Monday, November 26, 2012

ስለ ቤተክርስቲያን እርቀ ሰላም በአሜሪካ ድምጽ የተደረገ ውይይት



  •   “የመንግስት ተጽህኖ  መኖሩን ፈጽሞ አላውቅም” ብጹእ አቡነ ገብርኤ
  •   “መንግሥትን አባቶች ግልጽ ባለ ቋንቋ አናስገባም ብለው መከራከር የሚችሉበት ሁለተኛ እድል እግዚአብሔር ለዚች ቤተክርስቲያን የሰጠው አሁን ነው፡፡”
  •  “ፓትርያርክ የመሾምና የመምረጥ ጉዳይ ፍጹም መንፈሳዊ ነው ፤ እንኳን መንግሥት ይቅርና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት  እኛ ነን መምረጥ የምንችለው ማለት አይችሉም ፤ ይህ እግዚአብሔር  የሚመርጠው ነገር ነው፡፡” ዶ/ር ተክሉ
  •   “መንግሥት ከቤተክርስቲያን ላይ እጁን አንስቶ አያውቅም” ዶ/ ር ተክሉ

(አንድ አድርገን ህዳር 16 2005 ዓ.ም)፡- አንድ አድርገን በአሁኑ ሰዓት ትልቅ መነጋገሪያ በሆነው በቤተክርስቲያኒቱ እርቀ ሰላም ዙሪያ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ አማካኝነት ህዳር 14 2004 ዓ.ም የተደረገውን ከሁለቱም ሲኖዶሶች አንድ አንድ አባት የተወከሉበትን እና በቤተክርስቲያን ዙሪያ በቂ እውቀት አላቸው የተባሉ ሁለት ዶክተሮች መካከል የቀረበውን ውይይት እንደሚቀጥለው አቅርበዋለች፡፡


ቀኖና ፈረሰ ሕገ ቤተክርስትቲያን ተጣሰ በሚል ሰበብ ለ20 ዓመታት የተለያዩትና እስከ መወጋገዝ የደረሱት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ወደ እርቀ ሰላም እያመሩ መሆናቸው ቢታወቅም ቤተክርስቲያኒቱን ለሁለት የከፈለው ችግር መፍትሄ የማግኝቱ ነገር አጠያያቂ እየሆነ ችግሩም እየተወሳሰበ መምጣቱ ይነገራል ፤ ለምን ? መፍትሄውስ ምንድነው? 


የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ አቶ አዲሱ ሁለት የቤተክርስቲያኒቱን አባቶችና ሁለት በቤተክርስቲያን ዙሪያ እውቀት ያላቸውን ምዕመናን አወያይቷል ፤ እንግዶቹም ብጹእ አቡነ ገብርኤል ከኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ ብጽእ አቡነ ዮሴፍ ከስደተኛው ሲኖዶስ ፤ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተለያዩ ጽሁፎችን ለንባብ ያበቁት ዶ/ር ዋለ እንግዳሰው ከአሜሪካና ፤ ዶ/ር ተክለ አባተ ከኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡


ጥያቄ፡- በኢትዮጵያው ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ቀን አይቁረጥ እንጂ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ይገኛል ፤ አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው ለመመለስ እንደማይታሰብ ነው በጸሀፊው አማካኝነት የገለጸው ፤ ይህ ከሆነ ዘንዳ ሰላሙ እንደምን ይመጣል? የሚሉ ሰዎች አሉ ፡፡ እናንተ በዚህ ላይ ምን ትላላችሁ? ምን ቢደረግ ነው በተጀመረው እርቀ ሰላም መሰረት የቤተክርስትያኒቱን የቀደመ አንድነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚቻለው ? 


