማግኘት የሚያስቸግር አይመስሎትም?

      Delete
  23. There is an apt saying in Amharic Wosha bebelabet Yechohal. Rough translation - a dog knows who to bark for. So it goes Daniel is barking for his feeders. It is a shame that our country is filled with people who have no conscience. People with no principles. Even the houses of worship are not free from such practices. The Ethiopian Church which was known for its believers who choose death rather than compromise on their faith is filled with opportunists who sell themselves for the highest bidder. How low have we sunk. Shame

    ReplyDelete