ብጹእ አቡነ ገብርኤል ፡- የሲኖዶስ አባልነቴ እንዳለ ሆኖ በሲኖዶሱ ተወክዬ እገሌ ይስጥ ተብሎ ሳይሆን በፍቃደኝነት ያለኝን አስተያየት  ለመስጠት ነው የቀረብኩት ፤ እንደሰማነው ከሆነ ብዙ መልካም ነገሮች ታይተዋል ፤ አሁንም ውይይቱ እንዲቀጥልና በመልካም ሁኔታ እንዲፈጸም ነው የምንፈልገው ፤ ግን አራተኛው ፓትርያርክ እንደገና ወደዚህ መጥተው እንደ ድሮ  ይሁኑ የሚለው አከራካሪ ሆኖ የሚታይ ይመስለኛል ፤ በወዲያ በኩል ያሉ አባቶች  ይህ የሁሉ ነጥብ ከሆነ አራተኛው ፓትርያርክ ወደ ስልጣን ካልተመለሱ በምንም አይነት ሰላም ይገኛል ተብሎ አይታሰብም አይባልም ፤ ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ መነጋገር መከራከር ይቻላል ፤ ለምን ? እንዴት ? ተብሎ ብዙ ነገሮችን ማቅረብ ይቻላል ፤ ይህ ካልሆነ አይታሰብም  የሚለው ውይይት በር የሚዘጋ ይመስለኛል ፤ በውይይት ብዙ ነገሮች ይፈታሉ ፤ የተዘጋው በር ይከፈታል ፤ እንደዚያ ቢሆን መልካም ይመስለኛል ፡፡


አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡- ምን አልባት ከአዲስ አበባ የሚመጡት የልኡካን አባላት ከውይይት በኋላ አዲስ ነጥብ ላይ ቢደርሱ የኢትዮጵያው ቅዱስ ሲኖዶስ የያዘውን መስመር ይለውጣል?  ማለት  ምርጫውን የማዘግየት ወይም ደግሞ ፓትርያርክ ለጊዜው አለመሰየምን የመሰሉ  ነገሮችን ውሳኔውን ወደ ኋላ የማየትና የመመርመር ሁኔታ ይኖራል ይላሉ?


ብጹእ አቡነ ገብርኤል ፡- እሱን እንኳን ማወቅ አይቻልም ፤ እኔ ማወቅም አልችልም ፤ እኔ የሚከብደኝ እንዲህ ካልሆነ እንዲህ አይደረግም የሚለው አረፍተነገር የእርቀ ሰላሙን በር ይዘገዋል ብዬ ነው የማስበው እንጂ ምልአተ ጉባኤው እንዲህ ካልሆነ ውይይቱን አልፈቅድም ሊልም ይችላል ፤ ግን ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆርዮስ የመመለሳቸው ጉዳይ የሁሉም አባት ድምጽ ነውይ? 

አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡-የመንግሥት ተጽህኖ አለባችሁ?
ብጹእ አቡነ ገብርኤል ፡- እንግዲህ ሰው ማስረጃ ሊኖረው ይችል ይሆናል ወይም የመሰለውን ሊናገርም ይችላል ፤ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ ወይም የለም በሚለው ላይ ብዙ ይተቻል ፤ ይህ ከኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ አይነት ትችት ነበረ ፤ ታሪክ እንደሚያስታውሰን በደርግ ዘመነ መንግሥትም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ ወይስ የለም የሚል ክርክር ነበረ ፤ በአቡነ ጳውሎስም እንደዚህ አይነት ክርክር ነበረ ፤ አሁንም እኛ ያለነው በራሳችን ፍቃድና በራሳችን ውሳኔ ነው ፤ እርቅ ሰላሙ እንዲጀመር ሲኖዶስ ነው የወሰነው ፤ እኔ የመንግሥት ተጽህኖ ፈጽሞ መኖሩን አላውቅም ፤ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ውሳኔ ስለሆነ ምልዕክተኞችንም የመረጠ ሲኖዶስ ነው ፤ የላከም ሲኖዶስ ነው ፤ አጀንዳዎችን ቀርጾ የሰጠ ሲኖዶስ ነው ፤ አሁንም ቢሆን ስለ አዲሱ ፓትርያርክ ምረጡ ወይም አትምረጡ የሚል ትዕዛዝ ከመንግስት እንዳለ አንዳች የማውቀው ነገር የለም ፡፡
         ---------------------------------------------------------------------------------



አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡- ብጹእ አባታችን አቡነ ዮሴፍ አራተኛው ፓትርያርክ ወደ መንበሩ ካልወጡ እርቀ ሰላም ምን ዋጋ አለው የሚል አዝማሚያ ያለ ይመስለኛል ፤ የእርስዎን አስተያየት ይንገሩን እስኪ ?


አቡነ ዮሴፍ፡- ይህ ጊዜ በእውነት ቤተክርስቲያናችንን እግዚአብሔር ሊረዳ የመጣበት ጊዜ ነው ብዬ ነው የማስበው ፤ ከዚህ በፊት የዚህ የሁለት ሲኖዶስ ጉዳይ አስቸግሮ ቆይቷል ፤ አሁን ግን አንደኛው አባት  ወደ እግዚአብሔር ተጠርተው ሲሄዱ  የቤተክርስቲያኒቱን ችግር አንድ ሊያደርጋት የሚችልና ሊያጠነክራት የሚችለው ፤ ችግሩን ሊደፍነው የሚችለው ምንድነው?  የትኛውስ ነጥብ ነው ? ተብሎ ከታሰበና ከሁለት አንጻር ከታየ እንደ እኔ አስተያየትና በእኔ አቋም በህይወት ያሉት አባት ቦታው ላይ ሲቀመጡ እና ቦታው ሲይዙት ብቻ ነው ፤  አቡነ መርቆርዮስ አሁን ቦታው ላይ ተመልሰው ቦታውን መያዝ ስልጣን ላይ መቀመጥ ካልቻሉ የነበረው ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለኝም ፡፡

አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡-አሁን የተናገሩት ሀሳብ የምልአተ ጉባኤው ቃል ነው ?
አቡነ ዮሴፍ፡- ይህንን እንግዲህ የሰላም ኮሚቴዎች አሉ ፤ በሰላም ኮሚቴዎች መካከል ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ለአዲስ አበባው ሲኖዶስ መስራት እንደሚችሉ እና ቦታውን ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ ፤ ቤተክርስቲያኒቱን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆኑ አዲስ አበባ ላለው ቅዱስ ሲኖዶስ በደብዳቤ  አቋማቸውን ገልጸዋል ፤ የብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ መመለስና ቦታውን መያዝ ውጭ ያለው የሲኖዶስን ነገር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች በሙሉ ጉዳይ ነው ፤ በተለያየ መላ ህዝቡ አስተያየቱን ሲሰጥ እንሰማለን ፤ ህዝቡ የሚለው አጀንዳው ይሄ ነው ፤ ይህ የኛም ሃሳብ ነው ፤ የሲኖዶሱም ሃሳብ ነው፡፡



አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡-መልካም ይህን ጥያቄ ያቀረብኩት ቀደም ሲል ብጹእ አቡነ ገብርኤል በግሌ የምሰጠው አስተያየት እያሉ ስለሆነ ነው ፤ እርስዎንም ለመጠየቅ የፈለኩት ይህ ሀሳብ የግልዎት ነው? ወይስ የሲኖዶሱ አቋም ነው? ፡፡


አቡነ ዮሴፍ፡-አሁን የሰጠሁት አስተያየት የግሌ አስተያየት ነው፡፡

አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡-ይህ የፓትርያርኩ ሃሳብ ወይም አቋም አይደለማ?

አቡነ ዮሴፍ፡- ማለት የፈለኩት ነገር አቡነ መርቆርዮስ ቤተክርስቲያኒቱን በቀጥታ ለመምራት ደብዳቤ ጽፈው አዲስ አበባ ላለው ሲኖዶስ እንደላኩ ለመጠቆም ፈልጌ ነው ፡፡

አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡-ምን ብለው ጻፉ ? መንበሩ ላይ ተቀምጬ ማገልገል እፈልጋለሁ አሉ?
አቡነ ዮሴፍ፡- እንግዲህ ጠቅለል ባለ መንገድ ባላቸው እድሜ ቤተክርስቲያኒቱን ለማገልገል ፍቃደኛ እንደሆኑ የሚገልጽ ደብዳቤ ነው ፡፡
 -------------------------------------------------------------------------------------------------------

አዲሱ(የቪኦኤ ጋዜጠኛ) ፡- የኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፓትርያርክ ለመምረጥ ቀን ባይቆርጥም ዝግጅት ላይ እንዳለ ይታወቃል ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የሰላም ድርድሩ ውጤት ያመጣል ወይ? የሚል ነገር አለ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?

ዶ/ር ዋለልኝ ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሲኖዶስ ለሁለት የተከፈለበት ምክንያት መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የሚፈልገውን ፓትርያርክ በማስቀመጥ በቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ ትልቅ ጠባሳ እንደጣለ አድርጌ ነው የምቆጥረው ፤ አሁን   ከ20 ዓመት በኋላ መንግሥት ቤተክርስቲያኒቱ አንድ እንድትሆን የሚፈልግ ከሆነ ለአባቶች ሁሉንም ነገር መተው አለበት ፡፡ ራሳቸው አባቶች ሁሉን ነገር የሚወስኑ ቢሆን ኖሮ ፤ መንግስት ጣልቃ ሳይገባ ውሳኔ የሚወሰን ቢሆን የተበላሸውን መመለስ ይችሉ ነበር ፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ ምንድነው እነዚህ ሰዎች ተጽህኖ አድሮባቸው ውሳኔ ሊወስኑ የመጡ በመሆናቸው ድርድሩ የትም ቦታ አይደርስ የሚል ፍርሀት አለኝ ፤ ሁሉም የሚፈልገው ግን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድነትን ነው ፤ ይህ የ መንግሥት ጣልቃ ገብነት አለበት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
 

አዲሱ ፡- በኢትዮጵያው ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ቀን አይቁረጥ እንጂ ፓትርያርክ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ይገኛል ፤ አራተኛውን ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው ለመመለስ እንደማይታሰብ ነው የተወሰነው ፤ ይህ ከሆነ ሰላሙ እንደምን ይመጣል?

ዶ/ር ተክሉ (ከኖርዌይ)፡- እኔ ግን ትንሽ ጠንከር ለማለት እፈልጋለሁኝ ፤

አዲሱ፡- መልካም  ምእመናን አለመጠከራቸው ነው ነገሮች የተበላሹት ፤ እንዲያውም  አባቶችን እያከበሩ እነርሱ ግን ጠንከር አለማለታቸው ነው ይህን ሁሉ ችግር ያመጣው ፡፡


ዶ/ር ተክሉ (ከኖርዌይ)፡- ይህ ለ20 ዓመት ቤተክርስቲያኒቱን ሲያንገላታ የነበረ ችግር ሰው ሰራሽ ነው ብዬ በራሴ አምናለሁኝ ፤ የጎደለው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቅዱስ ወንጀልን በተግባር ተርጉሞ የማሳየት ጉዳይ ነው ያለው ፡፡ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለ ፤ ብጹእ አባታችን አቡነ ገብርኤል አላውቅም ብለዋል ፤ በእርግጥ በሚዲያ ላይ መንግሥት ጣልቃ ገብቶብናል ማለት ሊከብድ ይችላል ፤ ነገር ግን በአንድም በሌላም መልኩ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደነበረ አንብበናል ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ለወቅቱ የአሜሪካው አምባሳደር በግልጽ ተናግረዋል ፤ “አቡነ መርቆርዮስን እኔ በደብዳቤ በፊርማዬ እንዲነሱ አድርጌአለሁ ፤ ጫና በእርሳቸው ላይ መንግሥት ፈጥሯል” ብለዋል ፡፡ መረጃው በኢንተርኔት ተለቆ አይተናል ፤ አሁንም ቢሆን የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሊኖር አይችልም ማለት የዋህነት ሊሆን ይችላል ፤ ታሪክም የሚነግረን መንግስት ከቤተክርስቲያን ላይ እጁን አንስቶ አያውቅም ፤ በሕጉ ስንሄድ ግን መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ይላል ፤ በተግባር ሲታይ ግን ቤተክርስቲያን ላይ  የመንግሥት ረዥምና የማይታይ ክንድ አለ ፤ ስለዚህ የአባቶች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ያንን የማይታይ የመንግሥት የማይታይ እጅን መመከት መቻል አለባቸው ፤ እሱን ፈርተውና እሱን እያዩ ሁል ጊዜ በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ቤተክርስቲያኒቱን ወደፊት ሊያሸጋግሯት አይችሉም ፤ ስለዚህ አሁን የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ መንግሥት የራሱን የሚመቸውን አካሄድ ሃሳብ ሊሰጥ ይችላል ፤ እዚህ ጋር የቤተክርስቲያን አባቶች ህጉን ጠቅሰው መንግሥት እጁን እንዳያስገባ መከላከል መቻል አለባቸው፡፡ 

ፓትርያርክ የመሾምና የመምረጥ ጉዳይ ፍጹም መንፈሳዊ ነው ፤ እንኳን መንግሥት ይቅርና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ራሳቸው እኛ ነን መምረጥ የምንችለው ማለት አይችሉም ፤ ይህ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመርጠው ነገር ነው ፤  ስለዚህ መንግሥትን አባቶች ግልጽ ባለ ቋንቋ አናስገባም ብለው መከራከር የሚችሉበት ሁለተኛ እድል እግዚአብሔር ለዚች ቤተክርስቲያን የሰጠው አሁን ነው የሚመስለኝ ፡፡

እነሱን  ምንድነው የሚያስፈራቸው እነርሱ መነኩሴዎች ናቸው ፤ የግል ንብረት የላቸው ፤ ልጆች የላቸውም ፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ እንዴት በሚሊየን የሚንቆጠር ምዕመናንን አርአያ ሆነው ሊመሩን ይችላሉ? 

አዲስ አበባ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርክ ለመምረጥ ሕግ እያረቀቁ መሆኑን ሰምተናል ፤ አሜሪካ ያለውን ሲኖዶስ ስናይ ደግሞ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የቀድሞውን ቦታቸውን ካልያዙ እርቁ እንደማይሆን በአቡነ መልከ ጸዲቅ የተጻፈ ደብዳቤ አንብበናል ፡፡ አሁን ሁለቱን ስታገናኛቸው በጣም ተስፋን የሚፈታተን ሆኖ ታገኝዋለህ ፡፡ በሁለቱም ሲኖዶስ መሀል ቁርጥ ያለ አካሄድ አለመኖሩን ያመላክታል ፤ የአዲስ አበባው ሲኖዶስ እርቁን እንፈልጋለን ካለ እርቁ እስኪፈጸም ቢያንስ መጠበቅ ያስፈልጋል ፤ ሕግ ማውጣትና የወጣውን ሕግ  ለመተርጎም መሯሯጥ የማያስፈልግ ነው የሚሆነው ፡፡ 


አዲሱ ፡- አሜሪካ ያሉት አባቶች እርቁ ሊፈጸም የሚችለው ፓትርያርኩ ወንበራቸው ላይ ሲመለሱ ብቻ ነው ይላሉ  ፤ አቡነ መርቆርዮስ “መንበሩ ላይ መቀመጡ ይቅርብኝ ሀገሬ ገብቼ እቀመጣለሁ” ብለው ከአንደበታቸው ከወጣ እና ወደ ሀገር ቤት ለመሄድ ከፈቀዱ ይህም አንድ መንገድ ነው ፡፡ (ራሳቸው ፓትርያርኩ እስከ አሁን አልተናገሩም አለመናገራቸው ራሱ በራሱ ትልቅ ችግር ነው)፡፡


ዶ/ር ተክሉ (ከኖርዌይ)፡-አባታችን በሚዲያ ወጥተው ሲናገሩ ተሰምተው አይታወቁም ፤ በሚዲያ ወጥተው ለምዕመናን ያስረዱበት ሁኔታ እስከ አሁን አላገኝውም ፤ ነገር ግን አቡነ ጳውሎስ ካለፉ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከአቃቢ መንበር አቡነ ናትናኤል ስልክ ደውለውላቸው እንደተነጋገሩ እና እንዲያውም የጠቆሙት ነገር ቢኖር “ከአሁን በኋላ ሁሉም ነገር ይቅርብኝ ሀገሬ ገብቼ በጾም በጸሎት ተወስኜ በመቆየት ቀሪ ህይወቴን ወስኛለሁ ፤” የሚል ነገር አንብቤአለሁ ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነታ እንደሆነ አላውቅም ፤ ነገር ግን ያለቀ ነገር ነው እንደማይስማሙ የተስማሙ ይመስላሉ፡፡ 

ወደ እሳቸው ስንመለስ ድምጻቸው ተሰምቶ አይታወቅም ፤ ነገር ግን በመገናኛ ብዙሀን ሀሳባቸውን ቢናገሩ “ወንድሞቼ አትጣሉ ፤ እኔ ስልጣኔን አልፈልግም” ካሉ ወይም “ወደ መንበሩ ልመለስ” የሚሉ ነገሮች ከአንደበታቸው ቢሰማ ጥሩ ነበር” ፡፡

እርቅ እንዲመጣ ፍላጎት ካለ ሁለት መንገዶች ብቻ ነው ያሉት አንደኛው “ብጹእ አቡነ መርቆርዮስ ቦታቸውን እንዲይዙ መፍቀድ ነው” ይህ በሁለት መልክ ሊፈጸም ይችላል ፤ የመጀመሪያው “ከነ ሙሉ ስልጣንና ክብሩ ሊሰጧው ይችላሉ” ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እሳቸው የሚፈልጉትና የሚቀበሉ ከሆነ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በታላቅ አባትነት ቀሪ ህይወታቸውን በጸሎትና በጾም ቤተክርስቲያኒቱን እያገለገሉ ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶሱ በአቃቢ መንበር  እየተመራ መሄድ ቢችል አንድነት ሊመጣ ይችላል ፤ ሌላኛው መንገድ ደግሞ አቡነ መርቆርዮስ ለዚች ቤተክርስቲያን መስዋዕትነትን መክፈል የሚችሉና የተዘጋጁ አባት ከሆነ ነገሩን መተው ነው ፤ “ከዚህ በኋላ እኔ መንበሩ ላይ ተቀምጬ ቤተክርስቲያኒቱን ለመምራት ፍቃዱም ሆነ አቅሙ የለኝም ፤ ስለዚህ እናንተ ሁለት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተመካክራችሁ ቤተክርስቲያኒቱን አንድ ሊያደርግ የሚችለውን መንገድ መፍጠር አለባችሁ ፤ በእኔ የተነሳ ግን የምታደርጉትን ክፍፍል ከዛሬ ጀምሮ አቁሙ” ብለው ራሳቸው ግልጽ ሆነው ለመገናኛ ብዙሀን ወጥተው መናገር ቢችሉ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አንድነትን ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡



2 comments:

  1. I THINK THIS ARTICLE IS VERY IMPORTANT.THE CHANCE OF SOLVING THE TWO DECADE PROBLEM IS IN THE HANDS OF BOTH SYNODSES, IF THE THIRD PARTY IS CONTROLLED BY GOD.MAY GOD GIVE APIECE OF ADVICE TO ABUNE MERKORIOUS.MAY FATHER OF ABREHAM SOFTEN THE HEARTS OF ADDIS ABABA SYNODOSE.ONE OF THE SYNODOSES SHOULD
    RESPECT GOD AND GIVE IN HAND.BEING SELFISH IN THE NAME OF BREACH OF RULES IS EVIL.GOD FIRST.

    ReplyDelete
  2. I'M REALLY,REALY SORRY by Abune Merkorios. Why he didn't resign 4 EOTC unity. I'm realy sorry of him again. Let GOD bring unity.

    ReplyDelete